Saturday, 22 April 2023 19:14

መኖር እና መጻፍ

Written by  ስብሃት ገ/እግዚአብሔር
Rate this item
(2 votes)

እየኖርን ነው የምንጽፈው። ስንኖር እንደግለሰብ ሆነን የሌሎች ግለሰቦች ስብስብ በሆነ ማህበረሰብ ውስጥ ነው። እኛን በሚሊዮናት ልንቆጠር የምንችል ግለሰቦችን በየፊናችን ከመበታተን ይልቅ ተሳስረን ተባብረን እንድንኖር የሚያስችሉን መግባቢያ ቋንቋ፣ የስራ ክፍፍል፣ ገንዘብ የተባሉት ተአምራት ወይም ምትሃቶች ናቸው። ቋንቋ ጽህፈትን ያስከትላል።
ስንኖር እንደሚታየኝ ከሆነ ሁለት ዓለሞች ውስጥ ነን። ውስጣዊውና ውጫዊው ዓለም እንበላቸው። ሁለቱን ዓለሞች የሚለያቸው ወሰን ወይም ድንበር ቆዳዬ ነው። ጀርም፣ ቫይረስ፣ ቆሻሻ ምናምን ወደ ውስጣዊ ዓለሜ እንዳይገቡ ቆዳዬ ይከለክላቸዋል። “መግባት ክልክል ነው!” የሚል ጽሁፍ አለ - በጀርም ፊደላት፡፡ ሁለቱን ዓለሞች የሚያገናኛቸውም ያው ቆዳዬ ነው። የውጪው ሙቀቱ ብርዱ፣ የሳሩ መለስለስ፣ የኮረኮንቹ መቆርቆር በቆዳዬ በኩል ይደርሰኛል። ቆዳ ቅኔ ውዕቱ እንዲል ባለ ቅኔው።
እኔ ውስጣዊ ዓለም የሆንኩት ሰው የምኖረው ውጫዊ ዓለም ውስጥ ነው። እኔ ሰውየው እምኖረው ከሌሎች ሰዎች ጋር ነው።  ከሌሎች ጋር መኖር ደግሞ ብዙ ጥበብን ይጠይቃል። ደግነቱ ጥበቦቹ ከጥንት ተዘጋጅተው ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፉ መጥተዋል…
… ሰላምታን ያህል ግኝት- ፈጠራ- ምትሃት- ተዓምር። ሰላምታና ሰላምታን የሚከተሉት ምልልሶች ባይኖሩ ብዙ ሰንብተን ስንገናኝ ምን ይውጠን ነበር?
“እንደምን ከረሙ?”
“ደህና እግዚአብሔር ይመስገን። ደህና ከርመሃል”
“ደህና ይመስገን። ቤተሰብ ሁሉ ደህና ናቸው?”
“ደህና ናቸው ይመስገን። ዛሬ ነው እንዴ የገባኸው?”
እንዲህ እየተባባልን በአዲስ ባንለማመድ ኖሮ ገና እንደተገናኘን ምን እንባባል ነበር?
ምን እናደርግ ነበር? ለረጅም ጊዜ ተያይተን በተገናኘን ቁጥር ይጨንቀን ነበር። ይህ እንዳይሆን የሰላምታ ሥነስርዓት ተፈጠረ። አይ እነዚህ የማናውቃቸው አበው የምንላቸው ፈጣሪያችን! በአጭሩ አበው እንላለን እንጂ ፈጠራው ቢያንስ ግማሹ የእመው ወይም የጥንት እናቶች መሆኑ ግልጽ ነው።
… አብረን ስንኖር ከርመን ባጅተን ዓመታትን አስቆጥረን ስናበቃ አንድ ቀን መለያየት ይመጣል። መሳሳምና መልካም መመኘቱ እና እነገሌን ሰላም በልልኝ፣ እሺ በል ቸር ይግጠመን ወዘተ መባባሉ--የስንብት ስነስርዓት ባይኖር ምን ይውጠን ነበር? የመለያየቷ ደቂቃ ጭንቀት ራሷን የቻለች ሚጢጢ ሲዖል ትሆን ነበር።
… ሌላ ተዓምራዊ ግኝት አለ። ማህበራዊ ኑሮ ስንኖራት-ኡኡታ። ከግለሰብ አቅም በላይ የሆነ ሰውም ሆነ አውሬ ሊያጠቃኝ ቢቃጣ ኡኡ ብዬ ስጮህ፣ ጩኸቴ የማህበረሰቡን ጉልበት ትሰጠኛለች። በአገር ቤትና በአነስተኛ ከተማ ከሆነ ጩኸቴን የሰማ ሁሉ ዱላ ይሁን ድንጋይ ወይም ሌላ መሳሪያ ይዞ  ከየአቅጣጫው ወደ እኔ ይሮጣል፡፡ ያድነኛል ያስጥለኛል።
