ሞቱም፣ ስደቱንም፣ ውድመቱም፣ ጥሰቱም ቀጥሏል
ሰብአዊ ቀውሱ ወደ ጎረቤት አገራት እንዳይዛመት ተሰግቷል
የሱዳን የጦር ጄነራሎች በየፊናቸው አገሪቱን በበላይነት ለመቆጣጠር ለሦስተኛ ሳምንት መፋለማቸውን ቀጥለዋል-የተኩስ አቁም ስምምነቶችን በተደጋጋሚ እየጣሱ፡፡ እስካሁን በጦርነቱ ከ500 በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፤ ከ4500 በላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሱዳን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ጦርነቱን ሸሽተው ከሱዳን ወደ ጎረቤት አገራት የተሰደዱ ሱዳናውያን ቁጥር 100ሺ መድረሱን ያስታወቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ ግጭቱ ከቀጠለ ከ800ሺ በላይ ሱዳናውያን ሱዳንን ጥለው ለመሰደድ እንደሚገደዱ አስጠንቅቋል፡፡
ይህ በእዚህ እንዳለ፤ ሁለቱ ተፋላሚ ሃይሎች የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለአንድ ሳምንት ለማራዘም “በመርህ ደረጃ” ተስማምተዋል ተብሏል፡፡ እስካሁን ባለው እውነታ ግን ተፋላሚ ሃይሎቹ ከአራት ጊዜ በላይ የተኩስ አቁም ስምምነቶችን መጣሳቸው ይታወቃል፡፡ በዚህም ሳቢያ የአሁኑ ስምምነት ላይም ብዙዎች የተዓማኒነት ጥያቄ እያነሱበት ይገኛል፡፡
የአሁኑ ግጭት የተከሰተው ሁለቱ የጦር ጄነራሎች በጋራ ወታደራዊ ኩዴታ በመፈፀም ወደ ዲሞክራሲ የሚደረገውን ሽግግር ካደናቀፉ ከሁለት ዓመት በኋላ መሆኑን ያስታወሰው የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ፤ በዚህ ጦርነት ድል የቀናው የሱዳን ቀጣይ ፕሬዚዳንት የመሆን እድል ያለው ሲሆን፤ ተሸናፊው ወገን የስደት፣ የእስር ወይም የሞት እጣ ፈንታ ሊገጥመው እንደሚችል ጠቁሟል፡፡
በአገሪቱ ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ የእርስ በርስ ጦርነት ሊከሰትም ይችላል ብሏል- አሶሼትድ ፕሬስ፡፡
በቱፍትስ ዩኒቨርስቲ የሱዳን ኤክስፐርት የሆነው አሌክስ ደዋል በዚህ ሳምንት በፃፈው ማስታወሻ፣ግጭቱ እንደ “መጀመሪያ ዙር የእርስ በርስ ጦርነት” መታየት አለበት ብሏል፡፡
“ጦርነቱ በፍጥነት ካልቆመ በስተቀር ክልላዊና አንዳንድ ዓለማቀፍ ተዋናዮች ገንዘብ፣ የጦር መሳሪያ አቅርቦትና ምናልባትም የራሳቸውን ወታደሮች በመጠቀም ወይም በውክልና ጥቅማቸውን የሚያሳድዱበት ባለብዙ ደረጃ መጫወቻ ነው የሚሆነው” ሲል ፅፏል ደዋል፡፡
የሱዳን የጦር አበጋዞች ነገረ ስራ ያላማራቸው እነ አሜሪካና እንግሊዝ፣ ዜጎቻቸውን በአንድ ዙር ብቻ ከሱዳን የማስወጣት የመጀመሪያ እቅዳቸውን በመለወጥ በሁለትና ሦስት ዙሮች በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ዜጎችን ማስወጣታቸው ተዘግቧል፡፡ በሌላ በኩል፤ ግጭቱ ከተጀመረ ወዲህ በየቀኑ አያሌ ቁጥር ያላቸው ሱዳናውያን ነፍሳቸውን ለማትረፍ ከባድ የጭነት መኪኖችን ጨምሮ ባገኙት መንገድ ሁሉ ወደ ጎረቤት አገራት እየፈለሱ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡ 40ሺ የሚደርሱ ሱዳናውያን ድንበር አቋርጠው ግብፅ ሲገቡ፤ 30ሺ ያህል ደግሞ ደቡብ ሱዳን- ገብተዋል ተብሏል።
የአገራቸውን ጦርነት ሸሽተው በስደት ሱዳን ውስጥ ሲኖሩ ገብተው የነበሩ የሶሪያና የየመን ዜጎች ደግሞ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ተብሏል-ጦርነት ሸሽተው ጦርነት ገጥሟቸዋል፡፡ የአልጀዚራ ጋዜጠኛ ያነጋገረቻቸው የመናውያን የት እንደሚሄዱ እንኳን እንደማያውቁ ነው የገለፁት፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ደግሞ በካርቱም ያለምግብና ውሃ እንዲሁም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ቤታቸው ውስጥ ታስረው ይገኛሉ-ከአስከፊው ጦርነት ነፍሳቸውን ለማትረፍ፡፡
