Saturday, 29 April 2023 18:18

ከቀዶ ህክምና በፊት ብልትን ማጽዳት….

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

 የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር 31ኛውን አመታዊ ጉባኤ ባካሄደበት ወቅት ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የህክምና ባለሙያዎች የተለያዩ የምርምር ውጤቶችን አቅ ርበው ነበር፡፡ የምርምር ውጤቶቹም የእናቶችንና ጨቅላ ህጻናቱን ሁኔታ የፈተሹበት መን ገድ ነበር፡፡ ከቀረቡት ጥናቶችም መካከል ሴቶች በቀዶ ሕክምና ሲወልዱ አስቀድሞ ብልታ ቸውን ማጽዳት አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳየው Surgical Site Infection (SSI) በዶ/ር ዳዊት ይፍሩ የቀረበ ጥናት ነበር፡፡ ዶ/ር ዳዊት ከጃፓይጎ ኢትዮጵያ የፕሮጀክቱ ዳይሬክተር አስተባባሪ ናቸው፡፡
ዶ/ር ዳዊት ያቀረቡት የ Surgical Site Infection (SSI) ጥናት ከ2019 ጀምሮ ጃፓይጎ ኢትዮጵያ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የህሙማን ደህንነትን በማረጋገጥ ዙሪያ በተለይም የቀዶ ህክምናን ተከትሎ በህሙማን ደህንነት ላይ ሲሰራው የቆየው ፕሮጀክት አለ፡፡ ይህ ፕሮጀክት በየጤና ተቋማቱ እንዲተ ዋወቅ ተደርጎ በ23 የጤና ተቋማት ላይ እንዲሰራ ተወስኖ ተተግብሮአል፡፡ በእነዚህ ተቋ ማት ላይ የሚሰራውንና ጃፓይጎም ያለውን ልምድ ይዞ ደህንነቱ የተጠበቀ የቀዶ ሕክምና በምን መንገድ ይካሄዳል የሚለውን ለስልጠና በሚመች መንገድ ተዘጋጅቶ ተሰጥቶአል፡፡ ከእነዚህ የስልጠና ዝግጅቶች መካከል አንዱ የቀዶ ህክምናን ተከትሎ የሚመጡ ኢንፌክሽ ኖችን መከላከል ወይም መቀነስ የሚል አላማ ያለው ነው፡፡ ይህንን ኢንፌክሽን ወይንም መመረዝን ለመከላከል ከሚረዱ መንገዶች አንዱ ከቀዶ ህክምና በፊት (Vaginal preparation) ብልትን ማዘጋጀት ወይንም ማጽዳት የሚለው ነው፡፡  
በአለም የጤና ድርጅት WHO መጀመሪያ እንደውጭው አቆጣጠር በ2015፤በቅርቡ ደግሞ በ2021 መደረግ ያለባቸውን ነገሮች በሚመለከት ምክክር ወይንም መመ ሪያ አውጥቶአል፡፡ የአለም የጤና ድርጅት በ2021 እንዲተገበር ያወጣው መመሪያ በብዙ ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ ተግባራዊ መደረግ አልተጀመረም ነበር፡፡ ይህንን ምክረ ሀሳብ ጃፓይጎ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ጥናት ተደርጎ በተገኘ ውጤት የብልት ማጽዳት በቀዶ ሕክምና ለሚወልዱ እናቶች ምን ያል አስፈላጊ እንደሆነ በተመረጡት 23 የጤና ተቋማት ላይ የማስተዋወቅና የማስጀመር ፕሮጀክት እንዲዘረጋ ተደርጎአል፡፡ ይህ ጥናት የዳሰሳ ጥናት ሳይሆን በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ ቀስ በቀስ ስራዎቹ እየታዩ ምን ለውጥ እንዳመጣ እየተ ፈተሸ የጤና ተቋማቱ እየተከታተሉት ነው ወይ? የሚለው እየታየ የተሰራ ሲሆን ፕሮጀ ክቱም የጥራት ማሻሻያ ፕሮጀክት ነው፡፡ በቀዶ ሕክምና ማዋለድ ዞሮ ዞሮ አካልን በመክፈት ልጅ እንዲወለድ ማድረግ ቢሆንም ይህ ከመካሄዱ በፊት ብልትን ማጽዳት ኢንፌክሽንን ለመከላከል አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያት ምንድነው? ለሚለው ጥያቄ ዶ/ር ዳዊት የሚከተለውን መልስ ነበር የሰጡት፡፡
