Saturday, 22 April 2023 19:23

አንድ ዶሮ ለሦስትና እና የበግ ቅርጫ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

ኢድ ሙባረክ! እንኳን ለኢድ አልፈጥር በዓል አደረሳችሁማ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ...አብሮ አደግ ‘ዳያስፖራ’ እና ‘ግራ የገባው’ የሀገር ልጅ ለመጨረሻ ጊዜ ከተነጋገሩ ረጅም ጊዜ ከርመው ነው ሰሞኑን “ሀሎ!” የተባባሉት፡፡ ለነገሩ ‘ግራ የገባው’ የሀገር ልጅ አሁን፣ አሁን ብዙ የውጭ ጥሪ አያገኝም፡፡ ቀደም ሲል በአስራ አምስት ቀንም፣ በወርም ይደውሉለት የነበሩት አሁን በዘጠኝ ወርም በዓመትም ሲደውሉ...አለ አይደል... “እሱ እኮ ቶሎ፣ ቶሎ ነው የሚደውልልኝ፣” የሚባሉ አይነት ሆነዋል፡፡ ደግሞ የሚያወሩት እንደቀድሞው “ዩ ኖው አይ ቦውት ኤ መርሴዲስ ቤንዝ፣” “ቤቴን እኮ ብታየው! ፎር ቤድሩም ሆኖ ስዊሚንግ ፑል ሁሉ አለው፣” አይነት በሽልንግ ስምንት ጉራ ችርቸራ ሳይሆን የብዙዎቹ ወሬ ብሶት በብሶት ነው የሆነው፡፡ ግራ የገባው የሀገር ልጅ ከእነሱ “አይዞህ፣ ዚስ ቱ ሻል ፓስ!” “ከባሰም በሆነ መንገድ ወደዚህ እናመጣሀለን!” ሊሉት ሲፈልግ እነሱ ጭራሽ ዋነኞች ችግር አውሪዎች ሲሆኑበት እሱም ቁጥር እያየ ነው የሚያነሳውም፣ የሚተወውም፡፡   
“ላይፍ ኢን አሜሪካ ሀዝ ቢካም ቬሪ ታፍ!”
“ዚስ ባይደን ጋይ እዝ ዲስትሮዪንግ ዘ ካንትሪ!” (እና እኛ ምን እናድርግ! ትረምፕን ማን አውርዱት አላችሁ! ቂ...ቂ...ቂ...)
“ታውቃለህ በፊት ሁለትና ሦስት ሥራ ነበር የምንሠራው፡፡ አሁን አንዱም በመከራ ነው የሚገኘው፡፡”
እናማ... ግራ ገባው የሀገር ልጅ ሰሞኑን ‘የአማሪካን ቁጥር’ ሲያይ የለመደው ስላልነበር ቢሆንም፣ ባይሆንም ብሎ ነው ያነሳው፤
ዳያስፖራ፡- ሄሎ ኢዝ ዚስ....
ግራ የገባው፡- አዎ ነኝ፡፡
ዳያስፖራ፡- ሄሎ፤ ዚስ ኢዝ ጄከብስ፡፡ ሶ...ሀው አር  ዪ ዶዪንግ?” (ቆይ እንጂ! አትጣደፋ! ጄከብስ ነው ያለኝ.ማን...ማን አ...  አጅሬው ያዕቆብ፡፡) ግራ የገባው፡- ያዕቆብ እንዴት ነህ!
 ዳያስፖራ፡- ግሬት! ግሬት! ዛትስ ወንደርፉል፡፡ በአንድ ጊዜ አወቅኸኝ፡፡ (እዚህ ላይ “ምንም ብቀጥን ጠጅ ነኝ፣” ምናምን አይነት ጠጅ ራሱ በምክንያትነት ተጠያቂ ሊሆንበት የሚችል ፉከራ ሳይሆን ዲፕሎማሲ ቢጤ ነገር ነው የሚያስፈልገው፡፡
ግራ የገባው፡- ብረሳ፣ ብረሳ የአንተን ድምጽ እረሳለሁ እንዴ!
ዳያስፖራ፡- ካም ኦን! ላስት ታይም እኮ ጠፍቼህ አይዲ ካርድ ልትጠይቀኝ ምንም አልቀረህ፡፡ (መአት ዲፕሎማሲ ወይም ዲፕሎማሲ ነገር እየከሸፈ እንዳለው ይህኛውም ከሽፏል፡፡ ስለዚህ መልስ አያስፈልገውም፡፡)
ግራ የገባው፡- ለረጅም ጊዜ ጠፍተህ ከረምክ እኮ! (ትንሽ የፈረንጅ አፍ ጣል ማድረግ...እጅማ አንሰጥም!) ሀው አር ዩ! 
ዳያስፖራ፡- አም ፋይን ኤንድ ዩ!
