Saturday, 08 April 2023 19:51

“ተረኛ ነኝና፣ እንዳትቸገሪ”

Written by  -ሌ.ግ-
Rate this item
(4 votes)

ይሄንን ፅሁፍ ለመጻፍ ስቀመጥ ብዙ ሀሳቦች በጭንቅላቴ ውስጥ እየተመላለሱ ነው። ለሚመላለሰው የተዘበራረቀ ስሜት መንስኤ የሆነኝ አንድ ፎቶ ነው። ፎቶው በሶሻል ሚዲያ የተለቀቀና ብዙ ሰውንም ጮቤ ያስረገጠ ነበር።
አንድ ሰውዬ እጁ ላይ ካቴና ጠልቆበት፣ በሁለት ፖሊሶች እየተነዳ ሲወሰድ የሚያሳይ ነው። ሰውየው በአለባበሱም ሆነ በሌላው ሁኔታ እንደ በፊቱ ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት እንደሚመስለው ነው።
 እጁ ላይ የጠለቀችው ካቴና ግን የምስሉን መልዕክት፣ከዚህ በፊት ወደማይታወቅ ትርጉም አዙራዋለች። ሰውየው አሁን የህግ እስረኛ መሆኑን ትናገራለች። ከፎቶው በላይ አንድ ለምሬት የተመዘዘች የዘፈን ሀረግ አለች:- “ተረኛ ነኝና”  የምትል፡፡
እና ዋናው ጥያቄ ለምን ገረመኝ? የሚል ነው። ለምን ሰውየው አንድ ተራ ሰው መሆኑን ዘነጋሁ? አዎ፤ ዋናው ጥያቄ  ይሄ ነው። ጥያቄውን ግን ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለማንም የኢትዮጵያ ህዝብ መቅረብ  የሚገባው ነው፤ ካቴና ከጠለቀበት ሰውዬ ጭምር።
ብዙ ችግሮች የሚመጡት ሰው መሆንን ከመዘንጋት ነው። በመሰረቱ ሁሉም ተራ ሰው ነው። አንድ ተራ ሰው በስነ-ልቦና ወይም በባህርይ መወላገድ ምክንያት መሳሪያ ሊሆን ይችላል። ወይንም ደካማ። ወይንም ውሸታም። ወይንም አሉባልተኛ። ወይንም መንደር ውስጥ ወሬ እያፈነፈነ፣ ጎረቤት ከጎረቤት የሚያጋጭ…ወይንም ሌላ ብዙ፡፡ ለዚህ ሰውዬ ግን  ስልጣን  ከተሰጠው፣ ወይንም በሀገር ደረጃ ሃላፊነት ቦታ ላይ ከተቀመጠ ውሸታምነቱ በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን በሀገር ደረጃ ጥፋት የሚሰራ ይሆናል። የራሱን ብቻ ሳይሆን ትውልድን የባከነ የማድረግ አቅም ያገኛል።… ስልጣኑ፤ እሱን ራሱን ተራ ስለመሆኑ ያስረሳዋል። እኔንም አስረስቶኝ ነበር። ባያስረሳኝ ኖሮ አቶ በረከት ስምኦን በመታሰሩ አልገረምም ነበር።… ግን እኔን ብቻ አይደለም ያስገረመው። የሰው መልክን ማንበብ ክህሎት ባይሆንም፣ ራሱን ባለካቴናውንም የገረመው መስሎኛል። ለምን ገረመው ቢባል (እርግጥ ገርሞት ከሆነ)፣ “ተራ ሰው መሆኑን በማወቁ”  መልሴ ነው።
