Saturday, 15 April 2023 20:17

በወሊድ ወቅት የሚፈጠር ፊስቱላ

Written by  ሀይማኖትግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

በወሊድ ወቅት ስለሚፈጠር ፊስቱላ ምንነት እና ለመዳን(ለማገገም) ስለሚወስደው የጊዜ  እርዝማኔ በቀደመ እትም ለንባብ በቅቷል። በሀምሊን የፊስቱላ ሆስፒታል የተደረገ ጥናታዊ ፅሁፍ እንዲሁም በቀደመ እትም የቀረበ ታሪክ ቀጣይ ክፍል በዚህ እትም  ለንባብ ቀርቧል።
(ክፍል ሁለት)......እትዬ ጥላነሽ ከገቡበት ሰመመን ነቅተው አይኖቻቸውን ሲገልጡ የለመዱት የሳር ጣራ ሳይሆን በጂፕሰም የተሰራ ኮርኒስ ተቀበላቸው። ሰዎች የማይጎበኙት የተዘበራረቀ እቃ ጣል ጣል ያለበት ቤታቸው ንፅህናው በተጠበቀ እና ለእሳቸው ግድ በሚሰጣቸው ሰዎች ተተካ። ይህ ለእትዬ ጥላነሽ ከእንግዳነትም በላይ ተአምር የሆነባቸውን ሁኔታ ለመለየት ደቂቃዎች ፈጀባቸው። ያሉበትን ስፍራ በቅጡ ከለዩ በኋላ ግን የነበረው ሰላም ደፈረሰ፤ እትዬ ጥላነሽ በስፍራው መቆየት እንደማይፈልጉ በደከመ አንደበታቸው እየደጋገሙ ከመናገር አልፈው ተነስተው ለመሄድ መፍጨርጨር ጀመሩ። ይህን ቦታ ከ18 አመታት በፊት ነው የሚያውቁት፤ እናታቸው የመጨረሻ ልጃቸውን ለመውለድ በመጡበት ወቅት፤ የእናታቸውም ሆነ የተፀነሰው ልጅ ህይወት ያለፈበት ቀን፤ የእናታቸውን በወሊድ ምክንያት መሞት ሲረዱ ዳግመኛ እንደዚህ አይነት ስፍራ እንደማይመጡ ለእራሳቸው ቃል የገቡበት እለት፤ ከእናታቸው ሞት 16 አመታት በኋላም እትዬ ጥላነሽ ይህን ቃልኪዳናቸውን ጠብቀው ልጃቸውን በቤታቸው የወለዱበት፣ ልጃቸውን በሞት፣ ባለቤታቸውን በስደት እና የህይወታቸውን 2 አመታት በበሽታ የተነጠቁበት ሁነት፤ እንዴት ይረሳል! ትላንት የተፈፀመ እስኪመስል እያንዳንዱ ነገር ፍንትው ብሎ ይታያቸዋል። ያንገሸግሻቸዋል። ለሌሎች መዳኛ ለእሳቸው ግን መጥፊያ በሚመስላቸው የህክምና ተቋም መገኘታቸው እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል።
እትዬ ጥላነሽ እራሳቸውን ስተው ሲወድቁ ዓለም ድምፅ በመስማቷ፣ ለእርዳታ ለሰርግ ወደ ተሰበሰቡ ሰዎች በመሄዷ እና እንደአጋጣሚ ሆኖ በሰርጉ ላይ ከከተማ የመጡ የህክምና ባለሙያዎች በመኖራቸው ነው እትዬ ጥላነሽ ወደ ህክምና ተቋም ሊሄዱ የቻሉት። እንደዛ ባይሆንማ ወዳጅ ዘመዳቸው ከእናታቸው የወረሱት እርግማን ነው ብሎ በፈረጀው በሽታ እንደተገለሉ ወድቀው መቅረታቸው ነበር። ለ2 አመታት ሰው እንኳን እናዳያስታምማቸው፣ እንዳይቀርባቸው እና እንዲጠቋቆምባቸው አድርጎ ሲያሰቃያቸው የነበረው፣ እሳቸውም “እርግማን ነው እንጂ” ብለው የተሸነፉለት የፊስቱላ በሽታ ከእራሱ አልፎ ሌሎች በሽታዎችንም ጋብዞ ስቃያቸውን ሲያበዛው መክረሙን እትዬ ጥላነሽ በህክምን ባለሙያዎች አማካኝነት አወቁ።  
