Saturday, 29 April 2023 19:27

በኹርናውን የተቀማው “ጠመንጃና ሙዚቃ”

Written by  ክቡር መተኪያ ኃይለሚካኤል - (ኢኳቶሪያል ጊኒ)
Rate this item
(0 votes)


          “ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ስትወር የ13 ዓመት ልጅ የነበረችው ሜሪ አርምዴ፤ አገር ምድሩ ሁሉ “ኧረ ጥራኝ ጫካው” እያለ
በሚያንጎራጉርበት ወቅት ዝምታን አልመረጠችም፡፡ ይልቁኑስ በአፍላ ዕድሜዋ ብላታ ኅሩይ ከተባሉ የጦር አበጋዝ ጋር ወደ አምባላጌ
ዘመተች፡፡ በእዚያም ከሰራዊቱ ጎን ተሰልፋ ስትፋለም እግሯን በጥይት ተመታች፡፡--”
      
      በቅዱስ መጽሐፍ ከምናውቃቸው ባለ ብሩህ ቀለማት ታሪክ መደዳ የያይቆብ ታሪክ አንዱ ነው።ያይቆብ የኋላ ኋላ ዘሩ እንዳሸዋ እንዲበዛለት በአምላኩ ፊት ሞገስን ያገኘ ፣እስራኤልን ሆኖ አስራ ሁለቱን የእስራኤል ነገድ የወለደ ሰው ነው። ታድያ ይህ ሰው በአንዲት ክፉ ቀን በመንታ ወንድሙ ዘንድ የነበረውን በኹርና ፈልቅቆ በመውሰድ ምርቃት ከአባቱ ተዥጎደገደለትና፣ እስራኤልን ሆኖ እስራኤልን አኸለ።ይህ የታሪክ ጉንጉን ወደ ከተማው መናኝ መጽሀፍ ይወስደናል።
“የከተማው መናኝ” መጽሐፍም ልክ እንደ ያይቆብ ሁላ በውልደቷ ከታላቋ “ጠመንጃና ሙዚቃ” ለጣቂ ብትሆንም ቅሉ፣በታሪክ አገጣሚ በኹርናውን ከ “ጠመንጃና ሙዚቃ” ነጥቃና ከአይን ያውጣሽ ተብላ በሞገስ ተሞላች።
ጸሀፊው ይነገር ጌታቸው፤ይሄንን ጠመንጃና ሙዚቃ የተሰኘ ስራ ከብዙ አመታት ቀድሞ የጀመረው እንደሆንና በመሀል የሙዚቀኛ ኤልያስ መልካ ህልፈተ ህይወት “ የከተማው መናኝ” ብኩርናውን እንዲወስድ እንዳደረገው፣ በተለያዩ ቃለ ምልልሶች ላይ ሲናገር ተደምጧል።በተለይ በተለይ ከአመታት በፊት፣ በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 የትዝታን በዜማ ፕሮግራም ላይ በጥልቅ የቀድሞ ሙዚቃና ሙዚቀኞች እውቀቱ የሚያውቁት አድማጮቹ፤ “ይነገር ጌታቸው ከዛሬ ነገ ጽፎ ያበረክትልናል”ብለው የሚያስቡት መጽሐፉን የህትመት ወጋገን ሊያጎናጽፈው ከተገባ ጊዜ ቢያዘገይባቸውም ለእርማት፣ለዳበረ ታሪክና ለጠራ ስነጽሁፍ ነው ብለው መዘግየቱን በጸጋ ተቀብለው በኢትዮጵያ ህዝብ የሀገር ፍቅር ማህበር (በዛሬው የሀገር ፍቅር ትያትር) ትንሿ አዳራሽ ታድመው የመጽሐፉን ይፋዊ ምረቃ እየተጠባበቁ ነው ።
