Print this page
Saturday, 15 April 2023 20:25

የ”ሰላም ኢትዮጵያ” የ25 ዓመት የሙዚቃ ጉዞ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“ሰላም ኢትዮጵያ” የዛሬ 25 ዓመት ገደማ በስዊድን ስቶክሆልም፣ በኢትዮጵያዊው የሙዚቃ ባለሙያ ተሾመ ወንድሙ፣ የተቋቋመ ስመ-ጥር ተቋም ነው፡፡ የተቋሙ አላማም፣ የመላውን ዓለም ሙዚቃ፣ ባህልና እሴት ለስዊድን ማስተዋወቅ ሲሆን፤ በ25 ዓመት ጉዞውም የምእራቡን ዓለም፣ የአፍሪካንና የካሪቢያንን ሙዚቃና ባህል ለስዊድን ሲያስተዋውቅ መቆየቱን አቶ ተሾመ  ወንድሙ ያስረዳሉ፡፡ የዓለም ታላላቅ ሙዚቀኞች ስዊድን ስቶክሆልም ውስጥ በሚገኘውና የኖቤል ሽልማት ሥነሥርዓት በሚካሄድበት ‹‹ኮንሰርት ሀውስ›› የተባለ ታላቅ  አዳራሽ ውስጥ በሰላም ኢትዮጵያ አማካኝነት ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ ከሀገራችን አንጋፋ ሙዚቀኞች መካከል ደግሞ አንጋፋዋ ድምጻዊት አስቴር አወቀ፣ የኢትዮ ጃዝ አባት ሙላቱ አስታጥቄ፣ ዝነኛው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) እና ሌሎችም በዚህ ሥፍራ ሙዚቃቸውን ማቅረባቸውን ነው የሰላም ኢትዮጵያ መሥራች የሚናገሩት፡፡ ሰላም ኢትዮጵያ ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹ሙዚቃዊ›› የተሰኘ የሙዚቃ አሳታሚ ድርጅት  ከፍቶ የተለያዩ ወጣትና አንጋፋ አርቲስቶችን የሙዚቃ ሥራዎች እያሳተመ ይገኛል፡፡   የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ከሰላም ኢትዮጵያ መሥራቹ አቶ ተሾመ ወንድሙ ጋር በተቋሙ አመሰራረት፣ በአጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴውና በሙዚቃ ሙያቸው እንዲሁም በህልምና ራዕያቸው  ዙሪያ አነጋግራቸዋለች፡፡ እንዲህ ቀርቧል፡-


==========


እስቲ እራስዎትን ለአንባቢያን በአጭሩ ያስተዋውቁልን?
ተሾመ ወንድሙ እባላለሁ፤ ተወልጄ ያደግኩት አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት ነው የተማርኩት፡፡ የሙዚቃ ህይወቴም ከዚህ ት/ቤት ነው የሚጀምረው፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ የሙዚቃ ፍቅር ነበረኝ፡፡ በድሮ ጊዜ በየት/ቤቶቹ የሙዚቃ መሳሪያዎች መጫወት ይቻል ነበርና፣ እኔም ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ፣ ክላርኔት የተባለውን የሙዚቃ መሳሪያ በመጫወት፣ የት/ቤቱ ማርቺንግ ባንድ አንዱ አባል  ነበርኩኝ፡፡ ባልሳሳት ያን ጊዜ ሙዚቃ ስጀምር፣ 12 ዓመት ገደማ ነበር እድሜዬ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይሄው እስካሁን በሙዚቃ ውስጥ አለሁ፡፡
ለሙዚቃ ትምህርት ወደ ሩሲያ ተጉዘው እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ እስቲ ስለሱ ትንሽ ያጫውቱኝ?
እንዴት መሰለሽ ልክ አስረኛ ክፍል ጨርሰን እያለ የኢትዮጵያ ባህር ሀይል ሙዚቀኞችን ለመቅጠር ወደ አዲስ አበባ መጡ፡፡ የድሮ ባህር ሃይሎች አስመራ ምፅዋና አሰብ ነበር የነበሩት። ታዲያ ምኒሊክ ት/ቤት የነበርነውን ሙዚቀኞች አስራ ምናምን እንሆናለን ቀጥረውን አስመራ ይዘውን ሄዱ፡፡
መቼ ማለት ነው?
በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1973 ዓ.ም መሆኑ ነው፡፡
ከ42 ዓመት በፊት ማለት ነው፡፡ እሺ ይቀጥሉልኝ?
