Saturday, 08 April 2023 19:39

ጥበብ ሌላ ብልጣብልጥነት ሌላ፣ ብልሃት ሌላ፣ ሸር ሌላ

Written by  -ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

የዘፈኑን ርዕስ አይቶ፣… የግጥሙን የመጀመሪያ ስንኝ የሰማ ሰው፣… “እ?” ሊል ይችላል። ርዕሱና ስንኙ፣ አራምባና ቆቦ የተራራቁ፣ ከነጭራሹም ወይ አንተ ወይ እኔ ተባብለው የሚዝቱ ተቃራኒ ሃሳቦችን የሚዘምሩ ናቸው።
የዘፈኗ ርዕስ ማዕረጓን የሚገልፅ ከሆነ፣ mastermind ከሆነች… በጥበቧ ልሕቀት፣ በብልሃቷ ልዕልና፣… የሚደርስባት የለም። የመጪውን ዓመት ተግባራት ከነ ውጤታቸው፣… ከወዲሁ ታውቃለች።
ገና ድሮ፣ አስልታና ቀምራ፣ አቅዳና የጊዜ ሰንጠረዥ አውጥታ አዘጋጅታለች። አሳቻ ቦታ መርጣ፣ ካልተመቸም አድራሻዋን ሰውራ፣ ለማዘናጋት አድብታ፣ የተመኘችው ኢላማ ለመምታት፣ ያሻትን ታዳኝ ለማጥመድ አሸምቃ ትጠብቃለች። በአእምሮዋ የወጠነችው ሃሳብ እሷ በወሰነችለት ጊዜና ቦታ እንደሚከናወን፣… ሕልሟ እውን እንደሚሆን፣… ጥያቄ የለውም። ውስጥ ለውስጥ የቤት ስራዋን አምናና ካቻምና የምትጨርስ ብልጥ የብልሃት እመቤት፣ ቀንደኛ የጥበብ ልዕልት ናት።
ስውር የሃሳብ ውጥኗ፣ ገና በገሃድና በተግባር መታየት አልጀመረም እንጂ፣ ተከናውኖ እንደተፈፀመ ብንቆጥረው ይሻላል። ከመነሻው እስከ መድረሻው፣ ጊዜ ተቆርጦለት፣ መንገድ ተተልሞለት፣ እንደ ጅረት በከፈተችለት ቦይ ሄዶ ወዳለመችለት ቦታ እንደሚደርስ አትጠራጠሩ። የብልህ ጥበበኞች ሃሳብ፣… ተሰርቶ የተጠናቀቀ እቅድ፣ “ከወዲሁ ያለቀለት ጉዳይ” ነው።
እንደ እጅ ሰዓት ነው። ጥበበኛው ገና ድሮ የውስጥ ለውስጥ ስራውን ጨርሷል። ማን እንዳበጀውና እንዴት እንደቃኘው ባታውቁም፣… የውስጥ ለውስጥ አሰራሩን ወይም ሴራውን ማየት ባትችሉም፣… የእጅ ሰዓታችሁ አገልገሎቱን እንደሚያከናውን እርግጠኛ ናችሁ። ደቂቃና ሴኮንድ እየቆጠረ ያሳያችኋል። አገልግሎቱን ይፈፅማል።
እንዴት? የሰዓታችሁ ትናንሽ  ክንዶች ይሽከረከራሉ። የሚያንቀሳቅሳቸው ሃይልና የሚያሾራቸው መዘውር፣ ውስጠ ምስጢሩ አይታይም። ስውር ነው። ሰዓት የፈጠረና ያበጀ፣ብልሃተኛ ወጣኙና አቃጁ ጥበበኛ አሁን ከአጠገባችሁ የለም። ስራውን ገና ድሮ ጨርሶ አጠናቅቋል። የእጅ ሰዓታችሁ፣ ሁሉም ነገር አልቆለት ነው የመጣው።
የሰዓታችሁ ክንዶች፣… ደከመን ሰለቸን ሳይሉ፣ በሌላ አቅጣጫ ሽርሽር አሰኘን ሳይሉ፣ በእምቢታ ሳያምፁ፣ ለአድማ ሳይጠራሩ፣… ጥበበኛው ሰዓት ሰሪ ባቀደላቸውና በወሰነላቸው መንገድ፣ ጊዜያቸውን ጠብቀው ይጓዛሉ፤ ይሾራሉ፤ ያገለግላሉ።
“Mastermind”
Once upon a time, the planets and the fates and all the stars aligned
You and I ended up in the same room at the same time
And the touch of a hand lit the fuse
Of a chain reaction of countermoves
To assess the equation of you
Checkmate, I couldn’t lose
What if I told you none of it was accidental
And the first night that you saw me, nothing was gonna stop me
I laid the groundwork and then just like clockwork
The dominoes cascaded in a line
What if I told you I’m a mastermind?
