Saturday, 22 April 2023 19:20

ለውጥ ልጆቿን በየተራ ታጠፋለች? ወይስ ስብሰባ ታቅፋለች?

Written by  -ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)


“ለውጥ”፤ የዋዜማና የመባቻ መልኮች ቢኖርዋትም፤ “የለውጥ ማግስት” የሚሏት ደግሞ ትመጣለች፡፡ ከወር ከመንፈቅ በኋላ፣ ከዓመት እስከ አምስት ዓመት፣ በብዙ መልክ ትገለጣለች- የለውጥ ማግስት። እያሰበሰበች ታቅፋለች? ከነዚሁም ውስጥ እየነጠለች ታጠፋለች?
“ለውጥ እውን ሆነ፤ ስራው ተጠናቀቀ፤ ሩጫው ተፈፀመ፤ ከግቡ ደረሰ፣”… ተብሎ መዝገቡ ተዘግቶ፤… እረፍትና ጥሞና የሚወሰድበት፤ ሁሉም ተሰነባብቶ ወደየራሱ ኑሮና ወደ መደበኛ ስራው የሚመለስበት ይመስላል የለውጥ ማግስት፡፡ ግን አይደለም። እንዲያውም፣ ነገር የሚወሳሰበው ነገሩ ተጠናቀቀ ከተባለ በኋላ ባሉት ዓመታት ነው።
የለውጥ ፖለቲከኞችና አጃቢ ዜጎች የምኞታቸው መባቻ ላይ፤ የለውጥ አዋጅና የመተቃቀፍ እልልታ አይለያቸውም። ከዋዜማው እስከ  ከመባቻው ሲያስጨንቃቸው የከረመ የለውጥ ነውጥ እና ምጥ ከእልባት ደርሶ የግልግል እፎይታን ያገኛሉ፡፡ የታቀደው ተከናወነ፤ የታሰበው ተሳካ ብለውም መደሰታቸው አይቀርም፡፡ ቢሆንም ግን፤…. ቅሬታዎች የሚወለዱትና ችግሮች ጭራ ቀንድ የሚያበቅሉት ያኔውኑ ነው፡፡
አንደኛ ነገር፣ የተመኙት ለውጥ  እንደገመቱት እንዳሰቡት አይሆንላቸውም፡፡
በደፈናው ለውጥ ማለት አዲስ የመንግስት መዋቅርና አዳዲስ ባለስልጣናት ማለት ነው ለብዙ ሰዎች፡፡ ይህም በደፈናው አንዳች መልካም ለውጥ ያመጣል ብለው ይመኛሉ፡፡ ምን ዓይነት መልካም ለውጥ እንደሚፈልጉ በዝርዝር አያውቁም፡፡ የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚና የሕግ ባለሙያዎች እንኳ ይቸገራሉ-እንኳን ተራው ዜጋ፡፡ የንጉሡን ወይም የቀድሞውን ሥርዓት ወደ ባሰ ውድቀት የቀየሩ ወይም ተመሳሳይ የለውጥ አርበኞችና አብዮተኛ ፖለቲከኞች በታሪክ  በተደጋጋሚ ተፈጥረዋል፡፡ በየዘመናቸውም በያሉበት በርካታ አገራትን አናውጠው አተራምሰዋል፡፡ ስቃይና እልቂትን ፈጥረዋል፡፡


=========

የለውጥ ማግስት፣ ለአብዛኛው ዜጋ ጨርሶ ያልታሰበ ዱብዳ ይሆንበታል፡፡ ነገር ግን፤ ሊታወቅ ሊገመት የማይችል ተዓምረኛ ምስጢር ስለሆነ አይደለም። ለትንበያ ሊያስቸግር ይችላል። ግን፣ አስቡት። የሱዳንን መሰንበቻ ተመልከቱ።
ይኸውና አራት ዓመታቸው፣ የለውጥ ማግስት ውሽንፍር ውስጥ መከራቸውን ያያሉ። ግን ከመነሻውስ የመልካም ለውጥ ተስፋ ነበራቸው ወይ? ከተስፋው ይልቅ አደጋው የበዛ አልነበረም ወይ? በመፈንቅለ መንግስት ፕሬዚዳንት አልበሽር በተባረሩ ማግስት፣ ወታደራዊ አምባገነንነትን እንጂ መልካም ለውጥን ለማየት መጠበቅ ተገቢ ነው? በተስፋ የሚያስጨፍር አይደለም።
እንዲያውም አደጋው በጣም ስለሚያስፈራ የአገሪቱ አዋቂዎች በጥንቃቄ እንዲስተውሉ የሚያነቃ ደወል ነው። እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ ጎረቤቶችም እንደ አቅማቸው ለሰላም የሚረዳ ድጋፍ በቅንነት እንዲሰጡም የሚገፋፋ ነበር- የሱዳን የለውጥ አመጽና የመፈንቅለ መንግስት መባቻ። ለውጡ፣… አደጋው የበዛ ለውጥ ነውና። ታዲያ፣ ተራ በተራ የጥሎ ማለፍ አዙሪት በለውጡ ማግስት እየተወለደ እስከዛሬ መቀጠሉ ዱብዳ ነው?