ከሳምንታት በኋላ ከፊስቱላም ሆነ ተያይዞ ከመጣው የኩላሊት በሽታ እያገገሙ መጡ። ህክምናቸውንም እየተመላለሱ መከታተል ጀመሩ። የልጅነት ሀሳብ፣ ህልም እና ተስፋቸው የተመለሰላቸውም መሰላቸው። እንደ ወትሮው ዓለም እገዛዋ አልተለያቸውም። የባጥ የቆጡን ስለምታጫውታቸው እሷን ሲያዩ ፊታቸው በፈገግታ ይሞላል። በእርግጥ የእራሳቸው ዘመዶች እንኳን ፊታቸውን ባዞሩባቸው ወቅት የልጅነት ጓደኛቸው የሆኑት ልጅ ለእሳቸው ቅርብ መሆኗ ሁልጊዜም ያስገርማቸዋል። ከበሽታቸው ትንሽ ማገገም ከጀመሩ በኋላ እንኳን ከአከባቢው አንዳንድ ሰው አልፎ አልፎ ይጠይቃቸው ጀምሯል። እትዬ ጥላነሽ ደጃፋቸው ላይ ቁጭ ብለው በሀሳብ በተጓዙበት ቅፅበት አንዲት ልጅ ፈጠን ፈጠን እያለች ፊትለፊታቸው ወዳለው ቁጥቋጦ ስታመራ ተመለከቷት። “ሁለነገሯ አለምዬን ይመስላል” አሉ በወስጣቸው። እሳቸውን ለመጠየቅ የተላከች ልጅ ስለመሰለቻቸው በደስታ ስሜት “አንቺ ልጅ መንገዱ ጠፋሽ እንዴ? ኧረ ወዲህ ነህ” በማለት ሊጠሯት ሞከሩ። ልጅቷ ግን ከቋጥኙ አልፋ ወደ ደኖቹ መሀል ጉዞዋን ቀጠለች። እትዬ ጥላነሽ የልጅቷን ሁኔታ በደንብ ሲያጤኑ በእጇ ገመድ መያዟን አስተዋሉ። ከበሽታው በደንብ ያላገገመ ሰውነታቸው እየጎተቱም ተከተሏት።........ በቀጣይ እትም(ሳምንት) ይቀጥላል!
በዲላ ዩኒቨርስቲ ህይወት ባላቸው ነገሮች ላይ ጥናት እና ምርምር የሚያደርጉት (አናቶሚስት) መምህር ቸርነት ሙሉጌታ በአ.አ ሀምሊን የፊስቱላ ሆስፒታል ባደረጉት ጥናት በወሊድ ወቅት ከሚፈጠር ፊስቱላ በ1 ወር ጊዜ ውስጥ ማገገም እንደሚቻል አረጋግጠዋል።
በወሊድ ወቅት ከሚፈጠር ፊስቱላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማገገም(ለመዳን) ወይም ላለማገገም ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮች;
የትምህርት ደረጃ; የትምህርት ደረጃቸው ዝቅተኛ በሆኑ እናቶች ዘንድ የቅድመ ወሊድ ክትትል የማድረግ፣ የህክምና ተቋም የመውለድ እና ፊስቱላ ሲፈጠር ወደ ህክምና ተቋም ሄዶ የመታከም ሁኔታ አነስተኛ ነው። በተቃራኒ የተሻለ የትምህርት ደረጃ ያላቸው እናቶች ለፊስቱላ የመጋለጥ እንዲሁም ፊስቱላ ካጋጠመ በኋላ ሳያገግሙ ረዘም ላለ ጊዜ የመቆየት እድላቸው አነስተኛ ነው። ይህም በጥናቱ የተረጋገጠ ሲሆን ሙሉበሙሉ ካልተማሩ እናቶች መካከል 36በመቶ እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ እና ከዛ በላይ ከተማሩት ደግሞ 13በመቶ ከፊስቱላ አላገገሙም። በተመሳስይ ያልተማሩ እናቶች 68 በመቶ እና የተማሩ እናቶች 86በመቶ አገግመዋል።
በህይወት ያለ እና ህይወቱ ያለፈ ልጅ መውለድ; ህይወቱ ያለፈ ልጅ የወለደች እናት በሚያጋጥማት ሀዘን እና ጭንቀት ምክንያት የድብርት ስሜት ውስጥ ትገባለች። የድብርት ስሜት ደግሞ በሽታ የመከላከል አቅምን በመቀነስ የፊስቱላ ቁስል በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዳያገግም[እንዳይድን] ያደርጋል።
የፊስቱላ ደረጃ [የተፈጠረው ቀዳዳ ስፋት]; ፊስቱላ የተፈጠረበት ቦታ (ማህፀን ወይም ብልት፣ የሽንት ፊኛ እና ፊንጢጣ) ማለትም ቀዳዳ ያለው ስፋት ወይም ያደረሰው ጉዳት(ቁስል) ከፍተኛ ሲሆን ለማገገም የሚፈጀው የጊዜ መጠን ይጨምራል።

