Saturday, 15 April 2023 20:15

የሚሄድ ዝሆን ስር ነቅሎ ሲበላ የሚኖር ዝሆን ቀንበጡን ይበላል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

አጼ በካፋ አንድ በጣም የሚወዱት ለማዳ በግ እንደነበራቸው ይነገራል። በጉ ቀላዋጭ ስለነበር እንዳይቸገር ተብሎ አዋጅ ወጣለት። አዋጁም በደረሰበት ያሻውን እንዲበላ የሚያዝ ሲሆን፤ ያ ካልተደረገለት ግን ማንም ቢሆን ቅጣት እንደሚጠብቀው ይገልጻል። ሰው ግን ተማረረ። በጉ ማን አለብኝ ብሎ የተሰጣ ስጥ፣ ለወፍጮ የቀረበ እህል አልተርፈው አለ። እንዲህ እያደረገ አገሬውን አስለቀሰ። አንድ ቀን አንድ ደብተራ ቤት እግር ጥሎት ገባና የመጨረሻው ሆነ። ደብተራ ሆዬ በሩን ጥርቅም አድርጎ ዘግቶ ቀላዋጩን የንጉስ በግ አርዶ ቅርጥፍ አድርጎ በላው። አፄ በሁኔታው በሽቀው የእኔን በግ የሰረቀው ሰው የገባበት ገብታችሁ ያዙት አሉ። ያ ደብተራ ግን አርዶ መብላቱ አልበቃ ብሎት የበጉን ቆዳ በብራና መልክ ፍቆ እዚያ ብራና ላይ “የንጉሱን በግ አርጄ ጣፍጦኝ የበላሁት እኔ እራሴ ነኝ!” ብሎ ጽፎ የብራና ቁራጮችን በድብቅ ሄዶ በአደባባይ ሰቀላቸው። ነገሩ ንጉሱ ጆሮ ደረሰ። እጅግ አድርገው ተበሳጩ! መደፈራቸው የባሰ  አንጀታቸውን አቃጠለው! “አሁን ብልሃት መዘየድ አለብኝ። ይሄ ሌባ የዋዛ አይደለም ማለት ነው።” ብለው አንድ መላ መቱ። “የተመዘነ ወርቅ አምጡና ከአደባባዩ እስከ አውራ ጎዳናዎቹ ድረስ በሚስጥር በስሱ በትኑት። ከዚያም እናንተ ከአካባቢው ራቅ ብላችሁ በአይነቁራኛ ጠብቁ። የለመደች ጦጣ ሁልጊዜ ሽምጠጣ ነውና ልማደኛ ሌባ ሲመጣ እጅ ከፍንጅ ያዙት።” ደብተራ ሆዬ የተጠመደ ወጥመድ እንዳለ ስለገባው አዲስ ጫማ አሰፋፍቶ ሶሉን ሰም ቀባውና ወርቁን እያጣበቀ በመንገዱ ሁለት ሶስቴ ከተመላለሰ በኋላ መጭ አለ። በሰሙ ብዙ ወርቅ እያጣበቀ አንስቷል። ይህንን ቤቱ ወስዶ እያራገፈ ወርቁን አከማቸ።
ማታ “በሉ ወርቁን መዝኑት” አሉ አፄ። ቢመዘን ተሟጦ ተሰርቋል። መጉደሉን ሲሰሙ አፄ እጅግ በገኑ። ጠባቂዎቹ አንድም ሰው ጎንበስ ብሎ እንዳላነሳ አስረዱ።
ንጉሱ ግራ ገባቸውና ጠንቋዮች አስጠሩ፤ ሌባው የት እንደሚኖርና አሁን የት እንዳለ ጠየቋቸው። “እገሌ አፈር ላይ ጠይቁ” አሏቸው ጠንቋዮቹ። ደብተራው ግን ሲጨንቃቸው ምን እንደሚያደርጉ ቀድሞውኑ ጠርጥሮ ኖሮ አፈር እየለዋወጠ አልገኝ አለ። ንጉሱ ይብሱን ብሽቅ አሉና ሌላ ዘዴ ቀመሩ። ግብር አግብተው ደብተራ፣ አለቆችና ተማሪዎች አንድም እንዳይቀሩ አዘዙ። “በሰከሩ ጊዜ አንዱ ምስጢሩን መተንፈሱ ስለማይቀር፤ ያኔ ሲተኛ ጠብቆና ከጆሮው ትንሽ ቀንጥቦ ጠዋት ጆሮው የተቀነጠበውን ሰው ፈልጎ መያዝ ነው። አለቀ።” እውነትም ደብተራ ሆዬ በመጠጥ ላይ ንጉሱን እንዴት ጉድ እንደሰራቸው ለጓደኛው ሲያጫውት ተሰማ። ሰክሮ ሲተኛ ጆሮውን ተቀነጠበ። ከስካሩ ሲነቃም እንደተታለለ ገባው። ስለዚህ የተጋደሙትን ተማሪዎችና ደብተራዎች እያንዳንዳቸውን ጆሮአቸውን እንደተኙ ቀነጠባቸው። የደብተራውን ጆሮ የቀነጠበው ባለሟል ሽልማቱን ለመቀበል ወደ ንጉሱ ሄዶ የሆነውን ተናገረ። ንጉሱ ሌቱ አልነጋ ብሏቸው እንደጓጉ አደሩ። ጠዋት ግን ተማሪው ሁሉ ጆሮውን መቆረጡን ሲያዩ አንጀታቸው እርር አለ። ወሬውን ያመጣውን ባለሟል ጠርተው “የዚህን ሁሉ ሰው ጆሮ ቁረጥልኝ ብየሃለሁ ወይ!” ብለው ተቆጡት። “ኧረ እኔ የአንድ ተማሪ ለምለም ጆሮ ብቻ ነው የቆረጥኩት።” ሲል መለሰ። ንጉሱም “አሁንማ አጅሬ ስለነቃብህ አገሩን ሁሉ ጆሮውን መደመደው።” በብልሃቱ ተደነቁ። እንዲህ ያለውን ብልህና ጎበዝ ሰው ከመቅጣት መሾም መሸለም ይበልጣል! ለመንግስት ይጠቅማል ብለው፤ ሲያበቁ አዋጅ አሳወጁ። “በጌን የበላህ ደብተራ ምህረት ተደርጎልሃል! እንደውም ሸልሜ እሾምሃለሁ እኔ ነኝ በል!” የሚል ትዕዛዝ ሰጡ። ይሄኔ ደብተራ ሆዬ እየተጀነነ ብቅ አለ። ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ምን እንዳደረገ ለንጉሱ በዝርዝር አስረዳ! ንጉሱም አሳማኝ ቃሉን ተቀብለው ሹመት ሰጡት!
***
ንጉስ ያለበት ሃላፊነት እጅግ ትልቅ ነው። ንጉስ የመሪ፣ የሃላፊ፣ የሚንስትር፣ የአለቃ ምሳሌ ነው። ሁሉም ለበጌ ታዘዙ፣ በጌን መግቡ፣ በጌን አኑሩ ባለ ቁጥር ህዝብ እየተሽቆጠቆጠ ካስተናገደ በጉም ማን-አለብኝን ይቀጥላል፤ ባለበጉም የህገወጥና የአዛዥ ናዛዥነት ባህሪውን እያስታመመ በእልክና በንዴት ወደባሰ ጥፋት እንዲያመራ ይሆናል። እንዲህ ባለው ስርዓት ውስጥ ለአንድ ወቅት ያህል “ታላቅየው ሲመቸው ታናሽየው ሳይድህ በእግሩ ይሄዳል” እንደተባለው ሊሆን ይችላል። ውሎ አድሮ ግን በጉን ጨክኖ የሚበላ፣ በልቶም አድራጎቱ ትክክል መሆኑን በጽሁፍ የሚያኖር ብልህ ዜጋ በተፈጠረ ጊዜ፣ ባለበግ ከፉከራና ከያዙኝ- ልቀቁኝ ያለፈ አቅም አይኖረውም። አባትና ልጅ አውራሽና ወራሽ ናቸው። አውራሽ እሚያወርሰውን ሃብትና ንብረት በንፉግነት ያከማቸ፣ በሙስና፣ በኢ-ፍትሃዊ ምዝበራ፣ በማናለብኝና “የአገር ባለውለታ እኔ ብቻ ነኝ” በሚል አንድም በካሳ አንድም በሳንሳ የዘረፈ ከሆነና፤ ወራሽም “በአባቴ ንብረት ምን አገባችሁ፤ ባለጊዜ ነኝና ባፈሰው-ብዘራው ምን ጥልቅ አደረጋችሁ፤” የሚል ከሆነ፤ ሀገር ሁለት ጊዜ ትበደላለች ማለት ነው። አበው አንድ አባባል አላቸው፡-
 “የንፉግ አባትን ገንዘብ አባካኝ ሲዘራው
አባቱ ከራሱ በቀር ወዳጅ አልነበረውም።
ልጁ ግን ከራሱ በቀር ጠላት የለውም።”
ከራሱ በቀር ወዳጅ የሌለውና ከራሱ በቀር ጠላት የሌለው መሆን የሁለት ጥፉዎች ማለትም የባለበግና የበግ፣ የሐዋርያና የደቀ-መዝሙር፣ የሚንስትርና የምክትል ሚንስትር፣ የፖለቲካ አዛዥና በኩር ካድሬ፣ የበላይ በላይና የበላይ ተከታይ ታሪካዊ ገጽታ ነው። በታሪክ በተደጋጋሚ እንደታየው ወዳጅ ለማፍራትም ሆነ ጠላት የመቀነስ ጊዜው ሳይመሽ በፊት መሆን ይገባዋል። ምክንያቱን ሸክስፒር በኦቴሎ አንደበት እንደገለጸው፤
“ነበርን ማለት ግን ከንቱ ነው፣ ተውነው መጀነን በቅቶን
ጉራ መንዛት መዘባነን፣ የሚያዛልቅ ዘዴ ባይሆን!” የሚባልበትን ሰዓት ማፋጠን ይሆናል።