And now you’re mine
It was all by design
‘Cause I’m a mastermind
You see all the wisest women had to do it this way
‘Cause we were born to be the pawn in every lover’s game
If you fail to plan, you plan to fail
Strategy sets the scene for the tale
I’m the wind in our free-flowing sails
And the liquor in our cocktails
What if I told you none of it was accidental
And the first night that you saw me, I knew I wanted your body
I laid the groundwork and then just like clockwork
The dominoes cascaded in a line
What if I told you I’m a mastermind?
And now you’re mine
It was all my design
‘Cause I’m a mastermind
No one wanted to play with me as a little kid
So I’ve been scheming like a criminal ever since
To make them love me and make it seem effortless
This is the first time I’ve felt the need to confess
And I swear
I’m only cryptic and Machiavellian ‘cause I care
So I told you none of it was accidental
And the first night that you saw me, nothing was gonna stop me
I laid the groundwork and then saw a wide smirk
On your face, you knew the entire time
You knew that I’m a mastermind
And now you’re mine
Yeah, all you did was smile
‘Cause I’m a mastermind

 ምን ይጠየቃል? ምንስ አማራጭ አላቸው?
የብልሃት ጌቶችና የብልጠት እመቤቶች፣… የጥበብ ልዑላን፣ እንዲህ ናቸው።
እንግዲህ፣ ለራሷ ይህን ማዕረግ ሸልማለች። ሊቀ ጠበብት፣ ብልጧ የብልሃት ልዕልት ነኝ ብላ ሰይማለች። ትናንት ስራዋን ጨርሳችና፣… ዓለም ሁሉ፣ “ተሞልቶ እንደመጣ ሰዓት”፣… የዛሬ ታሪክም እንደ ታዛዥ አገልጋይ፣ የሷን አላማ ለማሳካት ተፍ ተፍ ይላሉ። ሳትናገር እያዘዘች፣ ሳትታይ እየመራች፣ በማይዳሰስ መዘውር፣ በማይጨበጥ ልጓም በስውር ታሾራለች፤ ታስጋልባለች።
በእርግጥ፣ ከሩቅ ሲያይዋት፣ ለጉዳዩ እንግዳ፣ እጇን ያላስገባች፣ የዋህ የዳር ተመልካች ትመስላለች። ደግሞም፣ ተመልካች መምሰሏ አይገርምም። የቤት ስራዋን አስቀድማ አጠናቅቃለች። ዙሪያዋን ፈትሻ፣ ወደ ግብ አነጣጥራ፣ ምሽግና መንገድ አዘጋጅታ፣ ዋሻና ቦይ ቆፍራ፣ ለራሷ አጋዥ ስንቅ ለሌሎች ደግሞ ማባበያ ቅምሻ ወይም ማሰናከያ ወጥመድ አሰናድታ… ሁሉንም ነገር ከጨረሰች በኋላ፣… አንዲት ጠጠር ጣል ማድረግ ብቻ ይበቃታል።
