Saturday, 22 April 2023 19:25

ከወሊድ በኋላ የሚፈጠር የድብርት ስሜት

Written by  ሀይማኖትግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)


   ከሩቅ ሲታይ አረንጓዴነቱ በሚስበው ሲጠጉት ግን የመንደሩ የቆሻሻ መጣያ ገንዳ በሚመስለው እና ጠረኑ በማያስጠጋው የደን ክምችት ውስጥ እትዬ ጥላነሽ እያቃሰቱ ገቡ። በህመማቸው ላይ ድካም የጨመረችባቸው ለአይናቸው እንግዳ የሆነችው ልጅ ረዘም ካለ ዛፍ ስር ገመድ ይዛ ቆማ ከቅርንጫፎቹ ጋር ተፋጣለች። እትዬ ጥላነሽ እየተጠጓት መሆኑን ስትገነዘብ አይኖቿን ከዛፉ ወደ እሳቸው አዞረች። “የእኔ ልጅ ምን ፈልገሽ ነው?” አሏት ጥርጣሬያቸውን ሸሸግ በማድረግ። “ምንም፤ ምነው” አለች ቆጣ ብላ።
አራስ የሚመስለውን ፊቷን እና የሰውነቷን ምቾት እየገረመሙ “መቼስ እንጨት ለቀማ አይደለም የመጣሽው። ወይም እንደ ሌሎቹ ከሰው የሚያስደብቅ ተግባር ያለሽ አትመስዪም። እንደው መንገድ ጠፍቶብሽ ከሆነ ልጠቁምሽ ብዬ ነው” በማለት ቁጣዋን ለማብረድ ሞከሩ። “አይ አይቸገሩ ምንም አልፈለኩም፤ ወደ መጡበት ይመለሱ” አለችና የእንባዋን መምጣት ለመደበቅ ፊቷን አዞረች። “አይ እኔ እንኳን እዚሁ ትንሽ አየር ልወስድ ነው የመጣሁት” ብለው ከአንዱ ድንጋይ ቁጭ አሉ። “እዚህ ቆሻሻ ውስጥ!?” አለች በጎሪጥ እየተመለከተች። እትዬ ጥላነሽ ቁጭ ሲሉ የድንጋዩ ቅዝቃዜ ስለጠዘጠዛቸው የሲቃ ድምፅ አሰሙ። ልጅቷም ደንገጥ ብላ “ምነው አሞታል እንዴ” በማለት ተጠጋቻቸው። እትዬ ጥላነሽ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም አንዳንድ ጥያቄዎችን መጠየቅ ጀመሩ። እሷም ታሪኳን አጫወተቻቸው። ሰብለ ትባላለች፤ 19 ዓመቷ ሲሆን 1 ልጅ አላት። መጫት ናት፤ ልጇን ከወለደች ገና 15 ቀኗ ነው። ገመድ ይዛ ወደ ጫካ እንድትሄድ ያደረጋትም ይህ እናት የመሆኗ ጉዳይ ነው። ከ1 ዓመት በፊት ትዳር ከመመስረቷ አስቀድሞ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነበረች። የ12ኛ ክፍል የማጠቃለያ ፈተና ውጤት ጥሩ ስላልሆነላት እና የቤተሰቧ ብሎም የአከባቢው ውትወታ ስለበረታባት ለዓመታት ገፍታው የነበረውን ጉዳይ ተቀበላ አገባች። ትዳር እንደመሰረተች ልጅ የመውለድ ፍላጎት ባይኖራትም ባለቤቷ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንድትጠቀም ባለመፍቀዱ ጸንሳ ወለደች። በወላጆቿ፣ በትዳሯ፣ በትምህርት፣ ባላት የገንዘብ አቅም እና በአጠቃላይ በህይወቷ ደስተኛ አይደለችም። ይህ ደስታ ማጣት ደግሞ ልጅ ከወለደች በኋላ ይበልጥ ባሰባት፤ ምንም እንኳን ቤተሰቦቿ ለአንዲት ወላድ እናት የሚደረገውን እንክብካቤ እያደረጉላት ቢገኙም ህይወቷ ብርሀን የሌለው ጨለማ ሆነባት። ባለቤቷ ትዳራቸው ከተመሰረተ ከጥቂት ወራት በኋላ እየጠጣ አካላዊ ጥቃት ሲያደርስባት ቆይቷል። ከዛም አልፎ ወደ ሌላ ሴት ጋር መሄድ እና ለቤት ፍጆታ የሚያስፈልግ ግብአት አለማሟላት ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል። እሷ የአቅሟን ሰርታ ገቢ እንዳታመጣ ደግሞ ማን ፈቅዶላት። ይህን ችግሯን ለወዳጅ ዘመዶቿ ስታማክር የተሰጣት ምላሽ “ሴት ልጅ ብልሀተኛ ናት ቀስ ብለሽ በዘዴ መልሽው፤ በአንቺ የተጀመረ ችግር አይደለም” የሚል ነበር። እናም ሰብለ ለልጇ እንኳን የሚተርፍ ተስፋ አጣች። ሁሉንም ጥላ ወደማይቀርበት ለመሄድም ወሰነች።
እትዬ ጥላነሽ ይህን ታሪክ ሲሰሙ እድሜያቸው ሀያዎቹ አጋማሽ ሲደርስ ከአከባቢው ሰው የደረሰባቸውን መሳለቅ አስታወሱ። “እስከ 25 ዓመት ሴት ልጅ እንዴት ትዳር ሳትይዝ ትቆያለች የሆነ ችግር ቢኖርባት ነው እንጂ” መባላቸው በአይነ ህሊናቸው ተመላለሰ። ከወደዱት ሰው ጋር ትዳር ከያዙም በኋላ ልጅ ሳይወልዱ በመዘግየታቸው የደረሰባቸው ማሽሟጠጥ ቀላል የሚባል አልነበረም። የፀነሱት ልጅ ሲሞት እና እሳቸው ሲታመሙ ደግሞ በኢፋ ሁሉም ጠላቸው። ሰብለ ከመንደሩ ራቅ ብላ ከአያቶቿ ጋር በማደጓ የእትዬ ጥላነሽን ታሪክ አታውቅም ነበር። ዛሬ ተስፋ በቆረጠችበት ወቅት የእሳቸውን ታሪክ መስማቷ በትንሹም ቢሆን ብቸኝነቷን አቀለላት። “የእኔ ልጅ ቢያንስ አንቺ ሙሉ ጤነኛ ነሽ፣ ልጅ ነሽ፣ ልጅሽም በህይወት አለች፤ የቀደመ ህልምሽን መኖር ትችያለሽ፤ በእኔ እና በአንቺ የደረሰ ለልጅሽም እንዳይተርፍ መከላከል ትችያለሽ፤ የአንቺ ችግር ከአንቺ ጋር ብቻ ተቀብሮ የሚቀር አይምሰልሽ፤ እንደውም በለጋነቱ የተውሽው ችግር አንቺ ባለመኖርሽ ምክንያት ይበልጥ ስሩ እየሰፋ እና እየተሰራጨ ይሄዳል እንጂ አይጠፋም’ በማለት ምክራቸውን ለገሷት።
በዓለምአቀፍ ደረጃ ከ6.5 እስከ 20 በመቶ በኢትዮጵያ ደግሞ ከ12 እስከ 38 በመቶ እናቶች በተለያየ ምክንያት ልጅ ከወለዱ በኋላ ለሚፈጠር የድብርት ስሜት (Postpartum depression) ይጋለጣሉ። እናቶች ልጅ ወልደው የድብርት ስሜት ውስጥ መግባት እና አለመግባታቸው የሚታወቀው(የሚመዘነው) በወለዱ በ4 ሳምንታት ወይም በ42 ቀናት ውስጥ ነው።
የኢትዮጵያ የፅንስ እና የማህፀን ሀኪሞች ማህበር ዓመታዊ ጉባኤ ባካሄደበት ወቅት ከቀረቡ ጥናታዊ ፅሁፎች መካከል የማህበረሰብ ጤና ባለሙያ እና ነርስ የሆኑት የረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን ፈታንሳ ጥናታዊ ፅሁፍ አንዱ ነው። ጥናታዊ ፅሁፉ በኢትዮጵያ በተለያዩ አከባቢዎች ከወሊድ በኋላ ስለሚያጋጥም የድብርት ስሜት የተሰሩ ጥናቶችን በማሰባሰብ የተሰራ ነው። ጥናቶቹ የተደረጉት እ.ኤ.አ ከ2016 እስከ 2019 ነው። በጥናቱ ላይ 6ሺ 7መቶ 74 እናቶች ተሳታፊ ሆነዋል። ከእናቶቹ መረጃው የተሰበሰበው በ2 መንገድ ሲሆን ይህም እናቶች ከሚገኙባቸው (መኖሪያ እና መሰል) አከባቢዎች እና ከህክምና ተቋማት ነው። እንደ ባለሙያው ንግግር በህክምና ተቋማት ያሉ እናቶች በይበልጥ የበሽታው ተጠቂ ናቸው። “ሰዎች ሲታመሙ ወደ ህክምና ተቋማት ይሄዳሉ” በማለት የልዪነቱን መንስኤ ተናግረዋል። ጥናቶቹን በማሰባሰብ በተሰራው በረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን ፈተንሳ ጥናት መሰረት 22.8 በመቶ የሚሆኑ እናቶች ከወሊድ በኋላ በሚያጋጥም የድብርት ስሜት ተጠቂ ናቸው። በችግሩ ስፋት እና ክብደት በኢትዮጵያ የተገኘው ውጤት ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ መሆኑን የህክምና ባለሙያው ተናግረዋል።
