Saturday, 01 April 2023 20:20

ተዓምር ያየሁበት የዳጊ የህይወት ክህሎት ሥልጠና

Written by  ትዕግስቱ በለጠ
Rate this item
(0 votes)

                  ፍልቅልቋ ወጣት ጠረፍ ከመሰበር ተርፋለች
                    በቅፅበት ውስጥ በፍቅርና በገንዘብ ተንበሽብሻለች
                             ጠረፍ ትባላለች፡፡ ተወልዳ ያደገችው እንደ ስሟ ጠረፍ ላይ ነው- ሞያሌ፡፡ እድሜዋ በአሥራዎቹ መጨረሻ ላይ ቢሆን ነው። ፍልቅልቅ ናት- ፈገግታ የማይለያት፡፡ ‹‹በትምህርቴ (ደደብ) ሰነፍ ነኝ›› ብትልም፤ 8ኛ ክፍል 92 ነጥብ አምጥታ ማለፏን ትገልፃለች፡፡ አስቸጋሪ በሆነ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ብታልፍም (በትርፍ ጊዜዋ እየሰራች ጭምር) 12ኛ ክፍልን አጠናቅቃለች፡፡ ጠረፍ በትምህርቴ ሰነፍ ነኝ ትበል እንጂ ከንግግሯና የህይወት ውሳኔዎቿ መረዳት የሚቻለው ብሩህ አዕምሮ እንዳላት ናት። ለህይወቷ ከራሷ ውጭ ማንም ሃላፊነት የሚወስድ እንደሌለ የገባት በልጅነቷ ነው። ከቤተሰቦቿ ከመጠበቅ ይልቅ ያገኘችውን እየሰራች ራሷን ለመቻል ጥራለች፡፡ ደጋግማ እንደምትናገረው፡ ከልጅነቷ አንስቶ ፍቅርና እንክብካቤ አግኝታ አላደገችም፡፡ ጠረፍ የህይወት ታሪኳን ስትናገር የሰማኋትና የተመለከትኳት በአዲሱ “ዳጊ ላይፍ ክላስ” ነው፡፡ ኢትዮጵያ ጠረፍ ላይ ተወልዳ ያደገችውና እድሜዋን ሙሉ ሞያሌ የኖረችው ወጣቷ፣ እንዴት በዳጊ ሾው አዲስ የሥልጠና መድረክ ላይ ተከሰተች? ከዳጊ ሾው ነፃ የሥልጠና ዕድል አግኝታ ይሆን? በፍፁም! ስፖንሰር ተደርጋ ይሆን? ጨርሶ! እራሷ ናት አስባና አስልታ፤ ወድዳና ፈቅዳ፤ (attract አድርጋ እንዲሉ) ከሞያሌ አዲስ አበባ ድረስ መጥታ፣ ለሥልጠናው የሚከፈለውን 6ሺ ብር ከፍላ በዳጊ የህይወት ክህሎት ሥልጠና የተገኘችው። ለዚያ ነው የበራና የነቃ አዕምሮ ያላት ወጣት ናት- ያልኩት፡፡ ገና የህይወት ክህሎት ሥልጠናውን ሳትወስድ ለማደግ፤ ለመለወጥ፤ ህልሟን እውን ለማድረግ ራሷን ያዘጋጀች ወጣት ናት የሞያሌዋ ጠረፍ፡፡ እስኪ የሥልጠናውን ታዳሚዎች በእንባ ያራጨውን ታሪኳን አለፍ አለፍ እያልን እንቃኘው፡፡ (ይቅርታ አድርጉልኝና እኔ ግን እያለቀስኩ አልነበረምየተከታተልኩት፤ ይልቁንም በመደነቅና በመገረም ነው፡፡ ድንቅ የሆነች ወጣት እኮ ናት!)
