Print this page
Monday, 24 April 2023 00:00

«እንደ ማበድ ብያለሁ!»

Written by  በጸጋው ማሞ
Rate this item
(3 votes)

ሀገራዊ ድንቁርና ውስጥ አልገባንም ወይ?

“የምሑራንን ምክር የሚቀበል መንግሥት ያላት አገር ምነኛ የታደለች ናት? ኢትዮጵያ ግን ከአፄ ምኒሊክ ውጭ የምሑራንን ሃሳብ የሚቀበል መሪ አላጋጠማትም። ሐቀኛ ምሑር የሌላት አገር ደግሞ ታሳዝናለች። ኢትዮጵያ አሁን ላይ የምሑራንን ምክር የሚሰማ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ያጣችው ሐቀኛ ምሑራንም ጭምር ነው።”


“ምን አልባት አብዷል የሚሉ ቢገኙም እውነት ነው ነጻነትን አብዝቶ በመውደድና የኢትዮጵያን ታላቅነትና ልማት በመመኘት... “እንደ ማበድ ብያለሁ” ፡፡ ከዛሬ 100 ዓመት በፊት ኪዳነ ማርያም አበራ የተባሉ ምሑር፣ በብርሃንና ሰላም ጋዜጣ ላይ የጊዜው የአገሪቷ የኋላቀርነት ሁኔታ እና የመጭው ዘመን ቀውስ ቢያስጨንቃቸው “እንደ ማበድ ብያለሁ” ብለው ጻፉ። ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜ እንደ ማበድ ያሉት ግን እርሳቸው ብቻ አልነበሩም። በተለያየ አጋጣሚና ሁኔታ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ተጉዘው የአውሮፓን ሥልጣኔ የተመለከቱና የተማሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እብደቱ ነካክቷቸው ነበር።
ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ “ፋና ወጊ የለውጥ አቀንቃኞች በኢትዮጵያ” ብለው በጻፉልን ግሩም መጽሐፋቸው ላይ የ19ኛው መጨረሻና የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ያለውን የለውጥ ናፋቂ ትውልድን ትጋት አስነብበውናል። ይህም ጽሁፍ በዋናነት መነሻ ያደረገው ይህ መጽሐፍና “የብርሃንና ሰላም” ጋዜጦች እንደሆኑ ልብ ይሏል። ስለነዚህ ዕንቁ የሆኑ ምሑራን ተጨማሪ ዳሰሳ እንድናደርግ መንገድ ስለከፈቱልን፣ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ እጅጉን ምስጋና ይገባቸዋል። ስለነዚህ ሰዎች ለውጥ እየናፈቁ ለአገር ሥልጣኔ ሰማእትነት ለመቀበል እየፈለጉ ለዚህ ዕድል አለመብቃት ያሳብዳል።
ከዛሬ 100 ዓመት በፊት እኮ ኢትዮጵያ በንጽጽር ከበርካታ የዓለም ሀገራት የተሻለች የምትባል አገር ነበረች፤ ቢያንስ በርካታ ሀገራትም ገና ሀገረ መንግሥት ሳይገነቡ ኢትዮጵያ ነጻና በእድገት ጎዳና ላይ ያለች አገር ነበረች። ኢትዮጵያውያን ተራማጅ ምሑራን ግን በዚህ ሊረኩ አልቻሉም፥ እንደ እውነቱም ቢሆን ግን የሚያረካ ነገር ብዙም አልነበረም። እነሱ ግን ለምን ኃያል አገር አልንሆንም ከሚል የአገር ፍቅር ስሜት፣ የዘውግና የሃይማኖትን ድንበር ጥሰው ሁሉም በአንድነት ለአንዲት ሥልጡን ሉዓላዊት አፍሪካዊት አገር ልእልና ከባሕር ማዶ እስከ አገር ቤት በአንድነት በቃልና በጽሑፍ ጮኹ፤ ጮኸውም አልቀረም፤ ብዙዎቹ ከንቱ ሰማእትነትን ተቀበሉ። የከሸፈው ምሑራዊ ንቅናቄ ቢባል ግነት አይመስለኝም።