Saturday, 29 April 2023 18:19

‹‹ኩሉ አመክሩ ወዘሰናየ አጽንዑ››- ሁሉንም ሞክሩ የተሻለውን ያዙ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

  ‹‹ሁሉንም ሞክሩ፤የተሻለውን ያዙ›› የሚለውን አባባል፣ ቢያንስ እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ (የዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ) ገብቶ የተማረ ተማሪ ያውቀዋል፡፡ በየድግሪው ላይ የተፃፈ መሪ ቃል እና ጥቅስ ነው፡፡ በህይወታችን ውስጥ በርካታ ውጣ ውረዶች ይገጥሙናል፤ እና በየፈርጅ በየፈርጃቸው እየሞከርን፣ እየወደቅን እየተነሳን፤ በጎና ሰናይ የሆኑትን እየለየን እና እያጠናከርን፤ የሚበጀንን መያዝ አለብን፤ ለማለት ነው፡፡ በእርግጥም በየአንዳንዱ ሙከራ ወቅት፤ እንቅፋት፣ ችግርና መከራ መኖሩ አይቀሬ ነው ለማለት ነው፡፡ ለዚህ አብነት ይሆነን ዘንድ የሚከተለውን የአበው ወግ እንይ፡፡
ሁለት ደገኛ ገበሬዎች ኑሮ አልገፋ ብሎ ቁም ስቅላቸውን ያሳያቸዋል፡፡ አንዴ ዝናቡ እንቢ ይላል፡፡ አንዴ በሬዎቹ ይለግማሉ፡፡ አንዴ ደቦ ወጪዎች አይመቻቸውም፡፡ አንዴ ደግሞ ሰብሉን ተባይ ይፈጀዋል፡፡ በእጅጉ ይቸገራሉ፡፡ አዝመራውም አልሰምር ይላል፡፡
አንደኛው ገበሬ አንድ ቀን መላ ዘየደ፡፡ ንግድ መጀመር አለብኝ ብሎ ወሰነና፣ አዲስ ሙከራ ጀመረ፡፡ በሬዎቹን ሁሉ ሸጠ፡፡ የዘር እህሉንም ከሰቀለበት አውርዶ፣ ለቤት የሚፈልገውን ያህል አስቀረና አውጥቶ ሸጠ፡፡ ከዚያም ባገኘው ገንዘብ ወደ ቆላ ወርዶ ለማረሻ ለዶማና ለማጭድ ወዘተ--መስሪያ የሚሆን ብረታ ብረት ገዛ፡፡ የገዛውንም ብረታ ብረት ወስዶ ለቸገረው ደገኛ ህዝብ ቸበቸበው፡፡ ቀስ በቀስ ኑሮው ተለወጠ፡፡ አዱኛም አገኘ፡፡ ለውጡ በቀዬውም በአገሩም ተወራ፤ ተሰማ፡፡ ሃብቱ ጣራ ነካ፡፡ ይጭነው አጋስስ ይለጉመው ፈረስ በደጅ በግቢው ሞላለት፡፡
‹‹አያ፤ እንዲህ በአንዴ ዲታ የሆንከው ምን ዘዴ ከውነህ ነው ጃል?›› ብሎ ይጠይቀዋል፡፡
ያም የድሮ ገበሬ፣ የዛሬ ነጋዴ፤ የተሰማራበትን ሙያ ያስረዳዋል፡፡ ወደህ ስራ ቢገባም በቀላሉ ካብታም እንደሚሆን ይገልፅለታል፡፡
ሁለተኛው ገበሬ፤ ሳይውል ሳያድር ምክሩን ተቀብሎ፣ በስራ ላይ አዋለና፣ ያለ የሌለ ንብረቱን ወደ ገንዘብ ለወጠ፡፡ ንግድ ጀመረ፡፡
ቆላ ወረደ፡፡ ያገሩን ብረታ ብረት ገዛ፡፡ ተሸከመና ሽቅብ ወደ ደጋ መንገድ ጀመረ፡፡ ሆኖም፤ ገና ዳገቱን አጋምሶ ሳያበቃ በተሸከመው ብረታ ብረት ክብደት ሳቢያ ወገቡም ጉልበቱም ከዳውና ተዝለፍልፎ ወደቀ፡፡ አወዳደቁም አጉል ነበረና አረፋ አስደፈቀው ፡፡
አንድ መንገደኛ የሰፈር ሰው ድንገት ሲያልፍ አይቶት ኖሮ ወደሱ ቀርቦ፤
‹‹አያ እገሌ፤ምን ሆነህ ነው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
ገበሬውም፤ ‹‹አይ ወዳጄ፤ ያ ጎረቤቴ አያ እገሌ የሰራኝን ስራ ለጠላት አይስጥ!›› አለና መለሰለት፡፡
‹‹ምን አደረገህ? የልብ ወዳጁ እማይደለህ እንዴ? በሞቴ ንገረኝ፤ ምን አደረገህ?››
‹‹ትርፉን ነግሮ መከራውን ሳነግረኝ፤ ይሄው ለዚህ ዳረገኝ!!›› አለው፡፡
