Saturday, 29 April 2023 19:24

ስድብ ምንድን ነው?

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

 በአራት እግሩ የሚሄድ ውሻ የሚባል የመለያ ስያሜ የተሰጠውን እንስሳ “ውሻ” ብሎ መጥራት መሳደብ አይደለም፡፡ የስሜት ህዋሳቶቹን በአግባቡ ተጠቅሞ ማወቅ ነው፡፡ እውቀት በጥንቃቄ አገናዝቦ መለየት ነው፡፡
በአራት እግሩ የማይሄድ በተክለ ቁመና ሰው የሚመስል ግን በባህሪ እንደውሻ የሚጮህ፣ የሚናከስ፣ የሚለቃቅምና ስርቻ የሚወድ እንስሳን “ውሻ” ብሎ መጥራትም… ከአምስቱ የስሜት ህዋሳት በላይ የሆነውን የነፍስ እውነት ገልጦ ማሳየት እንጂ መሳደብ አይደለም፡፡ በበግ ለምድ የተደበቀውን ተኩላ እንደመግለጥ… በሰው አምሳል የተደበቀውን ውሻ ከተከለለበት ጠርቶ ማውጣትም ስድብ አይደለም፡፡
ታዲያ ስድብ ምንድን ነው?
የስድብ ምንነትን መረዳት እንዲሁ ቀላል አይሆንም፡፡ ስድብ መንፈሳዊ ተልዕኮ ያለው ጉዳይ ነው፡፡ ማለትም በአካል/ ቁስ አካል ላይ በቀጥታ የሚፈጥረው ለውጥ ወዲያውኑ የለም፡፡ የተሰደበ ሰው ወዲያው በአካል ቁመናው አይመነምንም፡፡ ወይንም አጣዳፊ ትውከት እና ተቅማጥ በመሰደቡ ምክንያት አይይዘውም፡፡ እንደ ፀሀይ ንዳድም ስድቡ አያከስለውም፡፡ ወይንም እንደ ቅዝቃዜ እና ብርድ አያንዘፈዝፈውም፡፡
ካንዘፈዘፈው ስጋውን በቀጥታ የሚነዳው መንፈሱ ወይንም በስጋ እና በመንፈስ መሀል ቤት ሆኖ የሚያነካካውን የነፍሱን የስሜት ቤት በመንካቱ ምክንያት ነው፡፡ በማይገባው ቋንቋ የተሰደበ ሰው ምንም አይሆንም፡፡ የመንፈስ ቋንቋ ከክብር ጋር የተያያዘ ነው፡፡
መባረክ እና መረገም የሚችለው በሰው ውስጥ ያለ የነፍስ ማንነት ነው፡፡ የዚህ የመንፈስ ማንነት እና ክብደት ደግሞ ሊመዘን የሚችለው በመንፈሳዊ ቋንቋ ነው፡፡ በመንፈሳዊ ምንነቱ ልክ ተሰጥቶት ካልተቀመጠ ስድብ በሰው ላይ ምን ያመጣል? የሚለው ጥያቄ መቼም ቢሆን ሊገለጥ አይችልም፡፡ እንግዲህ ሰውን ውሻ ብለን ስንሰድበው የሚነካው ክብሩ ነው፡፡ ውሻን ውሻ ብለን ስንሰድበው የማይቆጣው ስለማይገባው አይደለም፡፡ ቢገባውም ክብሩን አያረክሰውም፡፡ ምክንያቱም ውሻ ክብር የለውም፡፡ ክብር ያለውን የሰውን ግቢ በፍርፋሪ ተደልሎ የሚጠብቀው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ልክ ጨረቃ የራሷ ብርሀን እንደሌላት እና ከፀሀይ በቀን የተሰበሰበውን እንደምንታፀባርቅ ሁሉ፣ ውሻም የሰው ክብር ነፀብራቅ እንጂ የራሱ ወጥ የክብር ልክ የለውም፡፡ ክብር ያለው ሰው ቤት በክብር የተያዘ ውሻ ግን ባለቤቱ ያለማመደውን አልፎ አልፎ ሲያንፀባርቅ ሊታይ ይችላል፡፡
ቅደም ተከተሉ ሁሉ የሚመነጨው ነፀብራቅ ከሚለው የቃል ትርጉም ነው፡፡ ትልቅ ክብር ያለው ከሌለ ትንሽ ክብር የሚሰማው ሊኖርም ሊታሰብም ከቶ አይችልም፡፡ ክብር በሌለበት ስድብም ሆነ ምርቃት ትርጉም የሚሰጥ ነገር አይደለም፡፡
