Saturday, 15 April 2023 21:57

ፍቅርን ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም!

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(4 votes)

ዛሬ፣ ድሮ ዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አብሮኝ የተማረዉን የወንዜን ልጅ ዳንኤል አስፋዉን መንገድ ላይ አገኘሁት፣ ዌስትሚንስተር ከሚገኘዉ መሥሪያ ቤቴ ወጥቼ ወደ መኖሪያ መንደሬ ብሪክስተን በእግሬ እያቀናሁ ሳለ፣ መሐል ለንደን ላይ፡፡ መንገድ የማያገናኘዉ ሰዉ የለ፡፡ ለካ ሰዉ ካልሞተ በቀር ዳግም ይገናኛል የሚለዉ አባባል እዉነት ነዉ፡፡ ዳንኤል ከእኔ ተቃራኒ አቅጣጫ በጥድፊያ ገስግሶ አልፎኝ ሊሄድ ሲል፡
“ዳንኤል!” ብዬ ተጣራሁ ዐይኔን ጋርጀበት የነበረዉን ጥቁር የዐይን መከላከያ መነፅር ከዐይኞቼ ላይ እያሸሸሁ፣ ለይቶ እንዲያዉቀኝ፡፡ ጥሪዬን የሰማዉ ዳንኤል ርምጃዉን ገቶ ዐይኖቹን ገፄ ላይ አተኮረ፡፡
“ኦ! ሐመልማል ግርማ! ከየት በቀልሽ? ይገርምል!” አለ ዳንኤል ዐይኖቹን ዐይኖቼ ላይ ሰፍቶ፡፡ ማንም ሰዉ ከአገሩ ልጅ ጋር ድንገት ባዕድ አገር ጎዳና ላይ ቢገናኝ መገረሙ አይቀርም፡፡ በልቦናችን ጊዜ የፈጠረዉን ትዕንግርት እያደነቅን ደጋግመን ተቃቀፍን፡፡ የአገሬ ሰዉ ርቦኝ ነበር፡፡ እንደ እኔዉ ጤፍ እንጀራ በዶሮ ወጥ፣ በድልህ፣ በስልጆ፣ በምስር ወጥ፣ በተልባ፣ በእልበት፣ በጎመን፣ በዳካ፣ በዱባ ወጥ፣ በሽንብራ ዓሣ፣ በሽሮ ወጥ ሲበላ ያደገ፡፡ በአስራ ሦስት ወር ፀሐይ አናቱን ሲያነድ የኖረ፡፡ በአደይ የተንቆጠቆጠ መስክ ላይ እየተንከባለለ ልጅነቱን የሸኘ፡፡ የሾላ፣ የዶቅማ፣ የዋርካ፣ የጀባ፣ የዋንዛና የእንኮይ ፍሬ ሸምጦ የበላ፡፡ አባይን፣ ተከዜንና አዋሽን ጠጥቶ ያደገ፡፡ ሲያቅፏት አሪቲ አሪቲ የምትሸት፣ አደስ አደስ የምታዉድ፡፡ ፈትል ቀሚስ የምትለብስ፣ በማርዳና ድሪ የምታጌጥ የወንዜ ልጅ እጅግ ናፍቃኝ ነበር፡፡ ለንደን ከተማ ጥቂት ሐበሾችን ነዉ በአካል አግኝቼ መተዋወቅ የቻልኩት፡፡ አሁን ባይተዋር ነኝ፡፡ ባዕድ አገር ያገኘሁት ሮበርት ጀምስ እንኳ አሁን ጎኔ የለም፡፡ አመት