Saturday, 06 May 2023 18:34

“የስዊድኑ አውሮፕላን አብራሪ በኢትዮጵያ”

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(1 Vote)

እውነተኛ የትርጉም ሥራ ማግኘት አዳጋች እየሆነ ነው፤ በተለይ ዛሬ-ዛሬ፡፡ ልብ ብለን ከሆነ ለመተርጎም የሚመለመሉት መጽሐፍት በአብዛኛው ደረጃቸው ያን ያህል ላቅ ያለ አይደለም፡፡ በአመዛኙ የመጽሐፍ ገበያው እሚፈልጋቸው የስነ-ልቦና፣ የስነ-ስኬት… የመሳሰሉትን ነው፡፡ አንድ መጽሐፍ በአንድ ሳምንት መተርጎም ፈታኝ ሳይሆን አዝናኝ ቢዝነስ ሆኗል፡፡ ጥሬ እውነታው ይኸው ነው፡፡
አለማየሁ ገዳ መምህርና የኢኮኖሚ ምሁር ነው፡፡ በሰለጠነበት መስክ የራሱን ትንሽ አስተዋጽኦ ለማድረግና ሌሎችንም ከማነሳሳት ባለፈ ልማትና ኢኮኖሚክስን ለማስተማር እሚፈልጉትን ለማገዝ ሲል፣ የ20ኛው ክፍለ-ዘመን ታላቅ ተፅእኖ ፈጣሪ ኢኮኖሚስት የሆነውን የሚካኤል ካልስኪን ንድፈ ሃሳብና ዕሳቤ የያዘውን መጽሐፍ “የታዳጊ ሀገር ኢኮኖሚ” በሚል ርዕስ በከፍተኛ ጥንቃቄና ትርጉም ለንባብ አብቅቷል፡፡ አለማየሁ በአገራችን በሁሉም ዘርፍ የተተረጎሙ በቂ መጽሐፍት እንደልብ አለመኖራቸው ከንክኖት በትርጉም ሥራው መግቢያ እንዳሰፈረው… “ መሠረታዊ የሆኑ የኢኮኖሚክስ  መጽሐፍት  ለምሳሌ እንደ አዳም ስሚዝ፣ ዴቪድ ሪካርድ፣ አና ኬየንስ ወ.ዘ.ተ… በአማርኛ ተጽፈውልኝ ቢሆን ኖሮ፣ በአንድ ሳምንት  አንብቤ ጨርሼ  ከፈረንጅ የኢኮኖሚክስ ተማሪዎች ደረጃ በፍጥነት እደርስ ነበር” በሚል ይቆጫል፡፡ መምህሩ አያይዞ… “የእያንዳንዱ ዜጋ ህይወት የሚወስን ጉዳይ ላይ መጽሐፍት አይተረጎሙም፡፡ ዜጎች በቀላሉ በሚረዱት ቋንቋና በተቻለ መጠን ቴክኒክ ነክ ባልሆነ መንገድ  የቀረበላቸው ትርጉም የለም፤ ቢኖር ባለሞያዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም የአገራችን አንባቢዎች ያነቡታል፣ በቀላሉም ይማሩበታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሀምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሀምሳ ሰው ግን ጌጡ ነው እንዲሉ፤ ሁሉም በሰለጠነበት መስክ አንዳንድ ዘመን ተሻጋሪ መጽሐፍ ቢተረጉም የት በደረስን፡፡ ይህን ስል ግን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርንም የሚመለከታቸው ሁሉንም አካላት አስቆጭቶ  ለማትጋትም ጭምር ነው!” ይላል፡፡
