Saturday, 29 April 2023 18:16

ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 • ከፍተኛ የጨው አጠቃቀም ለደም ግፊት በማጋለጥ፣ የልብና ደም ቧንቧ እንዲሁም ስትሮክ አደጋን ይጨምራል
     • በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሞት ምጣኔ 43 በመቶ ደርሷል
     • እ.ኤ.አ በ2017 ከ2.8 ሚ. በላይ ሰዎች በልብና ደም ቧንቧ በሽታ ተጠቅተዋል


      ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች፣ ሥር የሰደዱ በሽታዎች በመባል የሚታወቁ ሲሆን፤ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው የማይተላለፉና ለረዥም ጊዜ የሚቆዩ የጀነቲክ፣ የፊዚዮሎጂ፣ የአካባቢና የባህርይ ሁኔታ ውጤቶች ናቸው፡፡ እነዚህም የልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች፣ የልብ ድካምና ስትሮክ፣ ካንሠር፣ ሥር የሰደዱ የመተንፈሻ አካላት ህመሞች፣ ሥር የሰደደ የሳምባ ምችና አስም እንዲሁም የስኳር በሽታዎች ናቸው፡፡
ለእነዚህ በሽታዎች ዋና ዋና አጋላጮች ከሚባሉት መካከል ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ ትምባሆ ማጨስ፣ ጎጂ የአልኮል አጠቃቀም፣ ጫት መቃምና  የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግ ይጠቀሳሉ፡፡
“ጤና፣ ልማት እና ጸረ- ወባ ማህበር” ባሰራጨው ጥናታዊ መረጃ መሠረት፤ ጤናማ ያልሆኑ ምግቦች የሚባሉት የስኳር፣ የጨውና በመደበኛ የቤት ውስጥ ሙቀት የሚረጋ ዘይትና የአትክልቅ ቅቤ (Transfat and Saturatedfat) መጠናቸው የበዛባቸው ፈጣንና በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችና መጠጦች ሲሆኑ፤ እነዚህን አብዝቶ መመገብ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎችና ለሌሎች የጤና እክሎች እንደሚያጋልጥ ተረጋግጧል፡፡
የከተሞች መስፋፋትና የአኗኗር ዘይቤ መለወጥ የአመጋገብ ሥርዓትን እየቀየሩና ከዚህ ጋር ተያይዞ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦች አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን የጠቆመው ጥናታዊ መረጃው፤ ሰዎች እነዚህን የረጋ ስብ (Transfat and Saturatedfat)፤ የስኳርና የጨው ይዘት ያላቸው ምግቦችና መጠጦች አዘወትረው በመመገብ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች እንደሚጋለጡ አመልክቷል፡፡
በጤናማ አመጋገብ ላይ የማህበረሰቡ  የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎች ባለመሰራታቸው፣ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት በርካታ ዜጎች ለህመምና ለሞት እየተዳረጉ ነው ያለው “ጤና፣ ልማት እና ጸረ- ወባ ማህበር”፤ የመገናኛ ብዙኃንና የማህበራዊ ሚዲያ ጋዜጠኞች ይህን ክፈተት በመሙላት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ በዛሬው ዕለት በርዕሰ ጉዳዩ ዙሪያ  የግማሽ ቀን የአቅም ግንባታ ሥልጠና በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ሰጥቷል፡፡   
በርካታ የሚዲያ ባለሙያዎች በተሳተፉበት በዛሬው ዎርክሾፕ ላይ፤ ከጤና ሚኒስቴር እንዲሁም ከኢትዮጵያ ምግብ እና መድሃኒት ባለሥልጣን የመጡ ባለሙያዎች ጥናታዊ ጽሁፍና ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡  
