Saturday, 29 April 2023 18:22

የሁለቱ የጦር አበጋዞች ፍልሚያ ካርቱምን የምድር ሲኦል አድርጓታል

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(3 votes)

 ኢትዮጵያውያን ከሱዳንም ጦርነት ብዙ የምንማረው አለ “በዓለማቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ የሰብዓዊነት ፅንሰ ሃሳብን ጠፍቷል” ሱዳናውያን
             ኤሊያስ


      ባለፈው ሚያዝያ 7 ቀን 2015 ዓ.ም የተቀሰቀሰውና ላለፉት 14 ቀናት ተጠናክሮ የዘለቀው የሱዳኑ ውጊያ ሰሞኑን በአሜሪካ አሸማጋይነት በተደረሰው የ72 ሰዓታት የተኩስ አቁም ስምምነት ሳቢያ፣ በአንዳንድ ቦታዎች የተቀዛቀዘ መስሎ ቢታይም፣ የስምምነቱ የጊዜ ገደብ ማብቃትን ተከትሎ፣ ጦርነቱ ዳግም ተፋፍሞ መቀጠሉ ተነግሯል።
ሰሞኑን በካርቱም በተገኘችው መጠነኛ መረጋጋትም በርካታ የውጭ መንግስታት ከ7ሺ በላይ ዜጎቻቸውን ከሱዳን ማስወጣታቸው ተጠቁሟል። በተጨማሪም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያንም ጦርነቱን ፍራቻ ወደተለያዩ የጎረቤት አገራት መሰደዳቸው ተዘግቧል። በተመሳሳይ በሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ አገራት ዜጎችም ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ሰንብተዋል።
በጄነራል  አብደል ፈታህ አል ቡርሃን በሚመራው የአገሪቱ ጦር እና በጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ በሚመራው  አማፂ የፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች መካከል የሚካሄደው ጦርነት፣  ሱዳንን የምድር ሲኦል አድርጓታል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ከቤታቸው መውጣት አልቻሉም። በመዲናዋ የኤሌክትሪክ ሃይል፣ የውሃ፣ የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎት ከተቋረጠ ሁለተኛ ሳምንቱን አስቆጥሯል። ነዋሪዎች ምግብ ገዝተውም ሆነ በእርዳታ የሚያገኙበት መንገድ የለም።
በመዲናዋ ከሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ 70 በመቶው በጦርነቱ ወድመዋል። ያሉትም በቂ የጤና ባለሙያና የህክምና ቁሳቁስ የላቸውም ተብሏል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በከፍተኛ የሰብአዊ  መብት ጥሰትና  የጅምላ ግድያ  የሚጠረጠሩ የቀድሞ የሱዳን ፖለቲከኞች ከእስር ማምለጣቸው ተነግሯል። በኦማር አልበሽር አስተዳደር በተለያዩዩ ከፍተኛ የሥልጣን እርከኖች ላይ ያገለገሉትና ለዓለማቀፍ ፍርድ ቤት ተላልፈው እንደሚሰጡ ሲጠበቁ የነበሩት አህመድ ሃሩን ከእስር ካመለጡት ተጠርጣሪዎች አንዱ ናቸው ተብሏል። ይህም በአገሪቱ ስዓተ አልበኝት እንዳይፈጥር ተሰግቷል።
