Saturday, 06 May 2023 18:37

ቀና በይ ቀን አለ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የጉያሽ ቁስል ለዘመን
ሲድን ሲያገረሽ ያመመን
አይቀርም አልሽርም እንዳለ
አይዞሽ እማማ ቀና በይ ቀን አለ፡፡
የምትል ግሩም ስንኝ አንድ ዘፈን ውስጥ አለች፡፡ አዎ...“ቀና በይ ቀን አለ፣” ከማለት የበለጠ ምን ተስፋ ሊኖር ይችላል፡፡
ሚያዝያውም እየተገባደደ ነው፡፡ ስምንተኛው ወር ማለት ነው፡፡ የሰሞኑ የነሀሴ ወርን የመሰለ ዝናብና ደመናም ብዙውን  ሰው እየደበተውና ትከሻውን እየከበደው ነው...ልክ የሀገራችን ሁኔታ ለብዙዎች እንደከበዳቸውና  እንዳሰጋቸው፣  ለረጅም ጊዜ ሲጠይቁ የቆዩትን ጥያቄ አሁንም እየጠየቁ ነው፡፡  “ኸረ ለመሆኑ መጨረሻ የሚባል ነገር ካለ፣ የሀገራችን መጨረሻ ምን ይሆን!”
 ፍቅር ከኛ እንዳይለየን
እንዲቃናልን ሥራችን
መጨቃጨቅ ይወገድና
ሠላም ይሁን ለሁላችን፡፡
ትናንት እንደተዜመው ዛሬም “ሠላም ይሁን ለሁላችን...” የሚሉ ድምጾች በብዛት ያስፈልጉናል፡፡
ከምንም ጊዜ በላይ በአስጊ ሁኔታ እየባሰባቸው ያሉ ሁኔታዎችን የማረጋጋት ሙከራዎችን ለማድረግ የሚሞከሩበት፣ በሁሉም ወገን እየተባባሱ፣ እየጋሙ ያሉ ስሜቶችን በተቻለ መጠን የማለዘብ ጥረቶች ሊደረጉ የሚገባባቸው ወቅት ውስጥ ነን፡፡  እንዲህም ሆነን እያለን ነው በሁሉም ደረጃ በግለሰብም ሆነ በቡድን ክፋት የበዛ የሚመስለው፡፡ በግንብ እንጠረው ብንል አጥረን የማንከልለው፣  ወደ ጓሮ ዘወር አድርገን ከዓይን እንሰውረው ብንል የማንችለው የሆነ ክፋት በበዛበት ዘመን ውስጥ ነን፡፡  በግለሰብነታችን መለያ የሆነና “እሱ እኮ እንዲህ አይነት ባህሪይ ያለው ሰው ነው...” ተብሎ በቃላት ሊገለጽ የሚችል ባህሪይ እያጣን የመጣንበት ጊዜ ውስጥ የገባን ነው የመሰለው፡፡ በርካታ ወገኖች እንዲህ አይነት አዙሪት ውስጥ የገባነው፤ “እኛ፣” ማለት ቀርቶ “እኔና እኔ ብቻ...” እያዳበርን ስለሆነ ነው ይላሉ፡፡
ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ምን መሰላችሁ... ቀደም ሲልም እኮ “እኔና እኔ ብቻ...” የምንል በርካቶች ነበርን፡፡ አሁን ችግሩ እየባሰ የመጣው በማህበራዊ ኑሮ ደረጃችን በፍጥነት ወደ ላይ የምንወጣ፣ በሌላ በኩል ከዛ ይበልጥ በፈጠነ መልኩ ደግሞ ወደ ታች የምንንሸራተት መብዛታችን፣ ለመውጣታችንም ለመውረዳችንም አሳማኝ ምክንያቶች ያለመኖራቸው ሁላችንም ተጠራጣሪዎች ስላደረገን፣  በእምነታችን፣ በማንነታችን፣ በአንደኛው ወገን ሳይሆን በሌላኛው ወገን በመሆናችን ወይም “ናቸው...” በሚል እርስ በእርስ በመጠራጠራችን  ወይም እጅግ ተራ በሆነ ምቀኝነት፣ ጥላቻ፣ እብሪት...ምን አለፋችሁ መአት ነገሮች አሉን፡፡ በታሪካችን እጅግ አስጊ፣ አሳሳቢ፤ ነገና ከነገ ወዲያ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት የማይቻልበት መጥፎ ዘመን ውስጥ ነን...መትረን መራመድ ካቃተን፣ አርቀን ማስተዋል ካቃተን...ሁላችንም ተሸናፊ የምንሆንበት አደጋ ጋር የተጋፈጥነበት ጊዜ፡፡
አንደኛው ሲክብሽ፣ አንዱ ያፈርስሻል፣
አንዱ ሲያሳድግሽ፣ አንዱ ይዘርፍሻል፣
አንዱ ሲሞትልሽ ደግሞ፣ አንዱ ይሾምብሻል፡፡
ምንድነው ነገሩ፣ ጥሩ ያልበቀለብሽ፣
ምንድነው ነገሩ፣ ዘር ያልበቀለብሽ፡፡
