Print this page
Saturday, 22 April 2023 19:55

የእኔ ሞት

Written by  ድረስጋሹ
Rate this item
(4 votes)

ቀትር ላይ፣ታጣቂዎች የሚለብሷትን ሽርጥ ያሸረጠ፣ጨጎጎት ፊት ፣ ሌባ ቢጤ...]
ሽሚዛ ውስጥ ተቀርቅሮ ጩቤውን ሲመዝ አየሁት። የጩቤው ገላ ፍልቅ ሲልብኝ ዓይኔን መለስኩት። ጥግ ይዟል ፤ምናልባትም አላየኝም። «ሰው ያልፋል»የሚል እምነት ስላለው ተዘጋጅቶ እየጠበቀ ነው። እውነቱንም ነው መንገዱ አላፊ ይበዘዋል። ሁሉም በተራ ይነጉዳል። ዛሬ የኔ ተራ ነው ፤ከገላገለኝ።
የለበሰው በረንባሶ ነው ፤ሚስማር አይበሳውን። ያም በተናቀ ገላ ውስጥ ያለ ጥንካሬን ይገልጣል። ፍርሃት እንደ እግር ብረት ተቆጣጠረኝ። fight or flight ን የሚያመቻቸው ዕጢዬ የት እንደገባ አላወቅኩም። ማለፍን ፈለግኩ፤ግን በምን መልኩ?
«ሲሰብር አይቻለሁ ፍቅር እንደ ጓያ!» ባሕታ አምባርቆ ዘመረ_ ስልኬ ውስጥ። ልለፍ ...ልቅር? የሚል ውዝግቤ አከተመ። የስልኬን መጥሪያ ሲሰማ ከተደበቀበት ምዝዝ አለ (እንደ እባብ )...
 «ና» (በቁጣ ጠራኝ)።
«እኔ?..እ..ማን...እሺ» (ተንተባተብኩ)
 ጩቤውን በቀኝ እጁ አንገቴን በግራ እጁ አንቆ ያዘን። የምፈራት ሞት ይችን ነው። ያ ሞቶ...ተገንዞ፣ተከፈኖ፣እየተለቀሰ፣ጉድጓድ ውስጥ የመቀበሩን ኺደት አልፈራም። ከሞትኩ ወዲያ ሥጋዬ የትስ ቢወድቅ ምናገባኝ። «ነፍሴን ለመንግሥተ-ሰማያት ሥጋዬን ለአራዊት» ብሎ የጸለየው ዘመዴ በአውሬ መበላቱ ተአምር ፈጥሮብኛል። ምናልባት ትልቋ ሞት ከሥጋ ሞት በፊት ናት። ግብግቧ፤ከጠላት ጋር ግጥሚያዋ። ያችን እፈራለሁ።
ጓደኛዬ አጀኒ _ነፍስ ኄር።ሞተ አሉኝ ደርሰው። ቅስሜ ተሰበረ ...እንክትክት ..
