Saturday, 29 April 2023 18:08

የቀጥተኛ ሽያጭ ሥርዓትና ፒራሚዳዊ አሠራር ምንና ምን ናቸው?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ኢቲኬር የግማሽ ቀን አውደ ጥናት በጌትፋም ሆቴል አካሂዷል


      ኢቲኬር የውበት መጠበቂያ ምርቶች ሽያጭ ኃ.የተ.የግ.ማህበር፣ “የቀጥተኛ ሽያጭ ገበያ ሥርዓትና ህገወጥ ፒራሚዳዊ አሰራር ሥልት በኢትዮጵያ የህግ ማዕቀፍ አጠቃላይ ዕይታ” በሚል ርዕስ፣ ባለፈው ሰኞ፣የግማሽ ቀን አውደ ጥናት በጌትፋም ሆቴል አካሂዷል፡፡የአውደ ጥናቱ ዓላማ፣ በቀጥተኛ ሽያጭ ገበያ ሥርዓትና ህገወጥ ፒራሚዳዊ አሰራር ሥልት መካከል ስላሉ ጉልህ ልዩነቶች  ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው ተብሏል፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ የኢቲኬር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቲዮስ መባን ጨምሮ የኢኮኖሚና የህግ ባለሙያዎች፣ በርዕሰ ጉዳዮቹ ዙሪያ ጥናታዊ ጽሁፍና ማብራሪያ ለታዳሚዎች ሰጥተዋል፡፡
ኩባንያው ባዘጋጀውና ለግማሽ ቀን በተካሄደው በዚህ አውደ ጥናት ላይ፤ በቀጥተኛ ሽያጭ የገበያ ሥርዓትና ህገወጥ ፒራሚዳዊ አሰራር ስልት መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው፣ የቀጥተኛ ሽያጭና ፒራሚዳዊ አሰራር ሥልት በኢትዮጵያ ህግ እንዴት ይታያል፣ በገበያው የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ምንድን ናቸው፣ እንዲሁም የቀጥተኛ ሽያጭ የገበያ ሥርዓት ለሃገር የሚያበረክተው የኢኮኖሚ ጠቀሜታ--- የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ተዳስሰዋል፡፡ የኢቲኬር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቲዮስ መባ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ፣ የቀጥተኛ ሽያጭ የገበያ ሥርዓትና ፒራሚዳዊ አሰራር ስልት ያላቸውን ልዩነቶች በዓለም አቀፍ ተሞክሮ አስደግፈው ያብራሩ ሲሆን፤ የቀጥተኛ ሽያጭ የገበያ ሥርዓት ለአገር  ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን  ጥቅምና ፋይዳ  የራሳቸውን ኩባንያ በማስረጃነት በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡
የአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ት/ቤት መምህሩ  ዶ/ር ሰለሞን አባይ  በበኩላቸው፤ ሕገወጡ ፒራሚዳዊ የንግድ ስልት፣ የቁማር ዓይነት ባህርይ እንደሚታይበት ጠቁመው፤ ሙሉ ትኩረቱ ሰዎችን ምልመላና ገንዘብ መዋጮ መሰብሰብ ላይ ነው፤ብለዋል።
“በፒራሚዱ ሰንሰለትም ወደ ታች እየተዘረጋ ሲመጣ የላይኛዎቹ እየተደበቁ ይኼዳሉ ያሉት ዶ/ርሰለሞን፤ዚህም ምክንያት አንድ ችግር ቢፈጠር ኃላፊነትን የሚወስድ ተጠያቂ አይኖርም፡፡፡” ብለዋል፡፡
በግንዛቤ ማስጨበጪያ አውደ ጥናቱ ላይ እንደተገለጸው፤የቀጥተኛ ሽያጭ ሥርዓትን የሚከተሉ ድርጅቶች፣ የሚታወቅና በህግ የተመዘገበ አድራሻና የንግድ ፈቃድ ያላቸው ሲሆኑ፤ ለመንግሥትም ተገቢውን ግብር ይከፍላሉ፤ ፒራሚዳዊ አሰራርን የሚከተሉቱ ግን  አድራሻቸው የማይታወቅና ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸው በመሆኑ ለመንግሥት ግብር የማይከፍሉና በአየር ላይ የሚንሳፈፉ  ናቸው ተብሏል፡፡የሕግ ባለሙያው አቶ አብዱልራዛቅ ነስሮ፣ በኢትዮጵያ የንግድ ውድድርና እና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ፤ የቀጥተኛ ሽያጭና የገበያ ሥርዓትን በተመለከተ የጠቀሰው ነገር እንደሌለ ጠቁመው፣ በአንጻሩ  ግልፅና የተብራራ ባይሆንም፣ የፒራሚዳዊ አሰራር መጠቀሱን አንስተዋል፡፡ የፒራሚዳዊ አሰራር ግልፅ ሆኖ ቢቀመጥ፣ ከቀጥታ ሽያጭ የንግድ አሰራር ጋር  ያለውን ብዥታ ለማጥራት እንደሚጠቅም ተመልክቷል፡፡ኩባንያው በአውደ ጥናቱ ላይ ያሰራጨው አጭር የቅኝት ጽሁፍ፤”የቀጥተኛ ሽያጭ የገበያ ሥርዓት የሚከተሉ ድርጅቶች፣ ጥራት ያላቸውን  ምርቶች ለገበያ የሚያቀርቡ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለው ልምምድ፣ እነዚህ ድርጅቶች የሰዎችን የአኗኗር ዘይቤና ፍላጎቶች ለማሟላት ለፈጠራ ሥራና ለምርምር ከፍተኛ ገንዘብ ይመድባሉ፡፡
በአንጻሩ በፒራሚድ ሥልት የተሰማሩት ደግሞ ምንም ዓይነት ምርት የሌላቸው ወይም ቢኖራቸውም ለይስሙላና የገበያ ዋጋ የሌለው ሲሆን ፤ ዋነኛ ዓላማቸው ከሰዎች የገንዘብ መዋጮን መሰብሰብ ነው፡፡” ይላል፡፡ የቅኝት ጽሁፉ አክሎም፤”የቀጥተኛ ሽያጭ ሥርዓት በአቋራጭና በፍጥነት በአንዴ ሃብት የሚሰበሰብበት ሳይሆን፤ በዚህ የገበያ ሥርዓት ውስጥ ጠንክሮ በመሥራት፣ ብዙ ደንበኞችን በማፍራትና ብዙ ሽያጭ በማስመዝገብ የኮሚሽን ክፍያ የሚገኝበት ነው:: የፒራሚዳዊ አሰራር በአንጻሩ፣ በአንድ ጊዜ የሚከበርበት እንደሆነና ሃብት ለማፍራት ብዙ የገንዘብ መዋጮ የሚያደርጉ ሰዎችን መመልመል የሚያስፈልግበት ነው፡፡፡” ሲል ያብራራል፡፡ኢቲኬር፤ በውበት መጠበቂያ ምርቶች ሽያጭ ላይ የተሰማራ ኩባንያ ሲሆን፤ ለ100 ያህል ቋሚ ሠራተኞች  የሥራ ዕድል የፈጠረና ባለፉት 10 ወራት ለመንግሥት 10 ሚሊዮን ብር  ግብር የከፈለ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ኩባንያው በተጨማሪም፣ ባለፉት አሥር ወራት ወደ 1 ሺህ ለሚደርሱ የምርት አስተዋዋቂዎች 50  ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ክፍያ መክፈሉንና እኒህ የምርት አስተዋዋቂዎች  ፈቃድ አውጥተው ለመንግሥት ግብር እንዲከፍሉ ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡   


Read 1408 times