Saturday, 01 April 2023 20:06

ሺ ጊዜ ቢንጡት የቁልቋል ወተት ቅቤ አይወጣውም!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 አንድ ጠና ያሉ አዛውንት የስጋ አምሮታቸውን ሊወጡ አንድ ስጋ ቤት ገብዋል። መቼም ስጋ መጀመሪያ በአይን ነውና የሚበላው፣ማተር ማተር አደረጉት የተሰቀለውን ስጋ።ሽንጡ ጮማ ነው። ከመቶ ሻማ አምፖል ስር ይቅለጠለጣል። ዳቢቱ ይገላምጣል። ሻኛው ያለተልታል። አዛውንቱ፤”አንድ ኪሎ ቆንጆ አድርገህ ለጥብስ!” አሉና ወደ ጓዳ ገቡ። ስጋ ቤቱን ያውቁታል። ስጋ ቤቱም ያውቃቸዋል። ባለፈው ሰሞን አሟቸው ስለነበር፣ ዛሬ ጥሬ ስጋ አልፈለጉም።
 “ኪሎ ጥብስ አዝዣለሁ” አሉ ገና ቦዩ “ምን ልታዘዝ” ሊል ሲመጣ። “ደረቅ ይበል ታዲያ!” አሉት፤ ቦዩ ፊቱን አዙሮ ሲሄድ። የሰማቸው አይመስልም።
ጥብሱ ቀረበላቸው። ሽንኩርትና ቃሪያ ሰንጠቅ ሰንጠቅ ተደርጎ ተጨምሮበታል። መልኩም ያምራል። ጭሱ ቁና ቁና ይተነፍሳል። በዘመድ የተጠበሰ ሳይሆን አይቀርም። ፈገግ አሉለት አዛውንቱ - ለጥብሱ። “ዌል ካም” እንደማለት።
“ጎሽ እንዲህ ነው እንጂ” አሉና እጅጊያቸውን ሰብሰብ አደረጉ። ሊወርዱበት ነው እንግዲህ -የ78 አመቱ አዛውንት። በተለይ ጎድን ሲበሉ ነጭ አጥንቱ ከጥግ ጥግ  እስከሚታይ፣ እንደ እርሳስ ነው በጥርሳቸው የሚቀርፁት!
ቀና ብለው ሲመለከቱ ወጣት ወጣት ልጆች፣ ያዘዙት እስኪመጣላቸው እየጠበቁ ከፊት ለፊቱ ጠረጴዛ አግዳሚ ላይ ተኮልኩለዋል።
“ጎበዝ ኑ እንብላ እንጂ ታድያ” አሉ አዛውንቱ። ወጣቶቹ ጥቂት አመነቱ።
“ምን ሆናችኋል፤ ብቻዬን ይሄን ሁሉ ምን ላደርገው ነው? ኑ እንጂ ጎበዝ ነውር’ኮ ነው!”
ወጣቶቹ መጥተው ሽማግሌውን ከበቡና፣ ጥብሱን በነዚያ በመረመንጅ የጎረምሳ እጆቻቸው ይሻሙ ገቡ፡፡ በአንድ አፍታ ትሪዋ ወለልዋ ታየ፡፡ “Made in China” የሚለው ተነበበ፡፡ አይ ጉርምስና ደጉ፤ በሚል አስተያየት ልጆቹን አስተዋሉ፡፡ ወጣቶቹ ወደ ቦታቸው ተመለሱ፡፡ ሽማግሌውም ትንሿን ጉደር ወይን ጠጅ አዝዘው መጠጣት ጀመሩ፡፡
ጥቂት ቆይቶ ወጣቶቹ ያዘዙት ስጋ በትሪ ሙሉ መጣ፡፡ ወጣቶቹ ቀናም ብለው ወደ ሽማግሌው ሳያዩ፣ ያንን ትሪ ሙሉ ስጋ ተያያዙት፡፡ አዛውንቱም የወጣቶቹ ነገረ-ሥራ ገርሟቸው በትዝብት እያስተዋሉ ወይናቸውን ይጎነጫሉ፡፡
ወጣቶቹ ስጋውን አገባደው፣ ጉደር አዘዙና ዘና ብለው ተቀመጡ፡፡
ይሄኔ ሽማግሌው፤”ልጆች፣ ጎጂ ባህል ምንድነው?” ሲሉ ጠየቁ፡፡
አንደኛው፤ “ግርዛት ነዋ!” አለ::
‹‹አይደለም›› አሉ አዛውንቱ፡፡
ሁለተኛው፤ ‹‹እንጥል ማስቆረጥ›› አለ፡፡
‹‹አይደለም›› አሉ፤ አዛውንቱ አሁንም፡፡
ሦስተኛው፤ ‹‹ጉሮሮ መባጠጥ…በወር አበባ ጊዜ  መገለል … እ …በአንዳንድ ጎሳ የሴቶችን አካል…››
‹‹ኧረ በጭራሽ!›› አሉ አዛውንቱ እየሳቁ፡፡
አንደኛው፤ ‹‹ካለ እድሜ ከማግባት የሚከሰት የማህፀን ብልሽት ፌስቱላ!››
‹‹መልሱ አጠገብም አልደረሳችሁ›› አሉ ሽማግሌው።
ሁለተኛው፤ ‹‹እንግዲህ በሬዲዮ እና በቴሌቭዥን የሰማነውን ሁሉ ነገርንዎ፡፡ አሁን የእርሶን ንገሩን››
አዛውንቱም፤ ‹‹ልጆች፤ጎጂ ባህል ምን መሰላቹ?...‹‹ኑ እንብላ›› ማለት፡፡
XXX