42 ዓመት ሆነው? በስመአብ! ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ባህር ሀይል ቀጠሩን፡፡ ምክንያቱም እኛ ኦልሬዲ ሙዚቃ መጫወት ጀምረን ስለነበር ለእነሱ ቀላል ነው፡፡ አስመራ እንደሄድን የባህር ሃይልን ዲስፕሊን እንድናውቅ ትምህርት ተሰጠንና የባህር ሀይል ሙዚቀኞች ሆንን፡፡ በባህር ሀይል የማርቺንግ ባንድ ሙዚቀኞች ሆነን ስንሰራ እንደገና የምሽት ክበብም ነበር፤ እዛም እሰራ ነበር፡፡ ለማርቺንግ ባንዱ ክላርኔት ለምሽት ክበቡ ባንድ ደግሞ ሳክስፎን ተጫዋች ነበርኩኝ፡፡ ይህ እንግዲህ ከ1973 እስከ 1980 ዓ.ም ለሰባት ስምንት ዓመት ይመስለኛል፣ ካገለገልኩ በኋላ ባህር ሀይል ነፃ የትምህር እድል ሰጥቶኝ ነው ለትልቅ ትምህርት ወደ ራሽያ የሄድኩት፡፡ የገባሁት ራሽያ ውስጥ በዓለም ላይ ትልቅ የተባለ የሚሊታሪ የሙዚቃ ት/ቤት ሲሆን እንዳጠና የተላኩት ደግሞ ‹‹ኮንዳክቲንግ›› ነው፡፡
‹‹ኮንዳክቲንግ›› ማለት ማርቺንግ ባንዱን ከፊት ለፊት ሆኖ የሚመራው ሰው የሚማረው ነው?
ትክክል ነው፤ ማርቺንግ ባንዱን የሚመራው ሰው ነው ትምህርቱ፡፡ እኔ የተላኩበት አላማም ያንን ትምህርት ተምሬ ስመለስ የባህር ሀይሉን ማርቺንግ ባንድ እንድመራ ነበር፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ሶስት አመት አካባቢ እንደተማርኩ ኢትዮጵያ ከህወሃት ጋር ከፍተኛ ጦርነት ውስጥ ገባች፤ ጭንቅ ሆነ፡፡ ያን ጊዜ ለትምህርት ወደ ራሺያ የተላኩ ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሱ ሲባል ግራ ገባን፤ ምክንያቱም ሁሉም ነገር ዝብርቅርቁ ወጥቷል፤ የምናውቀውና የምንወደው ባህር ሀይልም ሰላም አይደለም፤ ብዙ ጓደኞቼም ሞተዋል፡፡ እኔ እንዴት ነው የምመለሰው፤ ጓደኞቼ የሉ ባህር ሀይሉ የለ ብዬ ቀረሁ፡፡
ከዚያስ ራሽያ ቆዩ ወይስ ?
 ከራሽያ ወደ ስዊድን ሄድኩኝ፡፡ ስዊድን ሄጄ ህይወትን እንደገና ከዜሮ ጀመርኩኝ፡፡ ይህ እንግዲህ በፈረንጅ በ1990 ዓ.ም ወይም በእኛ 1980 ዓ.ም መሆኑ ነው፡፡
 እስኪ በስዊድን እንደገና ህይወትን እንዴት ከዜሮ እንደጀመሩት ያጫውቱኝ?
እኔ ህልሜ የነበረው እዚሁ አገሬ ተመልሼ በተማርኩት ሙያ መስራትና እውቀቴን ማካፈል ነበር።  ነገር ግን አዲስ ህይወት በስዊድን ጀመርኩ፡፡ የሚገርምሽ ራሽያና ስዊድን ፍፁም የተለያዩ ዓለማት ናቸው፡፡ በፖለቲካም፣ በባህልም በኑሮም ሆነ በሁሉም ነገር የሰፋ ልዩነት ነው ያላቸው፡፡ ከለመድሽው አካባቢ ሄደሽ ሌላ አዲስ ዓለም ውስጥ ስትገቢ ደግሞ  ብዙ የቤት ስራ ይጠብቅሻል፡፡ ኑሮውን፣ አየሩን፣ ባህሉን ለመልመድ ማለቴ ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን ስደት በጣም ከባድና አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ ቋንቋውን መማር በራሱ ከባድ  ነው፡፡ እኔ ስዊድን ስገባ ቶሎ ብዬ የሀበሻ ማህበረሰብ ውስጥ ነው የተቀላቀልኩት፡፡
የባህል ቀውሱን ፈርተው ነው ቶሎ ሀበሻን የተቀላቀሉት?