ሞላን እህል ዉሃችን ከተቋጨ፡፡ በርነል ዩኒቨርሲቲ ለንደን ዉስጥ ተማሪ ሳለሁ ከተዋወቅኳት ጌራወርቅ ተሾመ ጋር በዐይነ ሥጋ ከተገናኘን ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ለንደን ከተማ ዉስጥ የሚገኝ ሙዚየም ዉስጥ ተቀጥሮ ይሠራ የነበረዉ ተስፋዬ ኩምሳ ጓዙን ጠቅልሎ አገር ቤት ከገባ ረጅም ዓመት ሆኖታል፡፡ ጎረቤቴ የነበረዉ ግርማ ደምሴ አገር ቤት ተመልሶ አሁን ዲታ ነጋዴ ሆኗል፡፡ ኪንግስተን ዉስጥ ቡና ቤት ከፍታ ትሠራ የነበረችዉ ወሎዬዋ ዘሪቱ ሲሳይ ፈረንጅ ባሏን ተከትላ ጀርመን ከሄደች ድፍን ሁለት ዓመታት አለፉ፡፡  
ዳንኤል ገና እንዳየኝ ነበር ለይቶ ያወቀኝ፡፡ የዳንኤል የፊት ገፅታ በአእምሮዬ ሸራ ላይ ታትሞ ከነበረዉ የቀድሞ መልኩ ብዙም አልተለወጠም፡፡ ብዙ ጊዜ፣ በኮረዳነት ዘመኔ ዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያሳለፍኳቸዉን ትዝታዎች ሳጠነጥን በግንባር ቀደምትነት ትዝ ከሚሉኝ ሰዎች መካከል አንዱ ዳንኤል ነዉ፡፡
ከዳንኤል ጋር እዛዉ ዌስትሚኒስቴር አካባቢ ወዳለ ዘ ሀይደን የተባለ ሆቴል ዘልቀን (ብዙ ጊዜ ወደ እዚህ ሆቴል ከሮበርት ጋር እንመጣ ነበር)፣ ብዙ አሮጌ ታሪኮችን እያነሳን ኮመኮምን፡፡ ዳንኤል ማዉጋት ይችላል፡፡ የቆዩ ኩነቶችን ትናንት የተደረጉ ያህል ዝርዝር ታሪካቸዉን ሳይጎራርድ ልቅም አድርጎ መተረክ ይችላል፡፡ ምን ምን አወጋኝ? ተማሪ ሳለን እኔ ላይ ጆፌ የጣለ የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ጎረምሳ ብዙ እንደ ነበር፣ እኔም ጎረምሶች የሚሰዱልኝን የፍቅር ደብዳቤ ከተቀበልኩ በኋላ ምላሽ ጽፌ የማልሰድ ትዕቢተኛ እንደነበርኩ፣ ምኒልክ ዉስጥ በቀለም ቀንድነቷ ትታወቅ የነበረችዉ ገነት አሰፋ መርዝ ጠጥታ ራሷን ልትገል የሞከረችዉ እሱ ፈንግሏት መሆኑን፣ የኮሎኔል ልጅ ከነበረቺዉ ኤልሳቤጥ ኃይሉ ጋር ኮብልለዉ ሦስት የክረምት ወራትን ሻሸመኔ እንደኖሩ … ወዘተ፡፡ ዳንኤል ምኒልክ ትምህርት ቤት ዉስጥ በሦስት ነገሮች ዝናዉ የናኘ ተማሪ ነበር፤ በዘፋኝነቱ፣ በቀልደኛነቱና በሴት አዉልነቱ፡፡ ቅቤ እሚጠብስ ምላሱ አባብሏት