17 ሳምንታት ይቀሩታል፤ በጀቱ ከ111 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው
ከ100ሺ በላይ የስታድዬም መግቢያ ትኬቶች ተሸጠዋል
በሐንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት የሚካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 18 ሳምንታት ይቀሩታል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናው በማዕከላዊ አውሮፓ ሲዘጋጅ በታሪክ የመጀመርያው ነው፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ፕሬዝዳንት ሴባስቲያን ኮው እንደተናገሩት አውሮፓ የዓለም አትሌቲክስ ዋና መናሐርያ ናት። በሀንጋሪ የሚዘጋጀው ሻምፒዮና ልዩ ትኩረት እና ድምቀት የሚያገኝም ይሆናል። የዓለም ሻምፒዮናውን የምታዘጋጀው የቡዳፔስት ከተማ በ1934 እኤአ ላይ የአውሮፓ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የተመሰረተባት ናት፡፡
አትሌቲክስ በአውሮፓ አህጉር ከ150 ዓመታት ላይ እድሜ ማስቆጠሩን መረጃዎች ያመለክታሉ። ቡዳፔስት በርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮችን በማስተናገድ ትታወቃለች ፡፡ የአትሌቲክስ ስፖርት ታሪክ በሃንጋሪ ከ125 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በከተማዋ የሚዘጋጀው ለመጀመርያ ጊዜ ቢሆንም ሌሎች አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች በከተማዋ በተሳካ ሁኔታ ተካሂደዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተካሄዱ ውድድሮች የሚጠቀሱት በ1989 እና በ2004 እኤአ ላይ የተካሄዱት የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ናቸው፡፡ በ1986 እና በ1998 እኤአ ላይ ደግሞ የአውሮፓ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ተካሂደዋል፡፡
አስቀድመው ከተጠቀሱት ትልልቅ ውድድሮች ባሻገር ቡዳፔስት በአትሌቲክስ የግራንድ ፕሪክስ ውድድሮችን፤ የፎር ሙላ ዋን የሞተር ስፖርት ሽቅድምድሞች፤ የአውሮፓ የወጣቶችና የታዳጊ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች እና ሌሎች ውድድሮች ተደርገውበታል፡፡
19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ቡዳፔስት ላይ የሚያስተናግዱት ሁለት የስፖርት መሰረተልማቶች ናቸው፡፡ የሃንጋሪ ብሄራዊ ቡድን ዋና ሜዳ የሆነው ኔፕስታድዮን ወይም የፈርንክ ፑሽካሽ መታሰቢያ ስታድዬም የመጀመርያው ነው፡፡ ይህ ስታድዬም ፑሽካሽ አሬና ተብሎ በ2018 ተመርቋል። ቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮናን እንድታዘጋጅ በዓለም አትሌቲክስ ማህበር የተመረጠችው በዚህ ወቅት ነበር።የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው አዘጋጅ ኮሚቴ፤ የቡዳፔስት ከተማ አስተዳደርና የሀንጋሪ መንግስት በከተማዋ የሚገኘውን ብሄራዊ አትሌቲክስ ማዕከል ለዓለም ሻምፒዮናው ማስተናገጃ እንዲሆን ወስነዋል፡፡ ከስታድዬሙ ጋር የሚያያይዘው ብሄራዊ የአትሌቲክስ ማዕከሉ ከ15ሺ ወደ 35ሺ ተመልካች እንዲያስተናግድ ሆኖ በከፍተኛ በጀት ታድሶ ተገንብቷል፡፡ የአትሌቲክስ ማዕከሉ በዘመናዊ መልክ ታድሶ የተገነባው ዳኑቤ በተባለ ወንዝ ዳርቻ ላይ ሲሆን ዙርያ ገባን በዘመናዊ ሆቴሎች የመዝናኛ ስፍራዎች፣ ታሪካዊ ስፍራዎች የቅርስ ማዕከሎች የተከበበ ነው።