በሌላ ቀን በሌላ ሰዓት ኡኡታ እኔ ብሰማ ተራዬን ይህን ሰይፍ ወይም ጦር ይዤ ወደ ኡኡታው እሮጣለሁ። ፍርሃት አይኖርብኝም፤  ምክንያቱም  ጩኸቱን የሰሙት ሁሉ እንደ እኔ ወደዚያ እንደሚሮጡ አውቃለሁ። ብዙሃን ይመውኡ እንዲሉ አበው። ብዙሃን ያሸንፋሉ…
ማህበራዊ ኑሮን ስንኖራት እነዚህ ስነስርዓቶች በተቻለ መጠን የሰመረች የተመቸች  እንድትሆንልህ በየበኩላቸው አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ልመናም አለ ምስጋናም አለ። አለማመኑ ቋንቋ ከነዜማው ከነታቦቱ ስም ባይኖርለት ኖሮ ምስኪኑ ለማኝ እንዴት ብሎ ይለምን ነበር? እፍረቱ ያስጨንቀው ነበር። የምስጋናውና የምርቃቱ የቃል ጥናት ባይኖርለት ኖሮም ሰጪውን ምን እንደሚያደርገው ይጨንቀው ነበር።
ምስጋና ብትሉ ያቺን ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ የምጽፍላችሁን የሱፊዎችን ታሪክ እነሆ በረከት እንበላችሁ። ከዚህ በፊት ያነበባት ቢደግማትም ላልደረሳቸው ትደርስ ዘንድ…
ሰውየው አርፎ እቤቱ ተቀምጦ እያለ ጓደኛው መጣና “አንተ ያ ምስኪን አሊ ችግር ደርሶበት ሊወጣው የማይችል… መቶ ዲናር (ስፋቱ ከሃምሳ ሳንቲማችን በለጥ የሚል የወርቅ ገንዘብ) ስጠኝና ልውሰድለት” አለው። ሰውየው መቶውን የወርቅ እንክብል ከኪሱ አውጥቶ ሰጠው። ጓደኛው ገንዘቡን ተቀብሎ በፍጥነት ወጥቶ ሄደ።
ከወራት በኋላ ጓደኝየው ተመልሶ መጣና “ባይገርምህ ያ ምስኪን አሊ ያን ጊዜ ደርሶበት የነበረው ችግር ድጋሜ ደረሰበት።”
ሰውየው መቶውን ዲናር ከኪሱም፣ ከመሳቢያውም፣ ከመኝታ ቤቱም፣ ከእንግዳ መቀበያ ክፍሉም ፈልጎ እንደምንም አሟልቶ ሰጠው። ጓደኝየው ገንዘቡን ተቀብሎ እንደምንም እየተጣደፈ ወጣ።
ከሌሎች ወራት በኋላ ጓደኝየው አሁንም ተመልሶ መጣ። “አንተ ያ ምስኪን እድለ-ቢስ አሊ ዛሬ ያ ችግር ራሱ ተመልሶ አይደርስበትም ለሦስተኛ ጊዜ! አይገርምህም? በል እስኪ መቶ ዲናር ስጠኝና ልውሰድለት”
ሰውዬው እቤቱ ውስጥ ፈላለገ በረበረ፤ ምንም ነገር አላገኘም።  ወጣና ከጎረቤቶቹ ፈላልጎ እንደምንም አሟልቶ ሰጠው። ጓደኝየው ገንዘቡን ተቀብሎ እየተጣደፈ ሊወጣ ሲል “ቆይ እስቲ!” አለ ባለቤትየው። “ምን?” አለ ጓደኝየው ቆም እያለ። “መጀመሪያ ከኪሴ መዝዤ ሰጠሁህ። ድጋሚ ቤቱን በሙሉ በርብሬ ተቸግሬ ሰጠሁህ። አሁን ሶስተኛ ከጎረቤቶቼ ለምኜ አሟልቼ ሰጠሁህ። አንዴ እንኳን አላህ ይስጥልኝ አይባልም?” ጓደኝየው ለቅጽበት አሰብ አደረገና እንዲህ አለው። “እ! ለምስጋና ነው እንዴ? ምስጋና ካስፈለገ ማመስገን ያለበት ሰጪው ነው።”
