Print this page
Saturday, 01 April 2023 20:41

እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ ከ1915-2015 ዓ.ም.

Written by  በሰርፀ ፍሬስብሃት
Rate this item
(1 Vote)

 ከድምጻዊነት ተሻግሮ፣  በሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችነት እና በሙዚቃ ቀማሪነት ደረጃ፣ የሴት ሙዚቀኞች ተሳትፎ፤ እስከ ዛሬ ለማየት ባልታደልንበት ኹኔታ፤ እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ ግን፤ በክላሲካል ሙዚቃ ዘርፍ በብቸኛ የሙዚቃ ቀማሪነት እና ፒያኒስትነት ጉልህ የታሪክ ቦታ ይዘዋል፡፡
እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ (ከምንኩስናቸው በፊት ይጠሩበት በነበረው ስማቸው የውብዳር ገብሩ) ታኅሣሥ 4 ቀን 1915 ዓ.ም. አዲስ አበባ ነበር የተወለዱት፡፡ ገና የስድስት ዓመት ሕጻን ሳሉ ከታላቅ እኅታቸው ከሥንዱ ገብሩ ጋር ወደ ስዊትዘርላንድ ሔደው “ሞንት ሚራል” በተባለ አካዳሚ ትምህርት ይጀምራሉ፡፡ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ከቀለም ትምህርቱ በተጓዳኝ ቫየሊን እና ፒያኖ አጥንተዋል፡፡
 የእማሆይን የልጅነት ትዝታ ከራሳቸው ከእማሆይ ማስታወሻ ወስደው እንዲህ ሲሉ አስፍረውታል፡፡ “በዚያው በሰባት እና በስምንት ዓመት ዕድሜዬ፣… ከሥነ ፍጥረት ጋር ወዳጅነት ነበረኝ፡፡ አበቦች ውብ ልዕልቶች፣ ዛፎች… እንደ ዘበኞቻቸው፣ ነፋስ… ወጣት መልዕክተኛ፣ ፀሐይ…ደግሞ የዓለም ኹሉ ንግሥት ኾነው ይታዩኝ ነበር፡፡
ያን ጊዜ በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ውስጥ በኔ ዕድሜ ልጅ ስላልነበረ…ብቸኝነት የሕጻንነት ጓደኛዬ ኾኖ አብሮኝ አደገ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አንድ የኀዘን ስሜት፣ የመንፈስ ዕረፍት ዕጦት አደረብኝ፡፡ ሙዚቃ እወድ ነበርና ስሰማው የኀዘን ስሜት ያመጣብኝ ነበር፡፡
ለገና ሥጦታ… ቫየሊን ጠይቄ ሲሰጠኝ ወዲያው አስተማሪ ተመድቦልኝ መማር ጀመርኩ፡፡ የአስተዳዳሪው ዘመድ የኾነች ልጅ ፒያኖ ስትጫወት እየተመለከትኩ እኔም እየተፍጨረጨርኩ መምታት እንደቻልኩ የመጀመሪያ ሙዚቃዬን ጀመርኩ፡፡ ስሙን ሲጠይቁኝ The storm ነው አልኳቸው፡፡ “ማዕበል” ለማለት፡፡ ቫየሊኑን ተወት አድርጌ ወደ ፒያኖ በማድላት ብዙውን ጊዜ ፒያኖን ነበር የማጠናና የምጫወተው፡፡” ይላሉ እማሆይ በማስታወሻቸው፡፡ (ወንድማቸው ኮ/ል ዳዊት ገብሩ “ከንቲባ ገብሩ የኢትዮጵያ ባለውለታ” በሚል ርዕስ ካዘጋጁት መጽሐፍ የተወሰደ።)
የውብዳር ገብሩ 11 ዓመት ሲኾናቸው፣ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡ በዚህ ጊዜ ጣሊያን ኢትዮጵያን ወራ ነበር፡፡ ከንቲባ ገብሩም መላ ቤተሰባቸውን ይዘው ወደ ጎሬ ለመሠደድ ተገደዱ፡፡ የእኅቶቻቸው እና የእርሳቸው ትምህርት ተቋርጦ ከደስታ ገብሩ እና ከገነት ገብሩ ጋር በስደት ቆይተዋል፡፡ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በእስር ወደ ጣሊያን ተወስደው ነበር፡፡ እዚያም በእስር ላይ እንዳሉ ወንድሞቻቸው በጥይት ተደብድበው ስለተገደሉ፤ “ይህ ሁሉ የባሰውን የመንፈስ ጸጥታዬን እያጠፋው ይሔድ ነበር” እንዳሉ ተፅፏል፡፡
