Saturday, 01 April 2023 20:34

“አእምሮ ወይስ ሆድ?”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ...የያዝነው ዓመት ሰባተኛዋ ወር ሽው ማለቷ ነው፡፡ እናላችሁ... ይህ የያዝነው ዓመት ከገባ ገና ወር ከምናምን ብቻ የሆነው የሚመስለን ለምንድነው! ያለፈው ዓመት እኩሌታውን ተሻግሮ ሲገሰግስ፣ “ይሄ ክፉ ዓመት ቶሎ ባለፈልን ብቻ!” ስንል ነበር፡፡ ዓመቱም አለፈና ይህኛውም እኩሌታውን ተሻግሮ እየገሰገሰ ባለበት በአሁኑ ሰዓት፣ ልመናችንና ተማጽኗችን አንድ ደረጃ አድጎ “ይሄ ክፉ ዘመን በቶሎ ባለፈልን ብቻ!” ወደ ማለቱ ሳንገባ አልቀረንም፡፡ እያንዳንዱ አዲስ ዓመት የተሻለ እንዲሆን መመኘቱና መለማመኑ ብዙም ወንዝ አላሻግር ስላለ፣ ምናልባት ጠቅለል ማድረጉ ይሻል ይሆናል፡፡ “የቸገረው ምን ይሆናል...” አይደል የሚባለው፡፡ ይህን ያህል አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ነን ለማለት ያህል ነው፡፡
 ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ!
አንድዬ፡- ማን ልበል?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምስኪኑ ሀበሻ ነኝ፣ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- ማን አልከኝ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አን... አንድዬ! ይሄን ያህል ረስተኸናል? ምስኪኑ ሀበሻ ነኝ እኮ!
አንድዬ፡- ቆይ፣ ቆየኝማ፡፡ በእርግጥ የትናንቱ፣ የጠዋቱ የማውቅህ ምስኪን ሀበሻ ነህ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ አዎ፣ የትንናቱ የጠዋቱ ምስኪን ሀበሻ ነኝ፡፡  ይህን ያህል ጠፋሁብህ ማለት ነው?
አንድዬ፡- አትፍረድብኝ...ምን መሰለህ፣ ዘንድሮ እኮ እናንተ ዘንድ ያልሆነውን ነኝ የሚል ስለበዛ እኔንም ግራ አጋባችሁኝ እኮ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እሱማ ልክ ነህ፣ አንድዬ፡፡ ግን እንደዛ ስንት ጊዜ እየተመላለስኩ ስጠይቅህ በደንብ የምታውቀኝ ምስኪኑ ሀበሻ፣ እንዴት ይህን ያህል የምጠፋብህ?
አንድዬ፡- አትቆጣኛ ምስኪኑ ሀበሻ፣ አትቆጣኛ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ አንድዬ፣ አልተቆጣሁም! ምንስ ቢሆን፣ እንዴት ብደፍር ነው አንተን የምቆጣው!
አንድዬ፡- እሱን እንኳን ተወው፡፡ መቼም ስትናገሩ እኮ ቃላቶቹን ከወዲህ ወዲያ ለቃቅማችሁ እየሰፋችሁ በቃ በምድርም ሆነ እኔ ዘንድም  ከእናንተ በላይ ቅዱስ የሌለ ነው የምታስመስሉት፡፡ አይደለም እንዴ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እ...እሱስ ልክ ነው፣ አንድዬ፡፡ ማስመሰሉን እናበዛዋለን መሰለኝ...
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ...
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ጠይቀኝ አንድዬ፣ ጠይቀኝ፡፡
አንድዬ፡- ምን መሰለህ...እናንተ እዛው እርስ በእርሳችሁ እንደ ፍጥርጥራችሁ ሁኑ፡፡ ግን እንደው “ያለአንተ ማን አለን!” “እረኛችን እኮ አንተ ነህ!” “ተስፋችን እኮ በአንተ ላይ ነው!“ እያላችሁ ስለደጋገማችሁ እኔን የምትሸነግሉኝ ይመስላችኋል? መልስልኛ ምስኪኑ ሀበሻ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እሱማ አንድዬ፣ እሱማ...