ግራ የገባው፡- እኔም አም ፋይን፡፡ (እሰይ! ፈረንጂኛውን ለእናንተ ብቻ በእርስተ ጉልትነት ያስያዘ አለ እንዴ!) ከተደዋወልን ብዙ ቆየን፡፡ (እዚህ ላይ መስተፃምር፣ ቦዝ አንቀጽ     ምናምን አይነት ክርክር አይሰራም፡፡ ልክ ነዋ... ወደ ፈረንጅ ሀገር እንኳን ልንደውል እንዴት እንደሚደወልም  ባናውቅም “ከደወልክ ቆየህ...” ሳይሆን “ከተደዋወልን ቆየን...” ነው የሚባለው፡፡)
ዳያስፖራ፡- “ያ ሜን፡፡ ቲንግስ ዌር ሀርድ፡፡ ዩ ኖው የአሜሪካ ኑሮ እንደ ድሮው አይደለም፡፡ (በተዘዋዋሪ “ስኒከር፣ ጋላክሲ ምናምን ስልክ፣ አፕል ላፕቶፕ ምናምን የሚል ነገር አይደለም ልትጠይቁኝ እንዲች ብላችሁ እንዳታስቧት!” ነው፡፡ “ሶ ኦቨር ዜር ላይፍ እንዴት ነው?”
ግራ የገባው፡- ያስጠላል! በጣም ያስጠላል!
ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... ቀደም ባለው ጊዜ “ላይፍ እንዴት ነው?” ተብለን ስንጠየቅ “ያስጠላል፣” የሚለው ቃል መዝገበ ቃላታችን ውስጥ የለም፡፡ “ለማን ይድላው ብዬ ነው ቸግሮኛል ብዬ መጠቋቆሚያ የምሆነው!” ምናምን ተብሎ “ላይፍ እንዴት ነው?” ስንባል “አሸወይና ነው! እንደ ዘንድሮም ደስ ብሎኝ አያወቅም!” ነበር መልሱ፡፡
ዳያስፖራ፡- ኤኒዌይ ሆሊዴይ ኤክስፔንሲቭ ነበር ሲሉ ነበር እዚህ ዲሲ አካባቢ፡፡
ግራ የገባው፡- በጣም እንጂ!
ዳያስፖራ፡- እስቲ አስረዳኝ፡፡ ለምሳሌ ቺክን ስንት ነበር?
ግራ የገባው፡- አንድ ሺህ ሦስት መቶ፣ አንድ ሺህ አምስት መቶ፡፡
ዳያስፖራ፡- ሁኋት! ሁኋት ዱ ዩ ሚን አንድ ሺ ሦስት፣ አንድ ሺህ አምስት? ኢትስ ክሬዚ፡፡
ግራ የገባው፡- ከዛም የባሰ ነው፡፡ (ምንም ነገር ሊከሰትባት የምትችል ሀገርና የሚቻልበት ዘመን ውስጥ ስለሆንን ከ‘ክሬዚ’ም የባሱ አንድ ሺህ አንድ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ ለማለት ነው፡፡
ዳያስፖራ፡- ዩ ኖው ልጅ ሆኜ ማዘር በመቶ ብር ሁለትና ሦስት ምን የሚያካክሉ ዶሮዎች ይዛ ስትመጣ ትዝ ይለኛል፡፡
ግራ የገባው፡- ምን ታደርገዋለህ... (ይህ ሰውዬ በሾርኒ ሊያናግረኝ ነው እንዴ፡፡ አሀ... እሱ በመቶ ብር ሁለትና ሦስት ዶሮ ሲል እኔም ነሽጦኝ “ያን ጊዜ በዲናሬ አሎሎ፣ አሎሎ የሚያካክል  ጮርናቄ እንበላ የነበረው በአምስት ኮከብ ሆቴል በር ላይ ባለፍኩ ቁጥር ትዝ ይለኛል፣” ምናምን ብዬ “የድሮ ናፋቂ!” “የአጼዎች ምናምን!” ብሎ ያሰኘኝ!)
ዳያስፖራ፡- ሌላውስ...አይ ሚን...አንደ በግ ምናምን የመሳሰለውስ... (እንዲሀ አስለፍልፎኝ ትንፋሼን በዶላር ካልመለሰልኝማ...)
ግራ የገባው፡- መለስተኛ የምትለው በግ አሥራ ሦስት አሥራ አምስት ሺ ብር፡፡
ዳያስፖራ፡- ኦ ማይ ጋድ! ኦ ማይ ጋድ! ዩ ፒፕል አር ሪሊ ክሬዚ!
