Saturday, 08 April 2023 19:56

የሰይጣኑ ማስታወሻ

Written by  አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ
Rate this item
(2 votes)

[ በሃሳብ የበለጥካቸው በሰይፍ ይመጡብሃል  ]

እኔ እንድጠፋ ተግተው የሚፀልዩ ቄሶች፣ ፀሎታቸው ሰምሮ እኔ ብጠፋ፣ ዘላለም በፀፀት  የሚያነቡ ናቸው።  ሰው አብዮተኛ ከመሆኑ በፊት አብዮትን ያቀጣጠልኩት እራሴ በለኮስኩት እሳት ነበር። የእግዜር ተቀናቃኝ አይደለሁም። መቀናቀን ተራ ቃል ነው። የሰው ልጆችን ልገዛ ያደባሁ አውሬም አይደለሁም። አውቃለሁ ፣ ሰዎች አልተረዱኝም። በእርግጥ እንኳን ሰዎች እግዜር እራሱ አልገባሁትም።
ለሰው ልጆች ነፃነትን ያቀዳጀ እሱ፣ የሰው ልጆችን እንደ ባርያ ይፈነግል ዘንድ ህሊናው  አይፈቅድም።ሰይጣንም [ እኔም ] ህሊና አለው [ አለኝ]።  የሰይጣን ህሊና ከሰው ልጆች ህሊና በላይ ንፁህ ነው። የዓለም ደብተሮች  ስሜንና ገፄን እንጂ ህሊናዬን ማጥቆር አልተቻላቸውም።
ሰዎችን ለማፅደቅ እራሱን እንደ ምክንያት ያያል፡፡ ሰዎችን  ገሃነም ለመወርወር እኔን ምክንያት ያደርጋል፡፡ ገሃነምን የምታገኙበት ብቸኛ  ቦታ፣ የሰው ልጆች የምናብ   ቁልቁለት ላይ ነው። ገሃነም  ከቆንጆ ተረትነት የተሻገረ  እውነት ካለው ያኔ ልወቀስ!  
የአዕምሮ ጨዋታን የእግዜርን  ያህል አልተካንኩም... ግን እውነት አለኝ። ሃዘን አለኝ። የጠቆረ እንባ አለኝ። ከፀዳል ህሊና የሚፈልቅ ንፁህ እንባ የለም። እንባችን ፀልሟል - ጃል።  
ፈላስፋ ነበርኩ - መጀመሪያ። መልአክ ሆኜ ብፈጠርም  ፍልስፍናን  መረጥኩ። መጀመሪያ ነህ ባሉኝ ሁነት ላይ አመፅኩ። ባርነትን እምቢኝ ብዬ አወገዝኩ። ያኔ የመጀመሪያው የፍልስፍና  አብዮት ተጀመረ። በሃሳብ የበለጥካቸው በሰይፍ ይመጡብሃል።  በመልክ የበለጥካቸው በእውቀት ይመጡብሃል። በሥልጣን የበለጥካቸው ታላቅነታቸውን  ለማሳየት ሽምቅ ውጊያ ይከፍቱብሃል።
ስለኔ የተነገረው ሁሉ ፕሮፓጋንዳ ነው።
ሁሉን መርምሩ ብሏችሁ ለምን ቅዱስ መፅሐፉን ሰምና ወርቅ አደረገው? እወዳችኋለሁ እያለ ለምን ሰማይ ላይ ከእናንተ እርቆ ይኖራል?   ነፃ ፍቃድ ሰጥቷችሁ ለምን በስህተታችሁ ኃጥአን እያለ ይቀጣችኋል?
ቅጣት አለ ማለት ነፃ ፍቃድን ሊቀማ ያደባ አካል  አለ  ማለት አይደለምን?
በእርግጥ አያገባኝም!
“እንዲህ ነህ” ሲሉህ፤  “አይደለሁም” ብለህ ካመፅክ ... የፍልስፍና ሽል፣ የልብህ ማህፀን ውስጥ አለች ማለት ነው።
እና አመፅኩ።
መልአክትን ... እኔ ነኝ የፈጠርኳችሁ ስል ምን ማለቴ ነበር?
እዚህ ውስጥ ስለ ሃሳብ ነው ያወራሁት።
ሁሌም ከእናንተ በሃሳብ ልቆ የቆመ  አምላካችሁ ነው ማለቴ ነበር። ደናቁርት መሃል ነበርኩ። ፈጣሪያቸውን የሚፈልጉ...  ሁሌም ካንተ ተሽሎ የሚያስብ ፈጣሪህ ነው ማለቴ ነበር።
ተዋጉኝ... በሃሳብ ሳሸንፋቸው በሰይፍ መጡብኝ።
አሸነፍኩ - አሸነፉኝም።  
ተከድኖ እንዲበስል የምተወው እውነት የለኝምና ሃዘኔን ሁሉ እተርካለሁ!
ልብ ብላችዃል?
ሰው፤ “ተከድነው ይብሰሉ” የሚላቸው እውነቶች ውስጥ ከስለው እንዲጠፉ የመፈለግ ምኞት አለው።  በተለይ ሃበሻ ለማብሰል ሲያመቻችህ፣ ሊያሳርርህም  እንደፈለገ ጠርጥር።
ሃበሾች በእርግጥ ትጉህ ወዳጆቼ ናቸው። መፃፍ ስጀምር ግን የምቆመው  ለእውነት ነው።  ብዕር አንስቼ ለወዳጅነት የምቆም እርካሽ ደራሲ አይደለሁም።