ከምሽቱ 2:00 አካባቢ አባቴ ደወለ። «ልጄ»አለኝ ...መቼም ግርማ ሞገሱ ይደንቃል። እረጋ ብሎ ነው የሚያወራኝ። የእሱን ዋና ሐሳብ ለማግኘት ከቅርፊት..ወደ ማዕከላዊ ...ከዛ ወደ አንኳር መሸጋገር አለብኝ።
የፈቃድ ሞት ብሎ ጀመረ።
«ክርስቶስ ለአዳም በፈቃዱ ሞተለት፤አዳነውም። አቡነ ጴጥሮስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የፈቃድ ሞት ሞተለት ፤ስሙንም ተከለ። ገዳይ አልኖራቸው ብሎ አይደለም በፈቃድ የምልህ «ለዓላማ ሲሉ ለመሞት መቁረጣቸውን» ነው። ወታደሩ ወንድምህ ጦር ሜዳ ኼዶ በፈቃድ ለአገሩ ሞተ። እነዚህን ሁሉ አስብ። ፈቃድ ማለት በእኔ አነጋገር ለሚመጣው ችግር ኃላፊነትን መውሰድ ነው። ጓደኛህ አጀኒም ይህን ሆነ። አባቱ በእጁ ነፍስ ጠፋበት። በውሽማ ተጣልቶ ተቀናቃኙን ገደለ። የሟች ወገን ደም ለመመለስ ምንሽራቸውን ወለወሉ። የአጀኒ አባት ግን ጠፋ። አጀኒ በእርቅ ደም ሊያደርቅ ቢለፋ አልሆነም። አውላላ ሜዳ ላይ ደም የሚመልሱትን ጠብቆ ከቤተሰቡ አንዱም ሲጎድል ላለማየት ግንባሩን ለጥይት ሰጣቸው ፤ገደሉት » ስልኩ ተቋረጠ።
የአጀኒን ሞት ያረዳበት መንገድ ራቀኝ። አባቴ ይኸው ነው ነገር ያረዝማል። ለአጀኒ ጥቂት እንባ አፍስሼ ዝም አልኩ።
[ ቀትር ላይ፣ጫካ ውስጥ ፣ አምስት ስድስት ሰባትን እያነበብኹ ፤ጭራሮም እየለቀምኩ ።]
ብቻዬን መኖር እወዳለሁ። ከቤተሰቦቼ ወጥቼ የሰላም አየር እየተነፈስኩ፣ የሚከለክሉኝን መጽሐፍ እያነበብኩ ቀኔን እገፋለሁ። የጋሽ ስብሐትን መጽሐፍ ይዤ ከተገኘሁ የቁጣ መአት ይጠብቀኛል። “ስድ ፣የተሰደድክ ፣ይኼን መጽሐፍ ወዲያ ጣልና የኢትዮጵያን ታሪክ አንብብ ...” ካሰኛቸው ዱላም አለበት። ታሪክ ማንበቡ ባልከፋ ግን የቱ ይነበባል? ብዬ እሞግታቸዋለሁ። ያለንበትን ዘመን ታሪክ አዋቂ የሚባሉት እንዴት እየተረዱት እንደሆነ አታዩም? 2090 ዓ.ም አካባቢ የዚች አገር ታሪክ ቢነበብ የቱ ሊታመን ? የታሪክ ጸሐፊ ብሔርተኛ ከሆነ፣ ጎጥ ካነቀው የሚፈጠረውን አስቡታ!..ለዚህም አላነብም ብዬ አምጻለሁ።
አሁን ነጻ ነኝ። «ትኩሳትን»፣ «ሌቱም አይነጋልኝ»፣ዛዚም ሆነ ሌሎችን አነባለሁ። ድሮም የተከለከለ ይጥማል። አዳምን ዕጸ-በለሷን አትብላ ብሎ ባይከለክለው ይተዋት ነበር እላለሁ ።አታድርጉ ማለት ፍቺው  አድርጉ ነው። ወይም እንድናደርግ መገፋፋት ነው። ወጣት ነና ።ከገሩ ስ ቀስ ብሎ..እሽት ...እሽት አድርጎ እንደማሽላ፣አልያስ ኖረው ቢሆን።
ጫካ ውስጥ የኼድኩት ላነብ ነው። መጽሐፌ ጋ የደረቀ ቅጠል እየወደቀበት ሳነብ ይገባኛል ።ሴተኛ አዳሪ ቤት አድሮ የጽሑፍ ሐሳብ የሚመጣለት አለ ፣ አረቄ ጠጥቶም የሚመጣለት አለ። ሁሉም በየዘርፉ አነሳሽ አለው። መጽሐፌን አጥፌ መሐል ጫካ ውስጥ እንከላወስ ጀመር። ከጥቂት እርምጃ በኋላ_ሞት።
ይኸው ሞት።
ሞት ጥላዬ ነው ይከተለኛል፣ያጅበኛል፣ይቀድመኛል። አንዴ ከፊቴ አንዴ ከጎኔ ሌላም ጊዜ ከኋላ።
ቀይ ወጣት ልጅ ነው። አንገቱን በገመድ አስገብቶ አንዱ ዛፍ ላይ ተንጠልጥሏል። በብልቱ በኩል የረጠበ ነገር አየሁ _ሸንቷል። ደነገጥኩ። ይኼ አሟሟት ሞትን ኪነት መንሳት ነው፡፡ ሞት ኪነት ነው። ወዮታ አለ ፣ሙሾ ይወርዳል ...ደስ የሚል elegy ይሰማል፤ለምን ለሞቱ ይኼን ነፈገ? በእርግጥ እኔም አይደንቀኝ...
ምክንያቱን ድንገት ከደረሱት ሰዎች ሰማሁ።
አባቱ እህቱን ደፈራት። ፍርድ ቤት አባቱን ከሰሰው። አባቱ ልጄ ነው እህቱን የደፈራት ብሎ አሳበበት። ይኼ ሟች በዚህ አዘነ፤አፈረ። ሞተ። ነገር ተከተተ። ለካ ሲያፍሩም ይሞታል...
ጫካ ውስጥ የገለጥኳት መጽሐፍ ተገልጣ ቀረች ፤ለዚህ ሟች እንባዬ ደረቀ። ሞቱን ወፍ ያረዳቸው ሰዎች ተግተልትለው መጡ። አንዷ ወጣት ሴት (ምናልባትም ፍቅረኛው) «ምነው ባለወቅኩህ» እያለች ስታለቅስ ሳቅኩ። ከሞቱ በላይ በምን ዓይነት መተዋወቅ አውቃው ይሆን? ብዬ ነው መሣቄ። ሌሎችም ሰዎች ደረት እየደቁ መጥተው አውርደው ወሰዱት። መጀመሪያ እኔ ስላገኘሁት እንደ ገዳይ አለመታየቴ ደነቀኝ። ለዚያውም የተሳሙት አረገዝን ፣ የተሰደቡት ተደበደብን በሚሉባት አገር። ከንባቤ ጎን ለጎን የለቀምኳቸውን ጭራሮዎች ታቅፌ ወደ ቤቴ ተመለስኩ። ሽሮ አገንፍዬ ልበላ፤ሞልቶ አይመርጉሹን ልደልል...
[የዕለቱ ስም የተረሳኝ ማታ ፤ዝናብ እየዘነበ ፣ በጨለማ ጉዞ ዝናብ ተጨምሮ...]
አካሌ ሳስቷል። በድንጋጤም በምንም። ረሃቡም ፋታ አይሰጥም። የማገኛት የቀን ገቢ በማነሷ የሌሊት ወፍን ግብር ገፍፊያለሁ። ዕድሜ ለበውቀቱ ስዩም«ጨለማዬን ሸጬ እንጀራዬን እየበላሁ ነው»። ምንድን ነው ሥራህ? ማለት አይቻልም።
ክው ክው እያልኩ በጋሽ ብሬ በር በኩል አለፍኩ። ጭቃዎችን ስረግጣቸው እየተፈናጠሩ ጨርቄን በከሉት (ከጅል ጋር ጠብ በሉት)። ወደ አጥሩ ጠጋ ብዬ ጭቃውን ስሸሽ ጨርቄን ቆንጥር ይይዘዋል። «አድነኝ»የሚል ነው እሚመስል አያያዙ። ኹሉንም እንደ ዓመሉ አለፍኩ፡፡ ሽሚዛውን አልወድም። ብዙ ሰዎች ያልሆነ ነገር ሲፈጽሙበት አያለሁ። እዚች ቦታ ስደርስ ወፍራም ባቴ ሲንቀጠቀጥ፣ዝንጥል ከንፈሬ ሲደንስ ይሰማኛል። ጠይም ፊቴ ዓይን ብቻ ይሆናል ፣ፀጉሬ ይቆማል...።
«ጋሽ ታፌ» እጣራለሁ። ምንም ሳይኖር...