ይህም ብቻ አይደለም።
በሶሻሊዝም መፈክር የሰከሩ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ያቀጣጠሉት አብዮት ሲሳካ፤ በማግስቱ ንብረት የመውረስ ዘመቻ ቢታወጅስ ዱብዳ ነው?
“ብቸኛ ገዢ ፓርቲ ያስፈልጋል” ብለው የሚያምኑ ናቸውና አንድ ፓርቲ ብቻ እስኪቀር ድረስ መተላለቃቸው ይገርማል?
የስነምግባር መርሆችና ግልፅ አላማ የሌለው አመጽ ተቀጣጥሎ ነባሩን መንግስት ሲገረስስ፤ የሶማሊያ፤ የሊቢያና የየመን ዓይነት ትርምስ በለውጥ ማግስት ቢከሰት፤ ዱብዳ ነው? ብዙ ሰዎች ዱብዳ እየሆነባቸው፤ በለውጥ ማግስት ይከፋቸዋል፡፡
በእርግጥ አንዳንድ አመፀኞች ደግሞ የተመኙት ያህል ነውጥ ስላልተፈጠረ ይበሳጫሉ። በስርዓት አልበኝነት ያሰኛቸውን ያህል ጥቃትና ዝርፊያ፤ ጭካኔና ውድመት የመፈፀም እድል እንደልብ ስላላገኙ፤ በለውጥ ማግስት በንዴት ይንገበገባሉ፡፡
ክፉ ክፉ ነገር ነው የሚታያቸው። “ለውጥ” ከተባለ፤ “ያዘው፣ እሰረው፣ዝረፈው፣ ግረፈው፣ አፍርሰው፣ ግደለው” በሚሉ ዘመቻዎች አገር እንደሲኦል ካልነደደ፣ ምኑ ለውጥ ሆነ? ይላሉ፡፡ በዚህም ቅር ይላቸዋል፡፡ ክህደት እንደተፈፀመባቸው ይቆጥሩታል፡፡ ድላችን ተጠለፈ፤ ለውጥ ተቀለበሰ ብለው በቁጣ ይንቀለቀላሉ፡፡
የለውጥ ማግስት ብዙ ነው ቀለሙና መልኩ፡፡
የህንፃው ቁመትና የጎዳናው ስፋት፤ የአፈሩ መልክና የመስኩ ቀለም በአንድ ጀንበር ተቀይሮ አለማደሩ፤… ከዳር እስከ ዳር በቀይ ወይም በአረንጓዴ ቀለም ሳይለወጥ፤ በልምላሜ ለፍሬ ሳይደርስ፤ ወይም በሰው ደም ሳይጥለቀለቅ መንጋቱ፤…. ለብዙ ሰዎች ግራ ያጋባል፡፡ ተስፈኞች እንደተመኙት፤ ሌሎች ደግሞ እንደፈሩት ሳይሆን፤… የአዳሜ ኑሮ ሳይበለፅግ፤ አገር ምድሩ ተሰነጣጥቆ ሳይፈራርስ አንድ ሳምንት ከተቆጠረ፤… ወይ አልሞቀ ወይ አልበረደ ብለው አንዳንዶቹ ይዳፈሩታል፡፡ከስደት ወይ ከእረፍት የተመለሱና ወደ ለውጥ አጀብ የተቀላቀሉ ፖለቲከኞች፣ “የተሟላ ለውጥ የሚሆነው እኔ የስልጣን ቦታ ላይ ስቀመጥ ነው” ብለው ውስጥ ለውስጥ ሊቧደኑ ይችላሉ። ለመተቃቀፍ ነው የተጠራሩት። ግን ለመጠፋፋት ነው የሚዘጋጁት።
አንዳንዶቹ ደግሞ፣… ለውጡ ሳይጀመር ደንዘዞ ቀረ ብለው ፈጣን የለውጥ አዋጆችንና እርምጃዎችን ይናፍቃሉ፤ “ወደፊት! ቆራጥ ውሳኔ፤ ስርነቀል የለውጥ ዘመቻ” እያሉ ይቀሰቅሳሉ፡፡ ምኞታቸው መጥፊያቸው እንደሆነ አያውቁም- የተመኙት እስኪሳካ ድረስ፡፡