ቀሚሷን ያልገለበችለት የምኒልክ ትምህርት ቤት ሸጋ የለችም ይባል ነበር፡፡ ግን ያዉ ሐሜት ነዉ፣ በተጨባጭ ያረጋገጥኩት ነገር የለም፡፡ ምናልባትም ተማሪ የሚነዛዉ ወሬ እዉነት ሊሆን ይችላል፤ መቸስ ሐሜት እንደ ሰርዶ፣ እንደ ሙጃ ያለ ምክንያት እንዲሁ በባዶ ሜዳ አይበቅል፡፡ ዳንኤል ሁሌ ሲታይ ሴት አቅፎ ነዉ፡፡ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ዉስጥ ሲዞር እጁን ሴት ወገብ ላይ ጠምጥሞ ነዉ፣ መማሪያ ክፍል ዉስጥ ሲቀመጥ ኮረዳ አቅፎ ነዉ፣ በመንገድ ሲሄድ ጎኑ ልጃገረድ ሸጉጦ ነዉ፡፡
ዳንኤልን ካገኘሁበት ዕለት አንስቶ የደበዘዙ፣ የተሰወሩ፣ የተፋቁ የሚመስሉ ግን በአሻራቸዉ በተበተቡኝ፣ በዘመን ብዛት ትተዉኝ ሸሽተዋል ያልኳቸዉ፤ በተቃራኒዉ ድንገት ከመሸጉበት ሥፍራ ተግበስብሰዉ በመዉጣት ዛሬም አንለቅሽም ብለዉ በሚነዘንዙኝ መንቻካ ትዝታዎች መባዘን ዕጣዬ ሆኗል፡፡ ቆየ፤ ደስታዬ ሸሽቶ ትካዜ ከከበበኝ፡፡ ሁሌ የሚያባዝኑኝ፣ ከአእምሮዬ ብራና ላይ ያልተፋቁት ትዝታዎቼ የሀኒባል ወርቁ ቁራኛዎች ናቸዉ፡፡
ሀኒባል ወርቁ የመጀመሪያ ፍቅረኛዬ ነዉ፣ ኮረዳ ቢራቢሮ ሳለሁ በርሬ የቀሰምኩት የአዱ ገነት ሸበላ፣ ቆነጃጅት በሰልፍ ዱካዉን ተከትለዉ የሚያረግዱለት የሸገር ጣዝማ፡፡ ሁልጊዜ ሳሎን ቤቴ ዉስጥ የሰቀልኩትን፣ ሥነ ጥበብ ኮሌጅ ተማሪ ሳለ ስሎ በስጦታ ያበረከተልኝን፣ እርቃኔን አሮጌ የቀርከሃ ሶፋ ላይ ተቀምጬ የምታይበትን የሸራ ላይ ሥዕል ሳይ አንጀቴ በትዝታዉ ማዕበል መናወጥ፣ በናፍቆቱ ረመጥ መንገብገብ ይጀምራል፡፡ እንዲያ ልቤ እስኪጠፋ እወደዉ የነበረዉ ሮበርት እንኳ ሀኒባልን ሙሉ በሙሉ አላስረሳኝም፡፡ 1995 ዓ.ም ማብቂያ ላይ ከሀኒባል ጋር ፍቅር በጀመርን በወሩ ሲኒማ ልናይ ፒያሳ ሲኒማ አምፒር ተቀጣጠርን፡፡
ቅዳሜ ተቀጣጥረን አርብ ሌሊትን እንዲሁ ሀኒባልን ሳስብ እንቅልፍ በዐይኔ ሳይዞር አነጋሁ፡፡ ከወንድ ጋር ስቀጣጠር የመጀመሪያዬ ነበር፡፡ የወንድ ወዳጅ የያዙ ታላላቆቻችን እኔ ያላለፍኩበት ብዙ ታሪክ፣ ብዙ ገጠመኝ ሲያወጉ አዳምጫለሁ፡፡ ለሁሉም ነገር ባይተtዋር ነኝ፡፡