እንዳለመታደል ሆኖ፣ በርካታ አንኳር የሆነው የሙዚቃችን ታሪክ ተሰንዶ ከመኖር ይልቅ በአንጋፋ የጥበብ ሰዎች፣በራሳቸው ሙዚቀኞቹና የሙዚቃው ተዋንያን ጋር አለፍ ሲልም በሌሎች አንጋፋ የጥበብ ቤተሰቦች ዘንድ አፈ ታሪክ ሆኖ ያለና እንደ ዋዛ እዚህም እዚያም ተበታትኖ በሚገኙ ሰነዶች፣የድሮ ጋዜጣና መጽሄቶች ላይ ተቀነጫጭቦ የተጻፈ በመሆኑ በመጽሐፍ አሳትሞ ለማዘጋጀት ሲበዛ አዳጋች እንደሚሆንባቸው ብዙዎች ከማማረር አልፈው ከብዙ አመታት በፊት መጻፍ ጀምረው ሳያሳትሙት የቀሩት ሰነዶቻቸውን ይዘው እንደቀሩ ይናገራሉ።ይህ ማለት የህትመት ዋጋው ከአመታት በፊት ከነበረው በእጥፍ ከመጨመሩና የመጽሀፍ አንባቢው ቁጥር በእጅጉ የማሽቆልቆሉ ፈተና እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው።
እንግዲህ እንዲህ ያሉትንና ሌሎች ፈተናዎችን ተቋቁሞ ነው ይነገር(ማዕረግ) ጌታቸው “ጠመንጃና ሙዚቃ” የተሰኘ መጽሀፉን ሊያስነብበን ዝግጅቱን ያጠናቀቀው።ይህ በበርካታ ምዕራፎች፣በታሪካዊ ፎቶግራፎችና ሰነዶች የዳበረው መጽሐፍ ለሌሎች የሙዚቃ ተመራማሪዎች ፍኖት ይሆን ዘንድ የቀድሞው ዘመን ድምጻዊያንን የሙዚቃ ስራ፣ግጥም፣ዜማ፣አቀናባሪ፣የሙዚቃ ቤት/ባንድና የመሳሰሉት መረጃዎች የተካተቱበት “ዲስኮግራፊ” አብሮ በመያዙ መጽሐፉን መንገድ ጠራጊ ያደርገዋል።
እንዳለመታደል ሆኖ ነው እንጂ እንደ ምዕራባዊያኑ ብንሆን ኖሮ፣ ስለ አንዱ ድምጻዊ በመቶ የሚቆጠር መጽሐፍ በጻፍን፣መንገዶችና ፓርኮችን በሰየምን፣ፊልሞችን በሰራን፣ፓናሎችን በየአመቱ ባዘጋጀን ነበር።ምዕራባዊያኑ በዚህ ባህላቸው ሁሌም እንዳስቀኑን ይኖራሉ። እነርሱ ስለ ታዋቂ ሙዚቀኞቻቸው መጽሐፍ ጽፈው አይጠግቡም፡፡ መንገድ ሰይመው አይበቃቸውም፡፡ፊልም ሰርተው አይረኩም፡፡ለምሳሌ ማይክል ጃክሰን በተለያየ ኮንሰርት ላይ የደፋው ባርኔጣ፣ያጠለቀው ጓንት፣የተጫማው ጫማ፣የደረበው ጃኬት፣የታጠቀው ሱሪና ሌሎችም መታወሻዎቹ በቅርስነት ተመዝግበው ቁጭ ብለዋል፡፡
እንደ አስፈለጊነቱም የናጠጡ ቱጃሮች ብቻ ለሚሸምቱት ጨረታ ይቀርባል። ስለ ኤልቪስ ፕሪስሊ ብቻ ከመቶ ሃምሳ በላይ የህይወት ታሪክና ልብ ወለድ መጽሐፍ ተጽፏል፡፡ስለ ዊትኒ ሀውስተን የህይወት ታሪክ በርካታ ዶክመንታሪ ፊልሞች ተሰርተዋል፡፡ የኛ ሃገር ግን የተገላቢጦሽ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ድምጽዊው ያዜመውን ዜማ ራሱ ድምጻዊው ለማስታወሻ ፈልጎ ያጣዋል፡፡የተቀረጸ ቪድዮ የሌላቸው ድምጻዊያኖቻችን ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ የአንዳንድ ድምጻዊያን ፎቶግራፍ የሚገኘው ከተቀጠሩበት የሙዚቃ ቤት ሳይሆን ፤ከፈረንጅ ሃገር ደጅ ተጠንቶና ብዙ ሺህ ብር ተከፍሎ ነው፡፡ሊያውም በፈረንጆች በጎ ፈቃድ።