ደራሲ ሚካኤል ሽፈራው ይህን በትርጉም ዘርፍ ውስጥ ያለብንን ክፍተት፣ የአገራችን የክፉ ቀን ወዳጅ የሆነውን የካርል ጉስታቭ ቮን ሮዘን እውነተኛ የህይወት ታሪክና የኢትዮጵያ ቆይታ የሚያስቃኘውን “An Air Borne Knight Errant” የተሰኘ መጽሐፍ፣ “ከማይጨው እስከ ኦጋዴን” በሚል ወደ አማርኛ በመመለስ፣ ቀዳዳውን ለመሙላት የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያ በተለያዩ ውጥረቶች ውስጥ በገባችበት ዘመናት ወደ አገራችን በመምጣት በቅንነትና በፍቅር ያገለገሉን፣ በረሀብ በተፈተንባቸው፣ በጦርነት በተጠቃንባቸው አመታት ያልተለዩን አያሌ ባለውለታ የውጭ ዜጎችን በታሪኳ አስተናግዳለች፡፡ የውጪ ሀገር ዜጋ ሆኖ ራሱን ለከፍተኛ አደጋ አጋልጦ ኢትዮጵያን በሙሉ ልቡና በቆራጥነት በማገልገል ረገድ ካርል ጉስታቭን እሚስተካከለው የለም ማለት ይቻላል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በ1928 ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ የከፈተችው ወረራ በስዊድን በተሰማ ጊዜ ከፍተኛ ቁጣ ተቀሰቀሰ፡፡ ምክንያቱም ስዊድን በወቅቱ በሚሲዮናውያን አማካኝነት ከኢትዮጵያ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ፈጥራ ስለነበር ነው፡፡ ጋዜጦቿም የኢጣሊያንን ወረራ በብርቱ አወገዙ፡፡ ጦርነቱ ከተጀመረበት እለት አንስቶ የስዊድን ቀይ መስቀል ኮሚቴ ስዊድናውያን  የህክምና ባለሞያዎችን ያካተተ የጦር ሜዳ ሆስፒታል ወደ ጦር ግንባር ለመላክ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ የጦርነቱን ሰለባዎች ለመርዳት የሚውል ገንዘብ መሰብሰብ ሲጀመር ህዝቡ ከልብ በመነጨ ስሜት ገንዘቡን ለነዚሁ ለቀይ መስቀል ኮሚቴ አባላት  መለገስ ጀመረ፡፡ ይህ ገንዘብ የጦር ሜዳ  ሆስፒታሉን የአራት ወር ወጪ ሙሉ ለሙሉ መሸፈን የሚያስችል ነበር፡፡ በጊዜው የ26 ዓመት ወጣት አብራሪ የነበረው ባለታሪካችን ካርል ጉስታቭ ቮን ሮዘን ከነበረበት የሰርከስ  ትርኢት በረራ ስራው ለቅቆ ያለ አላማ በዛለ መንፈስ ሆኖ በስዊድን ጎዳናዎች እየተዘዋወረ ሳለ ድንገት እግር ጥሎት በቅርብ ከአቢሲኒያ የተመለሱና የሚያውቃቸው ዶክተር ጉናር የተባሉ ሀኪም ትምህርታዊ ንግግር የሚጀመርበት ሰዓት ነበር፡፡ በአቢሲኒያ በወቅቱ ድንገት ስለተከፈተው የኢጣሊያ የግፍ ጥቃት የሚተርከውን የዶክተሩን አሳዛኝ ንግግር አዳመጠ፡፡ በሰማው ታሪክ ስሜቱ የተነካው ካርል ጉስታቭ ለአፍታም አላመነታም፡፡ ወዲያውኑ ለስዊድን ቀይ መስቀል ኮሚቴ ፕሬዚዳንት በጻፈው ደብዳቤ፣ የአምቡላንስ አውሮፕላን አብራሪ ሆኖ ወደ ጦርነቱ  ለመዝመት  ፍቃደኝነቱን ገለጸ፡፡ ካርል በዚህ ሳያበቃ የግል አውሮፕላኑን ለቀይ መስቀል አገልግሎት እንድትውል በስጦታ ማበርከቱንም ጨምሮ አሳወቀ፡፡ ከአራት መቶ በጎ ፍቃደኛ አመልካቾች መካከል መመዘኛውን ካርል የግል አውሮፕላኑን ጨምሮ በስጦታ ማቅረቡ ቦርዱ ከግምት በማስገባት እርሱን መምረጥ ይችል ዘንድ አሳማኝ ምክንያት ሆኖ በማግኘቱ መርጦ ወደ አቢሲኒያ ሊልከው ቻለ፡፡ ካርል ኢትዮጵያ ሲደርስ በጊዜው በጦርነቱ የነበሩት ሁለት ፓይለቶች ብቻ ነበሩ፡፡ አንዱ ኢትዮጵያዊ ካፒቴን ሚሽካ ባቢ ሼፍ እና ሉድዊግ ዌበር የሚባል በአንደኛ የአለም ጦርነት  የተዋጋ አውሮፕላን አብራሪም ነበር፡፡ ዌበር ንጉሱ የራሳቸው የግል አውሮፕላን አብራሪ አድርገው ቀጥረውት በዚህ ስራ ላይ ነበር፡፡ በኋላ ካርል ከንጉሱ በቀጥታ የተለያዩ ትዕዛዝ በመቀበል በመሳሪያና በመርዝ ጋዝ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ሲያነሳና ሲረዳ ቆይቷል፡፡ ከንጉሱና ከባለሟሎቻቸው ጋር እራት እንዲቀርብም ተጋብዟል፡፡ ካርል ከስዊድን ይዟት የመጣው አውሮፕላን በተራራማ ስፍራዎችና አስከፊ በሆነ የአየር ጠባይ ሳቢያ የማታገለግል ሆና መገኘቷ እጅግ የሚያሳዝን ነበር፡፡ ይሁንና በተመደበለት በማንኛውም መጓጓዣ በማምራት፣  ከጦር ሜዳ አቅራቢያ ተጠምዶ የነበረ ፈንጂ በማምከን፣ የተጎዱ ሰዎችን ወደ ቀይ መስቀል ሆስፒታል በማመላለስ ኃላፊነቱን በቁርጠኝነት ከመወጣት አልቦዘነም፡፡ የስዊድኑ የጦር ሜዳ  ሆስፒታል በቦምብ  በተደበደበ ጊዜ ግዳጁን እየተወጣ ሳለ ከሞት ለጥቂት ተርፏል፡፡ እንዲህ መሰል አያሌ የሞት አደጋዎች ገጥመውታል፡፡
ቮን ሮዘን በኢትዮጵያ በነበረው ቆይታ ቢሾፍቱ የተባለችውን ትንሽ መንደር ጎብኝቶ፣  የበረራ ትምህርት ቤትና ለስራው የሚያስፈልገውን አውሮፕላን ማረፊያ መስራት  የሚቻልበትን መንገድ ጥናት አድርጎ፣ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያገለግሉ ሲቪል አውሮፕላን አብራሪዎች ይሰለጥኑበታል በሚል ግምት አየር ኃይል አቋቁሟል፡፡ ንጉሱም አልተቃወሙትም፤ ምክንያቱም አገሪቱ ከአየር የሚደርስባትን ጥቃት ለመከላከል በማትችልበት ሁኔታ ተጋላጭ ሆና ላለመገኘት ቁርጥ አቋም ነበራቸውና! ስለዚህ ውጤታማ የሆነ አየር ኃይል መመስረትና ለዚሁ  የሚሆኑትን አብራሪዎች ማሰልጠን ለነገ የማይባል አቢይ ጉዳይ ነበር፡፡ እንዲያውም ከዚያ በኋላ ንጉሱ የአየር ኃይላቸውን ዕድገት  የሚከታተሉት በከፍተኛ ንቃት ነበር፡፡ ለዚህ ሲሉም በቢሾፍቱ ላይ የእረፍት ጊዜ ማረፊያ ቪላ ሰርተው እንደነበር ተዘግቧል፡፡ ከሰገነት ላይ ሆነው ወደ አየር ኃይሉ እያነጣጠሩ  ካዴቶቹ ሲነሱና ሲያርፉ ሲመለከቱ ይውላሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ  የአብራሪዎች ቡድን ሲመረቁ በምረቃ ሥነስርአቱ ላይ ተገኝተው የአብራሪዎች አርማ የሆነውን ክንፍ በደረቶቻቸው ላይ ያኖሩላቸው ንጉሱ ራሳቸው ነበሩ፡፡ ካርል ጉስታቭ አጥጋቢ አገልግሎት መስጠት የሚችል የአየር ኃይል (ከስዊድኑ አየር ኃይል ጋር በመወያየት) በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰርቶ ለንጉሱ ማስረከብ ችሏል፡፡ ለነገሩ በወጣትነት ዘመኑ በፍጥነት መወሰንን በሚፈልጉ በርካታ ድርጊቶች ውስጥ አልፎ የመጣ ሰው ነበር፡፡  በበረዶ መንሸራተቻ በከፍታ ላይ መዝለል፣ የሞተር የፍጥነት ሩጫ ውድድር፣ በፈጣን ጀልባዎች መሽቀዳደምን በመሳሰሉ፡፡