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እንዲህ ይላሉ፤ “አገራችንን፥ ወገናችንን የምንወደው ሲመቸንና ሲደላን፣ ስንሾምና ስንበለጽግ ብቻ ከሆነ የምንወደው ራሳችንን እንጂ አገራችንን አይደለም” ይላሉ። (አድማጭ ያጣ ጩኸት፣ ገጽ 135)። እንደ እውነቱ ከሆነ “ያ” ለውጥ ናፋቂው የ20ኛው መጀመሪያ ምሑራን፣ በንጽጽር ነዋይና ሥልጣን ብዙም አያጓጓውም ነበር፤ ደግሞ በጊዜው የተማሩ ብርቅዬ ስለ ነበሩ ነዋይና ሥልጣን ከፈለጉ ከያዙት በላይ ማግኘት ይችሉ ነበር። ዳሩ ግን እነሱን እጅጉን ያሳስባቸውና ያስጨንቃቸው የነበረው የኢትዮጵያ ኋላቀርነትና ድህነት ነበር። እነ በጅሮንድ ተክለሃዋርያት ተክለማርያም፣ ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ፣ ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ያችን የአድዋን ሉዓላዊት ኢትዮጵያን በሁለትና በሦስት አገራት በሞግዚት በቅኝ ግዛት ብትተዳደር ይሻላል ያሉት የአገሪቷ ኋላቀርነትና መጻኢ ጊዜ በቀላሉ የማይፈታ  እንደሆነ ስለተረዱት ይመስላል፥ የአገር ጉዳይ እንደ እብድ አድርጓቸው ያችን በጀግኖች አርበኞች የታፈረችውን አገር ቅኝ ግዛት የተመኙላት። “ወዮለት በድንቁርናው ለሚቀመጥ ሕዝብ ውሎ አድሮ ይደመሰሳልና” ይላል ገብረሕይወት ባይከዳነኝ፥” አጤ ምኒልክ” በሚለው መጽሐፉ ላይ። እንዴት ሕዝብ ይደነቁራል? ለምንስ ሕዝብ ይደነቁራል? ሕዝብን የሚያነቃው ማነው? በተፈጥሮው ይነቃል ወይስ ምሑራን ናቸው የሚያነቁት? ምሑር የሌለው ሕዝብስ ዕጣ ፈንታው፣ ጽዋ ተርታው ምንድነው? የተማሩ ምሑሮቹ የደነቆረበትስ ሕዝብ ምን ሊሆን ይችላል? ገብረሕይወት ባይከዳኝ፣ በሁለቱም መጽሐፎቹ፣ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ የምዕራቡን ሞዴል ተከትላ በፍጥነት ካላደገች ሉአላዊነቷን አስጠብቃ መዝለቅ እንደሚሳናት ደጋግሞ አስጠንቅቋል። “ኢትዮጵያውያን የኤሮፓን አእምሮ የተቀበለች እንደሆነ የሚደፍራት ጠላት የለም። ያልተቀበለች እንደሆነ ግን ትፈርሳለች፤ ወደ ባርነትም ትገባለች” በማለት የዐጤ ምኒሊክ ወራሽ የጃፓንን መንገድ እንዲከተሉ አበክሮ መክሯል። ባሕሩ ዘውዴ ገጽ 163፣ የምሑራንን ምክር የሚቀበል መንግሥት ያላት አገር ምነኛ የታደለች ናት? ኢትዮጵያ ግን ከአፄ ምኒሊክ ውጭ የምሑራንን ሃሳብ የሚቀበል መሪ አላጋጠማትም። ሐቀኛ ምሑር የሌላት አገር ደግሞ ታሳዝናለች። ኢትዮጵያ አሁን ላይ የምሑራንን ምክር የሚሰማ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ያጣችው ሐቀኛ ምሑራንም ጭምር ነው።
ክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤልም፤ “እኛ የተቀደምነው በቴክኖሎጂ ብቻ አይደለም በአስተሳሰብ ጭምር ነው” ይላሉ “ጃፓን እንደምን ሰለጠነች” በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 101 ላይ። ብሩህ አለምነህም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ፣ ኢትዮጵያውያን ከአውሮፓውያን በ200 ዓመታት ወደ ኋላ እንደምንቀር ይገልጻል። ይህ አገርንና ሕዝብን መናቅ ሳይሆን ከአንድ ሀገር ወዳድ ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር ነው። እውነተኛ ችግራችን ሲነገረን እየመረረንም ቢሆን መቀበል ካልቻልን የዓለም ዝቃጭ ሆነን እንቀጥላለን። እኛ ኢትዮጵያውያን በአስተሳሰብና በቴክኖሎጂ  በጣም ኋላቀሮች እንዳልሆንን በምን ማስተባበል እንችላለን? እኛ ንቁና ቴክኖሎጂን የመፍጠርና የመኮረጅ አቅም አለን ብለን ምሳሌ የምንጠቅሰው አንድ ምሳሌ ምንድነው? ምንም የለንም። በ500 ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው ምንድነው? የሌሎች አገር ሕዝቦች ምድሩን እየበረበሩ በህዋ ላይ ጥልቅ ምርምር በሚያደርጉበት በዚህ የሠለጠነ ዘመን፥ እኛ ግን ለክፉ ቀን የሚደርስልንን የገዛ ወንድማችንን በፈረንጅ መሳሪያ ለመግደል በተቋም ደረጃ ቢሮ ዘግተን ግዳይ ልንጥል አጀንዳ የምንቅረጽ እጅግ አሳዛኝ ሰዎች አይደለንምን? እንዴት በዚህ ዘመን ደሀ አገር ይዋጋል? ከዚህ የበለጠ ለድንቁርናችን ምን እማኝ ይጠቀሳል? ኢትዮጵያ ውስጥ እኮ በትብብርና በፍቅር ካለማነው የአንዱ ክልል መሬት ብቻ ከእኛ አልፎ ለምስራቅ አፍሪካም ይበቃ ነበር። በዚህች አገር በዚህ ዘመን ጨርቁን ጥሎ ያላበደ ምሑር እርሱ ይመርመር። ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ከኃያላኑ አገራት ጋር ትከሻ ለትከሻ እየተለካካች ግብግብ በምትፈጥርበት ዘመን የነበሩ ምሑራን ኋላቀርነታችን ወፈፍ ያደረጋቸው ዛሬ ቢኖሩ ወይ ጨርቃቸውን ጥለው ያብዳሉ ወይም ደግሞ አራሳቸውን ይገድላሉ።
ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ፥ አሮፓውያን ጎረቤት አገር መጥተው፤ አገራችንም ገብተው ትርፍ ሲያጋብሱ እያየ እጁን አጣጥፎ የተቀመጠውን ኢትዮጵያውያን ባዩ ጊዜ፥ “ኢትዮጵያውያን ከእናንተ በመፈጠሬ አፍራለሁ ...የለየላችሁ ሰነፎች ናችሁ” በማለት ምሬታቸውን ከ100 ዓመት በፊት ገልጸው ነበር። እንዴት አገር ለምዕተ ዓመታት ካለበት ቦታ ቁልቁል ያሽቆለቁላል?