ተመስገን! አንተ ስትሰጠኝ ቢኖርህ አይደል እኔስ ልሰጥ መቻሌ? ይሉ ነበር አበው ጻድቃን ወብጹአን  እንዲሉ አባ ኪዳነ ማርያም።
… ማህበረሰቡ እንዴት እንደተቀናጀ እንደተዋቀረ፣ እንዴት  እንደተሰባጠረ በጥንቃቄ በሙሉ ትኩረት ማስተዋል፡፡ ለመጻፍ እያቆበቆብን ነዋ! ከመጻፍ በፊት ስናተኩር ማነው ማንን ወይም ምንን እያየን ነው እያጠናን ያለው? ብለን እንጠይቅና ቆም ብለን ስናስብበት፣ ከሚሊዮናቱ በቆዳቸው የታጠሩ ግለሰቦች አንዱ ነው። ለካ ቅድም ማህበረሰቡ ስል በተዓምሩ፣ በምትሃቱ አይቼ ነው እንጂ ማህበረሰቡ የለም። ያለነው እኛ ግለሰቦቹ የምንዋለድ የምንዋደድ የምንጣላ የምንኳረፍ ነን። አንድ አንድ ሰው ነን በእውነታው ዓለም ያለነው እንጂ ህብረተሰብ፣ ድርጅት፣ መዋቅር፣ ቢሮክራሲ ምናምን የምንለው እኛን ግለሰብ የሆንን ሸረሪቶችን ማሰሪያ ድር ነው´ንጂ እሱ ለራሱ ነብስ የለውም፣ ባዶ ነው። ወረቀት ላይ የተሳለ የመስሪያ ቤት መዋቅር ወዘተ…
ጋዜጠኛና ደራሲ አንድም ሁለትም ናቸው። ብዙ ጊዜ ጋዜጠኛው ወደ ደራሲነት ይሸጋገራል። ብዙ ጊዜ አንድ ሰው ወይም አንዷ የጋዜጠኝነትና የደራሲነትን ሙያዎች ደርበው ይይዛሉ። ለነገሩማ ሁለቱም ሙያዎች በጣም ይቀራረባሉ። ደራሲ ስንል የልቦለዱም፣ የአጭር ልብወለድም፣ የቲያትርም፣ የግጥምም ማለታችን ነው። ጋዜጠኛ ስንል በየርካሹ እትም የመንደር ወሬ የሚያቀብለንን ይጨምራል። የማህበረሰቡ ጠባቂ አይን ሆኖ ራቁቱን ከደባቂዎቿ ፈልቅቆ አውጥቶ ይፋ የሚያደርጋትም ይጨምራል። ማንኛውም ሙያ ርካሽ ሰውም ይሰማራባታል። ሁነኛ ሰውም ይኖርበታል።
የሀቀኛ ጋዜጠኛ ምሳሌ ለእኛ የቀረበ። የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የወሎ ረሃብ ከዓለምም ከበዛው የኢትዮጵያ ህዝብም ተደብቆ በነበረበት ጊዜ ዲምብልቢ የተባለ እንግሊዛዊ የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ወሎ ሄዶ የረሃቡን ሁኔታ በድብቅ የሲኒማ ጋዜጣ ወስዶ በድብቅ ከእዚህ ሀገር አውጥቶ በይፋ መጀመሪያ ቢቢሲ ቴሌቪዥን ለመላው የእንግሊዝ ህዝብ አሳየ። ከዚያም የዓለም ህዝብ የረሃቡን ጽኑነት አይቶ አዝኖ ብዙ የምግብ የመድሃኒትና የልብስ እርዳታ ወደ ወሎ ላከ።
ሌላኛው ዓይነት ጋዜጠኛ ዝነኛ የሆኑ ሰዎችን በድብቅ በስውር እየተከታተለና እያጠና ጉዳቸውን መጎልጎል ነው። በጋዜጣ ይሁን በመጽሄት በራዲዮ በቴሌቪዥን የመንደር ወሬ አሩጥ በዘመናት እድገት ያሳይና በዘመኑ ቴክኖሎጂም ብርታት የመገናኛ ብዙሃን ወሬ አሰራጭ ይሆናል። የዚህ አይነቶቹ ጋዜጠኞች ወሬ እያናፈሱ የእንግሊዝ አገሩን አልጋ ወራሽ ፕሪንስ ቻርለስን  ከሚስታቸው ሊያፋቷቸው እየተሯሯጡ ነበር፤ እግዚሃር ይቅር ይበላቸውና። አሜን።
***
(አዲስ አድማስ፤ መስከረም 30 ቀን 1996 ዓ.ም)


Read 1530 times