የሙዚቃ ፍቅራቸው እጅግ ጠሊቅ እንደነበር በግል ማስታወሻቸው በርካታ ቦታዎች ላይ ተጠቅሷል፡፡ እማሆይ ጽጌ ማርያም የጽሕፈት መኪና ተምረው ስለነበረ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ለጥቂት ጊዜ በጸሐፊነት ሠርተዋል፡፡ ሙዚቃን በከፍተኛ ደረጃ ለመማር ቁርጥ ውሳኔ ላይ የደረሱት ከዚህ ጊዜ በኋላ ነበር፡፡ በማስታወሻቸው እንዲህ ሲሉ አስፍረውታል፡፡ “እንደገና አባባን አስቸግሬ፤ ጃንሆይን እንዲለምኑልኝ አስደርጌ ወደ ውጪ ሀገር ሔጄ የሙዚቃ ትምህርቴን እንድቀጥል ተፈቅዶልኝ ወደ ካይሮ ሔድኩኝ፡፡ ትካዜ እንደ ጓደኛ አይለየኝም ነበር፡፡ ብዙ የፍቅር መጻሕፍትን ስለማነብ ስለ ሰው ልጅ ጥሩ አስተሳሰብ አልነበረኝም፡፡ ሰው አታላይ ነው፣ ውሸታም ነው በማለት ሰውን እምብዛም አላምንም ነበር፡፡” ይላሉ- እማሆይ፡፡
ለከፍተኛ የሙዚቃ ትምህርት ወደ ግብጽ ሔደው “ቬሉኑስ ኮንሰርቫቶሪ ኦፍ ሉቺኒያ” በተባለው የሙዚቃ ትምህርት ቤት አሌክሳንደር ኮንትሮቪች በተባለ ፖላንዳዊ የሙዚቃ መምህር ሥር ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ አሌክሳንደር ኮንትሮቪች ኋላ ላይ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ፤ በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ትዕዛዝ የክብር ዘበኛ ሙዚቃን አደራጅቶ የመራ ታላቅ ሙዚቀኛ ነበር። እማሆይ ከትምህርታቸው በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው የሙዚቃ ቅማሬዎቻቸውን ማዘጋጀት ጀመሩ፡፡
 “በዚህ ጊዜ ውስጥ” ይላሉ ወንድማቸው ኮ/ል ዳዊት ገብሩ፡፡
 “በዚህ ጊዜ ውስጥ ከዕለታት አንድ ቀን የንጉሣዊ ቤተሰብ የኾኑ አንድ ሰው ለኹለት ዓመት ትምህርት ወደ እንግሊዝ እንድትሔድ ቢከፍሉላትም፣ የይለፍ ወረቀቱን ኹሉ ይዛ ሳለ፣ ‘ከበላይ የመጨረሻ ፈቃድ አልተገኘም’ ተብላ ቀረች፡፡ ይህ ልክ በእኔ የደረሰብኝ ዓይነት ነው፤” ይላሉ ኮ/ል ዳዊት ገብሩ በመጽሐፋቸው፡፡ “አባቴ በ1922 ዓ.ም. …ለትምህርት ወደ ጀርመን ሊልኩኝ ቢያስቡም፤ የትምህርት ሚኒስትሩ ሳህሌ ጸዳሉ ተመሳሳይ ዕግድ በማድረግ የትምህርት ዕድሌን አጨናግፈውብኛል፡፡ እኔ ብዙ ስላየሁ ቻልኩት። እኅቴ ግን አልቻለችውም፡፡” በማለት አጋጣሚውን በኀዘን ይገልፁታል፡፡
ከዚህ በኋላ፣ በሙዚቃ ብዙ የመግፋት ጉጉት የነበራት ወጣቷ የውብዳ ገብሩ፤ የሕይወት መስመሯ ሌላ አቅጣጫ ያዘ፡፡ የእማሆይ ማስታወሻ እንዲህ ይገልፀዋል፡- “የመጨረሻ ዕድሌ በመሰበሩ፣ መንፈሴ ተሰባብሮ፣ ሞትን ብቻ ፈለግኹ፡፡ ከ15 ቀን በላይ እህል ውኃ ሳልቀምስ ጥቁር ባዶ ቡና ብቻ እየጠጣሁ ስሰነብት፤ ያው የሞት ጥላ በላዬ ላይ ሲያንዣብብ፣ የመጨረሻ ቁርባን እንዲሰጠኝ ጠይቄ፣ አንድ ቄስ እስከነበርኩበት ምስካየ ኅዙናን መድኀኔ ዓለም አጠገብ እነበረው ሆስፒታል ድረስ መጥተው አቆረቡኝ፡፡ የዚህ ዓለም ፍቅር እና የመኖር ፍላጎት ከኅሊናዬ  ፈጽሞ ተወገደ፤” ይላሉ፡፡
