Saturday, 15 April 2023 20:12

አዋጭ ኢንሹራንስ ከሀምሌ ጀምሮ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተባለ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የተፈረመ ካፒታል አግኝቷል


በምስረታ ላይ የሚገኘው አዋጭ ኢንሹራንስ ከሦስት ወር በኋላ በሀምሌ 2015 ዓ.ም መደበኛ የኢንሹራንስ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡ ኢንሹራንስ ኩባንያው ይህን የገለፀው የዛሬ ሳምንት በኢንተርሌግዠሪ ሆቴል የፈራሚዎች መስራች ጉባውን ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡
የኢንሹራንስ ኩባንያው ለምስረታ የሚያስፈልገውን ከ300 ሚ.ብር በላይ የተፈረመ የካፒታል መጠን ማሰባሰብ መቻሉ ተገልጿል።
አዋጭ ኢንሹራንስ በአምስት ግለሰቦች አደራጅነት የተጀመረ ሲሆን ግለሰቦቹ በአዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር የነበራቸውን ውጤታማ አፈፃፀም ስንቅ በማድረግ፣ በኢንሹራንሱም ዘርፍ ትርጉም ያለው ስራ ሰርተው ውጤት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት ማደራጀት መጀመራቸው በጉባኤው ወቅት ተነግሯል፡፡  
ኢንሹራንስ ኩባንያው ‹‹በ2025 ዓ.ም የደንበኛውን ፍላጎት የሚያሟላ ተመራጭና ሁሉን አቀፍ የኢንሹራንስ አገልግሎት ሰጪ ሆኖ ማየት›› የሚል ራዕይ ሰንቆ ህዳር 29 ቀን 2014 ዓ.ም ‹‹አዋጭ ኢንሹራንስ›› የሚለውን ስያሜ ፈቃድ ከሚመለከተው የመንግስት አካል ማግኘቱ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ጥር 23 ቀን 2014 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የቅድመ ምስረታ ጥያቄ አቅርቦ ባንኩ መጋቢት 13 ቀን 2014 ዓ.ም በተመረጡ 6 ባንኮች ሂሳብ መክፈት እንዲቻል ፈቃድ መስጠቱን የአዋጭ ኢንሹራንስ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መስፍን ገብረስላሴ በጉባኤው መክፈቻ ላይ  ባደረጉት ንግግር አስታውሰዋል፡፡
ኢንሹራንስ ኩባንያውን ለመመስረት በተደረገ የጋራ ርብርብ ለምስረታው የሚያስፈልገውን 300 ሚሊዮን ብር የካፒታል መጠን ለማሰባሰብ ታቅዶ እንደነበር ያስታወሱት ሰብሳቢው፤ 61 ሺህ 181 አክሲዮኖች ለ1 ሺህ 755 አባላት በመሸጥ 305 ሚሊዮን 905 ሺህ ብር ማስፈረም መቻሉንና ከዚህም ውስጥ የተከፈለው 133 ሚሊዮን 805 ሺህ ብር (የተፈረመውን 43 በመቶ) በዝግ የባንክ የሂሳብ ቁጥር ማስቀመጥ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም፤ ለስራ ማስኬጃ 15 ሚሊዮን ብር በማሰባሰብ አስፈላጊው የምስረታና የማደራጀት ስራ መጠናቀቁ ተጠቁሟል፡፡
በሚቀጥሉት 3 ወራት ቀሪዎቹ ህጋዊ የስራ ፈቃድ ሂደቶችን በማጠናቀቅ ከሀምሌ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ የኢንሹራንስ ስራ ለመጀመር መታቀዱም ተገልጿል፡፡
በፈራሚዎች መሥራች ጉባኤው ላይ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ የአዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር የህብረት ስራ ማህበር አመራሮች፣ የኢንሹራንሱ አደራጆች፣ ባለ አክሲዮኖችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

Read 1941 times