‹‹…እናቴ ጉሊት ቸርችራ ነው የምታሳድረን፤ አባቴ ደግሞ ግንበኛ ነው፤ አባቴ ከልጅነቴ ጀምሮ ይለኝ የነበረው ‹መልከ ጥፉ ነሽ… አንቺ ከዘሬም የለሽም›... እና ደግሞ በጣም ነው የሚሰክረው፤ በየምሽቱ መገረፍ ነው ሥራዬ … ምናምን ብዙ ነገር አለ ብቻ (ልትናገር ያልደፈረችው)… እናቴ ደሞ ሲጀመር ሙሉ ህይወቷን ለኛ ስትል የሰጠች ሰው ናት፡፡ እዛ ገበያ ቁጭ ብላ እንኳን የሚያልፈውን ሰው ‹ይኼ ሰው ሊገዛኝ ነው፤ ይኼ ሊገዛኝ አይደለም› ብላ የምትጨነቅ ናት፡፡ በቀን 200 ብር እንኳን የማትሸጥበት ቀን አለ፤ ‹ዛሬ እኮ 50 ብር እንኳን አልሸጥኩም፤ ተበድሬ ነው ሽሮ እንኳን እየሰራሁላችሁ ያለሁት› ትላለች፡፡ እና ባለፈው ዳጊ ‹ለበዓል በግና ዶሮ አጥተን የምናሳልፍበት ጊዜ አለ› ስትል… ይሄን ዓመት ራሱ እኛ ቤት መስቀል ምናምን በጣም ነው የሚከበረው… አባቴ ጉራጌ ነውና… ክትፎ፤ አይቤ…. ጓደኞቼ ቢጠየቁ ይመሰክራሉ፤እኛ ቤት እንዴት በዓል እንደሚከበር፡፡ በዚህ ዓመት ግን አባቴ ሥራ ምናምን አጥቷል፤ ዝቅ ያለ ሁኔታ ላይ ነበር፤ መስቀልን እንኳን ያሳለፍነው ቢያንስ ስጋ እንዲመስለን ብለን ቴስቲ ሶያ ጠብሰን ነበር፡፡ …ከጓደኞቼም ጋር ያለኝ ህይወት ያን ያህል ደስ የሚል አልነበረም፡፡ ለእኔ የሚሰጡኝ ቦታ ዝቅ ያለ ነው፤ ይንቁኛል። ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ተማርኩኝ፤8ኛ ክፍል ስደርስ ወደ ጠረፍ አካባቢ ኬንያ ላይ ሽንኩርት ከኢትዮጵያ ይመጣና መሃል ላይ ኬንያዎች ይገዙና እኛ ለቅመን በማዳበሪያ እናደርግላቸውና ብር ይከፍሉናል… እና በሌሊት 12 ሰዓት እነሳና እሄዳለሁ፡ በሰዓቱ ትምህርት እማር ነበር … ግን ትንሽ ጦርነት ስለነበረ፣ ሰኞ አንድ ጥይት ከተተኮሰ ሳምንቱን ሙሉ ትምህርት የለም፤ እኔ ደሞ በዚያ አሳብቤ ሥራ እሰራ ነበር… ከዚያ ብር አጠራቅሜ ሞባይል ስልክ ገዛኹኝ … በሰዓቱ ጓደኞቼ ሁሉ አልነበራቸውም፤ ብቻ እኔ ሲጀመር ራሴን መቻል አለብኝ .. ከቤተሰቤ ምንም መጠበቅ የለብኝም ብዬ ነበር የማምነው..›› እርግጥ ነው ፍልቅልቋ ጠረፍ፣ ፍቅር ተነፍጋ ነው ያደገችው፡፡ በተለይ የአባቷ ‹‹መልከ ጥፉ›› የሚል ነቀፋ በእጅጉ ሥነልቦናዋን እንደጎዳት ትናገራለች፡፡ ለራሷ ዝቅተኛ ግምት እንድትሰጥ አድርጓታል፡፡ ምንም ብትለብስና ብታጌጥ እንደማያምርባት ነው የምታስበው፡፡
‹‹…እንደ ጓደኞቼ እንኳን መልበስ አልችልም፤ እንደነሱ ፀጉሬን መሠራት አልችልም፤ ፀጉሬን ሻሽ አስሬ ነው ት/ቤት የምሄደው፤ ግንባራም ነኝ፤ ምንም ብለብስ …ምንም ፀጉሬን ብሰራ አያምርብኝም፤ እኔ በቃ ከእነሱ እኩል አይደለሁም፤ ‹‹ወይኔ ስታምር፤ ወይኔ ታድላ›› ብዬ ብቻ ጓደኞቼን የማደንቅ ሰው ነበርኩ፡፡ ለራሴ ያለኝ ግምት ዝቅ ያለ ነበር፡፡ ጓደኞቼ ሁሉ ነገር አላቸው፤ እኔን ግን ይንቁኝ ነበር …›› የሚገርመው ግን ጠረፍ የገንዘብና ቁሳቁስ ችግሯን የአቅሟን ያህል ሰርታና ስትፈታ ቆይታለች ከ1ሺ አምስት መቶ ብር ደሞዝ እስከ 5ሺ ብር ደሞዝ የምታገኝበት ስራ ተቀጥራ መሥራት ችላለች፡፡ ወደ አዲስ አበባ ከመምጣቷ በፊት በዲኤስቲቪ ተቀጥራ ትሰራ እንደነበር ትገልፃለች፡፡