ሀገራችን በጋራ የሚያስቡ ልጆች ያስፈልጓታል፡፡ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የፖለቲካ ችግሮቻችን ብዛትና ስፋት በጥቂት ሰዎች፣ ድርጅቶች እና ፓርቲዎች አቅም ብቻ እንወጣው ከምንልበት ደረጃ ካለፈ ውሎ አድራል፡፡ በተለይ ዛሬ ይህ እውነታ ተፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው፡፡ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እርዳ-ተራዳ የሚጠይቅም ሆኗል፡፡ አንድ የፖለቲካ ውጥረት ሲፈጠር፣ አንድ የኢኮኖሚ ጫና ሲመጣ ወይም አንድ ማህበራዊ ቀውስ ሲከሰት ብቻ እንተባበር፣ እንተጋገዝ ብለን ብንጮህ፣ ከእንግዲህ የቱንም ወንዝ የሚያሻግር መላ አናገኝም፡፡ ችግሮች ተባብሰው መጨረሻው ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት ህዝብ እንዲነጋገርባቸው እድል መገኘት አለበት፡፡ ብሶቶች ከታመቁ የፈነዱ እለት የሚፈጥሩት ጎርፍ፣ በዋዛ የሚገደብ አለመሆኑን ብዙ ማህበራዊ ትእይንቶች አረጋግጠውልናል፡፡ ብሶቶች መተንፈሻ፣ ጥያቄዎች መልስ ይፈልጋሉ፡፡ ሁኔታዎች አንዴ ከቁጥጥር ውጪ ከሆኑ የፖለቲካ መተረማመስ፣ የኢኮኖሚ አደጋ እና የማህበራዊ ውጥንቅጥ መፍጠራቸው አይቀርምና በጊዜ መጠንቀቅ ያሻል፡፡
‹‹ዛር ልመና ሳይያዙ ገና
ከተያዙ ብዙ ነው መዘዙ›› የሚባለው ለዚህ ነው፡፡
ከአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ በየዘመኑ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች እና አመፆች ተከስተዋል፡፡ ወደ ጦርነትም አድገዋል፡፡ የሁሉ መንስኤ፣ ብሶት (Discontent) ነው፡፡ በመንግስት ባለሥልጣናት ላይ ያለ ብሶት፤በሥርአቱ ላይ ያለ ብሶት፣ በመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለ ብሶት፣ በሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳይ ያለ ብሶት፣ በዜጎች ግድያና መፈናቀል ያለ ብሶት፣ ሃሳብን በነጻነት በመግለጽ ዙሪያ ያለ ብሶት፣ ከአቅም በላይ በሆነ የኑሮ ውድነት ላይ ያለ ብሶትና ምሬት ወዘተ በተጠራቀመ ጊዜ ለማህበራዊ እንቅስቃሴ ፍንዳታ ምቹ ማኮብኮቢያ ይሆናል፡፡ ኢንቨስተሮች ይሸሻሉ፤ ሌላውንምያሸሻሉ፡፡ ሥራ አጥነት ያጥጣል፡፡ ማህበራዊ ቀውስ ግራ ቀኙን ያቃውሳል፡፡ ወሮ በላው በረንዳ ያጣብባል፡፡ ለያዥ ለገራዥ ያስቸግራል! ዛሬ አገራችን የደረሰችበት ሁሉን- ዳሰስ ችግር የባለሙያዎችን፣ የምሁራኑን፣ የፖለቲካ አዋቂዎችን፣ የዳያስፖራውን፣ የልዩ ልዩ ማህበራትን እና ድርጅቶችን ሁሉ ልባዊ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ ለማሳካት ደግሞ ሆደ- ሰፊ የሆነ የፖለቲካ አመለካከትን ይጠይቃል፡፡
