Saturday, 06 May 2023 17:13

ግሪን ቴክ፤ በኤሌክትሪክ መኪኖች ቴክኒሽያንነት ያሰለጠናቸውን 25 ተማሪዎች አስመረቀ ተማሪዎች አስመረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ግሪን ቴክ ፤ላለፉት ሦስት ወራት በኤሌክትሪክ መኪኖች ቴክኒሽያንነት  ያሰለጠናቸውን 25 ተማሪዎች ባለፈው ማክሰኞ ፣ ቃሊቲ ቶታል በሚገኘው የድርጅቱ ዋና መ/ቤት አስመረቀ፡፡
25ቱ ተመራቂዎች  በዘርፉ የመጀመሪያዎቹ ሰልጣኞች ሲሆኑ ፤ሥልጠናው የተሰጠው ከኤስኦኤስ የህጻናት መንደር ጋር በመተባበር  ነው  ተብሏል፡፡
ለተመራቂዎቹ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የግሪን ቴክ አፍሪካ ዋና ሥራ አስፈጻሚ  ኢንጂነር ቅደም ተስፋዬ፤” በዘርፉ ተቀጣሪዎች ሳይሆን ሥራ ፈጣሪዎች እንድትሆኑ ነው የምንፈልገው” ብለዋል፡፡ሰልጣኞቹ ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት የአምስት ቀናት የሥራ ፈጣሪነት (entrepreneurship) ሥልጠና እንደሚሰጣቸውም ተነግሯል፡፡
በአገራችን  በኤሌክትሪክ መኪኖች ቴክኒሽያንነት ሥልጠና የሚሰጥ ተቋም እንደሌለ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ያሁኖቹ ተመራቂዎች የመጀመሪያዎቹ ሰልጣኞች ናቸው ብለዋል፡፡በዕለቱ የተመረቁት ተማሪዎች በኤሌክትሪካልና መካኒካል ኢንጂነሪንግ በድግሪና በማስተርስ ድግሪ ደረጃ ትምህርት የወሰዱ መሆናቸው ታውቋል፡፡ግሪን ቴክ በአጠቃላይ 300 ወጣቶችን በኤሌክትሪክ መኪና ቴክኒሽያንነት  ለማሰልጠን ያቀደ ሲሆን፤ 27 ወጣቶች በሥልጠና ሂደት ላይ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
ግሪን ቴክ ኢትዮጵያ፤ በአገራችን የመንገድ ትራንስፖርት ዘርፍ ፈር ቀዳጅ የሆኑና ለማህበረሰቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት የሚሰጡ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክና በሶላር ቻርጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ለተጠቃሚው ህብረተሰብ እያቀረበ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

Read 1170 times