በዚያን ዘመን በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሹመት እጅግ ወሳኝ ነገር ነበር፡፡ ነገር ግን  ሹመት ሁልጊዜ በውርስ የሚገኝ ነገር አልነበረም፡፡ ኃይለ ሥላሴ የፈቀዱትን ሹመት ለፈቀዱት ሰው በራሳቸው ፈቃድ ይሰጣሉ፡፡ ካርል ጉስታቭ በ1960 ዓ.ም በንጉሱ ቤተ መንግስት  በቀዩ ሳሎን የክብር ኒሻን ተሸልሞ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለነጻነት ተዋጊዎችና ለአርበኞች፣ በድርቅ ለተጎዱ፣ በረሀብና በወረርሽኝ ለተጠቁ ፈጥኖ ምግብ በማቅረብ፣ ለህክምና እርዳታ፣ ለአርብቶ አደሮች መሠረታዊ ፍጆታ የምርት እጥረት ሲያጋጥም የአየር በረራ አገልገሎት ለሚፈልጉት ሁሉ ፈጥኖ  በመድረስ አቅሙንና  ዘመኑን ሙሉ አገራችንን ሲያገለግል ኖሯል፡፡ ከጀርባው  የሚፈፀምበትን ሴራ ተቋቁሞ መስራት እንጂ   ፈጽሞ አማርሮ  አያውቅም፡፡
ቀይ መስቀል ውስጥ በህክምና አብራው በቅርበት የሰራች ነርስ ስለ ካርል ባሰፈረችው ማስታወሻ ይህን አኑራ ነበር፡፡… “ቮን ሮዘን ከብዙ ረጅምና አድካሚ ጉዞ በኋላ ወደ ቤተሰቡ ሲመለስ ዘወትር  የተሸበሸበ ፊቱ ቁልቁል  ተንጠልጥሎ መቆም ተስኖት እስኪወድቅ ድረስ በድካም ዝሎ ነበር የሚደርሰው፡፡ ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ ሳገኘው እንዲህ ያለ ገፅታ ነበረው፡፡ ነገር ግን በጣም የሚገርመኝ ከአንድ ሌሊት ዕረፍት በኋላ  የተሸበሸበ  ፊቱ ተመልሶ  ይዘረጋና ወደ ወጣትነት ሲመለስ ዘወትር  ፈገግታ  ከፊቱ  የማይለየው “ህይወት እጅግ መልካም ነገር ነው” ወይም ደግሞ “ማግባት እኮ ደስ ይላል” ወ.ዘ.ተ ከሚሉ መልካም ቃላት በቀር ክፉ ነገር የማይወጣው ከትናንቱ ፈጽሞ የተለየ ሌላ ሰው መሆኑ ነበር፡፡” (ገጽ 167)
የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ “በአየር በረራ” ሲሉ የሰየሟት አነስተኛ መጽሐፍ ፅፈው  ማሳተማቸውን “ድሮና ዘንድሮ”  በተሰኘ ግለ-ታሪካቸው ተጠቅሷል፡፡ የዚያን ጊዜው ወጣቱ መቶ አለቃ ግርማ፣ የካርል ጉስታቭ  የልብ ወዳጅ ነበር፡፡ የሚቀራረቡትም የቤተሰብ ያህል ነበር፡፡ ትስስራቸውም ብዙ ምእራፎች ውስጥ ይወሳል፡፡ በፎቶ የተደገፈ ሰፊ ሽፋን ሰጥቶት ካርል ወዝ ባለው አግባብ ተርኮታል፡፡ በካርል ኃላፊነት መረከብ የሚችሉ በቂ አብራሪ ኢትዮጵያውያን ሰልጥነዋል፤ ከእነዚህ መሀል ግርማ አንዱ ናቸው፡፡ ከአየር ኃይል በኋላም በስዊድንና በካናዳ የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ትምህርት ተምረው መመለሳቸውን የህይወት ታሪካቸው ላይ ተዘግቧል፡፡ ካርል ልባዊ ጓደኝነታቸውን በገጽ 286 ላይ ሹክ ይለናል፡፡… “ከብዙ ኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ጋር ያስተዋወቀን እርሱ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ  በሠራነው ስራ ሁሉ እጅግ ትልቅ ድርሻ ነበረው፡፡ በብዙ ረገድ ይረዳን ነበር፡፡ ከስራ ሰዓት ውጪ የሚያዝናናን መልካም ወዳጃችን ነበር፡፡ ብዙ ጊዜም ግብዣዎች ሰርጎችና ፓርቲዎች ላይ ይጋብዘን ነበር፡፡ ትከሻ እያንቀጠቀጡ የሚደነሰውን የኢትዮጵያን እስክስታ ያስተማረኝም እርሱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሳለፍናቸው መልካም ጊዜያት ሁሉ ከእርሱ ጋር ያሳለፍናቸው ነበሩ፡፡”
ተርጓሚው ደራሲ ሚካኤል ሺፈራው በሙያው አርክቴክት እንጂ ፓይለት አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ሙያዊ ቃላትን አግባብ ባለው ሁኔታ ቦታው ድረስ በመሄድ፣ ታሪኩ በተከናወነበት ስፍራ ተጉዞ በማጥናት…ለዚህ ትርጉም ስራው ያደረገው የማይናቅ ጥረት ሊደነቅ የሚገባው ነው፡፡ ምንም እንኳን አንዳንድ የቦታ ቀደም ሲል የምናውቃቸው የታሪክ ሁነቶችን የኋላ ታሪካቸውንና መነሻ ሀሳባቸውን አሳጥሮና መጥኖ ከማደላደል ይልቅ  በረጃጅም አረፍተ ነገሮች መደገማቸው (በወፍ ማስፈራሪያ እና በማስጠንቀቂያ ደውል ስለ ለመድናቸው) የደራሲው መገለጫዎቹ  ወይም ምልክቶቹ ናቸውና እንደ ጉድለት ልናየው አንችልም፡፡ መጽሐፉ የባለታሪኩ የካርል  ጉስታቭ ቮን ሮዘን ታሪክ ብቻ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያውያን የቅርብ ጊዜ የትዝታ ማህደር ጭምር ነው፡፡ ባለታሪካችን በማይጨው ዘመቻ መጀመሪያ ምዕራፍ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣበት 1928 ይጀምርና ሶማሊያ በዚያድ ባሬ እየተመራች ኢትዮጵያን ለማጥቃት በተለይ ኦጋዴንን ስትወር 1969 ላይ የሚጠናቀቅ የአርባ አንድ አመት ሰነድ ነው፡፡ የጠፋውን የታሪካችንን ዱካ በካርል በኩል በምልሰት እሚያስቃኝ የአባቶቻችንም ታሪክ ነው፡፡ ዛሬ እናፈርሳታለን በሚል የሚናቆሩባት አገራችን፤ እንዴት ያለ የላብና የደም ዋጋ ተከፍሎባት ከኛ ትውልድ እንደደረሰች የሚነግረን የዘመን ታማኝ ምስክር ነው፡፡ ካርል ሊኖርባትና ሊኖርላት ብቻ ሳይሆን ሊሞትላትም ለተዘጋጀላት አገራችን፣ የነበረው ብርቱ ፍቅር ከምንም በላይ ልብ ይነካል፡፡      




Read 1831 times