እናም፣ እንደሌላው ሰው ከዳር ሆና ቆማ ታያለች። የነገ ታሪክ፣ ትናንት እሷ በቀደደችለት ቦይ ሲጓዝ ትመለከታለች - ምንም እንደማታውቅ ሆና። ሌሎች የዋህ ሰዎች፣ “ነገር ሁሉ የታሰበበትና ታቅዶ ያለቀለት!” እንደሆነ አይገባቸውም። “ወይ የእድል ነገር፣ ወይ ግጥጥሞሽ ተዓምር!” ብለው ሲያደንቁ እየሰማች፣ እሷም ታዳንቃለች።
የዘፈኗ ስያሜ፣ የግጥሟ ርዕስ፣… እንዲያ ዓይነት የጥበብ ልሕቀትን፣… አድብቶ የመሸረብ ብልሃትን፣… ብልጣብልጥነትን የሚገልፅ ነው። “ነገሩ ሁሉ፣ ገና ድሮ የታሰበበትና የታለመለት ነው” የሚል መልዕክት አለው።
ታዲያ፣ “ብልጥ የጥበብ ልዕልት” ሲባል፣… የባህርይና የዝንባሌ ልዩነት አይኖርም ማለት አይደለም። እንደ ንግሥተ ሳባ ጥበበኛ፣ ወይም እንደ ጣይቱ መለኛ መሆን ይቻላል። እንደ ብልጥ ጦጢት አልያም እንደ ጉደኛዋ ዮዲት፣ ወይም የተራቀቀች የወንጀል ጥበበኛና የማፍያ አለቃ መሆንም አያቅታትም። ወይም የሁሉም ቅይጥና ድምር። እንግዲህ፣ “ጥበቧና ብልጠቷ ለበጎ ያድርግላት!” ከማለት ውጭ ምን ይባላል?
ግን ችግር አለ። የግጥሟ ርዕስ ላይ፣ “mastermind” የሚል ስያሜና ማዕረግ የተሰጣት ልዕልት፣… የት እንደገባች እንጃ!
የመጀመሪያው ስንኟ፣… ስለ እድል ያወራል። ዓለማትና ከዋክብት የተገጣጠሙ እለት፣… እያለች ለmastermind የማይመጥን ትረካ ታመጣለች። (እንደሌሎች የዋህ ሰዎች፣ እሷም የዳር ተመልካች መስላ እያወራች እንደሆነ ወዲያውኑ አይገለፅልንም። ከሦስተኛው ስንኝ ኋላ ነው እንደገና ብልጧ የጥበብ ልዕልት ተመልሳ የምትመጣው።)
እስከዚያው ግን፣ ዓለማት መስመር እንደያዙላትና ከዋክብት እንደተገጣጠሙላት ሆና ትናገራች። ታስመስላለች። እድል ከነ እህቶቿ በአንድ ቃል የፈቀዱና የወሰኑ ቀን፣… እድልና ገድ የተቃኑ ጊዜ፣… የሚሉ መልዕክቶች በላይ በላዩ አከታትላ ትጨምርልናለች። ተዓምረኛ ግጥምጥሞሽ እንዴት እንደተከሰተ ትነግረናለች። ታሪክን የሚቀይር አንዳች ምትሃተኛ እድል እንዴት እንደተፈጠረ መነሻውን ታወራለች። እናም ማቀጣጠያው ተለኮሰ ትለናለች። በሶስት መስመር ነው ይሄ ሁሉ የተገለፀው - በታይለር ስዊፍት ድንቅ ግጥም።
Once upon a time, the planets and the fates and all the stars aligned
You and I ended up in the same room at the same time
And the touch of a hand lit the fuse…
ይሄ አስደናቂ የየዋህ ገፀባሕርይ ታሪክ፣ ለብልጥ የጥበብ ልዕልት ይሆናል? አይሆንም። እንዲህ ሲባል ግን፣ “አስደሳች እድል” መጥፎ ሆኖ አይደለም። ነገሮች ተሟልተው ስክትክት ቢሉ፣ ስኬት ተደራርቦ ቢመጣ ማን ይጠላል? “መታደል” ነው። ነገሮች በበጎ ተገጣጥመው ኑሮ ቢቃና፣ ዓለም ሁሉ ቢፈካ፣ ማን ቅር ይለዋል? ምኞትን የሚያሟላ መልካም “አጋጣሚ” እየደጋገመ ይምጣልን ያስብላል።
ነገር ግን፣ ምኞትና ስኬት፣… በእድልና በአጋጣሚ እንደሚሟሉልን አምነን፣ “ዓለማችን የማርና የወተት ሲሳይ ናት፤… ሕይወትም ግሩም ናት” እያልን ጣፋጭነቷን ለማጣጣም ብንጠብቅ፣ ሞኝነት አይሆንም? ቢያንስ ቢያንስ የዋህነት ነው።… በሕልም እንጂ በእውን አያስኬድም። አያሳምንም።… ቢሆንም ግን፣… እስቲ ጉዷን እንስማላት።
ደግሞስ፣ ባያሳምንም፣ ባያስኬድም፣… እንዲሁ ስናስበው፣… እድልና ገድ፣ አጋጣሚና እጣ ብሎ ነገር የለም ማለት ይቻላል?