ከሱዳን ተፋላሚ ቡድኖች ጋር በየጊዜው ግንኙነት እያደረጉ እንደሚገኙ የጠቆሙት የተመድ ዋና ፀሃፊ አንቶኒ ጉቴሬዝ፤ የግጭቱ ተፋላሚዎቹ  ጦርነቱን አቁመው ወደ ድርድር እንዲመጡ ጥሪ ማድረጋቸውን የገለፁ ሲሆን፤ ድርጅታቸው በሱዳን የሰብአዊ እርዳታማቅረብ ለመቀጠል ይችል ዘንድ ከእርዳታ ቡድኖች ጋር እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ባለፈው ሰኞ በኒዉዮርክ የፀጥታው ም/ቤት ስብሰባ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ጉቴሬዝ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሱዳን እንደማይወጣ አስታውቀዋል፡፡
“አንድ ነገር ግልፅ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሱዳን አይወጣም፡፡ ሱዳናውያን በአገራቸው ለማስፈን የሚመኙትን ሰላምና መረጋጋት የመደገፍ ሃላፊነት አለብን። በዚህ አስከፊ ወቅት ከሱዳን ህዝብ ጎን እንቆማለን፡፡” ብለዋል፤ ጉተሬዝ፡፡
ሁለቱ ተፋላሚዎች ባለፈው ማክሰኞ ለ73 ሰዓታት የሚዘልቅ የተኩስ ማቆም ስምምነት ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ በርካታ አገራት ዜጎቻቸውን ከሱዳን እያስወጡ መሆኑ በሱዳናውያን ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል፡፡
ሰሞኑን ከአሜሪካው ኤቢሲ ቴሌቪዥን ጋር ቃለ ምልልስ ያደረገችው አንዲት ሱዳናዊት የማህበረሰብ አንቂ፤ “እኔ የቅድምያ ትኩረት የምሰጠው ለድሃው የሱዳን ህዝብ ነው፡፡ እነሱ ደግም እርስ በርስ እየተረዳዱ ነው፡፡ ህዝቡ ተባብሮና ተደራጅቶ አንዱ ለሌላው እየደረሰ ነው” ብላለች፡፡
የማህበረሰብ አንቂዋ እንደምትለው ከሆነ፤ እነ አሜሪካና ሌሎች የአውሮፓ አገራት ዜጎቻቸውን ከሱዳን በማውጣታቸው ቅሬታ የላትም። “አገሪቱ ወደ ጦርነት ቀጠናነት በተለወጠችበት በዚህ ወቅት አገራት ዜጎቻቸውን በማውጣታቸው ግን  ምንም ቅሬታ የለኝም” ስትል አስረድታለች፡፡
አገራቱ ዜጎቻቸውን ከሱዳን ሲያስወጡ የህክምና ድጋፎች … መድሃኒቶችና ….የህክምና ቁሳቁሶች ይዘው አለመምጣታቸው በእጅጉ አስከፍቷታል። “በሱዳን አንድም ዓለማቀፍ የእርዳታ ድርጅት እንደሌለ ይታወቃል፤ ከመድሃኒት ጀምሮ ብዙ መሰረታዊ ችግሮች አለብን፡፡ የአገራቱ ነገረ ስራ በጣም ግራ ያጋባል፡፡” ብላለች።
በመጨረሻም ለጋዜጠኛው በሰጠችው ማሳሰቢያ፤ “እባካህ ተፋላሚ ቡድኖች ጦርነቱን እንዲያቆሙ ንገሯቸው” ስትል ተማጽናለች፡፡
ከጦርነቱን ሸሽታ ካርቱም ፖርት እንደምትገኝ ለአልጀዚራ የተናገረችው የእርዳታ ድርጅት ሠራተኛ ዳሊያ አብደልሞኒየም ተመሳሳይ ቅሬታና ወቀሳ አቅርባለች - በዓለማቀፍ ማህበረሰብ ላይ፡፡ “ዜጎቻቸውን ከሱዳን ለማስወጣት ሲመጡ የምግብና መድሃኒት አቅርቦት ይዘውልን ሊመጡ ይችሉ ነበር፡፡ ሆኖም አላደረጉትም፡፡ የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ አልተጠቀሙበትም” ብላለች ዳሊያ ከአልጄዚራ ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ፡፡
 “አሁን አገሪቱ በጦርነት ላይ ነች፤ ተፋላሚዎቹ ሁሉንም ዓይነት መሳሪያ ይዘዋል፤ እኛ ግን ባዶ እጃችንን ነን፣ ምግብም፣ ውሃም የለም፤ መብራትም የለንም፤ ገንዘብም የለም፤ ዓለም በባዶ እጃችን ራሳችንን እንድንከላከል ትቶናል” ብላለች- ተስፋ በቆረጠ ስሜት፡፡