አይደርስ የለም የጓጓሁለት ቀን ቅዳሜ ባተ፡፡ ረፋድ ላይ ከቤቴ ወጥቼ በታክሲ አሮጌዋ ፒያሳ ገባሁ፡፡ ፒያሳን ለመጀመሪያ ጊዜ የረገጥኩት ያን ዕለት ነዉ፡፡
ሀኒባል ከተቀጣጠርንበት ሰዓት ጥቂት ዘግይቶ ከመንገዱ ማዶ ብቅ አለ፡፡ በናፍቆት የተንሰፈሰፉት ዐይኖቼ እላዩ ላይ ተንከራተቱ፡፡ መለሎ መሆኑን ያስተዋልኩት ያን ዕለት ነበር፡፡ ነጭ ቲሸርቱ ላይ እጅጌ የሌለዉ ሰማያዊ የጅንስ ኮት ደርቧል፣ ፀጉሩን ፍሬንች ተቆርጧል፡፡ ደረተ ሰፊ ነዉ፣ ግርማ ሞገስ ያለዉ፡፡ በእጁ ቀይ ፅጌረዳና በቢጫ ወረቀት የተጠቀለለ ነገር ይዟል፡፡ አስፓልቱን አቋርጦ እንደ ተሻገረ ሄጄ አንገቱ ላይ እንደ ልጅ ተጠመጠምኩ፡፡
ሲኒማ ቤቱ ዉስጥ ሀኒባል ያመጣልኝን ቸኮሌት እየበላሁ ተቃቅፈን፣ በዕለቱ የሚታየዉ የባህር ማዶ ፊልም ትልቅ ፖስተር ፊት ተገትረናል፡፡ ፖስተሩ ላይ በጉልህ የተጻፈዉ የፊልሙ ርዕስ ላስት ታንጎ ኢን ፓሪስ ይሰኛል፡፡ እንደተቃቀፍን ፎቅ ወጥተን የመጀመሪያዉ ረድፍ መጨረሻ ወንበር ላይ ተቀመጥን፡፡ ዕለቱ ቅዳሜ ስለሆነ ሳይሆን አይቀርም ሲኒማ ቤቱ በተመልካች ተጨናንቋል፡፡ የሀኒባልን ትከሻ ተደግፌ የአንገቱን ዝባድ ጠረን እየማግሁ ከሲኒማ ስፒከር ጎላ ብሎ የሚንቆረቆረዉን የጥላሁን ገሠሠ ስትሄድ ስከተላት የፒያኖ ቅንብር በተመስጦ አዳምጣለሁ፡፡ ሀኒባል በግራ እጁ አንገቴን አቅፏል፡፡ ሙዚቃዉ ፊልሙ እስከሚጀምር መቆያ ነዉ፡፡  
 “ይህን ሙዚቃ በጣም ነዉ የምወደዉ፡፡”
 “የጥላሁን አድናቂ ነሽ?”
  “አዎ በጣም!”
 “አንተ የምታደንቀዉ ዘፋኝ ማን ነዉ?”
“ማን አለ ጥሩ ዘፋኝ? ያዉ ሙሉቀን መለሰ ነዋ! ሙሉቀን እኮ ልዩ ነዉ፡፡” ስለ ሙሉቀን መለሰ ታላቅ ዘፋኝነት የአባቴ ጓደኛ ደምሴ አዘዉትሮ ይናገራል፡፡ ሙዚቃ እናዉቃለን የሚሉ የሙሉቀን አድናቂዎች ናቸዉ፡፡
ደምሴን ሙዚቃ ያዉቃል ይሉታል፡፡ ሙዚቃዉ እንዳበቃ የፊልሙን መጀመር የሚያበስረዉ ደወል ተደወለና መብራቶች ጠፍተዉ ዐይኖች ሰፊ ስክሪኑ ላይ ተሰፉ፡፡
መሪ ተዋናዩ ማርሎን ብራንዶ የሚተዉነዉ ፖል የተባለ ሚስቱን በሞት ያጣ ገጸባሕሪን ተላብሶ ነዉ፡፡
