Saturday, 01 April 2023 20:14

ጠ/ሚኒስትሩ ሥልጣን እንዲለቁ መጠየቅ ፈጽሞ አያስቅም!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(6 votes)

 የፓርላማው አባል ግን ጥያቄውን የጠየቁት ከልባቸው ነው?
       የ”መደመር” ፍልስፍና የት ነው ያለው? ማን ወሰደብን?
       አቶ ጌታቸው ረዳ፤ የባህሪ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል


      በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ በፓርላማ ቀርበው ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ለተሰነዘሩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፤ እንደተለመደው፡ሁሉም ጥያቄዎች ግን የተለመዱት ዓይነት ነበሩ፤አንድ የቀድሞ ፖለቲከኛና የህግ ባለሙያ “ቦምብ ጥያቄዎች” ሲሉ ገልጸዋቸዋል፤አንዳንዶቹን ጥያቄዎች፡፡ “ዱብዕዳ” ማለትም ይቻላል፤ ያልተጠበቁ ነበሩና፡፡  
እውነት ለመናገር ባለፈው ማክሰኞ ከአንድ የም/ቤቱ አባል ለጠ/ሚኒስትሩ የቀረበላቸው ጥያቄ እስከ ዛሬ ገጥሟቸው የሚያውቅ አይደለም፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም እንዲህ ዓይነት ጥያቄም በቀጥታ እጠየቃለሁ ብለው አስበውም፣ አልመውም  የሚያውቁ አይመስለኝም፡፡ እንኳንስ ጠ/ሚኒስትሩ አብዛኞቹ የም/ቤቱ አባላትም መሰል ጥያቄ በፓርላማው ይነሳል ብለው ያሰቡም የገመቱም አይመስለኝም፡፡ (እንዴት ተደርጎ??) ለዚህ ነው ‹‹አብን››ን ወክለው በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል የሆኑት የተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ፣ ጥያቄውን ለጠ/ሚኒስትሩ ሲሰነዝሩ፣ አዳራሹ በሳቅ የተሞላው፡፡ በርግጥ ጥያቄው እምብዛም ሳቅን የሚጋብዝ አልነበረም፡፡ (ባይሆን ያስደነግጣል እንጂ!) በዓለም ላይ የአገሪቱ ዋና አድራጊ ፈጣሪ ማለትም ጠ/ሚኒስትር ከሥልጣን እንዲለቅ በምክር ቤት አባል ሲጠየቅ የሚስቅ ብቸኛው ፓርላማ የኢትዮጵያ ፓርላማ ይመስለኛል፡፡ ጥያቄው ከምር የሚያስቅ ቢሆን ኖሮ መጀመሪያ መሳቅ የነበረባቸው ራሳቸው ጠ/ሚኒስትሩ ነበሩ፡፡ (ግን ፈገግ እንኳን አላሉም፡፡) እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናትና የብልጽግና ከፍተኛ አመራሮችም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ለጉዳዩ  ኮስተር ያለ ምላሽ ነው የሰጡት - ጥያቄው ተገቢ አለመሆኑን በመሞገት፡፡  
እርግጥ ነው፤ ከዚህ ቀደም በፓርላማ ጠ/ሚኒስትር ሥልጣን እንዲለቅ ተጠይቆ አያውቅም፡፡ ተጠይቆ አያውቅም ማለት ግን ሁሌም አይጠየቅም ማለት አይደለም፡፡ በህዝብ መመረጥም ብቻውን በሥልጣን ላይ ለመዝለቅ ዋስትና አይሆንም፡፡ ህወሓት ከሥልጣን የተባረረው እኮ በምርጫ አገኘሁት ያለውን የሥልጣን ዘመን ሳያጠናቅቅ ነው - በህዝብ አመጽና ትግል ሳቢያ፡፡ ስለዚህ አያድርስ ነው የሚባለው፡፡ በሁለት ጣቱ ብልጽግናን የመረጠው ህዝብ ራሱ ከሥልጣን ውረድልኝ ብሎ ከጠየቀ ምንም ማድረግ አይቻልም፤ታንኩንም ባንኩንም መያዝ የሥልጣን ዋስትና ሊሆን እንደማይችል በህወኃት መራሹ ኢህአዴግ ዘመን አይተነዋል፡፡ ይልቁንም ብልጽግና መራሹ መንግስት የሚሻለው ለህዝብ ጥያቄዎች ጆሮ መስጠት ነው፡፡ የዜጎችን በህይወት የመኖር ዋስትና ማረጋገጥ ነው፡፡ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን ማንነት ተኮር የጅምላ ግድያና ማፈናቀል ማስቆም ነው፡፡ በጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች ላይ ከህግ ውጭ የሚፈጸም አፈናና ድብደባን ማስቀረት ነው፡፡ (አሳፋሪም ኋላቀርም አካሄድ ነውና!) ከሁሉም በላይ ተቃውሞ በተነሳ ቁጥር ዜጎችን ከውጭ ሃይሎች ወይም ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ከመፈረጅ መታቀብም ይገባቸዋል፤የብልጽግና ከፍተኛ አመራሮችና ካድሬዎች፡፡ (ለህወኃት ያልጠቀመው ለብልጽግና ሊጠቅመው አይችልም!)
እናም ዋናው ጉዳይ መሆን ያለበት (ለፓርላማ አባላቱም ሆነ ለብልጽግና አመራሮቹ)፤ ጠ/ሚኒስትሩ ከሥልጣን እንዲለቁ የሚያስጠይቅ ሃላፊነትን ያለመወጣት ወንጀል ፈፅመዋል ወይ የሚለው ነው፡፡ ወይም ደግሞ ለዚያ በሚያደርስ ደረጃ ሃላፊነትን ያለመወጣት ድክመት (የአቅም ማነስ) ታይቶባቸዋል ወይ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ የሚመሩት ብልጽግና ፓርቲስ? አብዛኞቹ ጥፋቶች የሚፈጸሙት በቀጥታ በጠ/ሚኒስትሩ ሳይሆን በሌሎች የብልጽግና ከፍተኛ አመራሮችና ካድሬዎች መሆኑ ይታወቃል፡፡ የፓርቲው መሪ እርሳቸው በመሆናቸው ግን ከተጠያቂነት አያመልጡም እንጂ፡፡
በፓርላማ ሥልጣን እንዲለቁ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ጠ/ሚኒስትሩ  የሰጡት ምላሽ ተገቢና አጥጋቢ ይሁን አይሁን፣ የመተንተን ሥራውን ለፖለቲካ ምሁራን እንተወዋለን፡፡ እኔ ግን ሌላ ጥያቄ አነሳሁ - ለጠያቂው፡፡ ለተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ ማለት ነው፡፡  ለጠ/ሚኒስትሩ ይህን ከሥልጣን የመልቀቅ ጥያቄ ሲያቀርቡ ምን ምላሽ ጠብቀው ነበር? ተጠይቆ የማያውቅ “ቦምብ ጥያቄ” ለመጠየቅ ብቻ ብለው ነው ወይስ መጠየቁ በራሱ መፍትሄ ያመጣል ከሚል እሳቤ ነው? እንዴት?
