Saturday, 22 April 2023 19:22

“ገባው አልገባው አይደለም የፖለቲካ- ቁም ነገሩ ተቀበለ ወይስ አልተቀበለም ነው! “

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ሁለት ወዳጆች በመንገድ ሲሄዱ አንድ አሮጌ ግድግዳ ላይ የተሰቀለ አንድ ያረጀ የሚመስል ስዕል ያያሉ። ሁለቱም ስዕል አድናቂዎች ነን ይሉ ነበርና ወደዚያ ስዕል ተጠግተው ቆመው ያስተውሉ ጀመር።
አንደኛው - “እንዴት ግሩም አድርጎ ስሎታል! እንደዚህ ያለ የጀምበር ጥልቂያ ስዕል (sun-set) እስከዛሬ አይቼ አላውቅም” አለ።
ሁለተኛው - “ይሄ እኮ ጀምበር ስትጠልቅ የሚያሳይ ስዕል አይደለም። ይሄ ጸሃይ ስትወጣ የሚያሳይ (Sun-rise) የንጋት ጎህ ስዕል ነው” አለው።
አንደኛው- “ምንም አትጠራጠር የጀምበር ጥልቂያ ስዕል ነው”
ሁለተኛው- “ማንም ይመስክር የጸሐይ መውጪያ ስዕል ነው”
 ሙግታቸው በረታ። ተካረሩ። ሙግታቸውን የሰማው ሰው ሁሉ በአቅራቢያቸው እየመጣ ሀሳብ መስጠት ጀመረ።
ከፊሉ - “ይሄ ተጥለግለግ (አመሻሽ) ነው። ፀሐይ አይኖቿን እየጨፈነች እንጂ እየገለጠች አይደለም እያለ ከአንደኛው ጀርባ ቆመ።
ከፊሉ ደግሞ- “በጭራሽ አካባቢዋን ሁሉ እያፈካች ዙሪያ ገባውን ጸዳል ልታለብሰው ተዘጋጅታለች። ሊነጋ ነው” ሲል ከሁለተኛው ጀርባ ቆመ። በመጨረሻ አንድ አረጋዊ የሰፈሩ ነዋሪ የተባሉ መጡ። እሳቸው ይናገሩ ተባለ።
አረጋዊውም- “ስዕሉ የጀምበር ጥልቂያ ማለትም የፀሐይ መግቢያ ይመስለኛል” አሉ፡፡ የተቃራኒው ወገን ህዝብ በማጉረምረም፤ “ምክንያቱን ያስረዱና!” አሏቸው።
አረጋዊውም- “ምክንያቱማ፣ እኔ ሰዓሊውን አውቀዋለሁ። በጭራሽ ጠዋት ጠዋት ከእንቅልፉ አይነሳም። ስለዚህም የንጋት ፀሐይ አይቶ አያውቅም። ካላየ ደግሞ አይስልም”
***
ጊዜው የህማማት ነው። ብዙ ህመም አለ። የሀገራችን የወደፊት እጣ ፈንታ ምን እንደሆነ አለማወቅ  በህዝብ ዘንድ ትልቅ ግርታን ፈጥሯል። ሕዝብ ኢንፎርሜሽን ካላገኘ ውሃ እንደአጣ አትክልት ነው። ይጠወልጋል።  በዚያው መጠን ልቡን ያሸሻል። ሰብአዊ መብቱን መጠየቅ ካልቻለና ካልተከበረለት ህመሙ ይበረታል። ሲቪል ህብረተሰብ መፍጠርም ዘበት ይሆናል። ህመም ሲጎነጎን እምቢተኝነትና አመጻም ይወልዳል። እያንዳንዷ ቀን ትናንሽ ምሬት መጸነሷ መጥፎ ምልኪ ነው! ሕዝብ በሀገር ውስጥ የሚፈጠር የሚደረገውን ሁሉ በዝርዝር ካላወቀ አይረጋጋም። መንግሥትና ሕዝብ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ይሆናል። መብቶቹ ቢረገጡ ቀና ብሎ “ለምን?” ለማለት ድፍረት አይኖረውም። ድብቅነትን እንደ ዘይቤ ይይዘዋል። ህዝብ ካልተረጋጋ ሀገር ችግር ላይ ናት ማለት ነው። ሰሞኑን ለሚታየው የፖለቲካ ሁኔታ ሁሉ በምክንያትነት የተለያዩ ሀሳቦች ሲሰነዘሩ ከርመዋል። አንዳንዴ ዝርዝሩ ከጥቅሉ ይጋጫል። ተጻራሪ ወገኖች አቋም የሚነጣጠቁ ያህል የአንደኛው አቋም የሌላው የሚመስልበት ጊዜ አለ። በትክክል እነዚህ እነዚህ ጉዳዮች ዋነኛ የልዩነት መንስዔ ናቸው ተብለው ነጥረው የወጡ ናቸው ለማለት አሁንም ያስቸግራል። ነገሩ ይበልጥ እየቀረብነው ስንሄድ ይበልጥ እየተሸሸገ ይሄዳል ለማለት ነው።