‘ክሬዚ’ አለ ለፈረንጅ የቀረበው የሀገር ልጅ፡፡ እውነት እውነቷን እንነጋገርና የዘንድሮ የፋሲካ ገበያን ሊገልጹ ከሚችሉት ቃላት አንዱ በእርግጥም ‘ክሬዚ’ የሚለው ነው፡፡ ምን መሰላችሁ...ግርም የሚለው ነገር እኮ እንዲህ ናቸው በማይባሉ አሳማኝ ምክንያቶች፣ ዋጋው ሰዋችንን በዚህ ደረጃ ባሳቀቀ መልኩ ከቁጥጥር ውጪ መሆን ደግሞም መነሻ ካለው ከየት እንደተነሳ፣ ቅንብርም ከሆነ የየትኛው ሰፈር እንደሆነ ግራ በተገባንበት ጊዜ እንደው ዘወር ብለንም ቀና  ብለንም እንባ  ለማበስ የሚሞክር እንጣ! መከራው አላልቅ ያለ ህዘብ... በቃ የወፍራሙም፣ ቀጭኑም ሩር ሆኖ ይቅር! የሺህ አምስት መቶ ብር ዶሮ፣ የአሥራ አምስትና የአስራ ሰባት ሺህ ብር በግ፡ የሀያ አምስትና የሠላሳ ሺህ ብር ፍየል...እንዴ የዋጋ ሱናሚ ነው እኮ የተለቀቀብን!
እናላችሁ... በዚህ ጊዜ እንደው ዕንባችንን ለማበስ ባይሞከር እንኳን አብሮን የተጨነቀ የሚመስል እንጣ! ስሙኛማ....በዚች በጦቢያችን የሥራ ሀላፊነት፣ ሪስፖንሲቢሊቲ ምናምን የሚባሉ ነገሮች ከመዝገበ ቃላት ወጥተው በተግባር የምናይበት ቀን አይናፍቃችሁም!
ሀሳብ አለን...እነኚህ ወፋፍራሞቹ ወንበሮች የሚሰጡት በዙር ይሁንልን፡፡ አለ አይደል...እኛም የህብረተሰቡ አባላት ስለሆንን (ወይም አባላት ነን ብለን ‘ስለምናስብ’)  ሁሉም የዕቁብ አባላት እጣው እንደሚደርሳቸው ለእኛም በሚሰምጠው ወንበር ተራ ደርሶን የማንሰምጥሳ!  ልክ ነው...በወፍራሙ የአለቅነት ወንበር ላይ ከሰመጡ በኋላ ሌሎችን አሻግሮ ለማየት ምን አይነት ችግር እንዳለባቸው  እንይላቸዋ! ቂ...ቂ...ቂ... መቼም በሀይቅ ውስጥ ጠልቀው ዋና ከገቡ በኋላ መሬት ላይ ያሉትንና ሀይቁን ለዋና ያመቻቹትን ለማየት እንደሚያስቸግረው ሁሉ በእልቅናና በፈራንካ ወንበር ሰምጠው የስልጣኑና የፈራንካው ምንጮች የሆኑት ለማየት የሚጋርዱትን ነገሮች እኛም እንያቸው ለማለት ያህል ነው፡፡ “ወይ ጣጣ!” ያለው ማነው?
እናማ...ዳያስፖራው “ኦ ማይ ጋድ!” ያለው እንደ ሀገር ልጆች ግራ ቢገባው መሆን አለበት፡፡
ዳያስፖራ፡- እና ኋት አር ዩ ጋይስ ዱዪንግ አባውት ኢት?
ግራ የገባው፡- ማለት...
ዳያስፖራ፡- አይ ሚን  ምን ስቴፖች እየወሰዳችሁ ነው?
ግራ የገባው፡- የምን ስቴፖች!
ዳያስፖራ፡- ማለት አንድ ነገር ካላደረጋችሁ ኔክስት ታይም እንዲሁ ሲጨምሩባችሁ ዝም ልትሉ ነው! ዩ ኒድ ቱ ቴክ ስቴፕስ፡፡ 
ግራ የገባው፡- የምንወስዳቸው ስቴፖችማ ለሚቀጥለው በዓል አንድ ዶሮ ለሦስት እንገዛና ብልቶቹ በእጣ ይከፋፈላሉ፡፡ በግ ደግሞ ለአንድ በግ አሥራ ሦስትም፣ አሥራ አምስትም ሰው እየሆንን ቅርጫ ለመጀመር እያሰብን ነው፡፡
ዳያስፖራ፡- ሶሪ ካርዴ እያለቀች ነው፡፡ አይ ዊል ኮል፡፡
ግራ የገባው፡- ስሙኝማ... የአንድ ዶሮ ለሦስትና የበግ ቅርጫን ሀሳብ ለመጠቀም ለምታስቡ የኮፒራይት ጥያቄ አላነሳም፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!
እንደገና ኢድ ሙባረክ!

Read 1585 times