 አዎ! ራስን የሚመስል አግኝቶ አገር ለመላመድ፣ ሀበሻ ኮሚዩኒቲ ውስጥ መግባቴ ጥሩ ነው፡፡ ህይወትን ለማስቀጠል የሚሰሩትን ሥራዎች በሙሉ ከባርቴንደርነት ጀምሮ ያሉትን ሁሉ ሰርቻለሁ። ከዚያ የሙዚቃ ትምህርት ለመቀጠል ሞከርኩና ትምህርቱ በሙሉ የማውቀው ሆነብኝ፤ ምክንያቱም እኔ ሩሲያ ውስጥ ትልቅ የሙዚቃ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ነበርኩኝ፡፡ ነገር ግን በ1996 እ.ኤ.አ  አንድ ትምህርት አገኘሁ፤ ‹‹ካልቸር አድምኒስትሬሽን›› የሚባል። ይህ ትምህርት ተሰጥቶኝ ነው ይህ ሁሉ እድል የተከፈተው፡፡ ምክንያቱም እኔ ሁሌም ስዊድንም ከገባሁ በኋላ ወደ ሀገሬ ተመልሼ የመስራት ህልም ነው የነበረኝ። ይህን ለማድረግና ወደ ሀገር ተመልሶ እውቀት ለማካፈል ማወቅም ያስፈልጋል፡፡ የሰለጠነውን አለም እውቀት አንቺ ቀድመሽ ጠንቅቀሽ ካላወቅሽው ለሌላ ማካፈል አትችይም፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያ ትኩረቴ የስዊድንን ሲስተም ማጥናት ነበር፡፡ የስዊድን የባህል ዘርፍ እንዴት ነው የተመሰረተው? ከላይ ጀምሮ ምን ይመስላል? ማን ምንድን ነው የሚሰራው? መንግስት ምን አይነት ፖሊሲ ነው ያለው? የመንግስት ፖሊሲ ዋና ሚናው ምንድን ነው? ተቋማት አሉ ወይ? ካሉ ምን ይሰራሉ? ት/ቤቶች አሉ ወይ? የሚዲያ ሚናስ ምን ይመስላል? የሚለውን በሙሉ ለአንድ ዓመት አጠናሁና እ.ኤ.አ በ1997 ዓ.ም “ሰላም ኢትዮጵያ”ን ለመሞከር አቋቋምኩት፡፡
እኔ ስዊድን በሄድኩበት ጊዜ አጠቃላይ የስዊድን ህዝብ ብዛት 9 ሚሊዮን ብቻ ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ 2 ሚሊዮኑ የውጪ ሀገር ዜጎች ናቸው፡፡ የውጭ ሀገር ዜጎችም ይሁኑ ራሳቸው ስዊዲኖቹ ዓለም አቀፍ ነገር ይወዳሉ፡፡ ነገር ግን ያንን ዓለም አቀፍ ነገር ፕሮፌሽናል በሆነ መልኩ ሰርቶ የሚያቀርብ የለም፡፡ እኛ ያደረግነው ምንድነው? የታወቁ ሎካል ቦታዎች ላይ ፕሮፌሽናል ኢቨንት ማዘጋጀት ነው፡፡ ጥሩ ሀሳብና ፈጠራ ካለሽ የፋይናንስም ሆነ ሌሎች ድጋፎች ይደረጉልሻል። እኔን ለየት የሚያደርገኝ ምን መሰለሽ? ከመጀመሪያው ጀምሮ በትክክል ለመስራት ነው ያቀድኩት፡፡ እናም በተጠና መንገድ ፕሮጀክቴን አቀረብኩ፤ በፈጣን ሁኔታ ተቀባይነት አገኘ፡፡
በዚያው አገር ሲስተም ነው “ሰላም ኢትዮጵያ” የተቋቋመው?
ሁሉ ነገሩ በስዊድን ደንብና ሲስተም ነው የተቋቋመው፡፡ ከዚያ ወዲያው ፈንድ ማግኘት ጀመርን። ከዚያም የአፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካና የካሪቢያንን ሀገራት ሙዚቃና ባህል ለስዊድን ማስተዋወቅ ዋና ሥራችን ሆነ፡፡ ትልልቅ የሚባሉ ቦታዎች ላይ ኢቨንቶችን ማዘጋጀት ጀመርን። ሌላው ቀርቶ እዚያው ስዊድን ውስጥ ስዊድኖችም ሆኑ ሌሎች የውጪ ሀገር ሙዚቃዎችን የሚጫወቱ አርቲስቶችን ሁሉ መደገፍ ጀመርን፡፡ ይህን ተከትሎ ሚዲያውም ሁሉም አወቀን። የእኛ ኢቨንት በጉጉት የሚጠበቅ ሆነ፡፡ ከዚያ በኋላ መንግስትም ትኩረት ሰጥቶን መስራት ጀመርን፡፡ ጎበዝ ጎበዝ ሰራተኞችን ቀጥረን ትልልቅ ስራዎችን መስራታችንን ቀጠልን ማለት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ከየትኛውም ዓለም ትልልቅና ስመጥር አርቲስቶችን እያስመጣን ማሰራት ቀጠልን፤ ከአፍሪካም ከኢትዮጵያም ጭምር፡፡ አሁን የእኛ ሀገር ትልልቅ አርቲስቶች እነ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፣ አስቴር አወቀ፣ ሙላቱ አስታጥቄና ሌሎቹም በእኛ ስር ነው ስዊድን እየመጡ የሚሰሩት፡፡ የሚሰሩትም በትልልቅ መድረኮች ላይ ነው፡፡ አብሮን ያልሰራ ታዋቂ አርቲስት የለም፡- እነ አልፋ ብሉንዲ፣ እዩ ስዱር፣ አንጀሊ ኪዶ… ስንቱን ልጥቀስልሽ። ትልቁ ሥራችን ይሄ ነው፤ የዓለምን ሙዚቃ ለስዊድን ማስተዋወቅ፡፡ የስዊድን መንግስትም ድርጅታችንን አምኖ ድጋፍ እያደረገልን እዚህ ደርሰናል፡፡
 ‹‹ሰላም ኢትዮጵያ›› ስዊድን ቢመሰረትም ስራው ዓለም አቀፍ እንደሆነ ነግረውኛል፡፡ ግን  ኢትዮጵያ በተቋማችሁ አማካኝነት በስዊድን ምን ያህል ታወቀች? በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ያደረጋችሁት አስተዋፅኦ እንዴት ይገለጻል?