የዛሬ ሦስት ሳምንት የሁለቱ ሃይሎች ግጭት በጀመረበት ወቅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም 3 ሰራተኞች መገደላቸውን ተከትሎ የእርዳታ ድርጅቶች በሱዳን ሥራቸውን ማቆማቸው ይታወቃል፡፡
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ግን በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በሱዳን ያቋረጠውን አገልግሎት ዳግም ሊጀምር መሆኑን አስታውቋል፡፡ ተቋሙ የምግብ እርዳታ የማከፋፈል ሥራውን የደህንነት ስጋት በሌሉባቸው የገዳሪፍ፣ የገዚራ፣ የካሳላ እና የዋይት ናይል ግዛቶች በመጪዎቹ ቀናት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል። “የተጋላጮችን እያደገ የመጣ ፍላጎት ለማሟላት ስንጣደፍ፣ የሰራተኞቻችንንና አጋሮቻችንን ደህንነት ለማረጋገጥ ከፍተኛውን ጥንቃቄ እናደርጋለን” ብሏል፤ ተቋሙ ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫው፡፡ ግጭቱ ከመከሰቱም በፊት ቢሆን በሱዳን ከ15 ሚሊዮን ህዝብ በላይ የከፋ የምግብ እጥረት ተጋላጭ የነበረ ሲሆን ጦርነቱ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ፣ ይሄ አሃዝ በከፍተኛ መጠን እንደሚያሻቅብ ይጠበቃል ተብሏል፡፡ የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ሃላፊ ማርቲን ግሪፍትስ፣ በሱዳን ያለውን ሁኔታ ለመገምገም ባለፈው ማክሰኞ ፓርት ሱዳን መግባታቸው ታውቋል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ካሪን ዠን ፔር ባስተላለፉት መልእክት፤ ሰብአዊ ድርጅቶች በሱዳን ሰዎችን መርዳት ይችሉ ዘንድ መንገድ ሊከፈትላቸው ይገባል ብለዋል፡፡ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ማይክል ዱንፎርድ የቀውሱን መጠነ- ስፋት አስመልክተው ሲናገሩ፤ “ቀውሱ የሱዳን ብቻ አይደለም፤ ክልላዊ ቀውስ ነው የሚሆነው” ብለዋል፡፡
ጄነራሎቹ ሱዳንን ለመቆጣጠር መፋለማቸውን ቢቀጥሉም፣ ክልላዊና ዓለማቀፍ አካላት ግጭቱን በሰላም ድርድር ለመፍታት ጥረት ከማድረግ አልቦዘኑም፡፡
የሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች የውይይት ተወካዮቻቸውን ለተባበሩት መንግስታት የድርድር ጠረጴዛ ለመላክ መስማማታቸውን የሱዳን የተመድ ልኡክ ቮልከር ፔርቴስ በዚህ ሳምንት ተናግረዋል፡፡ “ንግግሩ መጀመሪያ በአገር አቀፍና ዓለማቀፍ ታዛቢዎች ክትትል የሚደረግበት “ፅኑ እና አስተማማኝ” የተኩስ አቁም መፍጠር ላይ የሚያተኩር ይሆናል” ብለዋል፤ ፔርቴስ ለአሶሼትድ ፕሬስ፡፡ ሁለቱ ሃይሎች ተወካዮቻቸውን ሰይመዋል ያሉት የተመድ ልኡክ፤ የንግግሩ ሎጂስቲክስ ግን ገና አልተጠናቀቀም ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
በሱዳን የአልጀዚራ ዘጋቢ ሂባ ሞርጋን ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠችው አስተያየት፤ “ሁለቱ ወገኖች ለመነጋገር ተስማምተናል ይላሉ፤ ነገር ግን ለንግግሩ ቅድመ ሁኔታ እንደተበጀለት ከጦር ሰራዊቱ በተደጋጋሚ ሰምተናል፡፡
የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉም እንዲሁ ተመሳሳይ ነገር እያለ ነው” ብላለች፡፡
ቮልከር ፔርቴስ በበኩላቸው፤ ተፋላሚ ቡድኖቹ አንደራደርም የሚሉ ከሆነ ዓለማቀፍ መገለል ይገጥማቸዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
በሌላ በኩል የቀድሞው የሱዳን ጠ/ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ፤ የሱዳን ቀውስ ከሊቢያና ከሶሪያ የከፋ ሊሆን እንደሚችል አስጠነቀቁ። አሁን በሚፋለሙት ጄነራሎች በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ከመውረዳቸው በፊት ሱዳንን በጠ/ሚኒስትርነት የመሩት አብደላ ሃምዶክ፤ ጦርነቱ የሚቀጥል ከሆነ “ዓለምን የሚያስጨንቅ ቅዠት” ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡
የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር በናይሮቢ በተካሄደ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ሁለቱን ተፋላሚ ጄነራሎች ወደ ሰላም ንግግር ለማምጣት የተባበረ ዓለማቀፍ ጥረት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ያለምንም የሰላምና መረጋጋት ተስፋ ጦርነቱ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ፣ የተለያዩ የአፍሪካ መሪዎች ሁለቱን የሱዳን የጦር ጄነራሎች እየወቀሱና እየነቀፉ ይገኛሉ፡፡
የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፤ ሱዳንን በውስጣዊ ግጭት ቀጣይነት ላለው መከራ ዳርገዋታል ያሏቸውን ሁለቱን የጦር አዛዦች ክፉኛ ተችተዋል፡፡
“ሁለቱ ወገኖች ልዩነቶቻቸውን በንግግር መፍታት እየቻሉ፤ ጦርነት ውስጥ የሚያስገባቸው ምንም ምክንያት የለም” ብለዋል ፕሬዚዳንት ሩቶ፡፡
ኬንያ፤ አህጉሪቷ ወደ ወታደራዊ አገዛዝ ተንሸራትታ እንዳትገባ ለመግታት ቁርጠኛ ናት ብለዋል- ወታደራዊ አገዛዝ የትላንት እንጂ የአሁን ዘመን እውነታ አለመሆኑን በመግለፅ፡፡“ይህች አህጉር ማንኛውም ወታደራዊ አገዛዝን እንደማታስተናግድ ለሱዳን ወንድሞቻችን ግልፅ የሆነ መልእክት ልንልክላቸው እንፈልጋለን፡፡ በብዙ ዓመታት ጥረትና ልፋት እያደገች የነበረችውን ሱዳን በምንም ዓይነት ሁኔታ ማውደም አይችሉም። ህንፃዎችን፣ ሆስፒታሎችንና መሰረተ ልማቶችን በቦምብ ማደባየት ተቀባይነት የለውም… ተጠያቂ እናደርጋቸዋለን” ሲሉ አስጠንቅቀዋል-ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፡፡
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በበኩላቸው፤ የሱዳንን ቀውስ እልባት ለመስጠት የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የመሪነቱን ሚና መውሰድ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ባለፈው ሰኞ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን በአረብኛ ቋንቋ ቃለ ምልልስ የሰጡት ፕሬዚዳንቱ፤ “የሪፎርም ሂደቱ ብቸኛው ባለቤት ነን ለማለት አሁን ጊዜው አይደለም፡፡ ለፖለቲካ ሽኩቻም ሆነ ለስልጣን ትግልም አሁን ትክክለኛው ጊዜ አይደለም፡፡” ሲሉ ለሱዳን የፖለቲካ ሃይሎች ለሱዳን የፖለቲካ ሃይሎች መክረዋል፡፡
“በሱዳን የመከላከያና የደህንነት ተቋማት አንድነት ላይ ጥያቄና ብዥታ ሊነሳ አይገባም” ሲሉም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ “አሳዛኝ” እና “አስከፊ” ያሉት የሱዳን ግጭት፤ በፍጥነት መቆም እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
“አሁን በሱዳን የተፈጠረው ችግር መነሻው የአገሪቱ የጦር መሪዎች የህዝቡን ሲቪል መንግሥት የመመሥረት ፍላጎት ገሸሽ አድርገው ለሥልጣን መሻማታቸው ነው” ሲሉ ወቅሰዋል። ግጭቱ ያቆም ዘንድ የፈጥኖ ደራሽ ሃይል አዛዡ ጄነራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ፣ ሰራዊታቸውን ከአገሪቱ ጦር ሰራዊት ጋር እንዲያዋህዱ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጠይቀዋል፡፡
የኤርትራው መሪ፤ አስፈሪውን የሱዳን ጦርነት በመሸሽ መጠለያ ለሚፈልጉ ሱዳናውያንም ሆነ የለሌሎች አገራት ዜጎች የአገራቸው በር ክፍት መሆኑን አስታውቀዋል-በቃለ ምልልሳቸው፡፡
Saturday, 06 May 2023 18:27
መላ ያልተገኘለት የሱዳን አሳሳቢ ቀውስ
Written by ኤሊያስ
Published in
ፖለቲካ በፈገግታ