ሉቃስ 22: 23-24 በተከታታይ ብናስተውል፡፡ “ሰደበን” የሚል ክስ በፈሪሳውያን አማካኝነት ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ሲቀርብ እናነባለን፡፡ “የፈጣሪ ልጅ ነኝ” ማለቱ ነው ስድቡ፡፡ ወይንም እንደ ስድብ ተደርጎ የተቆጠረበት፡፡ “መች ተሳደበ?” ሊል ይችላል፣ በዚህ ዘመን ላይ፣ አሁን እማዶ ቆሞ ያለ አንባቢ፡፡ ለእነሱ ግን የሰው ስጋ ለብሶ በመሀላቸው የሚመላለስ… “ይሄ የማርያም እና የዮሴፍ ልጅ አይደለም? ወንድሞቹስ …..  ” አይደሉ ብለው ስለ ሰውነቱ አብረው በመሆን እማኝ በመሆናቸው ክብሩን ከፈጣሪ ልጅነት ጋር ማስተሳሰር ተስኗቸው “ተሰደብን” ብለው ነበር፡፡ ስለዚህ ክብርን ከፍ ማድረግም ለእነሱ ስድብ ነው፡፡ የፈጣሪነት ክብር ይገባዋል ብለው የሚያምኑት፣ ለማይወለድ እና በመስቀል ላይ ለማሞት፣ የነበረ እና በቀጣይነትም ጨምሮ የሚኖር፣  በስጋ የማይወለድ በሰው እጅም ለማይሞት ብቻ ነው፡፡ በዚህ የክብር ጥያቄ ምክንያት የክብርን ጌታ ሰቀሉት፡፡ ድርጊታቸውም ለዝንተ አለም የሚወራ ማስተማሪያ ሆነ፡፡ እናውቃለን ብለው ያመኑትን አምላክ ክብር ለመጠበቅ ሲሉ የራሳቸውን ክብር በክርስትና አንፃር ፈጥፍጠው ጣሉ፡፡ ሰደበን በማለታቸው ለሀይማኖታቸው የቀኑ ቢመስላቸውም፣ ሰደበን በማለታቸው ለካ ሳያውቁ ፈጣሪያቸውን ሰድበውታል፡፡
ክብር ከሌለ ስድብ ትርጉመ ቢስ ነገር ነው፡፡ የሚረገመውም ሆነ የሚመረቀው ክብር ያለው ነገር ነው፡፡ ክብር ያድጋል ወይንም ይቆረቁዛል፡፡ ይከብራል ወይንም ይኮነናል፡፡ ይታወሳል ወይንም ይዘነጋል፡፡ ይነግሳል ወይንም ይረክሳል፡፡
የሰው ልጅ ክብር አለው፡፡ ክብር ስላለውም ነው ፍትህ የሚሻው፡፡ እንደ እንስሳ በመሰለ ውልደት ተወልዶ፣ ግን በዛው እንስሳዊ መንገድ ሳይታወስ የማይጠፋው በክብሩ ምክንያት ነው፡፡ ክብሩን ደግሞ ራሱ በራሱ፣ ወይንም ተፈጥሮው ላይ ተገልፆ የተገኘ አይደለም፡፡ ውሻ በባለቤቱ ግቢ የሚከበርበት ምክንያት የግቢው ባለቤት ስላለ እንደሆነው ሁሉ፣ የሰው ክብርም ምንጩ ፈጣሪው ነው፡፡ “ማንም አይመካ፤ የሚመካ በእግዚአብሄር ይመካ” የሚለው ጥቅስ ልክክ የሚለው እዚህ ላይ ነው፡፡ ጨረቃ በሌሊት በምትፈነጥቀው ብርሀን የምትመካ እና ብርሀን የፈነጠቀችላቸው ደግሞ የሚያከብሩዋት ከሆነ፣ የብርሀኑ እና የክብሩ የቅርብ ባለቤት ግን ፀሀይ መሆንዋን አክባሪዎቿ ባለማወቃቸው ምክኒያት ነው፡፡ ግን የነፀብራቅነት ንፅፅሩ እዛው ጋር ብቻ አያቆምም፡፡ ለጨረቃ ፀሀይ እንዳላት ለፀሀይም የብርሀን ምንጭ አላት፡፡ ዘላለም የማትደበዝዝ የምትመስለውን ፀሀይ በክብር የሚበልጣት፣ ፈጥሮ  በህልውና እንድትታይ አድርጎ የሚገልጣት ዋና የብርሀን ምንጭ አላት፡፡ ፈጣሪዋ ማለትም ትርጉሙ ይኽው ነው፡፡