በወሊድ ወቅት የሚፈጠር ፊስቱላ የሚያደርሰው ጉዳት፤
አካላዊ ጉዳት; ኢንፌክሽን፣ የመሀንነት ችግር፣ ስር የሰደደ በሽታ ወይም ለረዥም ጊዜ የሚቆይ እና የማይድን በሽታ (Chronic disease)፣ የኩላሊት በሽታ እና ከባድ የህመም ስሜት ያስከትላል።
ስነልቦናዊ ጉዳት;  ከማህበረሰቡ መገለል፣ የድብርት ስሜት፣ ድህነት ውስጥ መግባት እና ከበሽታው ካገገሙ በኋላም ትዳር[ወንድ] መፍራት [መጥላት] ሊያስከትል ይችላል።
ፊስቱላ ህክምና ካላገኘ ለሞት ሊዳርግ ይችላል፡፡

“የህክምና ተቋማት ለፊስቱላ ህክምና ስለሰጡ ብቻ ፊስቱላ አይጠፋም” በማለት የህክምና ባለሙያው የተናገሩ ሲሆን ፊስቱላን ለማጥፋት መነሻ ምክንያቶቹ ላይ መስራት እንደሚገባ አክለው ገልጸዋል። ፊስቱላ በብዛት የሚያጋጥመው በገጠራማ አከባቢ በሚኖሩ እናቶች ላይ ነው። እኒህ እናቶች ፊስቱላን አስቀድሞ መከላከል እንደሚቻል አያውቁም። የቅድመ ወሊድ የህክምና ክትትል አያደርጉም። በጥናቱ ተካታች ከሆኑት እናቶች መካከል 70በመቶ የሚሆኑት ለቅድመ ወሊድ ክትትል ወደ ህክምና ተቋም ሄደው አያውቁም። ስለሆነም እንደ መምህር ቸርነት ንግግር የችግሩ ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል። በተመሳስይ ህክምና ሊሰጡ የሚችሉ የህክምና ባለሙያዎችን ማፍራት ለችግሩ መፍትሄ ይሆናል። እንዲሁም በገጠራማ አከባቢ የሚገኙ የጤና ተቋማት ለችግሩ ትኩረት በመስጠት ፊስቱላ ሲፈጠር የፊስቱላ ህክምና ወደሚሰጥበት ተቋም እንዲሄዱ ማድረግ ያስፈልጋል። የፊስቱላ ህክምና በሚሰጡ ተቋማት ያለምንም ክፍያ አገልግሎቱ[ህክምናው] ይሰጣል። 

Read 664 times