የተደረበ የፕሮፓጋንዳና የስልጣን ካባ (መሰረታዊውን፤) በክንብንቡ ስር ያለውን ጥሬ እውነት ያስረሳናል። ጥሬው እውነት፤ ሁላችንም ተራ ሰዎች መሆናችን ነው፡፡ በተራ ሰው  ላይ ቀጥለን ያስረዘምናቸው ተጽእኖዎች ሲያልቁ፣ የሚገኘው ተራ ሰውነት ብቻ ነው። ለተራ ሰው የሀገርንም ሆነ ማንኛውንም የአብሮነት እሴትን እንደፈለገው እንዲያጨማልቅ ሙሉ ስልጣን መሰጠት የሌለበት ለዚህ ነው።
ሰውዬውን መቅጣት ተገቢ ነው። ግን የበለጠ ተገቢ የነበረው መጀመሪያውኑ ስልጣን እንዳይቆናጠጥ ማድረግ ቢቻል ነበር። ሰውዬው እና እሱን መሰል ወንጀለኛ ሰውዬ በአንድ ካቴና የሚታሰሩ ናቸው። በቀላሉ ማሰር የማይቻለው በሀገር እጣ ፈንታ ላይ  ያደረጉትን ጥፋት ነው።
ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንዳረፉ በሰማሁበት ማለዳም፣ በሰው ፊት ላይ ተመሳሳይ መደንገጥ ነው ያየሁት። ዜናው ሲሰማ በተቀመጥኩበት ቁርስ ቤት ውስጥ የነበሩት በአብዛኛው የሰውየው ደጋፊ ነበሩ። ወይንም በዛ ወቅት ደጋፊ የማይመስል በፖለቲካው ባህል ስለማይደገፍ ደጋፊ መስለዋል። ዜናውን ለመቀበል ተቸግረው ሲያምጡ ሁሉ ትዝ ይለኛል።
ጠ/ሚኒስትሩ ራሱን የሀገሪቷ መሪ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪ አድርጎና መስሎ ለብዙ ዓመታት ስለኖረ፣ በድንገት መሞቱን መቀበል ተሳናቸው። መሞቱን መቀበል ሳይሆን፤ በድንገት ተራ ሰው መሆኑን መቀበል ነበር ትንቅንቁ። ምክንያቱም ተራ ሰው መሆኑን የተቀበለ፣ የተራ ሰው ድክመቶችንም መቀበል የግድ ይሆናል። ተራ ሰው ዘላለም እንደሚኖር ፈጣሪ፤ “ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለህም” አይልም። “ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለህም” ብሎ ዘላለማዊ በሚመስል ፕሮፓጋንዳ ቆይቶ በድንገት ከሞተ፣. አምላክቱን ዘንግቶ ሰውነቱን ለመቀበል በሚደረግ ግጭት ውስጥ አማኝ ግራ ይጋባል፡፡
አዎ፤ አማኝ ነው ያልኩት። ሰውነትን አስረስቶ ርዕዮተ ዓለምን የሚያስመልክ እምነት፣ መጨረሻ ላይ ከግድግዳ ጋር ያጋጫል። ግርግዳው እውነታው ነው። ወይም ብቸኛው እውነት፤ ሁሉም ተራ ሰው መሆኑ ነው። ለሀገሩ ወይም ለሰው ልጅ እጣ ፈንታ ማንኛውንም አይነት አስተዋጽኦ ስላደረገ፣ ወይንም ያደረገ ስለመሰለው፣ ሰው አምላክ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም አምላክ አይሞትም፤ አምላክ አይደማም፤ወይንም አምላክም ራሱ ለመድማት እና ለመሞት ከፈለገ፣ ተራ ሰው ሆኖ በምድር መወለድ  የግድ ያስፈልገዋል፡፡ በመሰረቱ ከተራ ሰውነት ባሻገር ቅጣይ ካስፈለገ፣ መቀጠል ያለበት ይረሳል።  “ስራው ወይ ያበለፅጋል አልያም ያጠፋፋል፡፡” ስራው ያወጣዋል ወይንም ይቀብረዋል፤ስራው ወይ ከራሱ ያለፈ ማንንም የማይነካ ነው ወይንም የሌሎችን ህይወትና ተስፋ በቀጥታ በእሱ ስራ ተፅእኖ ስር የሚጥል ነው››