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፤ “መክሸፍ በኢትዮጵያ ታሪክ መሰረታዊ ባሕሪ ቢሆንም የክሽፈቱ አይነት ከ1928 በኋላ የተለየ ነው” ይላሉ፣ “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” ገጽ 12 ላይ። አሁን ኢትዮጵያ አልከሸፈችም፤ በብልጽግና መንገድ ላይ ነች ማለት ራስን መደለል ነው። ሌላውን የፋብሪካ ሸቀጦች ትተነው ሽንኩርት፣ ቲማቲምና ብርቱካን እንኳ ሳይቀር በተመጸወተችው በፈረንጅ ዶላር የምትሸምት አገር አሳቢዎቿን ባያሳብድ ነው የሚገርመው። በደምና በአጥንት የተዋሐድን ሆነን ሳለን ባላንጣዎቻችን በፈበረኩልን የዘውጌ ማንነት በግፍ መተራረዳችን ለሥንፍናችንና ለድንቁርናችን ከዚህ የበለጠ ምን ምስክር አለ? ከዚህ የበለጠ ድንቁርና የሚለው ለማን ያገለግላል? ዶ/ር እጓለ “ለማወቅ የሚፈልግ መጠራጠርና መመራመር አለበት” ይላሉ። በእውነትም አሁን ያለንበትን ወይም የቆምንበትን እጅግ የተዋረደ የአስተሳሰብ ሁኔታ ማጤንና መናቅ መጀመር የለብንም ወይ? ተዋርደው አገራችንን ያዋረዷትን ልሂቅ ነን የሚሉ ሰዎችንና መሪዎች ካነገሥንበት መንበር በዕውቀት ሰፌድ እያበጠርን ምርቱን ከግርዱ መለየት መጀመር የለብንም ወይ?
“አገራቸው ሀብታም ሆና አንጎላቸው ደሀ የሆኑ ሕዝቦች ድሆች ናቸው... ጃፓን በአንድ ጊዜ ከ10 የሚበልጡ ታላላቅ ሰዎችን በማውጣቷ፥ ምንም እንኳን በተፈጥሮ ሀብት መናጢ ድሀ ብትሆንም በምርጥ ልጆቿ ብልኃት አውሮፓውያን በምዕተ ዓመታት ያመጡትን እድገት እሷ ግን በ60 ዓመት አሳክተዋለች። (ከበደ ሚካኤል፥ ጃፓን እንደምን ሰለጠነች፣ ገጽ 61)። ታዲያ እኛ ድሀ የሆነው አንጎላችን ድሀ ስለሆነ አይደለምን? እንዴት በዚህ በ21ኛው ክ/ ዘመን ቴክኖሎጂ መኮረጅና መራቀቁ ቀርቶብን፤ ዓለም ንቆ የተፋውን የዘውግ ፖለቲካ በማራመድ እንገዳደላለን? ከዚህ የበለጠ ውርደት ምን አለ?
ዓለም ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ በሰው ሰራሽ አዕምሮ (Artificial Intelligent) ዓለምን እያስደመመ ባለበት በዚህ ጊዜ፥ አገራት ዕለት ዕለት በአዳዲስ ግኝቶች እየተጨናነቁ በሚፎካከሩበት ዘመን፣ የግዛት አድማሳቸውን እያሰፉ በባሕርና በሕዋ ላይ በሚፎካከሩበት ጊዜ፣ የምርምር ተቋሞቻቸው 24 ሰዓት በዜጎቻቸው ጭንቅላት በሚፈተንበት በዚህ ሰዓት... ኢትዮጵያ ግን ከኋላቀርነት ሊያወጧት የሚችሉትን ሕጻናት እየገደለች ነው፣ እያንከራተተች ነው፣ ከውርደት ሊታደጓት የሚችሉትን ወጣት ዜጎቿን በዘረኝነት መርዝ እያጠመቀች ነው፣ አሁን ተስፋ የሚጣልበት የትኛው የልህቀት(excellence) ተቋም ነው? ያሉትስ ተቋማት እየፈረሱ አይደለምን? ታዲያ ኢትዮጵያ አሁን ያጋጠማትን ጥልቅ አደጋ አገራዊ ድንቁርና ቢባል ግነት ይሆናልን? የአሁኗን ኢትዮጵያ የተመለከተ አይደለም ኃቀኛ ኢትዮጵያዊ ምሑር ይቅርና አንድ ኃቀኛ አፍሪካዊ ምሑር ጥልቅ ኀዘን ውስጥ መግባቱ አይቀርም።