በሌላ በኩል፤ጠ/ሚኒስትሩ ድንገት በስሜት ተነሳስተው ወይም ተሳስተው ጥያቄውን ቢቀበሉት ኖሮስ? ለምሳሌ፤ ‹‹እሺ ከዛሬ ጀምሮ ከሥልጣኔ ለቅቄአለሁ፤ የዚህች አገር ጠ/ሚኒስትር መሆን ያተረፈልኝ የጨጓራ በሽታ ብቻ ነው፤የተሻለ እመራለሁ የሚል ሥልጣኑን ይረከበኝ፤ምስጋና ቢስ ሥራ ነው፤ በከንቱ መባከንና መባተል ታክቶኛል›› ቢሉስ? (አያድርገውና!?) እርግጠኛ ነኝ እርስዎም ሆኑ ፓርቲዎ ጠ/ሚኒስትሩን የሚተካ ሰው አላዘጋጃችሁም-በሃሳብ ደረጃ እንኳን፡፡
እርግጥ ነው፤ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን መልቀቃቸው ይታወቃል፤ የእሳቸው ግን ይለያል፡፡ አንደኛ፤ በፈቃዳቸው ነው ሥልጣን የለቀቁት፡፡ ሁለተኛ፤ ‹‹የመፍትሄው አካል ለመሆን›› የሚል ቁልጭ ያለ ምክንያት ነበራቸው ፤ አሳማኝ፡፡ እንዲያም ሆኖ የሳቸውም ድንገት ሥልጣን መልቀቅ በኢህአዴግ ውስጥ የፈጠረውን ሽኩቻና ምስቅልቅል አንዘነጋውም፡፡ የለውጡ መንግሥት የሚባለው የተፈጠረው እንዲህ በቀላል አልነበረም፡፡ እሱም ቢሆን ሌላ ያልታሰበ ጦስ  ይዞ ነው የመጣው፡፡ የህወኃትን ማኩረፍና ከህብረቱ መውጣት ተከትሎ፣ ፈጽሞ ያልታሰበና ያልታቀደ  ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ የገባነው፡፡ ከባድ አገራዊ ኪሳራና ቀውስ ያስከተለ፡፡
 በዶ/ር ዐቢይ አህመድ የሚመራው አዲሱ የለውጥ መንግስት የሚወስዳቸው ፈጣንና አዎንታዊ የለውጥ እርምጃዎች በወቅቱ ቢያስደምሙንም፤የህወኃትን አገር የማፍረስ ሴራ  በቅጡ መተንበይና መገመት ባለመቻሉ (በሃይልም ይሁን በስልት!) ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡  ለ2 ዓመታት ደም አፋሳሽ ጦርነት ዳርጎናል፡፡ የለውጡ መንግስት እኮ ከሥር-ነቀል ለውጥ (አብዮት) ይልቅ ሪፎርምን የመረጠው፣ መንግስት በተለወጠ ቁጥር የሚፈሰውን ደም፤የሚፈጸመውን ግድያ፣ እስራትና ማሳደድ ወዘተ-- በአጠቃላይ የጅምላ ዕልቂቱንና ውድመቱን ለማስቀረት ነበር፡፡ በመንግስት ሥርዓታችን ተሰምተው የማያውቁ የ”መደመር” እሳቤ እንዲሁም በ”ፍቅርና በይቅርታ ማለፍ” የሚሉ የተከበሩና የተቀደሱ ሃሳቦችንም ሰምተን ነበር - አንዳቸውም ግን መሬት ላይ ወርደው አልተተገበሩም እንጂ፡፡ (ዕድሜ ለህወኃት!) ሌላው ቀርቶ በጠ/ሚኒስትሩ መፅሐፍ የተፃፈለት የ‹‹መደመር›› እሳቤ (ፍልስፍና) እንኳን ነፍስ ዘርቶ በአካል ሳናየው እኮ ነው የጠፋብን፡፡ የብልጽግና ካድሬዎች ግን ሥራቸው ምንድን ነው? እኒህን የተከበሩ እሳቤዎች መስበክና ማስፋፋት ትተው፣ በአክራሪ የብሄር ፖለቲካ ተጠምደው አረፉልን፡፡ በሚገርም ሁኔታ፣ ህወሃት ለ28 ዓመታት የተከለውን የዘረኝነት ችግኝ ማፋፋት ይዘዋል፤የብልጽግና ካድሬዎች፡፡
በነገራችን ላይ የኢህአዴግን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ-ዓለምን የተካው ምንድን ነው? (ፈረንጅ ‹‹የ1ሚሊዮን ዶላር ጥያቄ›› የሚለው ዓይነት ይመስለኛል፡፡)
ለመሆኑ አሁን ብልፅግና የሚከተለው ርዕዮተ-ዓለም ምንድን ነው? (ማን ጠይቆ!) ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት፣ የመደመር እሳቤ በብልጽግና ፖለቲከኞች ውስጥ በቅጡ ሰርጾ ቢሆን ኖሮ፣ የዘረኝነት ፖለቲካ ባይጠፋ እንኳን እንዲህ የአገር ደህንነት ስጋት አይሆንም ነበር፡፡  
ወደ ጀመርነው አጀንዳ ስንመለስ፣ የለውጡ መንግሥት ድንገት ሳይዘጋጅ፣ በታሪክ  አጋጣሚ፣ ወደ ሥልጣን በመምጣቱ፣ ዘርፈ ብዙ ችግሮችና ተግዳሮቶችን ተጋፍጧል - በአብዛኛው ህወኃት-ወለድ የሆኑ፡፡
እናም ከዚህ ተምረን ድንገት እየተነሳን የመንግሥት ወይም የመሪ (ያውም የጠ/ሚኒስትር) “ሥልጣን ይልቀቁ” ጥያቄ ከማንሳት እንቆጠብ ዘንድ ለመምከር ነው፡፡ (የብልጽግና ደጋፊ አለመሆኔ ግን ይታወቅልኝ!)