 በራስ ያለመተማመን ስሜቷንና ለራስዋ ያላትን ዝቅተኛ ግምትም ከዕለት ወደ እለት እያሻሻለች መምጣቷን ከንግግሯ እንረዳለን- አዕምሮዋ የበራላትና የነቃላት ወጣት ናት ያልነው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡‹‹…11ኛ ክፍል ስደርስ የ5ሺ 500 ብር ሞባይል ገዛሁ፡፡ ፀጉሬን ሁሉ መሰራት ጀመርኩኝ …ግንባሬ በቃ ይሁና ብርቅ አይደለም፡፡ ልብስ እንደ ሆነ ሰልቫጅ አለ፤ እገዛለሁ…›› ወደ ዋናው ጉዳይ እንምጣ፡፡ ጠረፍ ምንም እንኳን ሞያሌ ጠረፍ ላይ ብትኖርም፤ ልቧና ሃሳቧ
እዚያ አልታሰረም ነበር፡፡ የዳጊ ሾውን ፕሮግራም በዩቲዩብ ትከታተል እንደነበር ተናግራለች፡፡ ምናልባትም ሃይልና ጉልበት የሆናት እሱም ሳይሆን አይቀርም፡፡
‹‹.. ከዚያ ‹‹ቆርጠው ለተነሱ›› የሚል የዳጊን ቪዲዮ አየኹኝ፡፡ እመዘገባለሁ ምናምን ብዬ አሰብኩኝ፡፡ እኔ እንደውም ነፃ ነበር የመሰለኝ (አዳራሹ በሳቅ ተሞላ)..የምር ነፃ ነበር የመሰለኝ…ከዚያ በቃ የሆነ ቀን ደውዬ ልመዘገብ ነበር፤ ምንድነው የሚያስፈልገው ስላት፤ 6ሺ ብር አለችኝ፡፡ ሃሳብ ገባኝ … ደሞዜ 5ሺ ብር ነው….15ቀን ስላለኝ ለ15ቀን ብሰራ 2ሺ 500 ብር አገኛለሁ፤ ያጠራቀምኩት 2ሺ ብር አለኝ፤ ስለዚህ አዲስ አበባ ለመምጣት ለትራንስፖርት ይሆነኛል፡፡ እሄዳለሁ ብዬ ተነሳሁ፣ አባቴ ጭራሽ አልተስማማም፤ሲጀመር ‹‹ልጄ አይደለችም፤ እሷ ማን ናት?›› አለ፤ እህቴ ‹ቤተሰቡን ሳታማክሪ ለምን ተመዘገብሽ› አለችኝ፡፡ ለምን አማክራቸዋለሁ፤ መፍትሄ ነው እኔ የምፈልገው፤ ባማክራቸው ኖሮ አልመጣም ነበር፤›› ጠረፍ አዲስ አበባ መጥታ የምትማር ጓደኛዋ ቤት አረፈች፡፡ የዳጊ ላይፍ ክላስ ክፍያውን ፈፅማ ሥልጠናውን ጀመረች፡፡ ከጓደኛዋ ጋር ምግብ ስትበላ እንኳን እየተሳቀቀች ሳትጠግብ ትነሳ እንደነበር ተናግራለች፡፡ እጇ ላይ 70 ብር ሲቀራትም ከእኒያ  ጉሊት ቸርችረው ካሳደጓትና ምን እንደምትማር ሳያውቁ መርቀው ከላኳት ምስኪን እናቷ 600 ብር እንደተላከላት ትገልፃለች- ከየት አምጥታ እንደሆነ አላውቅም በማለት፡፡ጠረፍ ለዳኒ ላይፍ ክላስ የሥልጠና ታዳሚዎች ታሪኳን ተናግራ ስትጨርስ በአዳራሹ ውስጥ የማያለቅስ ማንም አልነበረም፡፡ በኋላ ግን እንደተረዳሁት፤ አብዛኛው ታዳሚ ያለቀሰው ለጠረፍ ሳይሆን የራሱን ተመሳሳይ ታሪክ እያስታወሰ ነው፡፡ ጠረፍ ከመድረክ ከመውረዷ በፊት ዳጊ አንድ ጥያቄ አቀረበችላት - ‹‹እዚህ መማር ከጀመርሽ በኋላ ምን አዲስ ነገር አለ አንቺ ውስጥ..?