ይህን ጥያቄ ለተጠቃሚዎቹ ብታቀርቢ የበለጠ መረጃ ታገኚ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ የመጀመሪያው ነገር እኛ ይህን ስራ ለመስራት ይህን ትልቅ መድረክ ማግኘታችን እድለኞች ነን፡፡ ይህ ማንም የማያገኘው ዕድል ነው፡፡ እውነቴን ነው፤ በስዊድን ሀገር በጣም ትልልቅ ሥራ ከሚሰሩ በጣም ጥቂት የውጭ ሀገር ዜጎች አንዱ ነኝ፡፡ ይሄ ትልቅ እድል ነው። የእናቴም ፀሎት ይመስለኛል፡፡ እና በዚህ ሥራዬ ኢትዮጵያዊ እንደመሆኔ ለየት ያለ ስሜትም አለኝ፡፡ ለእኔ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በዚያ ትልልቅ መድረክ ማቅረብ ትልቅ ነገር ነው። ከዚህ ቀደም ተደርጎም አይታወቅም። ሌሎቹም የምር በእኛ ይቀናሉ፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በከፍተኛ ደረጃ በትልልቅ መድረክ አስተዋውቀናል፤ ለአርቲስቶችም እድል ሰጥተናል። እነ ዓለማየሁ እሸቴን፣ እነ ጋሽ ማህሙድ አህመድን ከወጣቶቹም ጭምር 20 ሺህ እና ከዚያ በላይ ታዳሚ ባለው መድረክ ላይ ነው የምናሰራቸው፡፡ የምናዘጋጅበትም ቦታም እዚያው ስቶክሆልም ውስጥ የኖቤል ሽልማት የሚሰጥበት ‹‹ኮንሰርት ሀውስ›› የሚባል ትልቅ መድረክ ላይ  ነው፡፡
እንደዚህ አይነት መድረኮች የዚያ ሀገርም ሆነ የውጪው ዜጋ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ያለውን ፍቅር የምናይበት መስታወት ነው፡፡ በተለይ ሀበሻው ደስታውን፣ ኩራቱን፣ አክብሮቱንና ፍቅሩን እየገለፀ ሲያመሰግነኝ፣ ከዚህ በላይ ደስታና እርካታ የለም፡፡ እውነት ለመናገር በዚህ ጉዳይ ከእኛ ይልቅ ሌሎች ቢናገሩ ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን እኛ በተቻለን መጠን በሙዚቃችን ኢትዮጵያ ያላትን ነገር እያስተዋወቅን ነው፡፡ እውነቱን ልንገርሽ፤ ሀገርሽን ለማገዝ የግድ ፖለቲከኛ መሆንና የፖለቲካ ንግግር ማድረግ የለብሽም፡፡ እኛ በሙዚቃችን ከፖለቲካና ከዲፕሎማሲ ስራ በላይ የሆነ ሥራ እየሰራን ስለመሆኑ በልበ ሙሉነት መናገር እንችላለን፡፡ በዚህ ሥራዬ እንደ ኢትዮጵያዊነቴ ብሎም እንደ አፍሪካዊነቴ እኮራለሁ።
ሌላው የስዊድን መንግስት በህክምና በግብርናና በመሳሰሉት ነገሮች ሌሎች አገሮችን ይረዳል፡፡ እኔም ከ20 ዓመት በፊት ከስዊድን መንግስት ጋር በመነጋገር የባህል ዘርፉን ለምን አናግዝም በሚል የተለያዩ ጥናቶችን መስራት ጀመርኩ፡፡ በእርግጥ የዛን ጊዜ ህልሜ የነበረው አሁን እዚህ የገነባነውን አይነት ፕሮፌሽናል መድረክ መገንባት ነበር፡፡ ምን ማለት ነው? በውጪ ሀገር ያለው ልምድ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ፣ ሙዚቃው እንዲያድግና ሙያተኛው በሙያ እንዲጎለብት ማድረግ ነበር፡፡ ምክንያቱም ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ፕሮፌሽናል ስቱዲዮ ያለው አበጋዝ ብቻ ነበር፡፡ ሌሎቹ ለመቅረፅ ስቱዲዮ ፍለጋ አሜሪካ ድረስ ይሄዱ ነበር፡፡ እኛ አሁን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስቱዲዮ እዚህ ገንብተናል (አሁን እኔና አንቺ የምንነጋገርበት ስቱዲዮ ማለት ነው)። ከዚያ ፕሮዲዩሰሮች እንዲሰለጥኑ እያደረግን ነው። አሰልጣኞችንም ከውጪ እያስመጣን እስካሁን አስራ ምናምን ፕሮዲዩሰሮችን አሰልጥነናል። አሁን ከተማ ውስጥ እነ ይትባረክና ኪሩቤል የተባሉ ልጆችን አብቅተን ሁሉን ነገር ይሰራሉ፡፡ ስቱዲዮ ፍለጋ ውጪ ሀገር መሄድም አያስፈልግም፡፡ ይህ እንግዲህ ከ20 ዓመት በፊት የነበረ ህልም ነው፤አሁን እውን አድርገነዋል። ለኢትዮጵያም ትልቅ አበርክቶ ነው ብዬ አምናለሁ። በውጪ ያለውን እዚህ ለመተግበር አክሰስ ስለሌለ እንጂ እውቀት ጠፍቶ አይደለም። እውነት ለመናገር እኛ ያንን ለማድረግ ሞክረናል፡፡
ወደ ጥናቱ ስመለስልሽ የባህል ሴክተሩ ከላይ እስከ ታች በሚገባ ካልተደረጀ በዘርፉ ለውጥ አይመጣም፡፡ አሁንም ትልቁ ተግዳሮታችን ይሄው ነው፡፡ መንግስት ጠንካራ ፖሊሲ ኖሮት ካልሰራ፣ የተለያዩ ተቋማት ካልተገነቡ፣ የተጠናከሩ የሙያ ማህበራት ከሌሉን፣ የኮሜርሽያል ዘርፉ ጠንካራ ካልሆነና በባህሉ ላይ መንግስት ኢንቨስት ካላደረገ አስቸጋሪ ነው፤ ማደግ አንችልም። በሁሉም ዘርፍ ደግሞ የተማሩና የሰለጠኑ ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ ለምሳሌ በእኛ በሙዚቃ ዘርፍ ብንመለከት በሙዚቃ ስቱዲዮ፣ በፊልም፣ በፕሮዲዩሰርነት፣ በሙዚቀኛነት በትዕይንት ዘርፍ ሁሉም ትምህርት ይጠይቃል፡፡ እኛም ይህን ለማገዝ “ሰላም ኢትዮጵያ”ን አቋቋምን። ይህ በፈረንጆች 2005 ዓ.ም አካባቢ ነው፡፡ እናም በዚያን ጊዜ የተለያዩ የሙዚቃ ማህበራትን ለመርዳት፣ ኮርሶችን ለመስጠትና የመሳሰሉትን ለማድረግ ሞክረናል። አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገርም ደረጃ ላይ ነን፤ ትልልቅ ሥራዎችን እየሰራን ነው፡፡ ግን ያን ጊዜም ይሄ ሁሉ ህልም ይታየኝ ነበር፡፡ ይህን ኢትዮጵያ ውስጥ ብናደርገው፣ ይህን ብናከናውን፣ ይሄኛው እዚያ እንዲለመድ ብናደርግ እል ነበር። ያው ለሁሉም ጊዜ አለውና ሁሉም በጊዜው ነው የሚሆነው፡፡ ያኔ የሪኮርድ ሌቭሉ እኛም ጋር ቢመጣ እል ነበር። ድሮ ምስጢር የሚመስለን ነገር አሁን ምንም ምስጢር አይደለም፡፡ እዚያው ስለምኖር አየዋለሁ። እኛ የጎደለን የእውቀት ሽግግሩ ብቻ ነበር። እኔ አሁን የምለው ከላይ ያሉት ሀላፊዎች ወርደው ፕሮዲዩስ ያድርጉ አይደለም፡፡ ነገር ግን ለዘርፉ አመቺ የሆኑ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ያዘጋጁ።  ይህን ካደረጉ ሌላውን ባለሙያው ደስ ብሎት ይሰራዋል፡፡
ስለዚህ “ሰላም ኢትዮጵያ” በውጪው ዓለም የሚሰራበትን የቴክኖሎጂ ደረጃ አሟልቶ ዘመናዊ የሙዚቃ ስቱዲዮ ገንብቷል። ቃለ ምልልሱንም እያደረግን ያለነው በዚሁ ዘመናዊ ስቱዲዮ ውስጥ ነው፡፡ አሁን ተቋማችሁ እንደ ስልጠና ማዕከልም እንደ ሙዚቃ አምራች ኩባንያም ሆኖ እያገለገለ ነው ማለት ይቻላል?