በካቴና ታስሮ ሲነዳ ያየሁት ሰውዬ፣ ስራው የግሉ  ብቻ ሳይሆን የሀገር እጣፈንታ በተዘዋዋሪ ሳይሆን በቀጥታ የቀረፀ ነበረ። ስለዚህ ከስራው አንፃር መጠበቅ አለበት።  ‹‹እሱንም የሚጠይቅ ህግ አለን ወይ›› የሚለው ነው ያስገረመን፡፡ ‹‹ግርምታችን እውነት ህግ እንዳለ በማወቃችን ከአዲስ እምነት ጋር ስንተዋወቅ የፈጠረብን አዎንታዊ ግርታ ነው›› ከግርታው ማለፍ በኋላ መፈንደቅ ይከተላል፡፡
ህያው ህግ ካለ የተለየ ሰው በመሰረቱ አይፈጠርም፤ ሌላ ምድራዊ አምላክ አያስፈልግም። ‹‹የዚህ ሰውዬ ኔትወርክ ከካቦ የጠነከረ ነው…. ስለዚህ የእነ አብይ መንግስት ከሱ ጋር ተስማምቶ ቢሰራ ይሻላል›› የሚል አይነት ፅሁ፣ ከፌስቡክ ተራ አስከባሪዎች በአንዱ ተፅፎ፣ ቀደም ሲል አንብቤአለሁኝ፡፡ ባለ ካቦ ኔትወርኩ በእስር ቤት ካቦ ስር እንዲተዳደር ከመላኩ ብዙ ወራት ቀደም ብሎ፡፡
ህያው ህግ ካለ የሰው ኔትወርክ፣ እንደ ካቦ ለፖለቲካ መጎተቻነት አያስፈልግም፡፡ የህግ ትርታ መኖሩን የሚያሳይ ነው፣ የትልቁ ሰውዬ መጠየቅ፡፡ ትልቁን ሰው እንደ ማንም ተራ ሰው ላጠፋው ወንጀል ለመጠየቅ የህግ ትርታ ያስፈልጋል፡፡ ሰውየው እንዲጠየቅ የሆነው በፖለቲካ ውሳኔ እንጂ የጨቅላው ህግ እርግብግቢት እየጠና በመምጣቱ አይደለም የሚሉ አሉ።
እኔ ግን የምለው እንደ ሀላፊና እንደ አጠፋው ጥፋት ከአናቱ ጀምሮ መጠየቅ የሚያስችል ፖለቲካ ከመጣ፣ እሱ ፖለቲካ የህያው ህግ ቀኝ እጅ ስለሆነ፣ እሰየው የሚያስብል ነው፡፡  ከታች ያሉ ተላላኪዎችን እየለወጡና በሌላ ስፍራ በሌላ ተልእኮ እያስቀመጡ፣ “ከሞት በስተቀር የሚጠይቀን የለም” ያሉበት ፖለቲካ ነው፣ ህያው ህግ እንዳይወለድ የከለከሉት ባይ ነኝ፡፡ እንደ ተራ ሰው የማስበው ይሄንን ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ሰውዬው ካቴና አጥልቆ ሳይ፣ የሀዘን ስሜት ተሰምቶኛል። በሰውየው አማካኝነት የተደረገውን ሁሉ እንደ ማንኛውም ሰው ተከታትያለሁኝ፡፡ የምጠላው ኢህአዴግ በመልክ ሲመስል፣ ይኼንን  እንደሆነም አውቃለሁኝ፡፡ የሚያደርገው ንግግር እንደኔ የሚያቃጥለው ሰው የለም፡፡ ግን ተራ ሰው ሆኖ እጁ ላይ ካቴና ገብቶ ሳይ አሳዘነኝ፡፡ ጥፋት የሚሰራበትን ተራ ሰውነቱን ቅጥያ ሲነጠቅ፣ ማንም ተራ ሰው እንደ አቅመ ቢስነቱ ያሳዝናል፡፡ ስልጣን ያባልጋል፡፡ ፍፁም የሆነ ስልጣን ደግሞ ፍፁም ሰይጣን ያደርጋል፡፡ ስልጣን የሆነ ነገር እንዳያገኝ ከተደረገ፣ ይኼም ሰው ተራ ይሆናል፡፡ ….