ሁሌ ባይሆን እንኳ አንዳንዴ፣… ለማመን የሚከብድ እድል ድንገት ቢከሰትስ? ሁሌም ባይሆን ከስንት ጊዜ አንዴ፣… ነገሮች ሁሉ ተገጣጥመው ኑሮ የሚሰምርበት ታሪክ ቢፈጠርስ?
ለማመን የሚከብደውን ትረካ፣ በአሳማኝ ጥበብ ለመግለፅ የሚረዳ የትረካ አጀማመር አለ። “ከእለታት አንድ ቀን”… Once upon a time።
የተረቶች ዘይቤ ነው። ጥበበኛ ዘዴም ነው - በብልሃት ለሚጠቀምበት።
የተረቶች አንዱ ባሕርይ፣ አጭርነታቸው ነው። እናም፣ የትረካቸውን ቦታና ጊዜ በሰፊው ለመግለፅ ወይም ለመዘርዘር አያመቹም። ቦታንና ጊዜን ከመግለፅ ይልቅ፣ “ውስጣዊ መልዕክትን ያዘለ የተግባር ትረካን” በጥበብ መጥኖ አሳጥሮ ማቅረብ ላይ ነው ዋናው የተረቶች ትኩረት። ደግሞም፣ በጊዜና በቦታ ያልተገደቡ ድንቅ መልዕክቶችን እስከያዙ ድረስ፣ ተረቶቹ የተዋጣላቸው ጥበብ ይሆናሉ። ታሪክ በእርግጥ፣ የግድ ጊዜና ቦታ ያስፈልገዋል። እናም አጭር ዘዴ ይጠቀማሉ። ከእለታት አንድ ቀን፣ በጣም ሩቅ አገር፣… ብለው ይተርካሉ። “ከተማና መንደሩ ባይገለፅ ችግር የለውም” እያሉን ነው። ታሪኩ የተፈፀመበት ዘመንና እለት ላይ አይደለም ዋናው ነገር። ታሪኩ ነው ድንቁ ነገር።… የሚል መንፈስም ያስተላልፉልናል።
“ከእለታት አንድ ቀን” የሚለው የትረካ መክፈቻ፣… ሌላ ተጨማሪ አገልግሎት አለው። ዘወትር የማያጋጥምና ለማመን የሚከብድ አስደናቂ ትረካ ማቅረብ፣… የተረት ብቻ ሳይሆን የልብወለድ ድርሰትና የድራማ ባሕርይ ነው። ኪነጥበባዊ የብቃት መለኪያም ነው።
ግን ደግሞ፣ የዘወትር ሕይወትን፣ ዘላለማዊ እውነታን ገልጦና አጉልቶ የማሳየት ኃይሉ ነው - የኪነጥበብ ጥበብነቱ።
ለማመን የሚከብድ ብርቅና ድንቅ ትረካን፣ በሚያሳምን ብልሃት ማቅረብና የዘወትር ሕይወትን ከዘላለማዊ እውነታ ጋር አፍክቶ ማሳየት፣… የኪነጥበብ ድርሻ ነው። የኪነጥበብ ድርሻ ነው። ሊወጡት የማይችሉት ከባድ ስራ ይመስላል።