 ለመታረም ምክርን የሚያዳምጥ፣ ለግለ ሂስ ቀና መንፈስና ፅናት ያለው፣ ከኔ በላይ አዋቂ ለአፈር የማይል፣ ጉራ ሳይሆን ትህትና፣ ድንፋታ ሳይሆን የጥሞና ውይይትን፣ መቅጠፍን ሳይሆን በሀቅ ማሳመንን የሚያምን ሃላፊ ያስፈልጋል፡፡ ዊንስተን ቸርችል እንዳሉት፤ ‹‹ድል በተገኘ ሰአት ደግ መሆን መቻል ትልቅነት ነው፡፡ በውድቀትም ሰዓት ሽንፈትን መቀበል ብልህነት ነው››፡፡ ከጉልበት ይልቅ ብልሃትን መጠቀም ያዋቂ መሪዎች መገመቻ ነው፡፡ ትላንት የጀመርነው መንገድ የግድ መቀጠል አለበት ብሎ መታበይ አያዋጣም፡፡ ይልቁንም ሰፋ ያለ ፖለቲካዊ የተሳትፎ መድረክ ለመፍጠር መትጋት  ያስፈልጋል፡፡
    ሆደ-ሰፊ የፖለቲካ አመለካከት ያለው፤ ከትምህክተኝነትም ሆነ ከጠባብነት አደጋ የመዳን እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ይህ አመለካከት ያለው የሥልጣንን ገበታ ብቻዬን ልያዘው አይልም፡፡ መቻቻልን ከጠረጴዛው የማይለየው አጀንዳ ያደርጋል፡፡ ልዩነትን በማጥበብ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ወደ ገበታው ይጋብዛል፡፡ ‹‹ኑ እንብላ›› ለማለት ይችላል፡፡ ለለውጥም በሩ ሁሌም ክፍት ነው፡፡ አለማወቅን እንደ ውርደት ሳይቆጥር የማያውቀውን ይማራል፡፡ በዙሪያው በአጨብጫቢነት የተኮለኮሉ ግለሰቦችን በጥንቃቄ ያፀዳል፡፡ ምላሳቸው እረጃጅም የሆኑ መጣፍ ገላጮችን እና ቲኦሪ አንጋቾችን የፕሮፓጋንዳ አፎቶችን፣ የልሳን እና የብእር አንጋቾችን፣ በክፉ ሰአት ሁሉ ይመዝናል፡፡ በትላንት በሬ አያርስምና ለአዳዲስ የፖለቲካ ፈለግና ራእይ በሳል የሀገሪቱን ሰዎች ከእንቅስቃሴ መስክ አያርቅም፡፡ ዜጋ ሁሉ በሀገሩ በሚመለከተው ጉዳይ ‹‹ለምን?››  ብሎ የመጠየቅ መብት እንዳለው አበክሮ ይረዳል፡፡ ስለ ጎረቤት አገሮች ጉዳይ ከአገሬው ጋር ይመክራል፤ ይዘክራል፡፡ ኢንፎርሜሽን ይሰጣል፡፡
ፖለቲካን እንደ ጊዜያዊ ስራ (Part time job) የሚይዙ፣ ሁሌ ቤቴ የሆኑ፣ ለህዝቡ እንደ ጊዜያዊ ወዳጅ (part time lover) የሆኑ እና ‹‹ቱሪስት እና ፒስኮር የማይለዩ›› ካድሬዎችን እንዲሁም እምቡጣዎችን አበጥሮ ያወጣል፡፡ ጭፍን አምልኮ-ሰብ (cult) ለመፍጠር የሚሹትን እንደሚያንገዋልል ሁሉ ከመሀይም ምእመናንም በጊዜ ይገላገላል፡፡ ኩርፊያ ሳይሆን ውይይትን ያደንቃል፡፡ በዚህ ሁሉ መካከል ግን በሩን ለትችት ክፍት ያደርጋል፡፡ ከተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመስራት የሚችልበትን መንገድ ይጠርጋል፡፡ የአንገት በላይ ፍቅር አንገት ሲቆረጥ ወድቆ ይቀራል ይሏልና፣ ለህዝብ ያለው ፍቅር ልባዊ መሆን ይኖርበታል፡፡
እነዚህ ሁሉ ዲስፕሊኖችና ባህሪያት ከእውነተኛ ሰብአዊ መብት፣ ከእውነተኛ ነጻነት እና ዲሞክራሲ አብራክ የሚወለዱ ናቸውና ተዓማኒ እንጂ የይስሙላ እንዳይሆኑ ብርቱ ጥረት ማድረግ አለበት፡፡
 ‹‹ዲሞክራሲ፣ ሰላም፣ ሰብአዊ መብት፣ እኩልነት፣ መቻቻል…›› ተደጋግሞ ቢጮሁ፣ የተግባርን ፀጋ ካልተጎናፀፉ አፋዊ አተታ ብቻ ናቸው፡፡ ሺ ጊዜ ቢንጡት የቁልቋል ወተት ቅቤ አይወጣውም እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ ተግባር፣ ተግባር አሁንም ተግባር፤ ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ኑ እንብላ›› ጎጂ ባህል የማይሆነው፣ ያኔና ያኔ ብቻ ነው፡፡

Read 1949 times