በሰላም መሽቶ የሚነጋ የለውጥ ማግስት፣… በጣም ትልቅ ስኬት እንደሆነ አይገባቸውም።
ሰላም ስለመሰለ፣ በዚሁ ይዘልቃም ማለት ግን አይደለም። መምሰል ብቻ አያዛልቅል። በእርግጥም የመረጋጋት መልክ የተላበሰ የለውጥ ማግስት፣ ብዙ ሰዎችን ያሳስታል፡፡
ሁሉንም ያዋደደ፤ ተራርቀው የነበሩ ጎራዎችን ያቀራረበ አቃፊ የለውጥ ዘመን ተገኘ ብለው ያስባሉ፡፡ ደግሞም፣ በለውጥ ዋዜማና መባቻ ላይ ብዙ ሰዎች ይሰባሰባሉ፤ በማግስቱም  ተቀራርበው ይተቃቀፋሉ።  ነባር መንግስት ላይ ቅሬታና እሮሮ ሲበዛ፤ የለውጥ ስሜት ሲብላላ፣… በተስፋ ወይም በጥላቻ መንፈስ ለአመፅ የሚጠራሩ ይበረክታሉ፡፡
ምንን መለወጥ እንደሚፈጉ ይናገራሉ፤ ይስማማሉ፤ ይግባባሉ፡፡
ወደ ምን እንደሚለውጡት ግን አይነጋገሩም፡፡
ብዙዎች ምን ዓይነት ለውጥ እንደሚፈልጉ አያውቁም፡፡ ቢያውቁትም እንኳ፣ የተቃዋሚ ጎራዎችን የሚከፋፍል ቅራኔ ላለመፍጠር፣ የለውጥ ሃይሎችን በልዩነት የሚያራርቅ ሃሳብ ላለማንሳት፣ መናገርና መስማት አይፈልጉም፡፡
የትኛውን ማፍረስ እንደሚመኙ ይናገራሉ፤ ይስማማሉ፡፡
ምን እንደሚገነቡ ግን አይናገሩም፡፡ በዚህም ይስማማሉ፡፡ ይሰባሰባሉ፡፡
የኢትዮጵያ የ50 ዓመታት ታሪክን ተመልከቱ። ወይም የሱዳን የቅርብ ዓመታት ዜናዎችን አስታውሱ።  የምድረ ሱዳን እልፍ የፖለቲካ ቡድኖች፣… የብሄር ብሔረሰብ ፖለቲካ አቀንቃኞች፣ ተገንጣዮች፣ የሃይማኖት አክራሪዎች፣ የዲሞክረሲ ተስፈኞች፣ የኑሮ ችግረኞች፣ የማህበራዊ ሚዲያ ቀስቃሾችና እድምተኞች፣ የጦር ሃይል መሪዎችና የታጣቂ ቡድን የጦር አበጋዞች፣… እነዚህ ሁሉ፣ የሱዳን ገዢ የአልበሽር መንግስትን ለመለወጥ፣… የሆነ ጊዜ ላይ ተረባርበዋል። የሚያስማማ ለውጥ ሆኖላቸዋል-ሁሉንም የሚያሰባስብ። ሁሉንም ያቀፈ የሽግግር መንግስትም ተቋቁሟል።
 “ጥሩ የለውጥ እድል” ተብሎ በአላዋቂዎች የሚጠቀሰው እንዲህ አይነት አቃፊ ስብስብ ነው። ያፈረሱትን አፈር ካበሉት በኋላስ፣ ምን ለመገንባት አስበዋል?
በለውጥ ማግስት፣ በምን አይነት አላማና ሃሳብ ያስተቃቅፋቸዋል?
የጦር ሃይል መሪ የታጣቂዎች የጦር አበጋዝ በጋራ ተቃቅፈው፣ ሌሎቹ የለውጥ አርኞች ላይ ይዘምታሉ። ይህን የጋራ ምኞት ከጨረሱ በኋላስ? እርስበርስ  ለመጠፋፋት ይጨፋጨፋሉ። ምን ለማለት ፈልጌ ነው?
