Saturday, 08 April 2023 19:54

የምስጋና ተዓምራዊ ሃይል!!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ለማሰብ እጅግ አስከፊ ከነበረ ሁኔታ ውስጥ በምስጋና ኃይል፣ ህይወታቸውን ሙሉ በሙሉ የለወጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አውቃለሁ። ፈጽሞ ተስፋ የሌለው የሚመስል የጤና ጉዳይ፣ ተአምር የሚያሰኝ ውጤት አምጥቷል።
ሥራቸውን ማከናወን ያቃታቸው ኩላሊቶች እንደገና ሲያንሰራሩ፤ የታመሙ ልቦች ሲፈወሱ፤ የታወሩ አይኖች ሲበሩ አይቻለሁ። የተበጠሱ የግንኙነት ክሮች ተቀጥለው ወደ ሰመረ ግንኙነት መቀየራቸውን አውቃለሁ- በምሥጋና ተዓምራዊ ሃይል!!
 አለቀለት የተባለ ጋብቻ ሲታደስ፤ የተራራቁ የቤተሰብ አባለት እንደገና ሲገናኙ፣ የወላጆችና የልጆች ግንኙነት እንደ አዲስ ሲገነባና መምህራን ተማሪዎቻቸውን ሲለውጡ ሁሉ አውቃለሁ።
በምስጋና አማካኝነት፣ ቤሳ ቤስቲን ያልነበራቸው ድሆች ባለጠጋ ሲሆኑ፣ የከሰረ ንግዳቸውን እንዲንሰራራ ሲያደርጉ፤ እድሜ ልካቸውን ከገንዘብ ጋር ግብግብ ገጥመው ሲንጠራወዙ የነበሩ፣ የተትረፈረፈ ሀብት ሲፈጥሩ አይቻለሁ።
አንዳንዶቹም እንዲያውም፣በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ፣ ከጎዳና ተዳዳሪነት ወጥተው ባለሥራና ባለመኖሪያ ቤት ሆነዋል። በድብርት ውስጥ የነበሩ ሰዎች አስደሳችና የተሳካ ህይወት መቀዳጀታቸውን አውቃለሁ። በጭንቀትና በተለያዩ የአዕምሮ ህመሞች ሲሰቃዩ የነበሩ ሰዎች፣ በምስጋና አማካኝነት ፍጹም የአዕምሮ ጤናቸው ተመልሶላቸዋል።
ሁሉም የዓለም አዳኞች፣ ምስጋናን ተጠቅመውበታል። ምክንያቱም ምስጋና እጅግ ላቅ ካሉት የፍቅር መገለጫዎች አንዱ መሆኑን ያውቃሉና። ምስጋናቸውን ባለማጓደል ሲያደርሱ፣ ህጉን  በትክክል ጠብቀው እየኖሩ መሆናቸውንም ያውቃሉ።
ኢየሱስ ክርስቶስ  እያንዳንዱን ተአምራት  ከመፈጸሙ በፊት፣ “አመሰግናለሁ” ይል የነበረው ለምን ይመስላችኋልሃል?
የሰዎች ውለታ በተሰማችሁ ቁጥር ፍቅርን እየሰጣችሁ ነው። የሰጣችሁት ደግሞ ተመልሶ ይሰጣችኋል። ሰዎችን ስታመሰግኑ ይሁን ለመኪናችሁ፣ ለአዲሱ ቤታችሁ፣ ለዕረፍት ጊዜያችሁ ወይም ለምትጠልቅ ጀንበር (Sun Set) አሊያም ለተበረከተላችሁ ስጦታ ወይም ደግሞ ለገጠማችሁ አስደሳች ክስተት ምስጋና ስታቀርቡ፣ ለእነዚህ ነገሮች ፍቅር እየሰጣችሁ በመሆኑ በአጸፋው የበለጠ ደስታን፣ የበለጠ ጤንነትን፣ የበለጠ ገንዘብን፣ የበለጠ አስደሳች ሁኔታዎችን፣ የበለጠ አስደናቂ ግንኙነቶችንና የበለጠ ምቹ አጋጣሚዎችን ታገኛላችሁ።
(ተአምራዊ ኃይል - The Power)

Read 983 times