ግን ማዘን የነበረብኝ በፊት ከእነ ስልጣኑ በሆነበት ጊዜ ነበር፡፡ ያኔ ነበር በእብሪት ካቴና  የታሰረው፡፡ በካቴና ታስሮ ሌሎችን ያስር እና ያሳድድ በነበረ ጊዜ ነበር  የሚያሳዝነው። የሚያሳዝነው ሞኝነቱ ነበር፡፡ ተራ ሰው የሚሆንበት ጊዜ ፣ ሲቀጥልም እንደ ማን ተራ ሰው የሚሞትበት ጊዜ መምጣቱ እንደማይቀር አለማወቁ ነው የሚያሳዝነው፡፡
የዶስትየቭስኪ ድርሰት (Brothers Karmazof) ውስጥ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ስልጣን ከመናፍቃን ለመጠበቅ በሚል ወንጀለኛ ናቸው የሚላቸውን እየመረመረ የሞት ፍርድ የሚፈርደው፡- ‹‹ግራንድ ኢንኩዊዚተር›› ይመጣብኛል፡፡
በመሰረቱ ግራንድ ኢንኩዊዚተር፣ ይኼንን የመናፈፍቃን አደን (witch hunt ) የሚያደርግ፤ ጥፋተኛ የሆነውን ካልሆነው ለይቶ ለመቅጣት ሳይሆን ለማሸማቀቅ ነበር።
በዶስትየቭስኪ ድርሰት ውስጥ በግራንድ ኢንኩዊዚተሩ፣ የሞተ ሲያስነሳ ተይዞ የሚቀርበው ወንጀለኛ እየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው፡፡ ግራንድ ኢንኩዊዚተሩም ክርስቶስን እንደያዘ አውቋል፡፡ እንዲህም ይላል፡- ‹‹አንተ ለምጠይቅህ ጥያቄ ምንም መልስ እንደማትሰጠኝ አውቃለሁኝ፡፡ ምክኒያቱም የምትናገረውን ሁሉ በመፅሀፍ ቅዱስህ ተናግረሃል፡፡ አሁን ምንም የምትጨምረው የለህም፡፡ ለእኛ (ለቤተክርስቲያኗ) ያንተን ትዕዛዝ እንድናስፈፅም ሀላፊነት ሰጥተኸን፣አሁን ከቃልህ በተቃራኒ በዚህ ዘመን መጥተህ በእኛ ስራ ለምን ትገባለህ?›› ይለዋል፡፡
እናም እነዚህ “ህግ እና ስርዓት እኛው ነን” ብለው ተቀምጠው የነበሩ ሰዎች፤ በፍርድ ቤት ቀርበው ሲጠየቁ፤ “ግራንድ ኢንኩዊዚተሩ ያለውን እንዳይደግመው” ስል በውስጤ አስባለሁኝ፡፡
‹‹ህግ በሰጠን ስልጣን ለሀገሪቷ ብልፅግና እና ልማት የተቻለንን ሁሉ ደከምን ነገር ግን ህግ የሰጠንን ስልጣን ስናስፈፅም መልስ ህግ ወንጀለኛን›› ምናምን ሊሉ ይችሉ ይሆናል፡፡
‹‹ህግ በሰጠን ስልጣን›› ሲሉ ህጉንም የሚፅፉት ሆነ፣ በፃፉት ህግ መሰረት ለራሳቸው ስልጣን የሚሰጡት እነሱው መሆናቸው ይዘነጋቸዋል።
“ለሀገሪቷ ብልፅግና እና ልማት የተቻለንን ሁሉ ደከምን…ወዘተ” ለሚለው ደግሞ መልሱ፡- “ለሀገሪቷ መድከም” ስራቸው ነው፡፡ ቢሳካ አያስመሰግናቸውም፤ ባይሳካ ግን ያስጠይቃቸዋል፡፡ በልፅጎ እና ለምቶ የተገኘው ሀገር ሳይሆን፤ ጥቂት የሰረቁ ግለሰቦች መሆኑ ያስጠይቃል፡፡ መጠየቅ የሚችለው ህያው ህግ ብቻ ነው፡፡ በሞተ ህግ የፖለቲካ ወንጀልን  ማፋፋት እንጂ መዳኘት አይቻልም፡፡

Read 1772 times