ትክክል ነው፤ እንደ ስልጠና ተቋምም እያገለገለ ነው፡፡ በተጨማሪም፣ ‹‹ሙዚቃዊ›› በተሰኘው የሙዚቃ ፕሮዲዩስ ማድረጊያ ተቋማችን የተለያዩ የሀገራችንን ባለሙያዎች ትልልቅ ስራዎች ፕሮዲዩስ እያደረግን እንገኛለን፡፡
 ‹‹ሙዚቃዊ›› በተሰኘው ተቋማችሁ አኒስ ጋቢ የተሰኘ ወጣት የኦሮሚኛ ሙዚቃ ተጫዋችን አንድ ነጠላ ዜማ ቪዲዮ እዚሁ ፕሮዲዩስ አድርጋችሁ ስታስመርቁ ጋብዛችሁኝ ተገኝቼ ነበር። በቅርቡም የአንጋፋው ሙዚቀኛ ዳዊት ይፍሩን በመሳሪያ የተቀነባበሩና ከ45 ዓመት በፊት የተሰሩ ሥራዎችን በሸክላ አሳትማችሁ ከሳምንታት በፊት በጊዮን ሆቴል አፍሪካ ጃዝ መንደር ስታስመርቁም ተመልክቻለሁ፡፡ ከሁለቱ ሌላ ፕሮዲዩስ ያደረጋችሁት ሌላ አልበም ወይም ነጠላ ዜማ አለ?
እስካሁን ፕሮዲዩስ ያደረግናቸውና የወጡ ስራዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ባልከው አለሙ የተባለ ጎበዝ ድምፃዊ ሥራን ሰርተናል፡፡ ‹‹ኢትዮ ከለር›› የተሰኘ አልበምም ፕሮዲዩስ አድርገናል፡፡ ስንታየሁ የተባለች አርቲስት ስራም በእኛው ስቱዲዮ ፕሮዲዩስ ተደርጓል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው የአኒስ ጋቢን ስራ ፕሮዲዩስ ያደረግነው፡፡ እንዳልሽው በቅርቡ የዳዊት ይፍሩን አልበም ፕሮዲዩስ አድርገን በሸክላ አሳትመናል፡፡
የሸክላው ሙዚቃ  ከሚያዚያ 30 ጀምሮ ለገበያ  ቀርቧል። የኦንላይን አልበሙን ጊዮን ካስመረቅንበት ጊዜ ጀምሮ በሁሉም የሙዚቃ መገበያያ ፕላት ፎርሞች ለገበያ ቀርቧል፡፡ የዳዊት ይፍሩ ትንሽ ለየት ያለ ነው፣ በደንብ መግለፅ እፈልጋለሁ። ከዚያ ውጪ ግን በጣም ብዙ ስራቸውን ጨርሰው የሚጠባበቁ አሉ፡፡
ወረፋ ነው የሚጠባበቁት?
 ወረፋ ብቻ ሳይሆን ገና ብዙ ሥራ የሚጠይቁ አልበሞች አሉ። ለእሱ በደንብ እየተዘጋጀን ነው፡፡ ለምሳሌ የእውቁ የጃዝ ሙዚቃ ተጫዋች ጆርጋ መስፍን ሥራ ቀጣዩ ፕሮጀክታችን ይሆናል፡፡ ሌሎችም ወጣቶች የሂፕ ሆፕ ሙዚቃ ተጫዋቾች ‹‹አዝማች›› የሚባል ባንድ አለ፣ ‹‹ጎንደር ፋሲለደስ›› የሚባሉ የጎንደር ሙዚቃ ቡድኖችም እንዲሁ አሉ፡፡ በጣም ብዙ ስራ ለመስራት ዝግጅት ላይ ነን፤ነገር ግን እዚህ አገር አንድ ትልቅ ችግር አለ፡፡
ምንድን ነው ችግሩ?
