Saturday, 15 April 2023 20:12

የክልል ልዩ ሃይሎችን የማደራጀቱ ውሳኔ ዜጎችን አደጋ ላይ በማይጥል ሁኔታ እንዲከናወን ኢሰመኮ አሳሰበ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

መንግስት የክልል ልዩ ሃይሎችን በፌደራልና በክልል መደበኛ የጸጥታ ሃይሎች ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ መልሶ ለማደራጀት  ሰሞኑን ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ለተግባራዊነቱ እንቅስቃሴ በጀመረባቸው አንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች የሰው ህይወት ማለፉ እጅግ እንዳሳሰበውና መንግስት የክልል ልዩ ሃይሎችን መልሶ የማደራጀት ውሳኔውን ዜጎችን አደጋ ላይ በማይጥል ሁኔታ ተግባራዊ ሊያደርግ እንደሚገባው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ።
ግጭት በተፈጠረባቸው አንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞችን ጨምሮ ሲቪል ሰዎች መሞታቸውንና ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውንም ኢሰመኮ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ መንግስት የክልል ልዩ ሃይሎችን መልሶ ለማደራጀት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በጀመረው ተግባራዊ እንቅስቃሴ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በተለይም በባህርዳር፣ በወረታ፣ በቆቦ፣ በኮምቦልቻና በደብረ ብርሃን ከተሞች ታላላቅ የተቃውሞ ሰልፎች፣ መንገድ መዝጋትና የአገልግሎት መቋረጥ ተከስቷል።
በዚህ ሳቢያም ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ግጭት መከሰቱን ያመለከተው ኢሰመጉ፤  በግጭቱም የእርዳታ ሰራተኞችና ሲቪል ዜጎች ሞተዋል ብሏል፡፡
በአካባቢው የተከሰተው የጸጥታ ችግር በአስቸኳይ እልባት ካላገኘ ለከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ስጋት መሆኑ አይቀሬ ነው ያለው የኢሰመጎ መግለጫ፤ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን በምክክርና በመግባባት እንዲፈቱ መክሯል።
መንግስት የፖሊሲ ውሳኔውን አስፈላጊነትና ጠቀሜታ ለሚመለከታቸው ሁሉ በትዕግስትና በጽሞና የሚያስረዳበትን ሁኔታ እንዲያመቻች የጠየቀው ኢሰመኮ፤ መንግስት ያልተመጣጠነና ህይወት የሚያጠፋ ሃይል ከመጠቀም እንዲቆጠብም አሳስቧል። በዜጎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት ሁሉ መንግስት አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ የጠየቀው ኮሚሽኑ፤ ሁሉም ሰው ሃሳቡን በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲገልጽ ኢሰመኮ ጥሪውን አቅርቧል።ከመደበኛው የክትትልና ምርመራ ስራው ጎን ለጎን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር የተፈጠረው ችግር በውይይት እንደፈታ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑንም ኢሰመኮ በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

Read 1761 times