ብሄራዊ አትሌቲክስ ማዕከሉ ከዓለም ሻምፒዮናው በኋላ የሃንጋሪ አትሌቲክስ ዋና መናሐርያ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ሃንጋሪ ከ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳካ መስተንግዶ በኋላ ከተማዋን የአውሮፓ የቱሪዝም መድረሻ እንድትሆን ተስፋ አድርጓል። በዓለም የስፖርትና የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ኢኮኖሚያዋን እንድታነቃቃም አስበዋል፡፡19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ቡዳፔስት ላይ ሲካሄድ ታላቁ የአትሌቲክስ ስፖርት መድረክ 40ኛ ዓመቱን የሚያከብር ይሆናል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1983 እኤአ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ በፊንላንድ ሄልሲንኪ እንደተካሄደ ይታወቃል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር በፃፈው ታሪክ እንዳተተው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ራሱን የቻለ አለም አቀፋዊ ውድድር ሆኖ እንዲጀመር ሶስት አውሮፓዊ የአትሌቲክስ ስፖርተኞችና ባለሙያዎች አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ የመጀመርያው ሆላንዳዊው የመካከለኛ ርቅት ሯጭ አድርያን ፓውሊን ናቸው፡፡ በአትሌቲክስ ስፖርት ከፍተኛ ባለራእይ ተብለው የሚጠቀሱት ሆላንዳዊው ከ1976 እስከ 1981 ድረስ የአለም አቀፉ አማተር አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር አይኤኤኤፍ ፕሬዝዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡ ለዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ምስረታ አስተዋፅኦ ያደረጉት ሌሎቹ አውሮፓውያን ደግሞ እንግሊዛዊው የአጭር ርቀት ሯጭ ሎርድ በርክሊ በማርኬቲንግ ባለሙያነት እንዲሁም ጣሊያናዊ የስፖርቱ አፍቃሪ ናቸው፡፡ቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን በ2023 እኤአ ላይ የማስተናገድ እድል ብታገኝም በ2007 እኤአ ላይ ለማስተናገድም ከፍተኛ ጥረት አድርጋ አልሆነላትም ነበር፡፡ በ2007 እኤአ ላይ 11ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለማስተናገድ የበቃችው የጃፓኗ ከተማ ኦሳካ ነበረች፡፡ በ2025 እኤአ ላይ 20ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ቶኮዮ እንደምታዘጋጅ የዓለም አትሌቲክስ ማህበር አስታውቋል፡፡የዓለም ሻምፒዮና በጀት፤ ገቢና ሌሎችም የዓለም አትሌቲክስ ማህበር በሰራው ጥናት መሰረት አንድ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአዘጋጅ ከተማ ላይ እስከ 244.5 ሚሊዮን ዶላር በአዘጋጁ ከተማ ላይ እንዲንቀሳቀስ ያደርጋል። በመስተንግዶው ብቻ እስከ 45 ሚሊዮን ዶላር፤ በምግብና መጠጥ እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር፤ በትራንስፖርት አገልግሎት 4.3 ሚሊዮን ዶላር፤ በተለያዩ ንግዶችና መዝናኛዎች 7.4 ሚሊዮን ዶላር ተንቀሳቅሶ፤ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ግብዓቱ ከ153 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሚዲያ የሚያስገኘው ጥቅም በአጠቃላይ ከ89.3 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሲሆን፤ ከቲቪና ከኦንላይን ስርጭቶች 59.3 ሚሊዮን ዶላር፤ ከኦንላይን ህትመት 19.3 ሚሊዮን ዶላር፤ ከጋዜጣና መፅሄትና ሌሎች ህትመቶች 3.5 ሚሊዮን ዶላር ከማህበራዊ ሚዲያ እስከ 7.2 ሚሊዮን ዶላር ይንሸራሸራል፡፡
በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ፕሮጀክቶችና ስራዎች እንዲሁም ከተለያዩ የማህበረሰብ አገልግሎቶች 2.2 ሚሊዮን ዶላር ይወጣል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ይህን ጥናቱን በመስራት በዝርዝር ይፋ ያደረገው በ2027 ላይ 21ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለሚያዘጋጁ ከተሞች ባወጣው የጨረታ ሰነድ ነው፡፡ስፖርት ኤክዛማይነር በሰራው ጥናታዊ ዘገባ ደግሞ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን የሚያዘጋጅ ከተማ ለስፖርት መሰረተ ልማቶች፤ ለመስተንግዶ፤ ለሽልማት ገንዘብ፤ እና የተለያዩ ተያያዥ ተግባራት እስከ100 ሚሊዮን ዶላር በጀት መመደብ ያስፈልገዋል፡፡ በ2022 እኤ ላይ በዩጂን ኦሬጎን ለተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው አዘጋጆች 85.6 ሚሊዮን ዶላር የበጀት ወጭ እንደነበራቸው ያመለከተው ስፖርት ኤክዛማይነር ፤ ቡዳፔስት ለምታዘጋጀው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 111 ሚሊዮን ዶላር በጀት ማድረጓንም ጠቅሷል፡፡ በ2017 እኤአ ላይ 16ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያስተናገደችው የኳታር መዲና ዶሃ እስከ 236 ሚሊዮን ዶላር በጀት በማውጣት በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛውን ኢንቨስትመንት አስመዝግባለች፡፡ የዶሃ የዓለም ኻምፒዮና የመስተንግዶ ወጭጥ ከፍተኛ ሊሆን የበቃው ሻምፒዮናውን የሚያስተናግደውን የካሊፋ ዓለም አቀፍ ስታድዬም በ120 ሚሊዮን ዶላው ወጭ ታድሶ መገንባቱ ነው፡፡ስፖርት ኤክዛማይነር በሰራው ልዩ ጥናታዊ ዘገባ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እጅግ ስኬታማና ትርፋማ የስፖርት መድረክ ነው፡፡ ዩጂን በ2022 ላይ 18ኛውን የዓለም ሻምፒዮና ስታዘጋጅ የነበረውን የመዋዕለንዋይ እንቅስቃሴ ናሙና እዲሆን የስፖርት ሚዲያው በዝርዝር አስቀምጧል። ለአስተዳደር ስራዎችና የሽልማት ገንዘብ 16.76 ሚሊዮን ዶላር፤ ለተለያዩ የማረፊያና የመስተንግዶ አገልግሎቶች 20.81 ሚሊዮን ዶላር፤ የማርኬቲንግ ወጭዎች 12.45 ሚሊዮን ዶላር፤ ለፕሮቶኮልና ለልዩ ልዩ ስነስርዓቶች 3.88 ሚሊዮን ዶላር፤ ለስፖርት መሰረተልማቶች፣ ለውድድርና ልምምድ ስፍራዎች ፣ ለህክምናና ዶፒንግ አገልግሎቶች ማንቀሳቀሻ ከ9 ሚሊዮን ዶላር በላይ፤ ለፕሬስ ስራዎችና ቴክኒካል ድጋፎች 6.10 ሚሊዮን ዶላር፤ ለቲቪ ፕሮሞሽን 14.20 ሚሊዮን ዶላር ለስልክ አገልግሎት 2.09 ሚሊዮን ዶላር ለአደጋ ጊዜ እና ሌሎች የመስተንግዶ ስራዎች እስከ 5 ሚሊዮን ዶላር በጀት ሆኖ ወጥቷል፡፡
እንደ ስፖርትኤክዛማይነር ገለፃ በዩጂን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አዘጋጅ ኮሚቴ ላወጣው በጀት የተለያዩ አካላት ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ከአሜሪካ መንግስት፤ ከዩጂን ከተማ አስተዳደርና ከስፖንሰርሺፕ የተገኘው 51 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ለሽልማት ገንዘብ የሚሆነውን 7.2 ሚሊዮን ዶላር ሰጥቷል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናው ከትኬት ሽያጭ፤ ከስፖርት ቁሶች እና የተያያዙ ንግዶች 18.04 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የቲቪ ስርጭት እና ባለመብትነት 16.55 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሆኖበታል፡፡ከ100 ሺ በላይ የስታዲየም መግቢያ ትኬቶች ተሸጠዋል፡፡ በሃንጋሪ ቡዳፔስት ለሚካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የቀሩት 127 ቀናት ናቸው። ሻምፒዮናው የሚካሄድበት ወቅት ልክ 200 ቀጥታ ሲቀሩት ከ100ሺ በላይ የስታዲዬም መግቢያ ትኬቶች መሸጣቸውን አዘጋጆቹ አስታውቀዋል። ከ420 ሺ በላይ ትኬቶች ለገበያ ቀርበው ነበር። በሻምፒዮናው ከ200 አገራት በላይን በመወከል እስከ 2000 አትሌቶች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡
ከአትሌቶች፤ አሰልጣኞች እና የውድድር ሰራተኞች ባሻገር ለዓለም ሻምፒዮናው በዓለም አትሌቲክስ ማህበር በደብዳቤ ተጋብዘው የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት ደግሞ ብዛታቸው ከ8000 በላይ ነው፡፡
Saturday, 22 April 2023 19:26
ቡዳፔስት 2023
Written by ግሩም ሰይፉ
Published in
ስፖርት አድማስ