በለውጥ ማግስት፣ ብዙ ሰዎችን የሚያሰባስብና የሚያቀራርብ አቃፊ መንፈስ ስለተፈጠረ፣ “መልካም የለውጥ እድል ነው” ማለት ላይሆን ይችላል።
የንጉሥ ኃይስላሴን መንግስት ለመገንደስ የሚፈልጉ በርካታ መሪዎች፣ ድርጅቶችና ፓርቲዎች በወቅቱ እጅግ ተቀራርበውና ተሰባስበው የተቃቀፉበት ጊዜ የተፈጠረው መቼ ነበር?  በለውጥ ማግስት እንደነበረ ታሪክ ይነግረናል።
“መልካም የለውጥ እድል” በማለትም ብዙዎች ያንን ጊዜ ያስታውሱታል።
አብዛኞቹን ፓርቲዎችንና ፖለቲከኞችን ያስተቃቀፋቸው ሃሳብ ምን እንደሆነ ገምቱ። የአንድ ፓርቲ ሶሻሊስታዊ ስርዓት ለማስፈን የሚፈልጉ ናቸው-ፓርቲዎቹ። ታዲያ አንድ ፓርቲ እስኪቀር እርስ በርስ መጠፋፋት እንደሚጀምሩ መገመት ያቅታል?
ያሰባሰባቸውና ያስተቃቀፋቸው ሃሳብ፣ በጥሎ ማለፍ ግጥሚያ የሚያፋልም የጸብ ሃሳብ ነው።
መልካም የለውጥ እድል ነበር ብለው የሚናገሩ ሰዎች፣ ምስክርነታቸው ይህን እውነታ የሚገልጽ አይደለም፣ መልካም ምኞታቸውን ያሳያል ካልተባለ በቀር።
መልካም መመኘት ጥሩ ነው። ነገር ግን፣ ከጭፍንነት ጋር ልናቆራኘው አይገባም። እውነታውን የሚያስክድ ዓይናችንን የሚጋርድ መሆን የለበትም። መልካም ምኞታችን ያለ እውነታ ተስፋ የለውም። ከጅምር እናመክነዋለን።
ይልቅስ፣ እውነታውን አስተውለን፣ የለውጥ ማግስት አደጋዎችንም ተገንዝበን ብናስብበት፣… አደጋዎችን ለማስቀረት ወይም ለመቀነስ የሚረዱ የመፍትሄ መንገዶችን ለማፈላለግ እንተጋለን፤ አስቀድመን ለመጠንቀቅ እንችላለን።
ያኔ ነው ወደ መልካም ምኞታችን የሚወስዱ እድሎችን የመፍጠር አቅም የሚኖረን። ቢያንስ ቢያንስ፣ የጥፋትና የውድቀት ሩጫዎችን ከማባባስና ከማፋጠን እንታቀባለን።
የጥሎ ማለፍ የመጠፋፋት ፍልሚያ
ከአብዮት ማግስት የተፈጠረው የመሰባሰብና የመተቃቀፍ ትዕይንት፣ ፓርቲዎች በመንግስት ጋዜጣ ጭምር ያካሄዱት “ነፃ ውይይትና ክርክር”፣ መልካም የለውጥ እድልን የሚያሳይ ማዕቀፍ አይደለም።
“አንድ ፓርቲ ብቻ!” ብለው የሚፎክሩ በርካታ ፓርቲዎች ለተወሰነ ጊዜ ተቃቅፈው ከተከራከሩ በኋላ፣… በሃሳብ ተማምነው፣ አብዛኞቹ ፓርቲዎች በፎርፌ በፈቃደኝነት ስልጣን ይቅርብን ብለው፣ ከአንድ ፓርቲ በቀር ሁላችንም እንፍረስ ብለው ይወስናሉ? በአንድ ፓርቲ ስር ይታቀፋሉ?
የማይመስል ነገር!
የውይይትና የክርክር ማዕቀፋቸው በአንዴ ወደ ፀብና ወደ መጠፋፋት ይቀየራል ማለት አይደለም። ሁሉም ተነጣጥሎ በሁሉም ላይ ይዘምታል ማለትም አይደለም።
በማጣሪያ ዙሮች ነው የሚጠፋፉት።
ገሚሶቹ ለብቻ ይቧደናሉ። ራሳቸውን አጥርተው ፍቅራቸውን እያጠበቁ በአዲስ መልክ መተቃቀፋቸውን ያውጃሉ፤ ግንባር ፈጠርን፣ ተጣመርን፣ ወደ ውህደት ተሸጋገርን ይላሉ። ሌሎቹን ፓርቲዎች በከሀዲነት እየወነጀሉ በጠላትነት ይፈርጃሉ። በዘመቻ አብረው ተባብረው ጠላቶችን ነጥለው ያጠፋሉ።
ግን ምን ዋጋ አለው?
