Saturday, 08 April 2023 19:36

መንግስት የክልል ልዩ ሃይሎችን ለመበተን ያወጣው ውሣኔ በአማራ ክልል ተቃውሞ ገጥሞታል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(6 votes)

አብን እና ባልደራስ የመንግስትን ውሳኔ ተቃውመውታል
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ውጥረት ነግሷል፤ ኢንተርኔት ተቋርጧል
መንግስት ሂደቱ ትጥቅ ከማስፈታት ጋር የሚገናኝ አይደለም ብሏል


የክልል ልዩ ሃይሎችን በመበተን አባላቱን ወደተለያዩ የፀጥታ መዋቅሮች ለማስገባት ከመንግስት የተላለፈው ውሳኔ ተቃወሞ ገጥሞታል። ትላንት በተለያዩ የአማራ አካባቢዎች ውሳኔውን በመቃወም ነዋሪዎች ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።
በባህዳርና ጎንደር ከተሞች ውስጥ ከፍተኛ ውጥረት መፈጠሩን የገለፁት ምንጮች፤ አንዳንድ ድርጅቶች ከባድ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል በመስጋት ሰራተኞቻቸውን በየቤታቸው እንዲቆዩ አድርገዋል ተብሏል፡፡
“የሀገሪቱን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት ለመጠበቅ የሚያስችል አንድ የተጠናከረ ሰራዊት ለመገንባት” በሚል ምክንያት የየክልሉን ልዩ ሃይሎች ወደተለያዩ የፀጥታ መዋቅሮች ለማስገባት የሚያስችል ውሳኔ ያሳለፈው መንግስት፤ ከትናንት በስቲያ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩን አስታውቋል።
መንግስት በበኩሉ እያካሄደ ያለው የልዩ ሃይል አባላትን መልሶ የማደራጀት መርሃ ግብር መሆኑን ገልጾ ይህ ከትጥቅ ማስፈታት ጋር የማይገናኝ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚንስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቀዋል።
የተጀመረው መልሶ የማደራጀት ሂደት የአገር ሉአላዊነትን ከማስጠበቅ፣ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የሚሰነዘርን ማንኛውንም አይነት ጥቃት ከመከላከል አንጻር ጠንካራ የመከላከያ ሃይል ለመገንባት የሚያስችል እድል ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ህውሃትን በተመለከተ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ትጥቅ የመፍታት ሂደቱ ያለማወላወል የሚፈጸም ነው ያሉት ወ/ሮ ሰላማዊት ሂደቱ ከሌሎች ሀገራዊ እቅዶች ጋር የሚገናኝም የሚጣረስም አይደለም፤ እራሱን ችሎ በራሱ መርሃ ግብር የሚከናወን ነው ብለዋል። ይህንን ሂደት ዓለማቀፍ ታዛቢዎች እየተከታተሉት መሆኑ መታወቅ አለበት ሲሉም አክለዋል።
የክልሎች ልዩ ሃይሎችን የመበተን ፕሮግራም በመላ አገሪቱ የሚተገበር አገር አቀፍ ፕሮግራም ነው ያለው የመንግስት መግለጫ ትላንት በተለያዩ የአማራ አካባቢዎች  ነዋሪዎች  ተቃውሟቸውን ገልጸዋል። ፕሮግራሙ በአማራ ክልል በሚገኙ የልዩ ሃይል ክፍሎች ውስጥ ተቃውሞ እንደገጠመውም አመልክቷል፡፡ ውሳኔው ተግባራዊ መደረግ በጀመረባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ከፍተኛ ውጥረት መንገሱን የጠቆሙ ምንጮች፤ በአማራ ክልል ባህርዳር ጎንደር፣ ደሴ፣ ወልዲያና ኮምቦልቻ ከተሞች ውስጥ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ተናግረዋል። በአንዳንድ የክልሉ ከተሞች የክልሉ ልዩ ሃይሎች ከመከላከያ ሰራዊት አባላት ጋር መጋጨታቸውም ተጠቁሟል፡፡