ታፌ የዋዛ አይደለም አይወጣም። «ተይው ጋኔን ነው የሚጣራ » ሚስቱን ያባብላታል። ሰው ፍርኀቱን ይደብቅበት አያጣም መቼስ። እኔም ተስፋ ቆርጬ...የቆረጥኩትን ተስፋ ደጋግሜ ቆርጬ አልፋለሁ። ማለፍ ነው የምፈልገው!
ይቺ ቀን ግን ከፋች። ከላይ ሰማይ ያለቅሳል (ማን እንደበደበው አላውቅም)። ከታች ምድር ተጨማልቃለች (ያየሁት አይቅረኝ ማለቷ ነው)። እያዳጥኩ ተጓዝኩ። እ...ያ...ዳ...ጥ...ኩ! የለበስኩት ቅጠል መሰል ልብስ ነው። ኮምኒስት መስያለሁ ወይም የዘመኑን አረንጓዴ አሻራ፡፡ ብወድቅ አረንጓዴው ላይ ደም መሰል የቦረቦር አፈር ይታተማል (ነገሩ አይደንቅም። መቼም ቢሆን አረንጓዴና ደም ሲራራቁ አለየሁም)።
«ቁም!» (አስደንጋጭ ድምጽ )
ቆሙኩለት፣ሞትኩለት (የኔዋን ሞት)። እጄን ወደ ላይ አደረግሁ። ጥሩ ማሳጀር ነው። ኪሴን በሚገባ አሽቶ፤የጎረበጠውን አወጣ። ወገቤ አካባቢ በቡጢ ነርቶ እለፍ አለኝ ፤አለፍኩ።
«በወንድ ልጅ አምላክ» (ከጀርባዬ የመጣ ድምፅ )ዞርኩ። በጨለማው አጮልቄ ሽጉጥ የደቀኑበትን ወጣት አየሁ። ደፍ ሲል ሽጉጡ ሟቹም እኔም ማሳረጊያ ድምጽ አወጣን። አፌን ደምደም እያለው ይኼን ቀፋፊ ሞት አይቼ ቤቴ ደረስኩ። ሰዎች ኑሯቸውን ለምን ከሌሎች ሞት ላይ ይፈልጋሉ?  ከሾላ ዛፍ ብርቱካን ይለቀማል?...ዘገነነኝ።
[ ቀጣይ ቀን ፣ ዝናብ እየጣለ ፣ዛፍ ሥር ተጠልለን ]
ልዝናና በወጣሁበት ዝናብ ያዘኝ። መቼም፣ሰፈራችንን እብድና ዝናብ አያጣውም። ለሰስ አድርጎ ጀምሮ እየጠነከረ ሲኼድ ትልቅ ዛፍ ሥር ተጠለልን። አሮጌ አጠገቤ አሉ። ስለ ክስተቶች ያወራሉ።
«መብረቅ የሚወድቀው ሰይጣንን ለመምታት ነው። በዚህ ጊዜ ሰይጣን ብልሁ ወደ ሰዎች ከተጠጋ ምቱ ወደ ሰዎች ይተላለፋል። ትላልቅ ዛፍ ሥር መጠለል ክፉ መዘዝ አለው። የሰይጣን መኖሪያ በብዛት ዛፍ ነው። በዝናብ ጊዜ ወደ ዛፍ ከተጠለሉ የመመታት ዕድል ከፍተኛ ነው።»  ሟርተኛ አልኩ በልቤ። የተማርኩት ፊዚክስ ነው እንድሳደብ የገፋፋኝ። የማውቀው (ከደመና ግርጌ ያሉት ነጌቲቭ ጃርጆች (ኤሌክትሮኖች)...