ለማመን የሚከብዱ ክስተቶችንና ተግባራትን መስማት ምን ይሰራልናል? በእውን የማይፈጸም ይፈፀማሉ። አንዳንዴ ብቻ ከሆነ፣… “ከእለታት አንድ ቀን”፣ ለማመን የሚከብዱ ታሪኮች ቢፈጠሩስ? ለማመን የሚከብድ ቢሆንም፣ አሳማኝ ሊሆን ይችላል ብለው ሊያግባቡን ይሞክራሉ- ተረቶች። ባያሳምኑንም እንኳ እስቲ ይንገሩን እንስማቸው ብለን ጆሮ እንድንሰጥ፣ አይናችንን እንድንከፍት ያግባቡናል። ብርቅና ድንቅ ነገር የመስማት ጉጉታችንን በመኮርኮር፤ የፈጠራ ልብወለድ ታሪክ ይጋብዙናል። ምግቡንና መጠጡን በየዓይነቱ እያቀረቡ ምናባዊው ዓለም ውስጥ ያስገቡናል። ዋናውንና አሳማኙን የኪነ-ጥበብ ምትሃት የሚመጣው ያኔ ነው። በእርግጥም ትረካቸው ለማመን የሚከብዱ አስደናቂና ብርቅዬ ታሪኮች ናቸው። ዘወትር የማይከሰት በእውን ያልተፈጸመ ታሪክ ነው የሚነግሩን። ውስጣዊ መልዕክቱ ግን፣ የእለት ተእለት ኑሮንና የሕይወት ሚስጥርን ገልጦ የሚያሳይ ነው።  የዘወትር ውሎና አዳራችንን ዘላለማዊ እውነታንና የሕይወት ትርጉምን ነው የምናጋራው።
የፈለጋችሁትን ቀን ተመልከቱ፣… ከእለታት አንዱን ቀን አስተውሉ። ኪነጥበባዊውን እውነት በዘወትር ሕይወታችን ውስጥ ታዩታላችሁ ድንቅና ብርቅ ነው ኪነ-ጥበብ።
ወደጀመርነው የግጥምና የዘፈን ጥበብ እንመለስ።
ዓለማት መስመር ይዘው፣ ከዋክብት የተገጣጠሙ ጊዜ፣… ዕድል፣ እጣና ፈንታ በአንድ ድምፅ የወሰኑ ዕለት ምን እንደተከሰተ ትተርካለች። እንደ አጋጣሚ እንደ ዕድል ሆኖ፤ እሱ እና እሷ በአንድ ቦታ እንደተገኙ፣ በአንድ ጊዜ እንደደረሱ ታወሳለች።
የቅፅበት ዕድሜ በሌላት የመዳፍ ጨረፍታ፤… “ያልታሰበ” ብልጭታ ተፈጠረ።
ድንገት የተጫረው ቅንጣት እሳት፣ “እንደ አጋጠሚ” ማቀጣጠያውን ነክቶ ለኮሰው።
የመንስኤና የውጤት፣ የሰበብና የመዘዝ ሰንሰለት ተያይዞ እየተቀጣጠለ እየተግተለተለ ይመጣል።  እርምጃና ስንዘራ፣ ምላሽና አፀፋ እየተከታተሉ፣ በየተራና በዙር፣ በምልልስና በቅብብሎች እንዲመጡና እየገሰገሱ እንዲሄዱ ነው፣ ማቀጣጠያው ቁልፍ የተለኮሰው።
የዘፈቀደ ውጣውረድ፣ የአጋጣሚ ደርሶ መልስ፣ ያለ ሃሳብ መሾር፣ በተገኘው ቀዳዳ መንደርደር… ይመስላል እንጂ ለካ የታሰበበት ነው። መምጫና መሄጃው በመሬት ስበትና በአውሎ ነፋስ፣ በእንቅልፍ ልብ ወይም በደመነፍስ ይመስላል። ግን የተታቀደ ነው። የሦስተኛው ስንኝ የመጨረሻ ቃላት ናቸው ይህ የሴራ ፍንጭ የሚጠቁሙን። ታዲያ፣… ማቀጣጠያው ቁልፍ ተለኮሰ ማለቷ ለምን ሆነና!