“ክልሉ የደህንነት ስጋት ካለባቸው አካባቢዎች ግንባር ቀደሙ እንደሆነና በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰነዘሩበትን ጥቃቶች ለመከላከል የሚያስችለው ምንም አቅም እንደሌለው እየታወቀ፣ የክልሉን ህዝብ ለአደጋ በማጋለጥ፣ ልዩ ሃይሉን ትጥቅ ለማስፈታት መሞከር እጅግ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው”  ብለዋል ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት።
“የመንግስት ውሳኔ ተገቢ ነው ተብሎ ቢታመንበትም፣ የህዝቡን ደህንነት ለአደጋ በማጋለጥና ህዝቡን ለጠላት አሳልፎ በመስጠት ተግባራዊ የሚደረግ አንዳችም ውሳኔ አይኖርም” ሲሉም ነዋሪዎቹ ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል።
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በክልሉ ልዩ ሃይልና በፊደራል ፀጥታ ተቋማት መካከል የተፈጠረው ከፍተኛ ውጥረት የአካባቢውን ህዝብ ከፍተኛ ስጋት ላይ የጣለ ሲሆን በርካታ የልዩ ሃይል አባላት መኖሪያ አካባቢያቸውን እየለቀቁ መሰደዳቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፤ የመንግስትን ወሳኔና ተግባራዊ እንቅስቃሴውን ተከትሎ ባወጣው የተቃውሞ መግለጫ፣ “መንግስት ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩ ህጋዊ ያልሆነና ወቅታዊና አገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ያላገናዘበ፣ ተግባር ነው” ብሏል።“ለአገር ሉአላዊነትና አንድነት ከፍተኛ መስዋህትነትን የከፈለ ሃይል ምንም አይነት ውይይት ሳያደርግበትና የጋራ መግባባትና መተማመን ላይ ባልተደረሰበት ሁኔታ በድንገትና ያለበቂ የፀጥታ ዋስትና ለማፍረስ የተላለፈው ውሳኔና የተጀመረው እንቅስቃሴ ሃላፊነት የጎደለው ውሳኔ ነው” ያለው አብን፤ “ዳፋው በአማራ ክልል ብቻ ሳይወሰን በአገር አቀፍ ደረጃም ከፍተኛ አለመረጋጋት የሚፈጥርና ክልሉንና ወደ ሌላ የቀውስ አዙሪት ውስጥ የሚከት አደገኛ አካሄድ ነው” ሲል ተችቷል።
የክልሉ ልዩ ሃይል እጣፈንታ ከልዩ ሃይል አመራሮች፣ ከመላው የሰራዊቱ አባላትና ከክልሉ ህዝብ ጋር በሚደረግ ውይይትና የጋራ መግባባት ብቻ ውሳኔ ላይ እንዲደርስበት ያሳሰበው ፓርቲው፤ የተፈጠረው ውጥረት ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣና አላስፈላጊ መስዋዕትነት እንዳያስከፍል የልዩ ሃይል አባላት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ብሏል። የመንግስትን ውሳኔ በመቃወም መግለጫ ያወጣው ሌላው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በበኩሉ፤ በመርህ ደረጃ የክልል ልዩ ሃይል መፍረስ እንዳለበትና አገራዊ ተክለ ሰውነት ባለው የመከላከያ ሰራዊት መተካት እንደሚገባው እንደሚያምን ጠቅሶ፤ ከወቅታዊ አገራዊ ሁኔታዎች አንፃር ግን ውሳኔው ተቀባይነት የሌለውና ጊዜውን ያላገናዘበ ነው ብሏል።የአማራ ህዝብና የክልሉ መንግስት ይህንን ህዝቡን ለአደጋ የሚያጋልጥ አደገኛ ትጥቅ የማስፈታት ውሳኔ እንዲቃወምም ባልደራስ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የመንግስትን ውሳኔ በመደገፍ መግለጫ ያወጣው ኢዜማ በአንጻሩ፤ ውሳኔው ከመዘግየቱ በስተቀር ተገቢነቱ ላይ ጥያቄ ሊነሳበት አይገባም ብሏል፡፡ የክልል ልዩ ሃይሎችን ወደ ፌዴራልና የክልል ህጋዊ የፅጥታ መዋቅር ውስጥ የማስገባቱ በጎ ጅማሬ፣ አላስፈላጊ ውዥንብር ፈጥሮ ሌላ አገራዊ አደጋ እንዲይጋብዝ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ፓርቲው አሳስቧል።
 

Read 2660 times