ሀገርና ታሪክ ወዳዱ ህዝብ፣ ይሄንን መራር ሀቅ በሚጋትበት ጊዜ፣ እንዲህ ያሉ መጽሐፎች ብቅ ሲሉ እንደ ስለት ልጅ በስስት ማየት የሚደንቅ ጉዳይ አይሆንም።”ጠመንጃና ሙዚቃ” ሲሻው ወደ ኋላ መቶ አመት ገደማ ይወስደንና ቀዳሚ የሙዚቃ ሸክላ አሳታሚውንና የልጅ እያሱን አንጋች ነጋድራስ ተሰማ እሸቴን ያስቃኘናል።
ወዲህ ደግሞ ወደ ድሬዳዋ ይወስደንና የኦሮምኛ ኮከብ ድምጻዊ አሊ ቢራን በአፍራን ቀሎ የሙዚቃ ቡድን በኩል አድርጎ፣የሙዚቃ ጅማሮውን እያስታወሰ ይወስደንና የወቅቱ የፖለቲካ ግለቱንና የአሊን ተሳትፎ በማንሳት፣ ከደህንነት ሰዎች እጅ እንዴት ባለ ተአምር እንዳመለጠ ያስታውሰናል።
ደግሞ ወዲህ “እንዳይላሉ”ን ያስተዋውቀናል። እንዳይላሉ አይነ ስውር ነው። በሁለተኛው የጣልያን ወረራ ወቅት ለአርበኞች በአኮፋዳው ጥይትና ጠመንጃ እየደበቀ ያመላልስ የነበረ አርበኛ ነው።አይነ ስውሩ እንዳይላሉ፣ የጣልያን አይናማ ሹማባሾችንና ካራቢኔሪዎችን  እንዴት ባለ ስልት ሲያሞኛቸው እንደሰነበተ ይነግረናል።
በዚያውም አስከትሎ የእነ ተሾመ አሰግድን ፣ የእነ አብዱቄ ከፍኒን፣የእነ ዘመድ ገብረአምላክና የሌሎች አይነ ስውራን ሙዚቀኞች ንብረት የነበረውንና በርካታ አስደናቂ የሙዚቃ ስራዎችን ሰርቶ ስለነበረው “ሬይንቦ ባንድ” እና የቀዳማዊ ኃይለስላሴን አስተዋጽኦ በሚገባ ያስቃኘናል፡፡“ጠመንጃና ሙዚቃ” ታሪካቸውን በአስደናቂ ሁናቴ ካስቀመጠላቸው ሰዎች አንዷ ባለ ክራሯ ሜሪ አርምዴ ነች። ሜሪ በሁለተኛው የጣልያን ወረራ ወቅት ገና በኮረዳነት እድሜዋ ጦር ሜዳ ድረስ ዘምታ የነበረችውንና የኋላ ኋላ፣በክራር ደርዳሪነትና በባለ ሻካራ ድምጽ አዝማሪነት፣ በፋሽን ተከታይነትና በሴቶች ጸጉር ቤት አስተዋዋቂነት ቀዳሚ ያደረጋትን፣በዘመኗም ጣፋጭ ህይወት የመራችውን ሜሪን እያስታወሰ፣ ታሪክ ግን እንዴት ጨክኖ ፊት እንዳዞረባት፣ እየሾመጠረንም ቢሆን እንድናነበው ያስገድደናል፡፡
 “ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ስትወር የ13 ዓመት ልጅ የነበረችው ሜሪ አርምዴ፤ አገር ምድሩ ሁሉ “ኧረ ጥራኝ ጫካው” እያለ በሚያንጎራጉርበት ወቅት ዝምታን አልመረጠችም፡፡ ይልቁኑስ በአፍላ ዕድሜዋ ብላታ ኅሩይ ከተባሉ የጦር አበጋዝ ጋር ወደ አምባላጌ ዘመተች፡፡
በእዚያም ከሰራዊቱ ጎን ተሰልፋ ስትፋለም   እግሯን በጥይት ተመታች፡፡ አጋጣሚው ያሳዘናቸው አርበኞች ወደ ቤቷ እንድትመለስ ጠይቀዋት ነበር፡፡ ነገር ግን በጄ  አላለቻቸውም፡፡ እንዲያውም ከአርበኞች እኩል ጋራ ሸንተረሩን  እያቆራረጠች ወደ ሽሬ ተጓዘች፡፡”  (ከመጽሃፉ የተወሰደ)