ቀላል ንክኪና ቅንጣት ብጭታ የሚበቃው፣ በቅጽበት የሚለኮስ፣ ተዘጋጅቶ የሚጠባበቅ ቁልፍ አስቀድማ አጥምዳለች። ተለኩሶ ዝም አይልም።
በእርግጥ፣ ይህን ምስጢር የምታውቀው እሷ እንጂ፣ ሌላው ሰው፣ እንደ ተዓምር ይገረማል። …ወይ ያጋጣሚ ነገር፣ ወይ የዕድል ነገር!… ይህ ሁሉ ይፈጠራል ብሎ ማን አሰበ?ይላል ብጠቷን ያወቀ ሰው።
እሱ እና እሷ መገጣጠማቸው የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም ለካ። እሱን ለመሰዘል። ለመሁኔታውን ለመፈተሸ፣ አኳኋኑን ለማጥናትና ወደ ግብ ለማመቻቸት፣ ወደ ድል ለማድረስ የታሰበ እንደሆነ ትገልፃለች። ነገረ ሥራዋ ሁሉ፣…እንደስለላና እንደ ምስጢራዊ ዘመቻ፣ እንደ ቼዝ ፍልሚያ አድርጋዋለች። ያነጣጠረችበት ኢላማ፣ እንደ ታዳኝ አንበሳ ወይም እንደተቀናቀቃኝ ንጉሥ፣ ትቆጥረዋለች።
ወይስ እንደ ሂሳብ ቀመር ሆኖ ነው የታያት? በምን ተካፍሎ ከነ ቀሪው ታይቶ፣ በምን ተባዝቶ፣ ስንት ተጨምሮበት፣ አንድ አለኝ ተብሎ… ግራ ቀኙ ሲሰላ ስንት ይሆናል ብላ የምትመረምር ስለላ የምታካሂድ መሆኗን ትናገራለች፣… ከዚያም አሰላለስላ ወደ ውጤት ልታደርሰው ነው ያሰበችው።
 በስለላና በእቅድ የተራራቀ የጥበብ ዘመቻም ይመስላል እንደ ቼዝ።  በቀኝ አስመስላ በግራ እየሄደች፤ ጦሯን ትወረውራለች። ከፊት ለፊት መጥታ በጀርባ በኩል እየዞረች፤ በሩን በርግዳ ትገባለች። የመጨረሻውን ቀስት ታነጣጥላለች። ወደ ግቧ ደርሳች። “ተያዝክ! ተቆጣጠርኩህ!” የማለት ያህል ነው ፉከራዋ።
ዕድል የሰመረ፣ ከዋክብት የተገጣጠሙ እለት ብላ ነበር የጀመረችው። እንደ አጋጣሚ መገናኘት፣ በድንገት መነካካት እያለች ነበር የምታወራው። በቅንጣት ጨረፍታ፣ ማቀጣጠያው ተለኩሶ፣ በዚህ ሰበብ የተጫረ እሳት ሌላውን አያይዞ፣ የስንዘራ እና የአፀፋ ሰንሰለት እየተመዘዘ መጣ - በግጥጥሞሽ፣ በእድል።
ትረካዋን እንዲህ ከጀመረች በኋላ፣… ይሄ ሁሉ ታሪክ በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን ቀድሞ የታሰበበት፣ በእድል የተከሰተ ሳይሆን ሆን ተብሎ የታለመና የተወጠነ፣ በጥበብና ዘዴ የተፈፀመ ታሪክ ነው ትላለች።
በእርግጥ በግልጽ አላወጀችም። እንዲያውም አምልጧት የተናገረች ነው የምትመስለው።
