Wednesday, 05 April 2023 19:07

ከ1 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ተሸላሚ የሚያደርገው የሳፋሪኮም የዕጣ ሽልማት መርሃ ግብር በይፋ ተጀመረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፤ ከ1ሚ.በላይ ደንበኞች የ07 ኔትወርኩን በመቀላቀላቸውና ምርትና አገልግሎቶችን በመጠቀማቸው ተሸላሚ የሚሆኑበትን የመጀመሪያ የዕጣ ሽልማት መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት በኩባንያው ዋና መ/ቤት በይፋ አስጀምሯል፡፡
ለ14 ሳምንታት በሚዘልቀው "ተረክ በጉርሻ" በተሰኘው የሽልማት መርሃ ግብር፤ ደንበኞች የሳፋሪኮም ሲምካርዳቸውን ሲያወጡ፣ የአየር ሰዓት ሲገዙና ጥቅሎችን ሲሞሉ እንዲሁም የዋትሳፕ ጥቅሎችን ሲጠቀሙ ፤ ለባለ ዕድለኝነት ብቁ የሚያደርጋቸውን የዕጣ ቁጥር ያገኛሉ ተብሏል፡፡
ደንበኞች በቀን ውስጥ እስከ 10 የሚደርሱ የዕጣ ቁጥሮችን እንደሚያገኙና ቁጥሮቹም የዕለት፣ የሁለት ሳምንት እንዲሁም የወር ሽልማቶችን ለማሸነፍ በሚወጡ ዕጣዎች ውስጥ የሚካተቱ እንደሚሆኑ ተነግሯል፡፡
የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አንዋር ሱሳ የሽልማት መርሃግብሩን አስመልክቶ ሲናገሩ፤" የዛሬው ሁነት ደንበኞቻችንን ለማመስገን የተዘጋጀ ነው፡፡ በተረክ በጉርሻ መርሃ ግብራችን፣ በቀጣዮቹ 14 ሳምንታት ከ1ሚ.በላይ ለሚሆኑ ደንበኞቻችን ሳፋሪኮምን ሲቀላቀሉ፣ የአየር ሰዓታቸውን ሲሞሉና ጥቅሎችን ሲሞሉ በሚደርሷቸው የዕጣ ቁጥሮች 3 መኪኖች፣7 ባጃጆች፣ 7 ሞተር ሳይክሎች፣ ስልኮች ታብሌቶችና ዕለታዊ የአየር ሰዓትን ሽልማትን ጨምሮ የተለያዩ ሽልማቶችን የምንሸልም ይሆናል፡፡ ቢዝነሳችንን እየገነባን ያለነው ደንበኞችን ታሳቢ ባደረጉ መልኩ ሲሆን፤ እያደግን በመጣን ቁጥር ደግሞ ደንበኞቻችንን ከእኛ ጋር በመዝለቃቸው ዕውቅና ልንሰጣቸው ይገባል፡፡" ብለዋል፡፡
ደንበኞች የአየር ሰዓት ለመሙላት ወይም የድምፅ፣ የፅሁፍ መልዕክት ወይም የዳታ ጥቅሎችን ለመግዛት በሚያወጡት እያንዳንዱ 10 ብር፣ 1የዕጣ ቁጥር የሚደርሳቸው ሲሆን፤ ሲምካርድ በመግዛት ኔትወርኩን የሚቀላቀሉ አዳዲስ ደንበኞች በ24 ሰዓት ውስጥ አየር ሰዓት ከሞሉ 3 የዕጣ ቁጥሮች ያገኛሉ፡፡ 1 ጂቢ የዋትሳፕ ጥቅሎችን ከተጠቀሙ ደግሞ 7 የዕጣ ቁጥሮች ያገኛሉ ተብሏል፡፡
ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ደንበኞችም ክፍት የሆነው የሽልማት መርሃግብር፣ እስከ ሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ.ም የሚዘልቅ ሲሆን፤ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኔትዎርኩን በዘረጋባቸውና ሥራ በጀመረባቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ ከ1 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ዕድለኞች የሚያደርግ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡
አሸናፊዎች ከብሔራዊ ሎተሪ ጋር በመተባበር በየሁለት ሳምንቱ በዕጣ ተለይተው የሚሸለሙ ሲሆን፤ የዕጣ አሸናፊ መሆናቸውም በ0700 700 700 ተደውሎ እንደሚነገራቸውም ሳፋሪኮም አስታውቋል፡፡
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
 
Read 2249 times