እውነት የሚከብረው ከእውነቶች ሁሉ በላይ እና የማይናወጥ ሲሆን ነው፡፡ ፈጣሪ እያለ ሰው የከፍተኛ ክብር ባለቤት ብቻውን ሊሆን አይችልም፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን በተጋራው የክብር ነፀብራቅ ምክንያት ሰውም ሲሰደብ ይታመማል፡፡ መንፈሱ ይነካል፡፡ የሆነውን አኮስሶ በአንደበቱ የሳለው ሰዳቢው ነው፡፡ ግን በአንድ አንፃር ብቻ አይደለም ስድቡ የሚሰራው፡፡ ከሚገባው በታች በእርግማን ሰድቦ መፈጥፈጥም ከሚገባው በላይ በሞገስ ያልሆነውን አድርጎ ማግዘፍም የስድብ እና የእርግማን አይነት ነው፡፡ ክብሩ በቦታው ላይ ሲውል ብቻ ነው ክብርም እውነትም የሚሆነው፡፡
የክብር ትርጉም ሳይተነተን የስድብ ትርጉም አይገለጥም፡፡ ማንም ሲሰደብ አለመውደዱን ብቻ ይሆናል ያኔ የሚያውቀው፡፡ ምክንያቱ ግን አይገለጥም፡፡ ስለዚህ ሲሰደብ ባይወድም፣ የራሱን ክብር የሚጠብቀው ሌሎችን በመስደብ ወይንም በመካብ መስሎት በሁለት አቅጣጫ ሊሳሳት ይችላል፡፡
የክብር ውሀ ልክ ፈጣሪን ከማወቅ ጋር ሲሆን ብቻ ውሃ ልኩን የሚጠብቅ ነው፡፡ የሰው ክብር በዘመናት ውስጥ በጥበቡ አማካኝነት ያከናወናቸው እና የጨበጣቸው አስገራሚ ድሎች ላይ ብቻ የሚጀምር ወይንም በዛ መነፅር ብቻ ታይቶ የሚተረጎም አይደለም፡፡ የሰው ክብር ከሚበልጠው ወይንም እኩያ ከሌለው ጋር ብቻ ሳይሆን ከሚያንሰው ወይንም ብዙ አቻዎቹ ከመሰሉት ጋር ተነፃፅሮ በነፀብራቅ እና በሚዛን ንፅፅር የሚገለጥ ነው፡፡ ሰው ለብቻው ከታየ አንድም ክብር የለውም… ወይንም በራሱ አለኝ የሚለው የተምታታ እና እራሱ ሲክብ እና መልሶ ሲንድ የሚገኘው አይነቱ ሀሳዊ ክብር ብቻ ነው፡፡
በስድብ ምንነት ተነስቼ ትርጉም ለማዋለድ ስለጣርኩ እንጂ እንደ ሰም እና ወርቅ  ዋናው የቅኔ ፍቺ በጥቅል ህብረ ቃሉ ላይ ካልተሟላ ብቻውን ሊገባኝ የሚችል አይደለም፡፡
ስድብ ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት፣ ክብር ምን ማለት እንደሆነ መረዳት አዳብሎ ያስፈልጋል፡፡ ሰሙ እና ወርቁ ብቻ ሳይሆን የህብረ ቃሉን የአፈታት ትርጉም ካልታወቀ ቅኔው ጥቅል እንቆቅልሽ ነው የሚሆነው፡፡ … ማወቅ እና መፍታት የሚችለው ደግሞ የሰው አእምሮ ነው፡፡  …የሰው ክብሩ ምንድነው ካላችሁኝ መርምሮ እና አገናዝቦ የማወቅ ጥበቡ ነው፡፡
ይሄንን ክብሩን ከሚገባው በላይ በድፍረት ከለጠጠው፣ አሊያም ከሚገባው በታች በድንቁርና ጨለማ ወደ ቁልቁል ከነዳው …ራሱን በራሱ ሰደበ ማለት ነው፡፡
ራሱን ከከፍተኛው እርከን ሰደበ የሚባለው እንዲሆን ለተፈጠረለት ክብር አቅሙን ክዶ ከለገመ ነው፡፡ ክህደቱ እና እና ስድቡ ደግሞ ራሱ ጋር ብቻ አይቀርም፡፡ ራሱን ሲሰድብ ፈጣሪውንም ለክህደት እና ለስድብ በዛው ምርጫው አሳልፎ ሰጥቷል፡፡
Read 396 times