መግቢያ ቁልፉን አግኝታ፣ በስልት ገብታ፣ የዋህ መስላና አድብታ መሳሪያውን አስጥላ፣ ወደ አጣብቂኝ ከተተችው። ማምለጫ እንደሌለው ስታረጋግጥ እጅ ወደ ላይ ብላ ልትማርከው በእጇ ልታስገባው ነው።
ጥበብና ብልጠቷ እንዲታወቅ ታላቅ የጀብድና የድል ዘመቻዋም በታሪክ እንዲመዘገብላት የምትጓጓ ጀማሪ ጦረኛ ናት? የባንክ ካዝና እየዘረፈች የገንዘብና የወርቅ ዙፋን ላይ ከተቀመጠች በኋላ የዝርፊያ ጥበብና ብልሃቷ ሳይታወቅላት መቅረቱ የሚቆጫት፣ ከዚህም ጎን ስርቆት ጥፋት መሆኑ፣ ሌባ መሆንም እንደሚያሳፍር ማሰቧ አይቀርምና ተናግራ ለመገላገል እንደምታምጥ ትመስላለች። እንደ ሃይለኛ የወንጀል ጥበበኛ ናት። አፍረጥርጣ ለመናገር፣ የተደበቀውን ሴራ ለመግለጥ ታመነታለች። ግን ደብቃ ለማቆየት አትችልም። አንዴ ከአፍዋ አምልጧል። ማቀጣጠያ ወጥመድ (fuse)፣ የሚል ቃል መናገሯ ስራዋን ያጋልጣል። ሰንዝራና አፀፋ፣ ስለላና ቀመር እያለችም ተናግራለች። እንዴት እንደማረከችው፤ አውርታለች።  ማንም እንደማይችላት፣ አሸናፊነቷ አይቀሬ እንደነበረ ገልጻለች- እንደቀረርቶ ቁጠሩት። የግጥም ጥበብ ድንቅ ነው። በ25 ቃላት ነው ይህን የነገረችን። ከዚህ በኋላ የዘመቻዋ ምስጢር የገድሏን ዝርዝር መደበቅ አትችልም። ግን ደግሞ፤ ለመናዘዝ የምትፈልግም አትመስልም።ብልጥ የጥበብ ልዕልት መሆኗን ስትነግረን፣ ተግባሯን ስታወራልን፣ የጀብድ መግለጫ፣ የድል ማግስት ፉከራ መሆኑ አያጠራጥርም። የተዋጣለት ድንቅ ሴራ በጥበብ እስኪሳካ ድረስ፣ ድብቅ ምስጢር ነው። ምስጢርነቱን ትፈልገዋለች። ከተሳካ በኋላ ግን፣ ምስጢርነቱ ያስጨንቃታል፤ ውስጧን ፈንቅሎ ከሚወጣ የድል ስሜት ጋር አይጣጣምላትም። እናም የስኬት  ፌሽታዋ፣ ምስጢርን የሚያጋልጥ የኑዛዜ መልክ እየተላበሰ የጥፋተኝነት ስሜትን ይቀላቀልባታል።
ይህን ላለመቀበል ትጥራለች -ብልጧ የጥበብ ልዕልት። ምክንያት ትደረድራለች።
ብልጥ መሆን ለጥበበኛ ሴቶች የግድ ነው ትለዋለች። ሴረኛ ወይም ሸረኛ የመሆን ጉዳይ እንዳልሆነ እንዲያምንላት፣ ስትራቴጂ ነው ትላለች። ነገሩን ለማካበድና ከምሁራዊ ዜማ ጋር ለማጠጋጋት።
“ለስኬት ሳታቅድ ከቀረህ፣ ከስኬት ለመቅረት ታቅዳለህ” ትላለች- በየጊዜው እንደፋሽን የሚናፈስ አባባል መርጣ።