በቤተሰቦቻቸው ርብርብ ሕይወታቸው ተርፎ ጥቂት የተጽናኑት እማሆይ፤ ቤተሰቦቻቸውን አዘናግተው ወደ ግሼን ደብረከርቤ ተጓዙ፡፡ “ ለኹለት ዓመታት አንድ ቀን ሳይቋረጥብኝ ሰዓታቱንም፣ ቅዳሴውንም ሥራውንም ከዘለቅሁት በኋላ ቆረጠልኝ፡፡ የኹለት ወር ፈቃድ እና ደመወዝ ይዤ ከአንድ ዓመት በፊት ከእናቴ ከወ/ሮ ካሣዬ ጋር ሔጄበት ወደነበረው ወደ ግሼን ማርያም ተጓዝኩ፡፡ ወደዚያ ስሔድ ግን ነፋስ መለወጥ አለብኝ ብዬ አባባን እና እናቴን አስፈቅጄ ነው፡፡ እነርሱ ምንም አልጠረጠሩም ነበረና ለሽርሽር የምሄድ መስሏቸው ፈቀዱልኝ፡፡” ይላሉ፡፡     ከዚያም ለግሼኑ አቡነ ሚካኤል መመንኮስ እንደሚፈልጉ ይነግሯቸዋል፡፡ “ዘመዶችሽ በኋላ መጥተው ቢያስቸግሩስ?” ቢሏቸው፤ “በነፍሴ የሚያዝባት ሰው ካለ ከእኔ ሌላ የለም፡፡” ስላሉዋቸው ምንኩስናው ተፈቀደላቸው፡፡
ከምንኩስናው በፊት በጸጉር የመላጨቱ ሥነ ሥርዓት ወቅት የተከሰተው ነገር እዚህ ላይ ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡
“ከእንክብካቤ እቅፍ ውስጥ ወጥቶ ተሞነጫጭሮ ትከሻዬ ላይ የተዘረገፈውን ፀጉሬን ዐይተው አቡነ ሚካኤል፤ ‘ይህ ጠጉር ደግሞ መላጨት አለበት፤ ’ አሉኝ፡፡     ኧረ እርሱስ ግድ የለም አልኳቸው። አባ ደሳለኝ የሚባሉትን የደሴ ግቢ መርቆርዮስ አስተዳዳሪ እንዲላጩኝ ጠየቅኳቸው፡፡
አባ ደሳለኝ ሲላጩኝ እጃቸው ለብዙ ጊዜ ሲያርፍ ‘ምን ኾነው ነው?’ ብዬ ዘወር ብዬ ሳያቸው፤ ዕንባ አውጥተው ሲያለቅሱ ዐየሁና ‘ምነው አባቴ ምን ኾኑ?’  አልኳቸው።
‘አባቴ እንኳን ሲሞት አላለቀስኩም፣ እንዲያው አዝኜ ነው’ አሉኝ፡፡
 እኔም ‘ምን ለፀጉሩ ነው ይህንን ያህል የሚያዝኑት’
ብዬ ቀለድኩባቸው፡፡ እንኳንስ ፀጉር ሌላም በነበረኝ ለጌታዬ የምሰጠው አልኳቸው፡፡” ይላሉ፡፡ በዚህ ዕለት ማግስት የምንኩስና ሥርዓቱ ተፈጸመ፡፡ ይህ ሲኾን ዕድሜያቸው 20ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡
በወጣትነታቸው በወሰኑት በዚህ የምንኩስና ሕይወት አባታቸው እና እናታቸው ከፍተኛ ኀዘን ላይ ወደቁ፡፡ ብዙም አልቆዩ፤ እማሆይ በመነኮሱ በኹለት ዓመታቸው አባታቸው ከንቲባ ገብሩ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ከዚያ በኋላ እማሆይ ሙሉ ጊዜያቸውን ለሙዚቃ ቅማሬ እና ለመንፈሳዊው ግልጋሎት ብቻ ማዋል ጀመሩ፡፡ የመጀመሪያ ቅማሬያቸውን ለማስቀረጽ ወሰኑ፡፡ ምክንያት ነበራቸው፡፡
 “ቅማሬዬን በሸክላ ለማስቀረጽ ያነሳሳኝ ዐቢይ ምክንያት ነበር፡፡ ጎንደር በነበርኩበት ጊዜ በየቤተክርስቲያኑ የማይጠገበውን ማኅሌት ሰምቼ ስመለስ፤ እደጅ የአገር ቤት ተማሪዎች በየሜዳው ጥቅልል ብለው ተኝተው አያለሁ፡፡ ብጠይቅ ሌሊት ቤተክስቲያን ያደሩ ናቸው፣ ቤት የሌላቸው፡፡ በዚህም ልቤ ተነካ፣ አዘንኩ፡፡ እኔ ሀብት የለኝ፤ ያለችኝ ያቺው ሙዚቃዬ፡፡ ስለዚህ እስኪ ሙዚቃዬን ላስቀርጽ እና ሽያጩን እነዚህ ልጆች ገብተው በነጻ የሚያድሩበት ቤት ላቋቁም አልኩ፡፡ መከረኞቹም አሉ። ሸክላውም ተቀረጸ፡፡ ነገር ግን ተንኮለኛ አይጠፋምና ለሽያጭ ከመቅረቡ በፊት እንጉሡ ጆሮ ስለ ደረሰ ሐሳቡ መና ቀረ። መሞከሬ ግን አልቀረም፡፡”