መሬት ለይ ባሉት ፖዘቲቭ ጃርጆች (ፕሮቶን) የመሳብ ኺደት እንደሚፈጥረው ነው። ልክ ላልሆን እችላለሁ ...ግን የእኒህ አሮጌ መሳሳት ላይ ልክ ነኝ። ሰው ነኝና በሰዎች ጉድለት ላይ ነው ሙሉነቴን የማየው። መብረቅ ጣለ። ደነገጥኩ። አጠገቤ ካሉት ውስጥ ከአሮጊቱ በቀር ገደላቸው።ይኼ አስከፊ ሞት ሆነብኝ። ተፈጥሮ ምነዋ? አልኹ። አሮጊቱም በመመታቱ መሬት ተቆፍሮ ግማሽ አካሉ ተቀበረ። ቻርጆቹ ከሰውነቱ  ወደ መሬት ሲሰርጉ ተረፈ። የሰው ልጅ አጥፊው ብዙ ነው።
[ጠባቧ ቤት ውስጥ ፣ መጽሐፍ እያነበብኩ ፣ድርቆሽ እየቆረጠምኩ...]
ቀን ቀን ከቤት የመውጣት ልምዴ ብዙም አይደል፤ሥራ ከሌለኝ በቀር። ጫካ ሳነብ እወጣ ነበር። ሞትን ሳይ ጫካን ጠላሁት። ወደ ዛፎች ስር ተጠልሎ መቀመጥን እወድ ነበር ፤እዛም ሞት አለ።ጊዜያት ሲያልፉ ቤቴ ውስጥ ማንበብ ጀመርኩ። ቆሎ እየቆረጠምኩ አነባለሁ፣ሳጣ ድርቆሼን!
አከራዬ የደመ-ወዝ ነው የምታየኝ። እሷን ሳያት ዕዳ በዕዳ የሆንኩ ያህል ስለሚሰማኝ እደበቃለሁ። ድንገት ካየሁዋት የኔዋን ሞት እሞታለሁ። 6:00 አካባቢ ኹካታ ተፈጠረ። አከራዬ ዘረጥ ዘረጥ እያለች ወጣች። ወፍራም ናት ፤ገበታ ፊት። ጸባይዋን ያደንቁታል፤እኔ ለአድናቆትም ለወቀሳም አትመቸኝም። ስሜን ደጋግማ ተጣራች፤ደጋግሜ «ወዬ» አልኳት። «ሰው ሞቷል (3×)» በዜማ። ይሙታ ..ሊሞት አይደል የተፈጠረ፤አመጽኩ። ስትርበተበት ጨነቀኝና ወጥቼ ከበራችን አካባቢ ያለውን ግርግር ተቀላቀልኩ።
የሞተ ወጣት ልጅ።በድንገት ኑሮው ቀጥ ያለችበት። ደረታቸውን ደቁ ፤ዋይ ዋይ አሉለት። አላለቀስኩም። ከአልቃሾች አንዷ ውኃ ለምኗት እምቢ ያለችው ሴት ነች። «ብሰጥህ ኖሮ ...ብሰጥህ ኖሮ» ትላለች። ሳቄ መጣ። ሞቱ ሳይሆን ምንድን ነው ልትሰጠው የነበር? የሚለው አሳሰበኝ። [የአከራዬ አባት ፣ጣእረ-ሞት ፣ገበቴ ፊቷ አከራዬ፣ተከራዩ እኔ]
የአከራዬን በር ረግጬ አላውቅም። የቤት ኪራይ ስከፍል እንኳ ተጣርቼ ወጥተውልኝ ነው። ዛሬ ተገደድኩ። አባቷን ጣእረ-ሞት እየተናነቀው ነው። ሞት ጅል ጸባይ አለው፡፡ ሰውዬው፣«አልተዘጋጀሁም ቆዩ እንጅ» ይላል በሰለለ ልሳኑ። ሰው ሊሞት ትንሽ ሲቀረው መላእክ ይሆናል፤ሁሉ ነገር ይታየዋል። የሚናገሩት ጠብ አይልም።