አንድዬ፡- አየህ፣ አንተ እንኳን የምትመልሰው ጠፋብህ፡፡ ደግሞ የቸገረኝ ወይም ግራ የገባኝ ሳይሆን እንደው ይሄ ምን ነበር የምትሉት... ይሄ እንኳን ይሄ የሆነ ሰው መድረክ ላይ ወጥቶ በውድም በግድም ሰዉን ሊያስቅ የሚሞክርበት...
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ስታንድአፕ ኮሜዲ...
አንድዬ፡- አዎ ስታንድአፕ ኮሜዲ የምትሠሩብኝ ይመስለኛል፡፡ ተበደልኩ ተገፋሁ ያለውምና እንዲሁም በእርግጥ የተበደለውና የተገፋውም፣ ደግሞ በዳይና ገፊ የተባለውምና እንዲሁም በእርግጥም በዳይና ገፊ የሆነውም ጎን ለጎን ቆማችሁ ነው እኮ የምትጸልዩት ወይም የጸለያችሁ የሚመስላችሁ፡፡ በል ንገረኛ ምስኪኑ ሀበሻ፣ ይሄ ታዲያ ፈገግ የሚያሰኝ ስታንድአፕ ኮሜዲ አይደለም!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እውነትህን ነው፣ እኛው ግራ ተጋብተን አንተንም ግራ አጋባንህ፡፡
አንድዬ፡- እዚህኛው ላይ እንኳን ግራ ታጋቡኛላችሁ ሳይሆን ልታስቁኝ ምንም አይቀራችሁም ማለቱ ይሻላል፡፡ ደግሞ እኮ ሁለታችሁም ወገኖች እኔኑ ነው “አንስተህ አፍርጥልኝ፣ ቁረጥልኝ፣ ራቁቷን አስኪድለኝ” የምትሉኝ! ስማኝ ምስኪኑ፣ የእናንተ ልመና እኮ ይህንን ፈጽምለኝ፣ ኑሮዬ እንዲሻሻል እርዳኝ፣ ከበሽታ ጠብቀኝ...አይነት በጎ፣ በጎና እናንተን የሚጠቅማችሁ ሳይሆን ቁረጥልኝ፣ አፍርጥልኝ እያላችሁ እኔኑ የወንጀል ተባባሪ የሚያደርግ  ነው፡፡ 
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ አንድዬ፣ እንደሱ አስበን አይደለም፡፡
አንድዬ፡- ግዴለም ምስኪኑ ሀበሻ፣ ግዴለም፡፡ ደግሞ ይህን ያልኩት ሁላችሁን ሳይሆን መሀላችሁም ብዙ ንጹህ ልቦች አሉ፡፡ ይልቅ ቅድም ምን እያወራን ነበር...?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ያልሆነውን ነኝ የሚል በዝቶ ግራ አጋባችሁኝ ብትል፣ እኔ ደግሞ በደንብ የምታውቀኝን እንዴት እጠፋብሀለሁ እያልኩኝ ነበር አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- አዎ፣ አሁን ትዝ አለኝ፡፡ ስማኝማ ምስኪኑ ሀበሻ፣ እንደውም ትንትናና ከትናንት ወዲያ በሚገባ አውቃቸዋለሁ ስላቸው የነበሩት ናቸው፣ ቆዳቸውን እየገለበጡ ግራ እያጋቡኝ ያሉት፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ለምን አንድዬ?
አንድዬ፡- አሁን ጥሩ ጥያቄ ጠየቅኸኝ፡፡ ግን ምስኪኑ ሀበሻ፣ የሆነ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ እዚህ የመጣኸው በባዶ ሆድህ ነው ወይስ የሆነ ነገር ቀማምሰሀል?.
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ እኔ እስከጠግብ ነው የበላሁት አንድዬ፡፡ ግን አትታዘበኝና እስከዛሬ ጠይቀኸኝ የማታውቀውን ጥያቄ ዛሬ እንዴት ጠየቅኸኝ?