ከኋላችን ተነስተው በአጭር ጊዜ ውስጥ የበረሩትን፣ ቻይና እንዴት እንደተመነደገች? ዱባይ የበረሃ ገነት እንዴት ልትሆን እንደቻለች? ቱርክ እንዴት እንደሰለጠነች? ህንድ እንዴት አንድነቷን ጠብቃ እንደ አደገች? ባላንጣችን ግብጽ እንዴት እንደሮጠች? ሲንጋፑር እንዴት ከፍታ ላይ እንደወጣች? ራሺያ እንዴት ኃያል እንደሆነች? ትላንት በቅኝ ገዥዎቻቸው በጎ ፈቃድ አገር የሆኑት ደቡብ አፍሪካና ናይጀሪያ ሳይቀሩ እንዴት የተሻለ አገር እንደገነቡ? ጠይቀን ሕያው ምስክር ቆጥረን መማር ያልቻልን እኛ ምንድነን? ሌላው ሁሉ ቢቀርብን፣ የኢኮኖሚ እድገት ቅንጦት ቢሆንብን እንኳን እንዴት ለሁላችንም እኩል የሆነ ሥርዓተ መንግሥት እስካሁን መገንባት አቃተን? ያ ፋና ወጊ የለውጥ አቀንቃኝ የተባለው በቁጥሩ እጅግ አነስተኛ የሆነው  የ20ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ ትውልድ፣ ኢትዮጵያ ትበለጽግ ዘንድ እልህ አስጨራሽ ውይይትና ክርክር “በብርሃንና ሰላም” ጋዜጣ ያደርግ ነበር። ያ የለውጥ ፋና ወጊ ትውልድ በአብዛኛው ከፊሉ በአገር ውስጥ በውጭ ሥርዓተ ትምህርት የተማረና ከፊሉ ደግሞ በውጭ አገር ዩኒቨርስቲዎች የተማረ እንደመሆኑ መጠን ኢትዮጵያ የውጭውን ሥልተ ምርትም ሆነ የአስተዳደር ሥርዓት ትጠቀም ዘንድ ይመክር ነበር። ከፊሉ ደግሞ ሀገር በቀሉንም ያማከለ እድገት እንዲመጣ ይታገል ነበር። ለእናት አገር ምሑራዊ የሃሳብ ፍትጊያውን አለማድነቅ አይቻልም።
እንደ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ አጠራር፥ “ፋና ወጊ የለውጥ አቀንቃኝ” የተባለው ትውልድ እንዲሁ በምኞት እንደነደደና እንደተቅበዘበዘ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንዲት ጠብታ ሳያበረክት የኢጣሊያ ወረራ መጣና ከፊሉ በስደት ላይ ሳለ ከነሃሳቡ ሲሞት፥ ከፊሉ ደግሞ በጣሊያን ኢትዮጵያ ውስጥ በግፍ ተረሸነ፤ የቀሩትም ሰሚ አጥተው እንደቆዘሙ አረፉ። ሌሎች አገራት በጥቂት ግለሰቦች ጥረት ከድቅድቅ ጨለማ ወደ አስደናቂ ሁለንተናዊ የሥልጣኔ ብርሃን በቅጽበት ሲለወጡ ኢትዮጵያ ደግሞ በየጊዜው ከደርዘን በላይ ምሑራን እየመጡላት መጠቀም ባለመቻሏ ከጨለማ ወደ ባሰ ሌላ ድቅድቅ ጨለማ እየተጓዘች ትገኛለች። አዎ! የኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታን ለተመለከተና መጭው ዘመንን ለተነተነ ምሑር ያሳብዳል።



Read 1746 times