“የእንጀራ እናትን እንጀራ፣ ወድቆም አታገኘውም” እንደሚባለው ተረት ሊሆን ይቃጣዋል።
በዚህ ላይ ከባለ ጉዳዩ በላይ በመሃል በመሃል የሚያዶሸድሸው መአት ነው። እንደ ቀንድ አውጣ ከሰንኮፉ ያልወጣ፣ የስልጣን-ጥማቱን ማርኪያ ሊያደርገው ወንዝ አቋርጦ የሚመጣ አለ። “በጠብታ ውሃ ውስጥ ጉማሬ አየሁ” እያለ የሚያጋንን የመኖሩን ያህል “ቢሆን አትጨፍሪ፣ ከጨፈርሽ አታበላሺ” መባል ያለበት አዲስ ዛር በአናቱ የፈላበት አፋሽ-አጎንባሽም ሞልቷል።
Beware of yes- men of Athens
They keep on saying ‘ Yes` ‘ Yes`
Till they put you into a mess
(“እሺ ጌታዬ” ከሚሉ አቴናውያን ተጠንቀቅ
“እሺ እሺ” እያሉ እየገፉህ ትርምስ ውስጥ እንዳትወድቅ) የሚባሉም አይጠፉም። በእነዚህ በእነዚህ ሳቢያ ኢንፎርሜሽን ይበልጥ እየተዥጎረጎረ ይጠራል የተባለው እየጎሸ፣ ተሰማ የተባለው እየተዳፈነ ይሄዳል። ጥርት ያለ ኢንፎርሜሽን ባለመቅረቡ ነገ ሀገሪቱን የሚጠብቃት የጀምበር ጥልቂያ ይሁን የፀሐይ መውጣት ከባቢ አየሯ አጠያያቂ ይሆናል። “በመጨረሻስ ለህዝቡ የሚተርፈው ምንድን ይሆን?” የሚለው ጥያቄ ይበረክታል። ይሄ ደግሞ የሁሉ ነገር ቁልፍ ነው!
ትላንትና ተጠይቀው ወይ ከነአካቴው ያልተመለሱ፣ ወይ በከፊል ብቻ የተመለሱ ዲሞክራሲያዊ ጥያቄዎች “መጨረሻቸው ምን ሊሆን ነው?” ማለት ግድ ይሆናል። የፖለቲካ ክፍፍል ያለነገር አይከሰትምና ስር ነቀልም ይሁን ጠጋኝ ለውጥ በመጣ ጊዜ ነባሮቹንም ሆነ አዲሶቹን ጥያቄዎች ዋነኛው ኢላማ እንኳ ቢስታቸው ፍንጣሪው ሳይመታቸው አይቀርም።
ከቶውንም የእስከዛሬው ዲሞክራሲ ውስጠ-ነገር ሲመረመር ታክሞ ተጠግኖ የሚድን ቁስል ይሆን ይሆን፣ ወይም አንቶኒዮ ግራምሺ እንዳለው፤ “ፓርቲ ሲነቅዝ የሚፈጠር፣ ጨርሶ የማይድንና የሚዛመት የፖለቲካ ደዌ (poltical gangrene) እመሆን ደረጃ ደርሶ ይሆን? መፍትሄውስ በሙሉ ኦፕራሲዮን ቆርጦ መጣል ነው ወይስ ሌላ መላ አለው? ማደንዘዣስ ያሻዋል አያሻውም?... ስለሁሉም ህዝብ ማወቅ ይፈልጋል። የሰማውን መረዳት የራሱ ፋንታ ነው።
እንጂ፤ በእናት- ዓለም ጠኑ ቲያትር እንደተጠቀሰው ዓይነት “ገባው አልገባው አይደለም የፖለቲካ ቁምነገሩ። ተቀበለ አልተቀበለም ነው!” የሚል አስተሳሰብ፤ ለመቼም ለማንም የማይበጅ መሆኑን ልብ ልንል የሚገባን አሁን ነው። 

Read 2286 times