በርካታ ወገናዊነት የተጠናወታቸው ድርጊቶች፣ ንፉግነት የተጫናቸው “የዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ” ጥሪዎች፣ እንዲሁም የመድረኬን አትንኩ ዛቻና ማስፈራሪያዎች፤ ቀን የጣለ ለታ፣ “የተያዘ ዓሳ በገዛ አንገቱ ይንጠለጠላል።” እንዲል መጽሐፍ በታሪካዊ ማስረጃነት የሚቀርቡና የሚጠቀሱ ዛሬ ባለሙሉ ስልጣን ሆነው በጉልበተኝነት የፈረዷቸው ፍርዶች ናቸው። የህብረተሰብ ሂደት አይመለሴ- አይሻሬ ነው። (Irreversible and Irrevocable እንደማለት) ከቶውንም “ፉርሽ ባትሉኝ!” የማይባልበት ነው! ያለበቂ ጥናት የሄድንበት መንገድ የጠለፍነው ውሃ፣ የገደብነው ግድብ፣ ዛሬ የምናቁረው ውሃ፣ ያወጅነው ያልተተገበረ አዋጅ፣ የይድረስ ይድረስ ውጤት-ተኮርነት፣ በቀን ሶስቴ ከመብላት በቀን ሶስቴ ፊታችንን ወደመታጠብ የተሸጋገርንበት ኢኮኖሚያዊ ምጸት፣ በሯጮቻችን ፍጥነት የመሰልነው ፈጣን እድገት ወዘተ ሁሉ የታሪክ መተዛዘቢያዎች የሚሆኑት ያለስክነት ለመጓዛችንና የተገቢው ሰው  በተገቢው ቦታ መርህ በወገናዊነት በመታጠሩ ነው።
በታሪክ በተደጋጋሚ እንደታየው ህብረተሰብን በመሪነት ወደፊት ያራምዳል የተባለ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ፓርቲ በቀሰቀሰው አውሎ ነፋስና ጎርፍ ራሱ እየታፈነ፣ እራሱ እየተጠለፈ፣ የገዛ ህዝቡ እንቅስቃሴ ሲያጥለቀልቀው ግንባር ቀደም (Vanguard) የተባለው ጭራ-ተጓዥ (Tailist movement) እየሆነ አገር ያለመሪ ስትዋልል፣ የቀናው ባለጊዜ ደግሞ በተራው ወንበሩን ሲረከብ፤ ሲረካከብ፤ ብዙ ዘመን አሳልፈናል። ከዘመነ መሳፍንት እስከ ዘመነ ሊቃነ-መናብርትና ዘመነ ፕሬዝዳንት፤ ድኸን፣ ተንፏቅቀን እዚህ ደርሰናል። ባለበጉና በጉ እከክልኝ ልከክልህ ሲባባሉ፣ ህዝቡም አንዴም በምሬት፣ አንዴም በቁጭት የበግ መጫወቻ ሆኜ ቀረሁ ሲል፣
“አርኮም ይሄድና ሊሬውም ያልቅና
ያስተዛዝበናል ይሄ ቀን ያልፍና!” እያለ ሲዝት ወይም ደግሞ ወረት አላፊ ነውና ልስማማ ልደራደር በሚል፤
“በትንሽ መለኪያ ይጠጣል አረቄ
በርታ አገሩ ገባ ከባልሽ ታረቂ” ብሎ እየሸነቆጠ፣ መጨረሻ ሲመረውም
“አስረው ደበደቡት ያን የዝሆን ጥጃ
ዛሬን ደስ አላቸው የነገውን እንጃ!” ሲል፤ አሊያም ደግሞ ተስፋውን ጭምር እየተራበ በአይነ-ስውሩ ለማኝ ቃና፤ “ያውና እዚያ ማዶ ብርሃን ያድላሉ
አሁን እኔ ብሄድ አለቀ ይላሉ” እያለ ጉዞ-ብሶቱንና ጉዞ-ፍትሃቱን ያካሂዳል።
የጠፋው ጥፋት ካላሳዘነንና ካልጸጸተን፣ ነገም እንድገመው አንድገመው ዋስትና ካልሰጠን፣ “ሆ!” ብለን አቅደን “ሆ!” ብለን ሳንተገብረው ዕድሜያችንን ለስብሰባ አድባር ገብረን የምንከርም ከሆነና ጥቂት ጥቂት የተግባር ብልጭታ የሚያሳየውን የህብረተሰብ ክፍል ከቁጥርም የማንጽፈው ከሆነ፤
“የሚሄድ ዝሆን ስር ነቅሎ ሲበላ
የሚኖር ዝሆን ቀንበጡን ይበላል” ከማለት የተሻለ ቋንቋ ለጊዜው አናገኝም!
መልካም የትንሳኤ በዓል!!      

Read 1337 times