በቀዶ ህክምና ልጅን ከማዋለድ በፊት የሴትየዋን ብልት ማጽዳትና ማዘጋጀት ይገባል ሲባል vaginal preparation የሚለውን አሰራር የሚገልጽ ወላድዋን ሴትም በዚህ ምክንያት ሊፈ ጠር ከሚችል ኢንፌክሽን ወይንም መመረዝ ለመከላከል የሚያስችል በአለም አቀፍ ደረጃ እንዲተኮርበት የሚፈለግ አሰራር ነው፡፡ ይህ ለምን አስፈለገ ሲባል በሳይንሳዊ አጠራራቸው የተለያዩ የብልት አካባቢ ፈሳሾች ወይንም በብልት ውስጥ የሚገኙ በመጸዳዳት የሚወገዱ ነገሮች የሚኖሩ ሲሆን ልጅን ለማዋለድ የሚደረገው የቀዶ ሕክምና ደግሞ ብዙም እርቀት የሌለውን ማህጸን በመክፈት የሚተገበር ነው፡፡ ስለዚህም በንክኪ ወደቁስሉ የሚገቡ ባእድ ነገርች እንዳይኖሩ እና ቁስሉም እስኪድን ድረስ የሚራቡ የኢንፌክሽን ቁስለቶችን ለመከላከል እንዲቻል አስቀድሞውኑ ብልትን ማጽዳት ተገቢ ይሆናል፡፡ ስለዚህም ጸረ ተሀዋስያንን በመ ጠቀም ከሰላሳ ሴኮንድ እስከ አንድ ደቂቃ በሚሆን ጊዜ ማጽዳት ከማዋለድ ስራው በፊት የሚጠበቅ ይሆናል፡፡ ይህ ብልትን የማጽዳት ስራ የሚከናወነው እናትየው ለመውለድ ወደ ኦፕራሲዮን ክፍል በምትገባበት ጊዜ በቀዶ ህክምና ለማዋለድ ዝግጁ በምትሆንበት ጊዜ መሆን አለበት፡፡
የአለም የጤና ድርጅት በዚህ ጉዳይ የሁሉንም ትኩረት የጠየቀበትና የብልት ማጽዳት ስራ መኖር አለበት ሲል ምክረ ሀሳብ ያቀረበው ከተለያዩ ሀገራት የተሰሩ ጥናቶችን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ በዚህም መሰረት የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ከቀዶ ህክምና በፊት የብልት ማጽዳት ስራ መከናወን በመጀመሩ ከ38-59% ያህል ቁስለትንና ኢንፌክሽንን መከላከል አስችሎአል፡፡ ይህንን ያሳወቀው የአለም የጤና ድርጅት ሲሆን ይህ በኢሶግ 31ኛ አመታዊ ጉባኤ ላይ የቀረበው የጃፓይጎ ጥናትም መሰረቱ ይህ ከላይ የተገለጸው የአለም የጤና ድርጅት ጥናት ውጤት ነው ብለዋል ዶ/ር ዳዊት፡፡
ሁኔታውን ከኢትዮጵያ አንጻር የተመለከቱት ዶ/ር ዳዊት በኢትዮጵያም ለስራው ከተመረጡ 23/ የጤና ተቋማት በተገኘው መረጃ መሰረት ኢንፌክሽኑ በጣም መቀነሱ ተስተውሎአል፡፡ በዚህ ጥናት ላይ የተካተቱት በጃፓይጎ ፕሮጀክት የተያዙት 23 የጤና ተቋማት ናቸው፡፡ እነሱም በቀዶ ህክምና የሚያዋልዱ ጤና ጣቢያዎች ሆስፒታሎች ሲሆኑ ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ፈለገ መለስ እና ኮልፌ ከሚባሉ ጤና ጣቢያዎች ጋር ፤ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከዘውዲቱ ሆስፒታልና ቸርችል ጤና ጣቢያ ጋር፤ጋንዲ ሆስፒታል ከሰ በታና ከመሹዋለኪያ ጤና ጣብያ ጋር፤ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ከገላንና ቸርኪ ጤና ጣቢያ ጋር በአዲስ አበባ በፕሮጀክቱ የታቀፉት ናቸው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ሆስፒታልና ሰካ ጨቆርሳ ጤና ጣብያ፤አዳማ ሆስፒታልና ቢሾፍቱ ጄኔራል ሆስፒታል እና ወለንጪቲ ትሬይነር ሆስፒታል በፕሮጀክቱ የተካተቱት ናቸው፡፡ በአማራ ክልልም በጥበበ ግዮን ሆስፒ ታል ስር አዲት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ቪዥን ማተርኒቲ ሴንተር፤በፈለገ ህይወት ክላስተር ስር ደግሞ አዲስ አለምና ምግባሩ ከበደ ሆስፒታሎች የፕሮጀክቱ አካል ናቸው፡፡ በፕሮጀክቱ የታቀፉት 23 የጤና ተቋማት የተጠቀሱት ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ ስድስቱ ስፔሻላይዝድ ሆስፒሎች ሲሆኑ አራቱ ደግሞ ጄኔራል ሆስፒታሎች ናቸው፡፡ የተቀሩት ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልና ጤና ጣቢያዎች ናቸው፡፡