 ለመሆኑ ግን የተከበሩ አቶ ክርስትያን፣ ከሥልጣን እንዲለቁ የጠየቁት ጠ/ሚኒስትሩን ብቻ ነው ወይስ ፓርቲያቸውንም ጭምር ነው? ጠ/ሚኒስትሩን ብቻ ከሆነ፣ ከብልፅግና አመራሮች እሳቸውን የሚተካ ሌላ የተሻለ ሰው ማንን አስበው ይሆን? ከሥልጣን የሚለቀው ሙሉ የብልፅግና ፓርቲ ከሆነ፣ በየትኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ሊተካ ነው? ምናልባት የፈረደበትን የሽግግር መንግስት አስበው ይሆን? ቢያስቡም ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተስማምተው (በሥልጣን ክፍፍሉ ማለት ነው!) መንግስት እስኪመሰርቱ ድረስ የብልፅግና ቀሪ የ3 ዓመት የስልጣን ዘመን እንደሚጠናቀቅ ጥርጥር የለውም፡፡ ሁሉም ፓርቲ አራት ኪሎን የመቆጣጠር የውስጥ ረሃብ ስላለው ለአገሪቱ ሌላ  ቀውስ ነው የሚያስከትለው፡፡ (“ትሻልን ትቼ ትብስን”--ዓይነት!)  
እናም የአብኑ የተከበሩ የም/ቤት አባል አቶ ክርስትያን፣ ለጠ/ሚኒስትሩ ያቀረቡት ከሥልጣን ይልቀቁ ጥያቄ፤ ምንም እንኳን ለሳቅ የሚጋብዝ ባይሆንም፤ (ቢያንስ ለጊዜው) ሊተገበር የሚችል  አይመስልም፡፡ (unrealistic ነው እንደሚለው ፈረንጅ!) በዚያ ላይ ጠ/ሚኒስትሩ ከ3 ዓመት በፊት የመንግስት ለውጥ ፈፅሞ እንደማይታሰብ ደጋግመው ተናግረዋል- አስረግጠው፡፡
እንዲያም ሆኖ ግን ብልፅግና መራሹ የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ መንግስት፣ በራሱ ላይ ፈጣን የእርምት (ማሻሻያ) እርምጃዎችን ካልወሰደ፣ ከተለያዩ ወገኖች ተመሳሳይ ‹‹ከሥልጣን ልቀቅ›› ጥያቄ መጉረፉ አይቀሬ ነው፤ ቢቀበለውም ባይቀበለውም፡፡ እርግጥ ነው የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ሲረግምና ሲወቅስ እንጂ ለኢትዮጵያ የሚበጀውን መፍትሄ ሲጠቁም ሰምተን አናውቅም፡፡  
እስቲ ወደ ሌላ ሰሞነኛ የፖለቲካ መነጋገሪያ አጀንዳ ደግሞ  እንለፍ፡፡ ባለፈው ሳምንት ፈፅሞ ሳይጠበቁ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር (ፕሬዚዳንት) ሆነው የተሾሙት የቀድሞው የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ሰሞኑን ከአዲሱ ካቢኔያቸው ጋር በአዲስ አበባ የሸገር ልማቶችን ሲጎበኙ መሰንበታቸው ተሰምቷል፡፡ (በድሮው አባባል ‹‹ተደምረዋል›› እንደማለት ነው!)