 በቦታው ስለነበርሽ የዳዊት ይፍሩን አልበም ስናስመርቅ የተናገርኩትን ሰምተሽኝ ይሆናል። ችግሩ የቅጅ መብት አለመከበር ነው። እዚህ አገር የቅጂ መብት አለመከበር፣ ለሙዚቃ ኢንዱስትሪው ትልቅ እንቅፋት ሆኗል፡፡ ይህ መሰረታዊ ችግር ካልተፈታ አሁንም በስራው ላይ ትልቅ ችግር ይፈጥርብናል። ሌላው ዓለም ይህንን መብት አስከብሮ ባለሙያ ከስራው ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሥርዓት አስተካክሏል፡፡ በዚህም አገር የቅጅ መብትን ለማስከበር የተቋቋሙ ድርጅቶች አሉ፡፡ ነገር ግን ተጠናክረው መስራትና ይህን ችግር መቅረፍ አለባቸው፡፡ ይህ እስካልተቀረፈ ድረስ እዚህ ዘርፍ ላይ ኢንቨስት ማድረግ በጣም ይከብዳል፡፡
የሮያሊቲ ክፍያ እንዲኖር፣ ባለሙያው ከልፋቱ እንዲጠቀምና ሙያውም በራሱ በአግባቡ እንዲከበር ነፍሱን ይማርና ስመ ጥሩው የሙዚቃ ባለሙያ ኤሊያስ መልካ ከጓደኞቹ ጋር እስትንፋሱ እስከቆመበት ጊዜ ድረስ ሲታገል እንደነበር ይታወቃል……
እውነት ነው፤በጣም ደክሞ ነበር። እስካሁን ግን በተግባር የታየ ውጤት የለም፡፡ እኛ ከዚህ በፊት ይሄ ነገር እውን እንዲሆን በተለያየ መንገድ ድጋፍ አድርገናል። ለምሳሌ ስልጠና ለመስጠት ሰዎች ከውጭ እያስመጣን፣ ከዚህም ወደ ውጪ እየሄዱ እውቀት እንዲያገኙ ስናደርግ ነበር፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ትልቅ ትብብርና ስራ የሚፈልግ እንጂ በሰላም ኢትዮጵያ ጥረት ብቻ የሚፈታ አይደለም፡፡
ወይም አርቲስቶቹ ሁሌ ስላለቀሱና ስለተቆጩበት ብቻ የሚቀረፍ አይደለም፡፡ ይሄ በመንግስትም ትልቅ ትኩረትን የሚሻ ነው፡፡ ይህን መብት ለማስከበር የተደራጁትን ድርጅቶች በገንዘብም፣ አመቺ ፖሊሲና ስትራቴጂ በማውጣትም ማገዝን ይጠይቃል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች በአቅማቸው ትልቅ ትግል ላይ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ እንደኔ እሳቤ ይሄ ነገር የሚሆነው በመንግስትም፣ በህብረተሰቡም ሆነ በሚዲያው ትልቅ ትኩረት ሲሰጠው ነው፡፡ እኔ በተለያዩ ሀገራት ስዘዋወርና የሙዚቃ ኢንዱስትሪያቸው እንዴት እንዳደገ ስመለከት፣ ሁሉም የቅጅ መብት የሚስከብሩላቸውን ጠንካራ ተቋማትና ኮሌክቲቭ ሶሳይቲ የሚባሉትን አቋቁመዋል፡፡ ሁሉም ህግና ሥነስርዓት ሲይዝ ኢኮኖሚውም ያድጋል፡፡ ያለበለዚያ ግን ችግሩ ቀጥላል፡፡
ለምሳሌ የዳዊት ይፍሩን እንውሰድ፡፡ ቅድም የዳዊት ይፍሩ የተለየ ነው በደንብ መግለፅ እፈልጋለሁ ብዬሽ ነበር፡፡ የዳዊት ይፍሩን ሸክላም ጭምር ነው ያዘጋጀነው፡፡ ሸክላ ስናዘጋጅ ከ45 ዓመት በፊት የሰሩትን ካሴት ያውም በደንብ የማይሰማ ካሴት ነው የሰጡን፡፡
 እኛ እሱን ወደ ስዊድን ወስደን ድምፁን አጥርተን፣ ወደ ሸክላ ቀይረን፣ ስራቸውን በኢንተርናሽናል የቅጅ መብት ባለቤትነት አስመዝግበን ነው የተቀረፀው። ማነው ያቀናበረው? ማን ነው ያጀበው? የሚለውን ሁሉ ፅፈን ለዘላለም ታሪክ ሆኖ እንዲቀጥል ነው ያደረግነው፡፡ ይሄ እንደ ልምድና እንደ ባህል እንዲቀጥል ነው የምንፈልገው። መጋቢት 30 ነው የተለቀቀው፡፡ በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ነው የተለቀቀው። ለውጪዎች ቅድሚያ እንዲያዝዙ ተደርጓል፡፡ ሸክላው በእጅሽ ላይ ታሪክ ሆኖ የሚቀመጥም ነው፡፡ ቀድማችሁ እዘዙ ብለን ማስታወቂያ ስንለቅ ከጃፓን፣ ከእንግሊዝ ከየትና ከየት ትእዛዝ እየመጣ ነው፡፡ ምን አይነት ሙዚቃ ነው እየተባለ፡፡ ይሄ የሚያሳየው ብዙ የሙዚቃ ሀብታችን አለም ሳያውቀው ተቀብሮ ቀርቷል የሚለውን ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል አሁንም እጃችን ላይ ያልተጠቀምንበት ትልቅ ሀብት መኖሩንም አመላካች ነው፡፡
 ቅድመ ትዕዛዙ ምናልባት የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ያለውን ፍላጎት ማሳያ ይሆናል ብዬ አስባለሁና እስኪ ስለ ፍላጎቱ በደንብ ያብራሩልኝ?
