Saturday, 22 April 2023 19:08

የሱዳን ግጭት ወደ እርስበርስ ጦርነት እንዳያመራ ተሰግቷል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ካርቱምን ለቀው እየወጡ ነው
አገራት ዜጎቻቸውን ከመዲናዋ ለማስወጣት እየሞከሩ ነው


በሱዳን ባለፈው ቅዳሜ በአገሪቱ መደበኛ ጦር ሰራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ልዩ ሃይሉ መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ድረስ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ጦርነቱን ሽሽት  መዲናዋን ለቀው  እየወጡ ነው ተብሏል፡፡   
ባለፈው ረቡዕ ጠዋት ሰዎች በመኪናና በእግራቸውም ጭምር ካርቱምን ለቀው ሲወጡ ማየታቸውን  እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡ ውጊያው ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ፣ በርካታ አገራት ዜጎቻቸውን ከካርቱም ለማስወጣት እየሞከሩ ሲሆን በተፋፋመው ጦርነት ሳቢያ አብዛኞቹ አልተሳካላቸውም ተብሏል፡፡
የሱዳን መደበኛ ጦር ሰራዊትና የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ሃይሉ ባለፈው ማክሰኞ ከ12 ሰዓት ጀምሮ ለ24 ሰዓታት የሚዘልቅ ተኩስ የማቆም ስምምነት ላይ ደርሰው እንደነበር ቢነገርም፤ ስምምነቱ ወዲያውኑ መክሸፉ ታውቋል፡፡ባለፈው ረቡዕ ቃላቸውን ለቢቢሲ የሰጡ ነዋሪዎች፤ በዕለቱ በካርቱም የጦር ማዘዣ ጣቢያና አየር ማረፊያ አቅራቢያ ጨምሮ በመኖሪያ መንደሮች የተኩስ ድምፅ ሲሰማ እንደነበር ተናግረዋል፡፡መቀመጫውን በካርቱም ያደረገው ጋዜጠኛ መሃመድ አላሚን ለቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ሬዲዮ እንደገለፀው፤ ተኩስ የማቆም ስምምነት ላይ ተደርሷል ቢባልም፤ የጥይት ድምፅ አልቆመም ብሏል፡፡
“በጣም አሰቃቂ ነው - እነዚህ ተፋላሚ ቡድኖች በየቦታው ዝም ብለው ነው የሚተኩሱት፡፡” ሲል አላሚን ተናግሯል፡፡ “እኔ ራሴ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ወደ አጎራባች አገራት ለመሸሽ ከካርቱም ለቀው ሲወጡ አይቻለሁ፡፡” ብሏል፡፡
አንዳንዶች ምን እየተካሄደ እንዳለ እንኳን አያውቁም - ሌሎች ደግሞ ቁጣቸውን በሁለቱም ተፋላሚዎች ላይ ይሰነዝራሉ፤ ተብሏል፡፡  
“ዜጎች በመሰረቱ ይሄ ጦርነት እነሱ ላይ ያነጣጠረ አድርገው ነው የሚያስቡት፡፡ በመንገድ ላይ ያገኘኋቸው ሰዎች የነገሩኝ ይሄንን ነው” ብሏል፤ ጋዜጠኛ መሃመድ አላሚን፡፡ ተኩስ የማቆም ስምምነቱን ለመተግበር ያለው አንድ ችግር፤ በከተማዋ ተበታትኖ የሚገኘው ተዋጊ ሃይል ሊሆን እንደሚችልም ግምቱን ሰንዝሯል፡፡
“በእነዚህ ወታደሮች መካከል ያለመናበብ ዓይነት ነገር ይታያል - እየተዋጉ ያሉት በተለያዩ አካባቢዎች፣ በተለያዩ ቦታዎች ነው-የግንኙነት ክፍተት ባለበት ሁኔታ…” ብሏል፡፡
ነዋሪዎች ካርቱምን ለቀው መውጣት የጀመሩት ባለፈው ረቡዕ ማለዳ ተኩስ የማቆም ስምምነቱ ከሽፎ ውጊያው ከቀጠለ በኋላ መሆኑን የዘገበው ቢቢሲ፤ በጦር ሰራዊቱ ማዘዣ አቅራቢያ የተከሰተውን ፍንዳታ ተከትሎ፤ ካርቱም በወፍራም ጥቁር ጭስ ተጠቅልላ እንደነበር አስታውሷል፡፡