›› ስትመልስም፤ ‹‹ሁሉንም ነገር እችላለሁ፤ ይቻላል፤ ትልቅ ህልም አለኝ፤ የራሴ ህይወት እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ፤ ይኖረኛል›› አለች በአንፀባራቂና በሚጋባ ፈገግታ ተሞልታ፡፡ ከዚህች ቅጽበት ጀምሮ በዚህች አዳራሽ ውስጥ ተዓምር የሚመስል ነገር ተከሰተ፡፡ ዳጊ፤ ጠረፍ  ለስልጠና የከፈለችው 6ሺ ብር እንዲመለስላት ለቡድኗ አባላት ትዕዛዝ ሰጠች፡፡ “The law of Attraction (የስበት ወይም የፍቅር ህግ) ሥራውን ላይቭ በቀጥታ ጀመረ፡፡ አንድ ታዳሚ፣ ጠረፍ ጀግና መሆኗን ተናግራ- ለጊዜው 5ሺ ብር እሰጣታለሁ አለች፡፡ ሌላዋ ታዳሚ፣ በየወሩ 5ሺ ብር ለሦስት ወራት ለመስጠት ቃል ገባች፡፡ አንዷ ደግሞ 10ሺ ብር እሰጣታለሁ አለች፡፡ አንዷ ታዳሚ ደግሞ ‹‹እኔ ገንዘብ እሰጣለሁ አልልም፤ ብቻዬን ነው የምኖረው፤ እንደ እህት እንደ ጓደኛ እኔ ቤት ሳትሳቀቅ መኖር ትችላለች›› አለች፡፡ ሌላዋ ‹‹ለ1 ወር ከሁለት ሳምንት ቤት የለሁም፤ ቤቴ አስቤዛው ሙሉ ነው፤ እንደ ራሷ ቤት ገብታ እንድትኖር ፈቅጄአለሁ›› ስትል ቃል ገባች፡፡ 20 ሺብር ለጠረፍ እሰጣታለሁ ያለች ታዳሚ ደግሞ፤ ‹‹በሚቀጥለው ሃሙስ ለእናቷ በአደራ የምታደርስልኝ 50ሺ ብር አመጣለሁ›› አለች፡፡ ሦስት የስራ እድሎችም አገኘች፡፡
ጠረፍ ከሞያሌ ጠረፍ ድረስ ዝም ብላ አልመጣችም፡፡ በቅፅበት ውስጥ በእጇ ላይ ከ100ሺ ብር በላይ አገኘች፡፡ መኖርያ ቤት ከአንድም ሁለት ሦስት አማራጭ ተሰጣት፡፡ሥራም እንዲሁ ሁለት ሦስት እድሎች ተከፈቱላት- አማርጣ የምትገባበት፡፡ ይኼ ሁሉ የሆነው በቅፅበት ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ለእኔ ተዓምራዊ ሃይል የለም፡፡
ጠረፍ አሁን ከሞያሌ ስትመጣ የነበረችውን ጠረፍ አይደለችም፤ በገንዘብና በፍቅር ተንበሽብሻለች፡፡ ሥራ አግኝታለች፡፡ መኖሪያ ቤት ሳትሳቀቅ የምትኖርበት ቃል ተገብቶላታል፡፡ ከእሷ አልፎ ለእናቷ 50ሺ ብር ይላክላቸዋል፡፡ (የሌላቸውን 600 ብር ለልጃቸው የላኩት እናት፤ 50ሺ ብር ሆኖ ተመለሰላቸው፡፡ The Low of Giving  ወይም  The Power of Generosity ልትሉት ትችላላችሁ፡፡ ያለምንም ጥርጥር ጠረፍ በደመነፍስ “The Law of Attraction”ን  ተጠቅማለች-ሰርቶላታልም፡፡  እፁብ ድንቅ  የሆነ ቪዲዮ ነው፡፡ የሥልጠናው ታዳሚዎች መንፈስ ይጋባል። ርህሩህ ልብ፣ በደግነት፣ በፍቅር፣ በገደብ የለሽ ለጋስነት …የተሞላ ነበር። በእጅጉ ያስገርማለል። ጠረፍን ለማዳን- ለመፈወስ- ለማሳደግ-ሁሉም ተረባረቡ። ከበረከቱ እንዳያመልጣችሁ ተሸቀዳደሙ፡፡ መላው ኢትዮጵያን እንዲህ ማድረግ ቢቻል ብዬ አሰብኩ፡፡ ተዓምር ነበር የሚፈጠረው፡፡ ለዚህ ሁሉ ምክንያት ለሆነው ለዳጊ ላይፍ ክላስ አድናቆቴን ሳልገልፅ ማለፍ ንፋግነት ነው፡፡ ፕሮግራሙ ይደግ ይመንደግ፤ብያለሁ። የሚሊዮኖችን ህይወት ይለውጥ ዘንድም ተመኘሁ። በመጨረሻም በዳጊ መሪ ቃል (መርህ) ልሰናበት፤ ‹‹ሰው መሆን ዘራችን፤ ፍቅር ሃይማኖታችን!!›› አሜን-ኬር ይሁን ብያለሁ!!

Read 1804 times