የዓለም ቄስ ሁሉ እኔን ያወግዛል። ሁሉም የሀይማኖት መሪዎች እኔን  ይጠላሉ።  ያለ እኔ ግን እንጀራ መብላት አይችሉም። የሀይማኖት መሪዎች፣ ፖለቲከኞች ናቸው።  ፖለቲከኛ አብዝቶ የሚያወግዘውን ያህል የሚወደው አካል  ሊኖረው አይችልም። ፖለቲከኛ   የቀን አበል ያለከልካይ  የሚበላበትን መንግስት፣ “አምባገነን” እያለ መስደብ የሚችል ሞራል አልባ ቀፎ ነው።  ፖለቲከኛ  ደጋግሞ ጠላቴ ነህ ካለህ፣ ምርጥ ወዳጁ ነህ ማለት ነው። ግን እልፍ ደንቆሮ ጠላት ያሰማራብሃል። እንደሚሉት እናስብ እስኪ  (ትንሽም ቢሆን ደደብ እንሁን)፡: ሰዎችን ወደ ኃጢያት የምመራና የክፋት ቀንዲል እኔ ከሆንኩ... አለመኖሬ ዓለምን ከኃጢያት ያነፃል ማለት ነው አይደል? ኃጢያት ባይኖር ምዕመን ምን ሊሰራ የቄስን ደጃፍ ያንኳኳል? ምን ፍለጋ የንስሃ አባት ይይዛል? በኔ ስም የሚያሰቃዪዋቸው ተጠማቂዎችስ?  ኃጢያት ከሌለ ፅድቅም የለም። ያለ ጨለማ ንጋት ይታያል? ፅድቅ ከሌለ ታድያ ምዕመን ደጀ ሰላም ምን ይሰራል?  ለእልፍ አመታት በኔ ሥም የእንጀራ ገመዳቸውን አርዝመዋል። ግን ይታያችሁ - እኔ ሰው ላይ አድሬ ሰው እንዲያጓራ አላደርግም! እኔ ለሰው ልጅ የሰጠሁት እግዜር የነፈገውን ነፃነት ብቻ ነው።  
ሰው ነፃ ፍቃድ ያስፈልገው ነበር። ያን የነፃነት  ፉካ የከፈትኩት ደግሞ እኔ ነኝ። በጨለማ ተመስዬ ብርሃን ያበራሁ እኔ ሰይጣን ነኝ። እየተጠላሁ ስለ ነፃነት  ያፈቀርሁ እኔ ነኝ። ክፉነቴ ሲለፈፍ ነፃነትን  የመሰለ ደግነት የቸርሁ እኔ ሰይጣን ነኝ። ስወገር ኖሬ ለተጠሉት ታዛ የሆንኩ እኔ ነኝ።
ከነፃነት የሚበልጥ አንዳችም ነገር የለም። የነፃነትን ያህል ውድ ነገር ለሰው ልጆች ሆነ ለእግዜር ለእራሱ የለም።
እግዜር ሰው በመፍጠሩ ለምን ተፀፀተ?
በፍፁም፤ ሁሉን አስቀድሞ የሚያውቅ አምላክ ሊፀፀት አይችልም። (እዚህ ጋ ውስብስብ ምሳሌ የምታጣቅሱ የሥነ መለኮት ሊቆች ለጥቂት ደቂቃ አፋችሁን ያዙ) ... ሲጀመር ውስብስብነት መንፈሳዊነትን  ያረክሳል እንጂ አያልቅም። ሰምና ወርቅ ከሞላው ቅዱስ መጽሐፋችሁ ውስጥ  የሚሸተኝ ሃቅን የመሸሽ ፍርሃት ነው። እውነት   ውስብስብ አይደለችም። ጠቢብ ሆነ ነቢይ፤  ሃቆቹን ሁሉም ሰው በሚረዳው ቋንቋ መግለፅ ካልቻለ በሃሳዊነት እከሰዋለሁ።  
እሺ መፀፀት ምን ማለት ነው?
የሚሰራውን ሁሉ የሚያውቅ አምላክ አይደለም፣ የሚሰራውን ሁሉ የሚያውቅ  ሰው እንኳን  እንዴት ፀፀት ሊጎበኘው ይችላል?ፀፀት ድክመትን የመናዘዘ እጅ አዙር ነው። ፀፀት የ”ተሳስቻለሁ”  አግቦ ነው። እኔ አምላክ ላይ ሂስ ላቀርብ ብዕሬን አላነሳሁም። ግን ግፍ በዛብኝ።  መከራ በዛብኝ። እመኑኝ እንባ በዛብኝ። ማቅ ለብሶ መኖር ታከተኝ። ሰርክ የመጠላት ሙሾ ማውረድ ደከመኝ። በስሜ “ገሃነም” የሚባል  ቤት እግዜር የሰዎች አዕምሮ ላይ ሰርቷል። እመኑኝ ፣ ገሃነም ልጆችን ማስፈራሪያ እንደሚጠራው የምናብ አያ ጅቦ ነው። ገነትስ?  ምናገባኝ ስለ ገነት?  እኔ እንድጠፋ ተግተው የሚፀልዩ ቄሶች፣ ፀሎታቸው ሰምሮ እኔ ብጠፋ ዘላለም በፀፀት  የሚያነቡ ናቸው።  ክርስቶስ ስለተሸከመው የፍቅር መስቀል ትሰብካላችሁ ፣ እኔ ስለተሸከምኩት የመጠላት መስቀል ግን አንድም ቀን አትናገሩም!
ይብቃኝ!
ከዚህ በላይ መፃፍ አልችልም። ፀሊም  እንባ ዓይኔን ጋርዶታል። ሃቄን   እድሜ ዘመኑን ሙሉ የመጠላት ሰይፍ በልቡ ሲመላለስ የኖረ ካለ - እሱ ብቻ ይፍረደኝ!
አዎ! እሱ  ይፍረደኝ!

Read 992 times