የዓይን እማኞች እንደተናገሩት፤ ከባድ መሳሪያ የታጠቁ የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ሃይል ተዋጊዎች በፒክ አፕ ተሽከርካሪዎች ከተማዋን ሲቃኙ፤ ለጦር ሰራዊቱ ታማኝ የሆኑ ተዋጊ ጀቶች በልዩ ሃይሉ እንደተያዙ የታመነባቸው ዒላማዎች ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ነበር፡፡
አንድ መዲናዋን ለቆ እየወጣ የነበረ ሱዳናዊ ለቢቢሲ እንደተናገረው፤ የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ሃይል በከተማዋ ዙሪያ ባሉ መንገዶች የፍተሻ ጣቢያ ያቋቋሙ ሲሆን የልዩ ሃይሉ ተዋጊዎች ዘረፋ ፈፅመውበታል-ሞባይል ስልኩንና ጥቂት ገንዘብ በመንጠቅ።
በመዲናዋ አንዳንድ አካባቢዎችም ዘረፋዎች መፈፀማቸው ተነግሯል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ የልዩ ሃይሉ አባላት በየቤቱ እየዞሩ ውሃና ምግብ ሲጠይቁ እንደነበር የካርቱም 2 አካባቢ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡
ውጊያው እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ፣ በርካት አገራት ዜጎቻቸውን ከአገሪቱ ለማስወጣት ዝግጅት መጀመራቸውን አስታውቀዋል።ጃፓን፤ የመከላከያ ሃይሏ የኤምባሲ ሠራተኞችን ጨምሮ 60 የሚደርሱ የጃፓን ዜጎችን እንዴት ከሱዳን እንደሚያስወጣ እያሰበበት መሆኑን ተናግራለች- ለዚህም የጦር አውሮፕላን በተጠንቀቅ ላይ መሆኑን በመግለፅ፡፡
የታንዛንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስቴርጎሜና ታክስ፤ መንግስታቸው 210 ያህል ዜጎቹን ከሱዳን ማስወጣት ይቻል እንደሆነ በመገምገም ላይ እንደሚገኝ ለፓርላማ ተናግረዋል፡፡ህንድም በሱዳን የሚገኙ ዜጎቿን ደህንነት ለማረጋገጥ ከሌሎች አገራትና ዓለማቀፍ ድርጅቶች ጋር ቅንጅት እየፈጠረች መሆኑን አስታውቃለች፡፡
በካርቱም የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በበኩሉ፤ በመዲናዋ ባለው አስጊ የጸጥታ ሁኔታ የተነሳ ዜጎቹን የማስወጣት እቅድ እንደሌለው አስታውቋል፡፡
እስከ ትላንት ድረስ በዘለቀው የሱዳን ውጊያ 300 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና በሺዎች የሚቆጠሩ ጉዳት እንደደረሰባቸው የዓለም ጤና ድርጅትና የሱዳን ዶክተሮች ህብረት አስታውቀዋል፡፡
በመዲናዋ ካርቱም የሚገኙ አብዛኞቹ ሆስፒታሎች በደረሰባቸው የከባድ መሳሪያ ጥቃት ወይም ዘረፋ ሳቢያ ዝግ ሲሆኑ ክፍት የሆኑትም ቢሆኑ በአቅርቦት እጥረት የተነሳ የተሟላ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ተብሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ባለፈው ረቡዕ ሚያዝያ 11 ቀን 2015 ዓ.ም ከአምስት  ቀናት በፊት በሱዳን የተከሰተውን ጦርነት ለማርገብና ሁለቱን ጄነራሎች ለማደራደር ካርቱም ይገባሉ ተብለው የነበሩት የሦስት አገራት መሪዎች ጉዟቸውን መሰረዛቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ የካርቱም ጉዟቸውን የሰረዙት የሦስቱ አገራት መሪዎች የሱዳን ጎረቤት የሆኑት የኬንያ፤ የደቡብ ሱዳንና የጅቡቲ መሪዎች ናቸው፡፡የባለፈው ማክሰኞ የ24 ሰዓት ተኩስ የማቆም ስምምነት ተግባራዊ ቢደረግ ኖሮ፤ የሦስቱ አገራት መሪዎች፤  የሱዳን የጦር ሃይል አዛዥ ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ አዛዥ መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎን ለማደራደር ወደ ሱዳን እንዲገቡ ምቹ ሁኔታን ይፈጥር ነበር ተብሏል፡፡    ቀደም ሲል የግብፅ ፕሬዚዳንት አብደል ፈታህ አል-ሲሲ ከደቡብ  ሱዳን ጋር በመሆን የአገሪቱን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ሃይል አባላቱን ለማደራደር ጥያቄ ማቅረባቸውን ባወጡት መግለጫ አስታውቀው ነበር፡፡