ለነገሩ ህወኃት ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር ብሎ፣ እልቂቱንና ውድመቱን ሲያጧጧፍ፣ የፌደራል መንግሥቱ እየተዋጋም፣ የሰራቸውን አስደማሚ የሸገር ፕሮጀክቶች መጎብኘታቸው  መገረም ብቻ ሳይሆን መነቃቃትም ሊፈጥርላቸው ይችላልና ደግ  ሃሳብ ነው፡፡
ነገር ግን ጉብኝቱ፣ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሂደት አካል እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ከፌደራል መንግሥቱ ሆደ-ሰፊነትና ይቅር ባይነት የመነጨ እንደሆነ ይገመታል፡፡ አንዳንዶች “የጫጉላ ሽርሽር” እያሉ የሚሳለቁበትን ይህን የእነ አቶ ጌታቸው ረዳ ጉብኝትን፤ብዙም ባያጣድፉትና ባያበዙት ይመከራል፤ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች፡፡ ለምን ቢሉ? አሁንም  ህወሃትንና መሪዎቻቸውን “ወደፊት ሌላ ዙር ጦርነት ሊከፍቱብን ይችላሉ” ብለው የሚሰጉ አካባቢዎችና ህዝቦች መኖራቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡ ከዚህ አንጻር ምናልባት እነ አቶ ጌታቸው  በክልሎችም ተመሳሳይ የጉብኝት እቅድ ካላቸው፣ ትንሽ ቢያዘገዩት ነው የሚመረጠው፡፡ ለምሳሌ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ - ኤክስፖርት የተመረተውን ስንዴ የማየት ጉጉት ሊያድርባቸው ይችላል፡፡
 በእርግጥም ያጓጓል፡፡ አሁን ግን ወቅቱ አይደለም፡፡ በጣም ከቸኮሉ ግን ቢያንስ ከጉብኝቱ በፊት በሁለት ዓመቱ ጦርነት በእጅጉ የተጎዳውንና መከራና ሰቆቃ የደረሰበትን የአጎራባች ክልሎች ህዝብ፤ ይቅርታ መጠየቅ ያለባቸው ይመስለኛል፤ አቶ ጌታቸው ረዳና አዲስ ካቢኔዎቻቸው፡፡ ለነገሩ የትግራይ ህዝብንም ይቅርታ ስለመጠየቃቸው የምናውቀው ነገር የለም፡፡
ለማንኛውም ግን አንዲት በጦርነቱ ሁለት እግሮቿን ያጣች አንዲት ውብ ትራዋይ ወጣት በተሽከርካሪ መቀመጫ (ዊልቼር) ላይ ሆና የተናገረችውን  እንስማት፡-
“መጀመርያ ከእድሜ በታች ነሽ ተብዬ ነበር፤ በኋላ ሰው ስላለቀ ነው መሰለኝ ጠሩኝ፤ በቃ ሁለት እግሬን አጣሁ ..እንደ ድሮ ቆሜ አለመሔዴ ያሳዝነኛል፤ቆሜ እየሄድኩ እንደነበርኩ የታወቀኝ አሁን ነው፤ እና ከተቻለ ቆሜ መሄድ የምችልበት መንገድ ይናፍቀኛል። እኔ ሀገረ ትግራይ ትመሰረታለች ብዬ ነበር ፤ግን አልሆነም።”
 በመጨረሻ ግን ለቀድሞው የህወኃት ቃል አቀባይ፣ ለአሁኑ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አንድ ጠቃሚ ምክር ልለግሳቸው እወዳለሁ፤በአክብሮት፡፡ አሁን የክልል መሪ ሆነዋልና (ጊዜያዊ ቢሆንም) የባህርይ ለውጥ ለማምጣት መሞከር ይኖርብዎታል፤ንግግርዎም---አስተያየትዎም---ቁጣዎ ሳይቀር መገራት፤መታደስ፤መሻሻል አለበት፡፡ ማን ያውቃል ወደፊትም በምርጫ የክልሉ ፕሬዚዳንት የመሆን ዕድል ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ መልካም የሥልጣን ዘመን ይሁንልዎ፤በተረፈ ባገኙት ጊዜ ሁሉ የጠ/ሚኒስትሩን “መደመር” እና የ”መደመር ትውልድ” መጻህፍትን እንዲያነቡ እጋብዝዎታለሁ፡፡


Read 1909 times