ወላዶች(እናቶች) ልጅ ከወለዱ በኋላ ለሚፈጠር የድብርት ስሜት የሚያጋልጡ ምክንያቶች;
ያለ ፍላጎት ልጅ መውለድ; አንዲት እናት ያለ ፍላጎቷ በትዳር አጋሯ ፍላጎት ብቻ(ተፅዕኖ) ከፀነሰች ወይም የቤተሰብ እቅድ እየተጠቀመች ባለችበት ወቅት በተለያየ ምክንያት ፅንስ ከተፈጠረ ለድብርት ስሜት ልትጋለጥ ትችላለች።
በጥንዶች መካከል ያለ አለመስማማት ወይም ግጭት; የህክምና ባለሙያው ባደረጉት ጥናት መሰረት 4.6 በመቶ በጥንዶች መካከል ያለ ግጭት ለእናቶች ድብርት መንስኤ ሆኗል። እንደ ባለሙያው ንግግር ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ የተለመደ፣ የትዳር አንዱ አካል የሚደረግ እና እንደ ችግር የማይቆጠር ነው።
ከዚህ ቀደም (እርግዝና ከመፈጠሩ አስቀድሞ) የድብርት ስሜት ከነበረ; ይህም 4.5 በመቶ ከወሊድ በኋላ ለሚፈጠር የድብርት ስሜት ምክንያት መሆኑ በጥናቱ ተረጋግጧል።
ማህበረሰቡ ለወላድ እናቶች የሚያደርገው ድጋፍ; እናቶች ልጅ ሲወልዱ ማህበረሰቡ በቁሳቁስ እና በስነልቦና የሚያደርገው ድጋፍ ለድብርት ስሜት ከመጋለጥ ወይም ካለመጋለጥ ጋር ግንኙነት አለው። ይህን ድጋፍ አጥተው ለድብርት ስሜት የተጋለጡ እናቶች 6መቶ መሆናቸውን የህክምና ባለሙያው ተናግረዋል።
የልጅ ህይወት ማለፍ; ህይወቱ ያለፈ ልጅ መውለድ ወይም የተወለደው ልጅ ህይወት ካለፈ አሊያም ከዚህ ቀደም ልጅ የሞተባቸው እናቶች ለድብርት ስሜት የመጋለጥ እድል አላቸው። ጥናቱ ውስጥ ከተካተቱት እናቶች መካከልም 3.7ከመቶ የሚሆኑት እናቶች በዚህ ምክንያት ከወሊድ በኋላ ለሚፈጠር የድብርት ስሜት ተጋልጠዋል።
በትዳር ደስተኛ አለመሆን; በትዳራቸው ደስተኛ ያልሆኑ እናቶች ደስተኛ ከሆኑት እናቶች ጋር ሲነፃፀሩ 5በመቶ የመጋለጥ እድል አላቸው[ይጨምራል]።
ከወሊድ በኋላ በሚያጋጥም የድብርት ስሜት [ Postpartum depression] የተጠቁ እናቶች ላይ ከሚስተዋሉ ምልክቶች መካከል ለብቻ የመሆን፣ እራስን ለመጉዳት ወይም ለማጥፋት መሞከር እና ለተወለደው ልጅ ትኩረት (እንክብካቤ) አለመስጠት ይጠቀሳል። የህክምና ባለሙያው እንደተናገሩት ከወሊድ በኋላ የሚፈጠር የድብርት ስሜትን ለመከላከል የእናቶች የስነልቦና እና አእምሯዊ ጤና ላይ መስራት ያስፈልጋል። እንደ ባለሙያው ንግግር ይህ የሚተገበረው የቅድመ ወሊድ እና የድህረ ወሊድ ክትትል ላይ ትኩረት በማድረግ ነው። ስለሆነም ለችግሩ ትኩረት መስጠት በሽታውን አስቀድሞ ለመከላከል እንዲሁም ሲፈጠር ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል።

Read 888 times