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከፍተኛ ኤክስፐርት የሆኑት ዶ/ር ሙሴ ገ/ሚካኤል፣ “ጤናማ ያልሆኑ አመጋገቦች በጤና ላይ የሚፈጥሩት አሉታዊ ተጽዕኖና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚያሳድሩት ኢኮኖሚያዊ ጫና” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት፤ ጤናማ ያልሆኑ አመጋገቦች ለስኳር በሽታ፣ ለካንሰርና ስትሮክ እንደሚዳርጉ አስረድተዋል፡፡ በቂ አትክልትና ፍራፍሬ አለመመገብ ለልብ ህመምና ለካንሰር የመጠቃት ዕድልን ይጨምራልም ብለዋል፡፡ በየሁለት ሰከንዱ አንድ ሰው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች አማካኝነት ያለዕድሜው እንደሚሞትም ነው የጠቆሙት፡፡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በኢትዮጵያ ጤና እና ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ስጋት መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን ያለጊዜ ሞትና ህመም እንዲከሰት በማድረግ፣ የሃገሪቱን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማዘግየት ትልቅ ጫና ማሳደራቸው ተመልክቷል፡፡ እ.ኤ.አ በ2017 ዓ.ም፣ 313 ቢሊዮን ብር  (ቀጥተኛና ቀጥተኛ ባልሆነ ወጪ) የኢኮኖሚ ኪሳራ መድረሱ ታውቋል፡፡ በልብና የደም ቧንቧ በሽታ 1.97 ቢ. ብር፣ በካንሰር 0.98 ቢ. ብር፣ በስኳር በሽታ 0.58 ቢ.ብር እንዲሁም ሥር በሰደዱ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች 0.85 ቢ.ብር እና በሥራ ላይ አቅም መቀነስና ሞት 26.9 ሚ. ብር ኪሳራ ደርሷል  ተብሏል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት፣ አገራት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመቆጣጠር እንዲያስችላቸው “ቤስት ባይ” በሚል ካስቀመጣቸው የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦች መካከል፡- ጤናማ ያልሆኑ ምግቦችን ለመቆጣጠር የሚያስችል አስገዳጅ ህግ ማውጣት አንዱ ሲሆን፤ ይህም በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምርቶች የፊት ለፊት ማሸጊያዎች ላይ የሚቀመጡ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች እንዲኖር ማስገደድ፤ የገበያ ቁጥጥር ማድረግ፣ የማስታወቂያ ገደብና ከፍተኛ ታክስ መጣል በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
ከፍተኛ የጨው፣ ስኳርና ስብ መጠን ያላቸው የታሸጉ ምግቦች ላይ የሚቀመጥ የፊት ለፊት የማስጠንቀቂያ ምልክት ከሚጠቀሙ አገራት መካከል ቺሊ፣ አርጀንቲና፣ ብራዚልና ሜክሲኮ የሚገኙበት ሲሆን፤ ይህም መደረጉ ጤናማ ያልሆኑ ምግቦች ግዢ እንዲቀንስና ሸማቾች ጤናማ ምግቦችን መለየት እንዲችሉ አድርጓቸዋል ተብሏል፡፡
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሥርጭት መጠን በኢትዮጵያ  
•  በ2016 በተደረገ ጥናት፣ አንድ ኢትዮጵያዊ  ዋና ዋና በሚባሉት ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ያለዕድሜው ወይም ከ70 ዓመት በፊት የመሞት ዕድሉ 18.3 በመቶ ነው፡፡
•  እ.ኤ.አ በ2018 የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው፤ በኢትዮጵያ በልብና ደም ቧንቧ በሽታ፣ የሟች ቁጥር 47ሺ712 ደርሷል፡፡
•  እንደ “ግሎባል በርደን ኦፍ ዲዚስስ” ጥናት፤ ስትሮክ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ፣ 44 በመቶ ለልብና የደም ቧንቧ በሽታ ያጋልጣል፡፡
•  እ.ኤ.አ በ2019 ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የተከሰተው ሞት 34.2 በመቶ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 14 በመቶ በልብና የደም ቧንቧ፣ 12 በመቶ ሥር በሰደዱ የመተንፈሻ አካላት፣ 4 በመቶ ደግሞ በስኳርና ኩላሊት በሽታዎች ነው፡፡
(ምንጭ፡- “ጤና፣ ልማት እና ጸረ- ወባ ማህበር”)


Read 1334 times