Tuesday, 04 April 2023 13:40

ኢትዮ ቴሌኮም እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ዲጂታል የዳኝነት አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ ለማገዝና ለዜጎች ይበልጥ ተደራሽ፣ ቀልጣፋና ፈጣን ፍትህ ለመስጠት የሚያስችል፣ በዲጂታል የታገዘ የዳኝነት አገልግሎትን ተግባራዊ ያደርጋል የተባለ  ስምምነት፣ በኢትዮ ቴሌኮም እና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መካከል ተፈጸመ፡፡

በዛሬው ዕለት በተፈጸመው ስምምነት መሠረት፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ አስተማማኝና ደረጃውን የጠበቀ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ-ልማት:- አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት፣ የመጠባበቂያ ኔትወርክና የኔትወርክ ደህንነት ያለው ዘመናዊ የሞጁላር መረጃ ማዕከል፣ የኔትዎርክ ኦፕሬሽን መቆጣጠሪያ ማዕከል፣ የዋይድ ኤሪያና ሎካል ኤሪያ ኔትወርክ ግንባታ እንዲሁም የሶፍትዌር ደረጃ ዋይድ ኤሪያ ኔትወርክ ማስተዳደሪያ (SD-WAN) ዓለም አቀፍ ደረጃውንና ጥራቱን ጠብቆ በመገንባት ያስረክባል፡፡

ይህም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተግባራዊ በሚያደርገው የኢ-ኮርት ሲስተም አማካኝነት በፌደራል ፍርድ ቤቶች የሚሰጡ የዳኝነት አገልግሎቶች ለተጠቃሚዎች ቀልጣፋ፣ ውጤታማ፣ ዘመናዊና ተደራሽ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ስምምነቱ ከዚህ ቀደም በሁለቱ ተቋማት መካከል የነበሩትን የቴሌኮም አገልግሎቶች የትብብር ሥራዎችን በተጠናከረ ሁኔታ ተፈጻሚ ለማድረግ በተለይም በሁለቱ ተቋማት መካከል የአቅም ግንባታ፣ ሥልጠና፣ የእዉቀት፣ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲከናወን  ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር  እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡

የመሠረተ ልማቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአሁኑ ወቅት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚሰጠውን የዳኝነት አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመደገፍ፣ ባለድርሻ አካላት በቀላሉ መረጃ እንዲያገኙ ለማድረግ፣ ጊዜና ገንዘብን ለመቆጠብ፣ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ግልጸኝነትን  ለማስፈን እንዲሁም ዜጎች በፍትሕ ስርዓቱ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሏል፡፡

Read 1499 times