“ጠመንጃና ሙዚቃ” ወዲህ ዝቅ ብሎ ደግሞ የራስ ባንድ ድምጻዊያን ስለነበሩት ስለነ ምኒልክ ወስናቸው፣ ስለ በአታ ገብረህይወት፣ ስለ ሰይፉ ዮሃንስ፣ የማናውቃቸውን በርካታ ቁምነገሮች ያስነብበንና መልሶ ደግሞ ወደ የአራት ኪሎን ፖለቲካ ከሙዚቃ ሲገምደው እናገኘዋለን።
የአጭር ግዜውን ጠቅላይ ሚኒስቴር ልጅ እንዳልካቸው መኮንንን ከሙዚቃ ጋር ተቆራኝተው እናገኛቸዋለን ብለን መች ጠርጥረን እናውቅና?! ነገሩ ግን ወዲህ ነው።ብዙዎች ልጅ እንዳልካቸውን የሚያውቋቸው የክቡር ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ልጅ መሆናቸውንና አባታቸው የተቀመጡበትን የጠቅላይ ሚኒስቴርነት ስልጣን እርሳቸውም መያዛቸውን፣ከዚያም የ1966 አብዮት ተከትሎ በደርጎች አቅራቢነት ጠቅላይ ሚኒስቴር የነበሩና በዛች ክፉ ቀን (በህዳር 1967) ከሌሎች ሃምሳ ዘጠኝ የንጉሰ ነገስቱ ባለስልጣናት ጋር የተረሸኑ ሰው መሆናቸውን ነው፡፡ይነገር ጌታቸው፣ ልጅ እንዳልካቸውን የሲምፎኒ ኦርኬስትራ መስራች እንደነበሩ በመጽሃፉ እንዲህ ብሎ ይነግረናል፡፡
“ኢትዮጵያን በጠቅላይ ሚንስትርነት የመሩት መኮንን እንዳልካቸው፣ በንጉሠ ነገሥቱ የስልጣን ጠቅላይነት አባዜ በፖለቲካ ሰማያችን ላይ ጎልተው አለመታየታቸው እውነት ቢሆንም፣ ከሴራው ይልቅ ለኪነ-ጥበብ ማድላታቸው ግን የራሱ ሚና እንደነበረው አያጠያይቅም፡፡ ለዚህ ደግሞ በሚኒስትርነት ቦታቸው ላይ ሆነው በርካታ መጻሕፍትን ለንባብ ማብቃታቸውና በአገሪቱ አዲስ የሆነውን የሲምፎኒ ኦርኬስትራ መመስረታቸው አብነት ይሆናል፡፡ መኮንን በፕሬዚዳንትነት የመሩት ቀዳሚው የሲምፎን ኦርኬስትራ “The society of friends of music” የሚል መጠሪያ ነበረው፡፡”
እንዳለመታደል ሆነና በዚህ መጽሐፍ የተጠቀሱት የሙዚቃ ባንዶች “በጠቅላላ” ዛሬ ላይ ቀደም ባለው ግዜ የሰሩት የሙዚቃ ስራ ትውስታ ሆኖን ካልሆነ በቀር በገሃድ ተገልጠው መድረክ ላይ አናያቸውም፡፡ልክ ሙዚቃ ባንዶቹ ሁሉ በመጽሐፉ ዝክረ ነገራቸው  ከተከተበላቸው ሙዚቀኞችም መካከል በጣም ጥቂቶቹ ካልሆኑ በስተቀር ብዙዎቹን በአጸደ ስጋ አናገኛቸውም።
በመጽሐፉ መግቢያ ላይ በጸሀፊው እንደተጠቀሰው….
“ጠመንጃና ሙዚቃ” በፖለቲካ የተሸመነ፤በደም የቀለመ፤ በአርነት የፈካ የኢትዮጵያዊያን የሙዚቃ ሰዎች ድርሳን ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ጊዜ ሥልጣን    አለው፡፡ የአገር መውደቅ መነሳት ፣ የሕዝብ መራብ መጠማት ዘመንን እየመሰለ ይግተለተላል፡፡ ባሕልና ጥበብም ወቅትን ተከናንቦ ያልፋል፡፡”Read 678 times