ይህ የብልት ጽዳት ወይንም ከቀዶ ህክምና በፊት ዝግጅት መደረግ የሚለውን ሀሳብ ከዚህ ፕሮጀክት በፊት የትኛውም የጤና ተቋም ውስጥ አይፈጸምም ነበር ብለዋል ዶ/ር ዳዊት፡፡
ስለዚህ የፕሮጀክቱ አላማ ይህንን በጎ ተግባር ማስጀመር ነው፡፡ የዚህ ተግባር አላማም በቀዶ ሕክምና መውለድን ተከትሎ የሚመጣ ኢንፌክሽንን ለመቀነስ ነው፡፡
ይህ ጥናት አላማው የአለም የጤና ድርጅት ባወጣው ሀሳብ መሰረት ለቀዶ ህክምና የሚዘ ጋጁ ሴቶች አስቀድሞ ብልታቸው መጽዳቱ ሊከሰት የሚችለውን ቁስለት ወይንም መመረዝ ሊያስወግድ ይችላል የሚለውን መሰረተ ሀሳብ መነሻ በማድረግ የተተገበረው አገልግሎት ምን ውጤት አስገኝቶአል? የሚለውን ለማሳየትና አሰራሩም ወደፊት በተጠናከረ መንገድ በሁሉም የጤና ተቋማት እንዲተገበር የሚያስችል መንገድን ለመጠቆም ነው፡፡
በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ እንደ ጥራት ማሻሻያ አሰራር በጤና ጣቢያዎችና መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ምንም ችግር ያልገጠመ ሲሆን በከፍተኛ ወይንም ሪፈራል ሆስፒታሎች ግን አተገባበር ላይ በመጠኑም ቢሆን ችግር እንደገጠመ አይካድም፡፡ ስለዚህም በተለያዩ ስልጠናዎች እንዲሁም ለንባብ የሚሆኑ ጽሁፎችን በማቅረብ በመሳሰሉት አቀራረቦች ወደ ድርጊቱ እንዲገቡ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ተችሎአል፡፡ ስለዚህም የፕሮጀክቱ አላማ
ድርጊቱን ማስጀመር ፤
ኢንፌክሽንን መቀነስ ነው፡፡
ዶ/ር ዳዊት ከጄፓይጎ እንደገለጹት የፕሮጀክቱ አላማ ድርጊቱን ማስጀመርና ኢንፌክሽኑን መቀነስ እንደመሆኑ በተለይም በጤና ጣቢያዎችና በመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ከነበረው 0% ወደ 80-85 % ያህል ከቀዶ ሕክምና በፊት የብልት ማጽዳት ስራ ትግበራው እየተካሄደ መሆኑንና የኢንፌክሽን መጠኑም ቀድሞ ከነበረበት እንደቀነሰ ለማየት ተችሎ አል፡፡ ሪፈራል ሆስፒታችም ጭርሱንም ያልነበረውን ተግባር ወደ 30 % ያህል እንዲ ደርስ ለማድረግ ፕሮ ጀክቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጎአል፡፡ ስለዚህም በአጠቃላይ ጤናጣብ ያዎች፤መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች፤መካከለኛ ደረጃ ሆስፒታሎች፤ሪፈራል ሆስፒታሎች ያለውን ከቀዶ ህክምና በፊት ብልትን የማጽዳት እና የማዘጋጀት ተግባር ስንመለከት ከነ በረው 0% ወደ 67 % ለማድረስ ተችሎአል፡፡
በቀዶ ህክምና በመውለድ ጊዜ ኢንፌክሽን የሚያጋጥማቸው ሴቶች ምን ያህል እንደሚሆኑ ቀድሞ በተደረገ ጥናት የተገኘው ውጤት የሚያሳየው ወደ 5.1% የሚሆኑ እናቶች ከቀዶ ህክምናው በሁዋላ ኢንፌክሽን ይኖራቸዋል የሚል ነበር፡፡ ይህ በቀዶ ህክምና የምትወልድ ሴት ብልት አስቀድሞ መጽዳትና መዘጋጀት አለበት የሚለው ፕሮጀክት ስራ ላይ ከዋለ በሁዋላ ያለው ሁኔታ ሲታይ ወደ 46-47 % ያህል ኢንፌክሽን ቀንሶአል እንደ ዶ/ር ዳዊት ማብራሪያ፡፡  Read 413 times