***
ሁሉም ስራ ችግሩ የሚታወቀው ሲሞከር ብቻ ነው፡፡ ንግዱ፣ትምህርቱ፣ ልማቱ፣አስተዳደሩ፣ ፓርላማዊ ስነስርዓቱ፣ ምርጫው፣ ፍትሃዊ ባህሉ ወዘተ ሁሉም ተሞክሮ፣ ተሰርቶ ታይቶ ነው፡፡ ካላዋጣ ደግሞ ካፈርኩ አይመልሰኝ ሳይሉ፣ የማይሰራውን ፈጥኖ ጥሎ ሌላ መንገድ መፈለግ ግድ ነው፡፡ ስህተትንም በወቅቱ አርሞ፣ ሰናዩን አለምልሞ፣ ጠንካራውን አጎልብቶ፣ መያዝ ደግ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ከአምናው ምን ተምረናል? ለነገስ ምን ጨብጠናል? የማለት ድፍረትና ግልፅነት እንዲኖረን ያሻል፡፡
አዲስ ፈር ለመቅደድ መስዋዕትን መክፈል፣ ያልተሞከረውን መሞከር ያልታየውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ትላንት በሄድንበት መንገድ ዛሬም ብንመላለስበት ኮቴአችንን ከመጨረስ በቀር፣ ወደላቀ ግብ መድረስ እርም ነው፡፡ ትላንት በተሟገትንበት፣ በተዛለፍንበት፣ ላንደማመጥ በተጯጯህንበት ሸንጎ፣ ዛሬም ያንኑ እሪታና ጩኸት፣ ያንኑ ችኮላና ድንፋታ፣ ያንኑ እርግማንና ውግዘት ብናላዝን ብናስተጋባበት፤ ድምፃችን ከመዛሉ፤ ጉዟችን ከመሰናከሉ በቀር ብዙ አንራመድም፡፡ ከመበቃቀል መተራረም፣ ቂም ከማርገዝ የቂምን ሥነ-ነገር መርምሮ ለመንቀል መጣጣር ዋና ጉዳይ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡
ከቶውንም ትላንት እጅግ ጨለማ የመሰለንን ንፍቀ ክበብ፣ ዛሬ በመጠኑ እንኳን ደብዛዛ ውጋጋን ካየንበት ውጋጋኑን ለማስፋት እንጂ ‹‹ይሄውላችሁ፣ ዛሬም በደምብ አላነጉትም!›› እያልን ቡራ-ከረዩ ብንል አንድም የለውጥን አዝጋሚ ሂደት መካድ፣ አንድም ያ ውጋጋን ብሩህ ፀዳል እንዳያገኝ የእኛን አስተዋፅዖ መንፈግ ይሆናል፡፡ ባለፈው፣ ባልሞከርነው ነገር ሳቢያ ባጠፋነው ጊዜ ስንፀፀት አዲስ ሙከራ የምናደርግበትን ሌላ ውድ ጊዜአችንን እንዳናጨልም መጠንቀቅ ይበጃል፡፡ ሀገራችን አሁን ላለችበት ቦታ የበቃችውኮ በደጉም በክፉውም ሂደት ሳቢያ ነው፡፡ ማህበረሰባችንም እንደዚያው፡፡ ክፉውን አስወግዶ አንድ እርምጃ ለመራመድ ግን አዲስ ሙከራ እንደሚስፈልግ በመገንዘብ መንቀሳቀስ ይጠይቃል፡፡ የሌሎችን ድምፅ በትዕግስት መስማት፣ መንገዳቸውን በጥሞና ማየት፣ እኛ ያደረግንላቸውን ያህል እነሱም ያደርጉ ዘንድ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፡፡ ለዚህ ደግሞ ትርፉን ብቻ አውቀን መከራውን ሳናውቅ ከተጓዝን ህልማችን ሁሉ ከላይ እንደተጠቀሰው ገበሬ ጉልበት አጥቶ ይወድቃል፡፡ የራእያችንም ክንፉ ከወዲሁ ይሰባበራል፡፡ ተስፋችን ሳይጫር ይከስማል፡፡ በዚህ መንገድ የሄዱ ቄሱም፣ ሼኪውም፣ ሹሙም ዜጋውም፣ የፖለቲካ ቡድኖቹም፣ መንግስታዊ የሆኑና ያልሆኑ ድርጅቶቹም አበክረው ማስተዋል ያለባቸው ቁምነገር ይሄ ይመስለናል፡፡
‹‹ያለፈ ጥረታችንን ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ፣ ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው እሚቆጨኝ››
ለማለት መቻል አለብን፤ እንደ ‹‹ቴዎድሮስ››፡፡ ያልሞከርነውን ለመሞከር ዝግጁነት ወሳኝ ነው!! የመንፈስም የአካልም፡፡
ከዚያ በኋላ፤ ‹‹ሁሉንም ሞክሩ፣ የተሻለውን ያዙ››! ለመባባል እንችላለን፡፡



Read 1790 times