በአዲስ ማዕቀፍ የዘመቱ ተባባሪዎች፣ በድል ማግስት በመሃላቸው እንደገና ጸብ ይፈጠራል፤ እንደገና የማጥራት ዘመቻ ይጀምራሉ።
ከመሃላቸው ከፊሎቹ በአዲስ ማዕቀብ ህብረት ፈጥረው፤ ሌሎቹን ነጥለው ኢላማቸውን ያነጣጥሩባቸዋል። በእሩምታ ይጥሏቸዋል። በዚህም አያበቃም። የመጠፋፋት ዙሮች ይቀጥላሉ- አንድ ፓርቲ ብቻ እስኪቀር ድረስ።
አስገራሚው ነገር፣ መጠፋፋትን የሚጋብዝ ሃሳባቸውን እንደገና ለመመርመርና ለማስተካከል አይሞክሩም። በጊዜያዊ ስሌት እየተቃቀፉ በየተራ እየተነጣጠሉ እርስ በርስ በሚያካሂዱት የመጠፋፋት ዘመቻ፣ በጥሎ ማለፍ ፍልሚያ ላይ ተጠምደው፣ የማሰቢያ ጊዜ ቢያጡ አይገርምም።
በለውጥ ማግስት እየተሰባሰቡ መተቃቀፍና በጥሎ ማለፍ አዙሪት መጠፋፋት ብዙ ጊዜ እየተደጋገመ የሚከሰት አሳዛኝ ታሪክ ነው።
ደርግ የፈራረሰበት የለውጥ ጊዜ ላይም፣ የመጠን ጉዳይ እንጂ የመተቃቀፍና የመጠፋፋት አባዜ እንደገና መከሰቱ አልቀረም- በለውጥ ማግስት።
በእርግጥ ደርግ ስልጣን በያዘ ማግስት ከተፈጸመው ጥፋትና እልቂት ጋር ሲነጻጸር፣ በኢህአዴግ ድል ማግስት የተፈጠረው ፍልሚያ ለዘብ ያለ ነው።
ቀላል ግን አልነበረም።
ደግነቱ፣ “አንድ ፓርቲ ብቻ” የሚለው የሶሻሊዝም መፈክር በ1980ዎቹ በፍጥነት መደብዘዙ፣… ሲዘምሩለት የነበሩ ፓርቲዎችም ድምጻቸው መለዘቡ ጠቅሟል።
“የግለሰብ መብት፣ የገበያ ኢኮኖሚ፣ ብዙ ፓርቲዎችን የሚፈቅድ ፖለቲካ”… የሚሉ ሃሳቦች በዓለም ዙሪያ ደመቅ ብለው የታዩበትና የተደመጡበት ነበር-ጊዜው። ይሄ፣ የመጠፋፋት አዙሪቶችን ለመቀነስና ለማለዘብ ረድቷል።
ቢሆንም ግን፣ በለውጥ ማግስት በአዲስ አበባ የተሰባሰቡት ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች፣ ተከባረው ዘልቀዋል ማለት አይደለም። ከኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአጋርነት መጥተው የጉባኤው ታዳሚ ሆነው ነበር። የኦነግ መሪዎችም በለውጥ ማግስት በአዲስ አበባ ተገኝተዋል።
የመሰባሰብና የመተቃቀፍ ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል። ነገር ግን የፀብ አዙሪት መነሻም ነው- የለውጥ ማግስት። በዓመት በሁለት ዓመት፣ የኢህአዴግና የኦነግ ፀብ ለየለት። በሰባተኛው ዓመት ደግሞ “የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት” ፈነዳ።
በለውጥ ማግስት የተፈጠረው መተቃቀፍ፣ ወደ ግጭትና ወደ ጦርነት እንደሚያመራ መገመት ይቻል ነበር ወይ? ከተቻለስ በአስተዋይነትና በጥበብ አደጋዎቹን ማስቀረት ይቻል ነበር ወይ?
 ከላይ የተጠቀሱት የለውጥ ማግስት ክስተቶችን እንደ ማነጻጸሪያ በመጠቀም፣ ያለፉትን አምስት ዓመታት ለማገናዘብ ብንሞክርስ?
ማገናዘብ ጠቃሚ ነው። ተጨማሪ አደጋዎችን ለመቀነስ፣ ወደ መጠፋፋት የማያመራ አቃፊ የመፍትሔ ሃሳቦችን ለማሰላሰል ይረዳናል።

Read 1369 times