 በጣም የሚገርምሽ እኛ ስዊድንና በዚያ አካባቢ ያለ ትልቅ ኔትወርክ ስላለን አለም አቀፉ ማህበረሰብ ምን እንደሚፈልግ እናውቃለን፡፡ የሸክላው ጉዳይ በጣም እየተፈለገ ነው፡፡ ይሄ የዲጂታል ሁኔታ እንዳለ ሆኖ የሸክላው ህትመት እየተፈለገ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የድሮ ሙዚቃ ጥራት ያለው ነው፤ ቅንብሩ ድምፁ ሁሉ ምንም ሳትነካኪው በራሱ እዚያ ሲያዳምጡት ዋው ነው የሚሉት! ስዊድን ያሉ ሰራተኞቻችን ሲያዳምጡ በጣም ነው የሚደነቁት። ምን አይነት ሙዚቃ ነው እያሉ ማመን ያቅታቸዋል፡፡ አሁን የዳዊት ይፍሩን በዚህ አይነት አሳተምን፡፡ ስራው ሁለት ሶስት ወር ፈጅቷል። ፈረንሳይ አገር ነው የታተመው፡፡ በሁለት ሶስት ሳምንት ውስጥ ከመላው ዓለም የማይመጣ መልዕክት የለም፤ በተለይ ከጃፓን ከጀርመን፣ ከእንግሊዝ፣ ሌላው ቀርቶ ከአሜሪካ ሁሉ ይመጣል። ይሄ እንግዲህ በሁለት ሳምንት ውስጥ ነው፡፡ ይሄ ግን የሚያመላክተው ትልቅ ነገር አለ፡፡ ያልተጠቀምንበት አንድ ትልቅ ሀብት አለን፡፡ እንደ ሙዚቃዊም ይህን ዘርፍ መረዳት እንችላለን፡፡ በአጠቃላይ የሙዚቃ ዘርፍ አለም አቀፍ እንዲሆን እዚህ ያለው መሰረታዊ ነገር መስተካከል አለበት፡፡ ሌላው እኛ ሸክላውን ለውጪ ገበያ ብለን ነው ያዘጋጀነው፡፡ ነገር ግን ባልጠበቅነው መንገድ አገር ውስጥም ከፍተኛ ፍላጎት አለ፡፡ የት ነው የምንገዛው እያሉ ኢሜል እያደረጉ ነው፡፡ በተለይ ወጣቱ የተማረው ክፍል ፍላጎት እያሳየ ነው፡፡ ስለዚህ አገራችን ውስጥ ያለን ሀብት እንደ ቡናችን ለአለም አቀፍ ገበያ ኤክስፖርት መደረግ የሚችል ነው፡፡
 ዋናው ነገር መንግስት በዚህ ጉዳይ አረዳዱ ቢስተካከልና ቢገባው ትልቅ ሀብት እጃችን ላይ አለ፤ ልንመነዝረው እንችላለን፡፡ እኔ በዚህ ጉዳይ መለፍለፍ ከጀመርኩ 20 ዓመት ሆኖኛል፡፡ ግን ሰሚ ጠፋ፡፡
ለምሳሌ የጋሽ ሙላቱ ‹‹ኢትዮ ጃዝ›› በውጪው ዓለም እንደ ቡናችን ነው የሚታወቀው፡፡ ስለ ሙዚቃ ስታወሪ ‹‹ኢትዮ ጃዝ›› ይሉሻል፡፡ ከስዊድን ጓደኞቼ ጋር ስናወራ ቡናና ኢትዮ-ጃዝን ነው የሚጠሩት፡፡
ያንን አቅም አልተረዳነውም፡፡ መንግስት ሙያተኛውን አጠናክሮ ቢደግፍ የውጪው ዓለም የደረሰበት ደረጃ ላይ መድረስ ይችላሉ፡፡ እኛም የተለያዩ ጥናቶችን ሰርተን ሰጥተናቸዋል።




Read 1624 times
Administrator

Latest from Administrator