ይህንን በመሰለ “እርሳቸው ያልተረጋጋ” በሚሉት ሕይወት እስከ 1975 ዓ.ም. ከቆዩ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሔዱ፡፡ እማሆይ በደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት ከሦስት ዐሥርት ዓመታት በላይ ኖረዋል፡፡ ስላሉበት ኹኔታ ምንም ዓይነት ዐዲስ ዜና ተሰምቶ ስለማይታወቅ በሕይወት መኖራቸውን የተጠራጠሩ ብዙዎች ነበሩ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን፣ ሥራዎቻቸው የታላቅ ሙዚቀኞችን ቀልብ መሳብ ጀመረ፡፡ በወጣትነታቸው ብዙ መሥዋዕትነት የከፈሉለት፣ ማንም ልብ ሳይለው የዘሩት የረቂቅ ሙዚቃ የቅማሬ ዘር፤ ዛሬ ላይ ብዙዎች እርሳቸውን ብለው፣ የእርሳቸውን ሙዚቃ እንዲያጠኑ እያደረገ ነው፡፡
የዓለም ታላላቅ የዜና አውታሮችም ከ2013 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ.) ጀምሮ ስለ እማሆይ ሙዚቃዎች አዳዲስ ነገሮችን ማቅረብ ጀምረዋል፡፡ በ2013ቱ የኢየሩሳሌም የባህል ክብረ በዓል ላይ ከተከናወኑ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ በእማሆይ የሕይወት ታሪክ እና የሙዚቃ ሥራዎች ዙሪያ ያተኮሩ ተግባራት ነበሩ፡፡
 ኹለት ጥራዝ መጻሕፍት ታትመዋል በእማሆይ ሕይወት እና የሙዚቃ ሥራዎች ላይ። የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን በኖታ የያዘ ባለ 146 ገጽ መጽሐፍም ታትሟል፡፡ እንደ ናዳቭ ሀርፐር ያሉ የእስራኤል ታላላቅ ሙዚቀኞች ስለ እማሆይ ሥራዎች ጥልቀት ምስክርነት እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡በወጣትነት ዕድሜ የተሠራ የአስተውሎት ሥራ የኋላ ኋላ የራሱ ትንሣኤ ይኖረዋል፡፡ እማሆይ ጽጌ ማርያም በሙዚቃ ምክንያት ብዙ ተፈትነዋል፡፡ ከመንፈሳዊ ሕይታቸው ጋር የሚቃረን የሚመስላቸው አንዳንዶች፣ ሙያቸውን እና የሙዚቃ ፍቅራቸውን አጣጥለውባቸዋል፡፡  የሕይወታቸውን አቅጣጫ ፍጹም በማይገመት መንገድ እንዲጓዝ ያደረገም ነው፡፡ ከሀገራቸው አሰድዶ ተነጥለው እንዲኖሩ ያደረገ ነው፡፡
ግን ከዚህ ኹሉ በኋላ የስማቸው ትንሣኤ፣ ከዘጠኝ ዐሥርት ዓመታት በኋላ በታላቅ ክብር ለብዙዎች ታይቷል፡፡ በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት ከንጉሠ ነገሥቱ ብቻ በቀር ማንም በትዕግሥት ሊያዳምጠው ያልቻለው ኮንሠርታቸው፤ ሐምሌ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ሥራዎቻቸውን በሚጫወቱ ወጣቶች አማካኝነት ከ1800 በላይታዳሚያን በተገኙበት በአድናቆት ተመልካች አግኝቷል፡፡ ከዚህም ጎን ነው አዳዲሶቹ ስድስት ክላሲካል ቅማሬዎቻቸው በትልቅ ኦርኬስትራ ሊቀርቡ ዝግጅት የተጀመረው፡፡
(ይህ ጽሑፍ፤ በዐዲስ ነገር ጋዜጣ ላይ የጻፍኩት ጽሑፍ ነበር፣ ለክብርት እናታችን፣ ለታላቂቱ የረቂቅ ሙዚቃ ጥበበኛ ለእማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ፣ ለኅልፈታቸው መታሰቢያ በድጋሚ አቀረብኩት፡፡)


Read 2224 times