ሴቷ መሪ ተዋናይ ማሪያ ሽናይደር የምትጫወተዉ ጄን የተባለች ኮረዳ ገጸባሕሪን ተላብሳ ነዉ፡፡ መሪ ተዋናዩ ወንዳወንድና ሞገሳም ነዉ፡፡ የሀኒባል ዐይኖች የፊልሙ ትዕይንት ላይ ቢተከሉም እጆቹ ሥራ አልፈቱም፡፡ የጡቶቼን ጫፎች ነካክቶ ያጋመበት ቀኝ እጁ ጭኖቼ መካፈያ ወዳለዉ አፍረቴ ገባ፣ ኤሌክትሪክ የጨበጥኩ አይነት አካላቴ ተንዘረዘረ፡፡ ቀስ ብዬ እጁን ከጭኖቼ መሐል አሽሽቼ ዐይኖቹን ላይ ስቃና ከንፈሮቹ ከንፈሮቼን ጎረሱ፡፡ ከንፈሮቼ አፉ ዉስጥ እንደ ሰም የቀለጡ መሰለኝ፡፡ ሁለመናዬ በወሲብ ቋያ ነደደ፡፡
በእዛች ለመጀመሪያ ጊዜ ወንድ ተከትዬ ፒያሳን በረገጥኩበት እለት ብዙዎችን  የነፈግሁትን ብር አንባሬን በሀኒባል አስገሥሼ ቤቴ ተመለስኩ፣ ፍቅር ረቶኝ፡፡ ለሚወዱት ሰዉ ምን የሚከለክሉት ነገር ይኖራል? በእዛ ቀን፣ እንደ እኔ ደስተኛ የነበረ ሰዉ ዓለም ላይ ቢፈለግ አይገኝም፡፡  
     *  *  *                                         
የወንዜ ልጅ ዳንኤል አስፋዉ እንግሊዝን ለቆ ስዊዘርላንድ በገባ በወሩ (ልሰናበተዉ ቤቱ የሄድኩ ዕለት እንዴት በለቅሶ እንደፈረስኩ) ሮበርት እርቅ ሊጠይቀኝ ቤቴ መጣ፡፡ ዳግም ዐይኑን ማየት እንደማልሻ እቅጩን ነግሬ ሸኘሁት፡፡ ሮበርት እየወደድኩት ነዉ የከዳኝ፣ ታምኜለት ሳለ፡፡ ሮበርትን እንግሊዝ ከገባሁ በኋላ ነዉ የተዋወቅሁት፡፡ ምድር በዳ እንደ ተጣለ ሰዉ የባይተዋርነት ጅራፍ እየላጠኝ ሳለ ነዉ፣ ወደ ሕይወቴ የመጣዉ፡፡ ዘጠኝ ዓመት እንግሊዝ ስኖር የፍቅር አጋር አልነበረኝም፡፡ ሮበርት ከሀኒባል ወርቁ በኋላ የልቤን ቅጥር ጥሶ የገባ ሁለተኛ ወንድ ነዉ፡፡ ሮበርት የሚወደዉን ከድቶ ሄዶ ምን አተረፈ? ምን ያህል ደስታ ሸመተ? የሁሉም ሥጋ ጣዕሙ እንደሁ ተመሳሳይ ነዉ፡፡ እኔ ምን አጎደልኩበት? አቅፎኝ ባደረ ማግስት ነዉ የከዳኝ፡፡ መካድ የሚወልደዉ ስብራት ቶሎ አይሽርም፡፡ የተኛሁበት አልጋ ላይ ነዉ፣ ሀኒባልን ከሌላ ጋር ሲወሰልት እጅ ከፍንጅ የያዝኩት፡፡
 ወዜ በተንሰራፋበት አልጋ ላይ ነዉ፣ ባዕድ አቅፎ የተኛዉ፡፡ ያን ኩነት ዐይኔ እንዳያይ ለዘላለሙ ቢታወር እወድ ነበር፡፡ ግን የዐይኔ ብረት ያን ደባሪ ትዕይንት ተመለከተ፡፡ሀኒባልን ለመጨረሻ ጊዜ ያየሁት ለምልጃ መጥቶ ፊት ነስቼ የሸኘሁት ዕለት ነዉ፡፡ የምንወዳቸዉን ከልባችን አዉጥተን ከቀበርን ሁሉም ነገር ተቋጭቷል፡፡

Read 997 times