ሁለቱ ተፋላሚ ቡድኖች ከማክሰኞ ጀምሮ ለ72 ሰዓታት የሚዘልቅ የተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተነግሮ የነበረ ቢሆንም፤ በሱዳን የአልጀዚራ ሪፖርተር ሂባ ሞርጋን ባለፈው ረቡዕ በሰጠችው ማብራሪያ፤ የተኩስ ማቆም ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተተግብሯል ማለት አዳጋች ነው ብላለች። “የተኩስ ማቆም ስምምነቱ ተከብሯል ማለት አይቻልም፡፡ የተኩስ ድምፅ ይሰማል፤ የአየር ጥቃት አልቆመም፣ ነዋሪዎች ከቤት መውጣት አልቻሉም፤ ከቤት ወጥቶ እቃ መግዛት አይቻልም፡፡ ገበያውም በውጊያው ወድሟል” ብላለች፡፡
አንድ የካርቱም ነዋሪ በመዲናዋ ተጠናክሮ የቀጠለውን ውጊያ በተመለከተ  በሰጠችው አስተያየት፤ “ሰዎቻችን በጦርነቱ እየተጎዱብን ነው፤ እጅጉን ፈርተናል፤ ሁለቱ ወገኖች እርስ በርስ መዋጋት የሚፈልጉ ከሆነ ከሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ ርቀው መዋጋት ነበረባቸው” ብላለች በብስጭት፡፡
“ዓለማቀፉ ማህበረሰብ የሰብአዊነት ፅንሰ ሃሳብ ጠፍቶበታል” ያለችው ደግሞ በህክምና ሙያ ላይ የተሰማራች ሱዳናዊት ናት። የትምህርት ባለሙያ የሆነው የ43 ዓመቱ ሱዳናዊ ሱሌይማን አዋድ፤ ምዕራባውያን ጣልቃ ገብተው ጦርነቱን ማስቆም አለባቸው ባይ ነው።
“የምዕራብ አገራት ዜጎቻቸውን በከፍተኛ ፍጥነት ማስወጣታቸው አገሪቱ በመፈራረስ አፋፍ ላይ መሆኗን ያሳያል።
ሆኖም ግን ምዕራባውያኑ በሁለቱ ተፋላሚ ቡድኖች ላይ ጫና በማሳደር ጦርነቱን እንዲቆምና አገሪቱ እንድትረጋጋ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ብለን እንጠብቃለን” ብሏል።
ሰሞኑን አሜሪካና እንግሊዝ እንዲሁም ከአረብ ባህረ ሰላጤ አገራት እስከ ሩሲያ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ድረስ ሁሉም አገራት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውን ከሱዳን ማስወጣታቸው ታውቋል።
ጃፓን ከሱዳን መውጣት የሚፈልጉ ዜጎቿን በሙሉ ማስወጣቷን የገለፀች ሲሆን ፈረንሳይ ደግሞ 196 ዜጎቿንና 36 የሌሎች አገራት ዜጎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 491 ሰዎችን አስወጥታለች።
በተመሳሳይ የፈረንሳይ የጦር መርከብም ተጨማሪ ዜጎችን ለማስወጣት ወደ ፖርት ሱዳን እየተጠጋች እንደነበር ባለፈው ሳምንት ተነግሯል።
 አራት የጀርመን አየር ሃይል አውሮፕላኖችም ባለፈው እሁድና ሰኞ ከ400 በላይ የተለያዩ አገራት ዜጎችን ያስወጡ ሲሆን የሳኡዲ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ባለፈው ማክሰኞ 106 የሳኡዲ ዜጎችንና ሌሎች የ26 አገራት ዜጎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 365 ሰዎችን ከካርቱም ማስወጣቱን አሳውቋል።
አሁንም ድረስ አገራት በተቻለው ቀዳዳ ሁሉ ዜጎቻቸውን ከካርቱምና ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች እያስወጡ ሲሆን በመቶ ሺዎች ሚቆጠሩ ሱዳናውያንም ወደ ጎረቤት አገራት በገፍ እየጎረፉ ነው-ከጦርነቱ ለመትረፍ።
በዚህ ሁሉ መሃል ታዲያ ሁለቱ የሱዳን ከፍተኛ ጀነራሎች ልዩነቶቻቸውን በጦርነት ብቻ ለመፍታት መፋለማቸውን ቀጥለዋል። ለጊዜው ድርድር የሚባለውን ነገር ያሰቡበት አይመስልም። ሱዳናውያን በጦርነት አለንጋ መገረፋቸውን ይቀጥላሉ ማለት ነው። አሳዛኝ ነው!Read 1324 times