Saturday, 01 April 2023 20:50

የልዩ ኃይል አደረጃጀት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲበተን ውሣኔ ተላለፈ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(9 votes)

ትጥቅ ፈተው ለሚበተኑ 250 ሺ ተዋጊዎች ማቋቋሚያ 29.7 ቢ. ብር ያስፈልጋል
                  
        የክልል ልዩ ኃይል የተባለው ወታደራዊ አደረጃጀት ሙሉ በሙሉ እንዲፈርስ ትዕዛዝ ተላልፏል፡: ልዩ ኃይሉ ሲፈርስ ወደ መደበኛ መከላከያ ሠራዊትና ወደ መደበኛ ፖሊስ ይቀላቀላል ተብሏል። ትጥቅ ፈተው ለሚበተኑ 250 ሺህ ያህል  ተዋጊዎች ማቋቋሚያ 29.7 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡    
ልዩ ሀይሉ ሲፈርስ  ወደ መደበኛ መከላከያ ስራዊት የሚቀላቀሉ ወገኖች መኖራቸው የተገለጸ  ሲሆን፤  አስፈላጊው የአገልግሎት ዘመን ክፍያ ተከፍሏቸው በሲቪል ስራ ላይ እንዲሰማሩ የሚደረጉ ወገኖችም አሉ ተብሏል ።የክልል ልዩ ኃይል አጀማመር ከ2000 ዓ.ም. በኋላ ባሉት ዓመታት፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ኃይልን ለመቆጣጠር ታስቦ የተመሠረተ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በተያያዘ ዜና፤ ትጥቅ ፈተው ለሚበተኑ 250 ሺህ ተዋጊዎች ማቋቋሚያ 29.7 ቢሊየን ብር ያስፈልጋል ተብሏል።   ከሰሜኑ ጦርነት ተዋጊ ኀይሎች በተጨማሪ   “የኦነግ ሸኔ”  ታጣቂዎችን በመልሶ ማቋቋሙ ሂደት ለማካተት  መታቀዱም ታውቋል ።
የብሄራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን፣ ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትና ሌሎች አካባቢዎች ካሉ ግጭቶች ጋር በተገናኘ ለመልሶ ማቋቋም የሚያስፈልገውን 29.7 ቢሊዮን ብር (555 ሚሊየን ዶላር) እገዛ እንዲያደርጉለት መቀመጫቸውን በአዲስ አባባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች ጥሪ አቅርቧል፡፡ ኮሚሽኑ በቀጣይ ሁለት አመታት ሊያከናውነው ላቀደው ትጥቅ የማስፈታት፣ የመበተንና ወደ ሰላማዊ ህይወት የመቀላቀል ስራ ከዲፕሎማቶች ጋር ምክክር አድርጓል ።  በተሃድሶ  ፕሮግራሙ ከሰባት ክልሎች  (ከኦሮሚያ፣ አማራ፤ አፋር. ትግራይ፤ ቤንሻንጉል፣ ከደቡብ ብሄር በሄረሰቦችና ከጋምቤላ) የተገኙ ተዋጊዎችንና የአካል ጉዳተኞችን ለማካተት ዕቅድ ተይዟል። ይሁን እንጂ በመጀመሪያ ዙር ተሃድሶ ፕሮግራሙ የሚካተቱት በትግራይ፤ በአማራና በአፋር ክልሎች የሚገኙ ተዋጊዎች ናቸው፡፡
ለፕሮግራሙ ከሚያስፈልገው አጠቃላይ ገንዘብ ውስጥ ከ 20 እስከ 25 በመቶ የሚሆነውን  በፌደራል መንግስት ለመሸፈን የታቀደ ሲሆን፤ ቀሪውን ደግሞ በለጋሽ ድርጅቶች እርዳታና በከፊል ብድር ለመሸፈን ታስቧል። በዚህ የተሃድሶ ፕሮግራም እያንዳንዱ የቀድሞ ተዋጊ ከጦርነቱ በፊት እንደነበረው ሃብት፣ በስሩ እንደሚተዳደሩት የቤተሰብ ብዛት እና የጤና ሁኔታ እየታየ፣ ለእያንዳንዱ ታጣቂ ከ36 ሺህ እስከ 60 ሺህ ብር የመቋቋሚያ  የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግለትም ታውቋል ። የአካል ጉዳት ለደረሰበት ተዋጊ ደግሞ ለእያንዳንዱ  45 ሺህ ብር የመቋቋሚያ ገንዘብ እንዲሁም በአጠቃላይ ትጥቃቸውን የሚፈቱ ኃይሎች ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ ለእያንዳንዳቸው 50ሺህ  ብር ይሰጣቸዋል ተብሏል።
ብሄራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ከዲፕሎማቶች ጋር ሰሞኑን ባደረገው ምክክር፣ ኮሚሽነሩ አምባሳደር ተሾመ ቶጋና ሌሎች የመንግስት አካላት ለዲፕሎማቶቹ ስለጉዳዩ ማብራሪያ ሰጥተዋል ።
 በዚሁ ወቅትም በመንግስት ‹‹ኦነግ ሸኔ›› ተብለው የሚጠሩትና በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎችም በተሃድሶው  እንደሚካተቱበት መግለጻቸውና  በርካታ ዲፕሎማት ‹‹ኦነግ ሸኔ›› ከተሰኘው ታጣቂ  ቡደን ጋር ስምምነት ባልተደረሰበት ሁኔታ ላይ ታጣቂዎች በዚህ ፕሮግራም ይሳተፋሉ ተብሎ መቅረቡ መንግሰት ከየትኛው ስምምነት ተነስቶ ነው የሚል ጥያቄ  ማንሳታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም የመንግስታቸውን የግማሽ አመት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በተመለከተ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከአባለቱ ለተነሳላቸው ጥያቄ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፣ ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረው ነበር፡፡
 ይሁን እንጂ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት  ከኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበልኝ ምንም አይነት  የሰላም ንግግር ጥሪ የለም በማለት ማስተባበሉ ይታወሣል። “የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ጥረት አደረኩ የሚለው፣ የቡድኑን አመራሮችና አባላት የትጥቅ ትግላቸውን ትተው ለመንግሥት እጃቸውን እንዲሰጡ በአካባቢ ሽማግሌዎች አማካኝነት ያደረገውን ያልተሳካ ሙከራ ነው” ሲል ቡድኑ ገልጿል።


Read 3809 times