አንድዬ፡- እንደው አሁን፣ አሁን ሳያችሁ ምን ይመስለኛል መሰለህ...ግን እንዳትቀየም ምስኪኑ ሀበሻ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ! ለምን ብዬ ነው የምቀየመው! አንድዬ፣ አንተን ተቀይሜ የት ነው የምገባው? ምንስ ነው የምሆነው?
አንድዬ፡- ይቺን፣ ይቺን እንኳን ተዋት ምስኪኑ ሀበሻ፡፡ በነገራችን ላይ ግን በእናንተ ቋንቋ እኔን እንሸውደው እያላችሁ መከራችሁን ስትበሉ ሳይ ምን እል መሰለህ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምን ትላለህ አንድዬ?
አንድዬ፡- እነኚህን ሰዎች ስፈጥራቸው እንደው ጭንቅላታቸው ውስጥ ያጎደልኩባቸው ነገር ይኖር ይሆን እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ አለበለዛማ እንዲህ ሊሆኑ አይችሉም ነው የምለው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ ስትፈጥረን ምንም ያጎደለክብን ነገር የለም፡፡ ደግሞ ይህን ያህል አስከፍተንሀል ማለት ነው?
አንድዬ፡- ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ፣ ማስከፋት አለማስከፋቱን ተወውና እንደው አንዳንዴ እዛ ታች ዙሪያ ገባህን ስታይ በሌላው ዓለም ከእናንተ እኩል የተፈጠረው የሰው ልጅ፣ ድሮ የተዋቸውን ነገሮች፣ እናንተ የሙጥኝ ብላችሁ እርስ በእርስ የምትባሉባቸው ለምን እንደሆነ ልትነግረኝ ትችላለህ? ዘመን አልፎ ዘመን በተተካ ቁጥር ነገራችሁ ግራ  ሲሏችሁ ታች፣ ቀኝ ሲሏችሁ ግራ እየሆነ እስከመቼ ሊቀጥል ነው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንተ ይቀር እስክትለን ነዋ!
አንድዬ፡- አየህ... አሁንም ራሳችሁ በፈጸማችሁት ስህተት፣ ራሳችሁ ባደፈረሳችሁት ኩሬ፣ ራሳችሁ ምድረ በዳ ባደረጋችሁት ለም ሥፍራ፣ ራሳችሁ ባደረቃችሁት ወንዝ ብቻ ምን አለፋህ---በትንሹም በትልቁም ከእኔ ራስ ላይ መውረድ አትፈልጉም፡፡ ለነገሩ እኔም ስለለመድኩት የተለየ ነገር አልጠብቅም፡፡ ይልቁንስ ስማኝማ...ቅድም የሆነ ነገር መቀማማስ አለመቀማመስህን  የጠየቅሁህ ለምን ይመስልሀል?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ለምንድነው አንድዬ?
አንድዬ፡- መቼም እንደማትቀየም ነግረኸኝ የለ አሁን፣ አሁን ብዙዎቻችሁ አዕምሯችሁ ሀያ አምስት ከመቶ ያህል እንኳን ሳይሞላ፣ ሆዳችሁ በሦስት አራት መቶ የሚሞላ እየመሰለኝ ራሴን ምን ብዬ እንደምጠይቅ ታውቃለህ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምን ብለህ ትጠይቃለህ?
አንድዬ፡- እነኝህ ሰዎች ዘንድ “አእምሮ ነው ሆድን የሚያዘው ወይስ ሆድ ነው አእምሮን የሚያዘው?” እያልኩ እጠይቃለሁ፡፡ ደግሞ ሄደህ እንዲህ አለኝ በልና ሰደበን ተብሎ ሀገሩ እንዳይታመስ፡፡ መቼም ዘንድሮ በጎ፣ በጎ የሆኑ ነገሮችን እንዴት ጠምዝዛችሁ ክፉ እንደምታደርጓቸው እናንተኑ ሊገርማችሁ ይገባል፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ ስትመጣ አእምሮ ወይስ ሆድ የሚለውን መልሼ እጠይቅሀለሁ፡፡ በል በሰላም ግባ፡፡
አሜን አንድዬ፣ አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1316 times