እስካሁን ድረስ ምዕራባውያን፤ የአረብ አገራትና የአፍሪካ ህብረት ሁለቱ ተፋላሚዎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርቡም ውጊያው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
የአፍሪካ ህብረት፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ አሜሪካና ብሪቴይን ያደረጓቸው የሽምግልና ጥረቶች ያልተሳኩ ሲሆን ሱዳን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ልትገባ ትችላለች የሚለው ስጋት እያየለ መጥቷል፡፡
ሁለቱ ጄነራሎች እንዴት ወደ ግጭት ገቡ?
ከሁለት ዓመት በፊት በሱዳን ውስጥ መፈንቅለ መንግስት ከተካሄደ በኋላ የጦር ጄነራሎች ሉዓላዊ ምክር ቤት የሚባል አቋቁመው አገሪቱን ሲመሩ ቆይተዋል - ሁለቱ ጄነራሎች፡፡ አርኤስኤፍ የተባለው ፈጥኖ ደራሽ ሚሊሻ በጄነራል ሞሃመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራ ሲሆን  ጄነራሉ የሉአላዊ ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንትም ናቸው፡፡ የሉአላዊ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት የሆኑት ጄነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ደግሞ የአገሪቱን ጦር ሃይል ይመራሉ፡፡
ሱዳንን ወደ ሲቪል መንግስት ለማሸጋገር የቀረበው ዕቅድ፤ የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉን ከአገሪቱ ጦር ሰራዊት ጋር በማዋሃድ የጊዜ ሰሌዳ ዙሪያ ከስምምነት ላይ ሳይደረስበት ቆይቷል፡፡ አርኤስኤፍ ውህደቱ በአስር ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲፈፀም የሚፈልግ ሲሆን የአገሪቱ ሰራዊት ግን በሁለት ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን ይፈልጋል። የግጭታቸው መንስኤና ጦር ያማዘዛቸውም ይኼው ጉዳይ ነው፡፡ ጄነራል ቡርሃን በሚቋቋመው ሲቪል መንግስት ውስጥ የሚመሰረተውን የተዋሃደ የአገሪቱን ጦር ማን መምራት አለበት በሚለው ጥያቄ ዙሪያ የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ከጄነራል ዳጋሎ ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልፀው ነበር፡፡ ሆኖም ከንግግሩ በፊት በሁለቱ ቡድኖች መካከል ግጭት ተከሰተ - ባለፈው ቅዳሜ፡፡  የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፤ አሁን ሁለቱ ጄነራሎች አንጃ ፈጥረው የሥልጣን ሽሚያ ውጊያ ውስጥ ገብተዋል። የማናቸውም ማሸነፍ ደግሞ ለሱዳን ህዝብ ፋይዳ የለውም ተብሏል፡፡
 ለምን ቢሉ? የሱዳን ህዝብ የሚፈልገው ወታደራዊ አስተዳደር ሳይሆን በህዝብ የተመረጠ የሲቪል አስተዳደር ነውና፡፡ በተደጋጋሚ አደባባይ እየወጣ ሲጠይቅ የነበረውም ወታደሩ ለሲቪል አስተዳደር ሥልጣኑን እንዲያስረክብ ነው፡፡


Read 1425 times