በሌላ በኩል ነገሮች እየጠነከሩና ስጋት እየበዛ ሲመጣ፤ ሰከን ያሉ፣ ከማንኛውም አይነት ውግንና የጸዱ አእምሮዎች “ኸረ ወዴት ናቸው!” ልንል በሚገባበት ጊዜ፣ በግለሰብ ደረጃም ጠባያችን እየተገለባበጠ፣ ነገራችን ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ ነው፡፡
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል በተለይ እኮ እንደ ሙዚቃ ባለሙያዎች አይነት የጥበብ ሰዎች የሚፈለጉበት ጊዜ ነው፡፡ አሁን እየበዙ እየተባዙ ያሉ ማህበራዊ ችግሮቻችንን እየነቀሱ የሚያሳውቁ፣ የመፍትሄ ሀሳብ እግረ መንገድ ማቅረብ የሚችሉ፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ሰላም፣ ሰላምና ሰላምን ብቻ በህዝብ ልብ ውስጥ የሚያሰርጹ ሥራዎችን የሚያቀርቡ ባለሙያዎች ያስፈልጉናል፡፡
እናላችሁ...ይቺን ከአንዲት የቀድሞ የአቤ ጉበኛ መጽሐፍ ላይ ያለች ግጥም እዩልኝማ፡፡
ያንዳንዱ ሰው ጠባይ እጅግ ያስደንቃል
ሲንቁት አክብሮ ሲያከብሩት ይንቃል፡፡
ሰው ሲደሰት አዝኖ ሰው ሲያዝን ይስቃል
ሲሸሹት ይቀርባል ሲቀርቡት ይርቃል፡፡
እንዲያው ምን ያደርጋል
እንዲያው ምን ያደርጋል ቢደረድሩ ቃል
“ዐመሉ ግራ ነው!” ይህ ብቻ ይበቃል፡፡
ይቺ ከብዙ አስርት ዓመታት በፊት የተጻፈች ስንኝ የአሁን፣ የአሁን አትመስላችሁም! የምትሰሙት ነገር ሁሉ እኮ ጉድ ነው፡፡ “እውነት ሰዋችን ይህን ያህል ተጨካክኗል!” የሚያሰኙ መአት ነገሮች ትሰማላችሁ... መዘርዘሩ አስፈላጊ አይደለም እንጂ!
 በሁሉም ደረጃ ያለውን የምር እኮ ቴክኒካዊ ነገሮች ምናምን ትተን በተለይም ማህበራዊ የምንላቸውን አይነት መልእክቶችን በተመለከተ ቀደም ያሉ የጥበብ ሰዎች የሠሯቸውን ሥራዎች መለስ ብላችሁ ስትመለከቱ፣ የእውነትም እኮ የሚገራርሙ ሀሳቦችን ያነሱ ነበር... በርካታ አሥር ዓመታትን ተሻግረውም መልእክታቸው የማይቀዘቅዝ፡፡
እንደ ወንዝ ድንጋይ አሳ እንደላሰው
ሙልጭልጭ እያለ አስቸገረኝ ሰው፣
እድሌ ሆነና የጭንቅ የመከራ
አልመሰግንም ምን ጥሩ ብሠራ
አወይ የእኔ እድል ሞኝ ነው ተላላ
እኔ በለፋሁት ተመስጋኙ ሌላ፡፡
--ተብሎ ነበር፡፡ ይቺም የዛሬ፣ የዛሬ  አትመስላችሁም!
እናላችሁ... ሀገር ፈተና ላይ ነች፡፡ መቼም በጎ፣ በጎውን ማሰብን የሚያክል ህክምና የለም፡፡ እናም... ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ ዜጋ በጎውን ያስባል... ለራሱም፡ ለወገኑም፣ ለሀገሩም፡፡  ግን ደግሞ በጎውን ማሰብ የምንችለው እውነታው ላይ ጀርባችንን አዙረን፣ ሀቁ ፊት ለፊታችን አፍጥጦም “ዐይኔን ግንባር ያድርገው!” ብለን ሊሆን አይችልም...“ህመሙን የደበቀ መድሀኒት ማግኘት አይችልም...” አይነት ነገር አይደል የሚባለው! በሽታን ደብቆ መድሀኒት ፍለጋን አይነት ነገሮች በብዛት ስለምናይ ነው፡፡
በአንድ ወቅት እንዲህ የምትል ስንኝ አንድ ሙዚቃ ውስጥ ነበረች፡፡
ቆሜ... ልመርቅሽ
ተቀበይኝ እማ
ህይወትን መርቀሽ
ሰጠሺኝ እኔማ
ይህ ቀረኝ የምለው የሚቆጨኝ በዓለም
ኢትዮጵያ እድሜ ለአንቺ ያላየሁት የለም
አንገትሽ እራስሽን ችሎ ልየውና
ማግስቱን ይውሰደኝ አስር ሞት ይምጣና፡፡
እንዲህ የሚሉ ድምጾች በብዛት ያስፈልጉናል፡፡
የጉያሽ ቁስል ለዘመን
ሲድን ሲያገረሽ ያመመን
አይቀርም አልሽርም እንዳለ
አይዞሽ እማማ ቀና በይ ቀን አለ፡፡
አዎ...ቀና፣ ቀና፣ ቀና በይማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 890 times