እና ጥፋቴ ምኑ ላይ ነው ብላ ትከራከራለች። የጥበበኛ ሴቶች ተቆርቋሪ ለመሆን ይቃጣታል። የግዙፍ ተቋም መሪና የምሁር ቃላትን ታመጣለች። ዘመነኛ አባባልም አልቀራትም።
እንዲያውም ይባስ ብላ እንደገና ትፎክራለች። ሰዎች፣ በዘፈቀደ ፈረሱ እንደመራን ሽርሽር ሄድን፣ ሞቅታ ስለገፋፋን ጨፈርን ይላሉ። ብልጧ የጥበብ ልዕልት እንደምታሽከረክራቸው አያውቁም። ጀልባዋን የማስኬድና አቅጣጫዋን የምወስን ነፋስ ነኝ ትላለች። የፈረስ ልጓም ነኝ። የመጠጥ ውስጥ አልኮል ነኝ ትላለች።
በእርግጥ፣ እስካሁን ሙሉ ለሙሉ አልተናዘዘችም። ጥፋተኛ ነሽ ብሎ የከሰሳትም የለም።
“ብልጥ የጥበብ ልዕልት ነኝ ብዬ ብነግርህስ?” በሚል አሻሚ አባባል ተከልላ ነው የምትፎክረው። እንደመናዘዝ የምትሞክረው። ከጥፋተኝነት ስሜት ማምለጥ አልቻለችም። ብታንገራግርም  መናዘዝ አልቀረላትም። እንደ ወንጀለኛ ውስጥ ለውስጥ በምስጢርና በጥበብ መስራት ለምዶብኝ ነው ብላ የጥፋት ማቅለያ ሃሳብ ታቀርባለች። በልጅነት እድሜ አብሮኝ የሚጫወት ጓደኛ አጥቼ፣ እንዲወዱኝ ፈልጌ… እያለች ምክንያትና ሰበብ ታቀርባች። ይህም ግን አላዋጣም። ጥፋቷን ሸፋፍና ማለፍ አልፈለገችም።  የጥበብ ልዕልት መሆን አንድ ነገር ነው። ሰውን እንደ ማሽን፣ ተሞልቶ እንደመጣ ሰዓት መቁጠር ግን፣ በጎ አይደለም። በሰው ለመወደድ ሰው ላይ ለማሴር መሞከር፣ ለጥፋት ነው። እናም ትናዘዛለች።
መናዘዟም እሷ ልብ ውስጥ ለእሱ ቦታ ስለምትሰጥ ነው ትላለች። ክፋ አለማሰቧንም ትጠቁማለች። ትምላለች። በይቅርታ ስሜት።
ቢሆንም ግን፣ ብልጥ የጥበብ ልዕልት መሆኗን ደግማ ትናገራለች። እንደ ጥፋት አትቆጥረውም። ብልጣብልጥነትን አስቀርታ ጥበብን አጥብቃ እየያዘች ይመስላል።አስገራሚው ነገር፤ እሱም ቀድሞውኑ አውቋታል። እሷ በስውር አዘውራለሁ ብትልም፤ ገና ከመነሻው ገብቶታል። ገብቶትም ፈቅዷል። የሴራ የሸር መንፈሷን ሳይሆን፤ የጥበብና የብልሃት ልዕልትነቷን ያደነቀ የወደደ ይመስላል።
ዞሮ ዞሮ፣ በእጇ የገባው፣ በጥበብ ልዕልትነትዋ ተማርኮ ነው ማለት ይቻላል።
ጥበበኛው ግጥም፣ እንደ ሌሎቹ ድንቅ የኪነጥበብ ትረካዎች፣ በአስደናቂ የትረካ እጥፋቶች፣ የአድማጮችን መንፈስ እያሾረ ወደ አይቀሬ ኢላማው ደረሰ።
ከጥበብ ልዕልት የፈለቀ፣ በብልሃትና በእውቀት የተቀናበረ ድንቅ ግጥም ነው።

Read 988 times