በጀርባው ተኝቶ፣ሁለት እግሮቹ ቀጥ ብለው፣የወደቀ መሠላል መስሏል። የአልጋውን ሸንኮር ይዘው እንባ ያፈሳሉ ቅርቦች። እሱ አበባ እነሱ አትክልተኛ ነው የሚመስሉት። በየመሐሉ «ይኼን ያህሉን ለእገሌ ፣ይኼን ያህሉን ለእገሌ» እያለ ለንስሃ አባቱ ተናዘዘ፤ሞተ።
ሰው በወግ ከሞተ ፤ነገር ተከተተ። የኑዛዜን ዋጋ ልብ አልኩ። ለኑዛዜ ፋታ የሚሰጥ አሟሟት ቆንጆ ሆኖ ተሰማኝ። ማምሻም ዕድሜ ነው እንዲል የአገሬ ሰው (ኑዛዜም ሌላ ኑሮ ነው)።ራሱን ያጠፋው፣በአደጋ የሞተው፣በመብረቅ የሞቱት...ኑዛዜ አልባ።
ገበታ ፊቷ አከራዬ ደረቷን ደቃች። «ብዙ አስለምደኸኝ...ብዙ አይቼ» እያለች አባሸች። እኔ ለቅሶ መሐል ሳቄ መጣ። ሞቱ ሳይሆን ምን አስለምዷት ይሆን ? እያልኩ አስቤ ነው መሣቄ።
ከሣቅ መልስ...
የከፈን ጨርቅ ልገዛ ከተወሰኑ ሰዎች ጋር ወደ ሱቅ ተላ’ኩ። መንገዱን ፍጥን ፍጥን አደረጉት ።በመሐል ሽንቴ መጥቶ ልሸና ወደኋላ ቀረሁ። «ወንድ ልጅ አይፈራም ይመጣል» ተባብለው ጥለውኝ እራቁ። ወንድ ልጅ፣ይፈራ ...ይንቦቀቦቅ እያልኩ ሸንቼ ጨረስኩ። ብቃና ከዓይኔ እርቀዋል። በእነሱ እደርስ ብዬ ሮጥኩ። ሽሚዛዋ ጋ ስደርስ ፀጉሬ ቆመ። ይቺ ሽሚዛ የመንገዶች ሁሉ አከፋፋይ ናት፤የስቃይም። በየትም አላጣትም። ፍርኀት ሲበዛ ብርድን ያስንቃል፤ያንቀጠቅጣልም። እንቅጥቅጥ ተጋባብኝ። ልኺድ?...ልቅር? ተመናታሁ። ሽሚዛው ውስጥ የእሳት ክፋይ አያለሁ። የተቆረጠ ሲጋራ ይሆናል። በጨለማ ላይ የብርኀን ጉልበት ነግሧል። ዓይኔን በእንጨት ቢወጉት እስካላይ ደረስኩ። ፈርቼ እንደቆምኩ በጣም መሸ። fight or flight ን የሚሰጠው ዕጢዬ አሁንም ምላሽ ነሳኝ። ሕይወትም መነሻዋ ላይ ደረሰች።
«እንዳልዋጋ ቀንድ የለኝ  
እግዜር ጎዳ አድርጎኝ »...ይሉት ቅኔ ብቻ ታወሰኝ። የፈራሁት አልቀረም የተለመደው ጥሪ ደረሰኝ...ይህኔ የእኔዋን ሞት ሞትኩ።
«ምን ፈልገህ ነው?» (አሉኝ በህብረት)
«ማለፍ» (አልኳቸው)
«እንሸኝሃ»
«ሸኙኝ»።

Read 1107 times