Saturday, 06 May 2023 18:39

“ጠመንጃ እና ሙዚቃ”

Written by  ዘሪሁን ብርሀኑ (ረ/ፕሮፌሰር) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲት
Rate this item
(2 votes)

ርዕስ፡ ጠመንጃ እና ሙዚቃ ደራሲ፡ ይነገር ጌታቸው አሳታሚና አከፋፋይ ፡-
ጠይም መጻሕፍት መደብር የገጽ ብዛት፡ 37

መግቢያ
የኢትዮጵያ ሙዚቃን ረዥም ጉዞ ለተከታተለ እና ላስተዋለ ሰው፡ ሞያው ካለው የጠለቀ እና የተወሳሰብ ሀገራዊ እና ማህበረሰባዊ ቁርኝት አንፃር ታሪኩን በአንድ ሰድሮ ማስቀመጥ ምን ያህል አዳጋች እንደሆነ ማሰብ አይከብደውም። ይህን ከባድ እና ውስብሰብ ታሪክ በአንድ ግለሰብ ቀርቶ በተቋም ደረጃ እንኴ በርካታ ጊዜ እና አቅም የሚጠይቅ ነው። በተለይ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ከመላው ኢትዮጵያውያን ባህል ፣ አኗኗር፣ ሀይማኖት እና ፖለቲካ ጋር በእጅጉ የተያያዘ በመሆኑ አንዱን ጫፍ ሲነኩት ሰፊው ባህር ስለሚታይ የስራውን ከባድነት በግልፅ የሚያሳይ ነው። ይህ “ጠመንጃ እና ሙዚቃ “ የተሰኘው መጽሀፍ ሊፈታ የሚታትረው ይኼን ቋጠሮ ነው:: በአንድ ግለሰብ ያውም በወጣትነት ዕድሜ ላይ በሚገኝ ጐበዝ የአብሪ ጥይት ያህል የሚቆጠር የመክፈቻ ስራ ነው:: ይሄን ስል ይህ መፅሀፍ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ የሞያውን ታሪክ የዳሰሰ የመጀመሪያው ወይም ብቸኛው ነው ማለቴ አይደለም:: በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና መምህራን፣ በሙዚቃ ባለሞያዎች፣ በጋዜጠኞች ፣ እንዲሁም ሞያው እና ጥናቱ ይገደናል ባሉ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ባለሞያዎች ከተለያየ አቅጣጫ ፣ በተለያየ መጠን፣ በተለያዩ ቋንቌ ጥናቶች እና ስራዎች ቀርበዋል :: ነገር ግን በእኔ እይታ ይሄ ዛሬ የምንመርቀው “ጠመንጃ እና ሙዚቃ” የተሰኘው መጽሐፍ በሚከተሉት ዋና ዋና ብዬ በማስቀምጣቸው ሀሳቦች ከሌሎች ህትመቶች ለየት አድርጌ እመለከተዋለሁ።
ሙዚቃን ከነማጀብያዋ
የመጀመርያው ጉዳይ መጽሀፉ የሙዚቃን ጉዳይ ለብቻው ነጥሎ የተመለከተ አለመሆኑ ነው፡፡ በዩኒቨርስቲ የምርምር ስልት ስናስተምር እና ስንማር አንድን ርዕሰ ጉዳይ ጉዳዩን የምርምር አጀንዳ ያደረጉትን፣ ወይም ለታሪክነት መሰረት የሆኑትን ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በሚገባ ማጤን የምርምሩ መሰረታዊ ገዢ ሀሳብ ነው እንላለን። ማለትም የምንመረምረውን ጉዳይ፡ ጉዳዩን ለብቻው ነጥሎ ከመተንተን ይልቅ፣ ያንን ጉዳይ እንዲያ እንዲሆን ምክንያት የሆኑትን አጃቢዎች እንደተፅኗቸው መጠን መመርመር ማለት ነው:: ለምሳሌ አንድን ቴአትር ወይም ሙዚቃ ለመገምገም ቴአትሩ ወይም ሙዚቃው የታየበትን ዘመን ማህበረ ፖለቲካዊ ታሪክን ማጤን ለምንሰራው ትንተና የተሟላ ግብዓት ይሆነናል።
“ጠመንጃ እና ሙዚቃ” ይህንን ስልት ባግባቡ እና በተጠና መልኩ ተግባራዊ አድርጐታል እላለሁ፡፡ ቴዎድሮስ ገብሬ “በይነ ዲሲፕሊናዊ” ብሎ የተረጐመው Interdisciplinary የሆነው የጥናት እና የጽሁፍ ስልት፤ ይነገር ጌታቸው በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ጥናቱ ውስጥ ተክኖበታል። ይህ መፅሀፍ የሙዚቃ ታሪክ ብቻ አይደለም - የሀገር ፣ የሀይማኖት ፣ የባለሞያዎች ፣ የፖለቲካ እና የስልጣን ሽኩቻ ታሪክ ነው:: እነዚህ በጣም የበዙ እና ውስብስብ ታሪኮች ደርዝ ባለው መንገድ ተጠንተው እና ተሰናስለው መቅረባቸው ነው ዛሬ የዚህን መፅሀፍ ምስል የፈጠሩት :: የቤተ ክርስቲያን ታሪክ - ከማህበረሰብ አኗኗር ታሪክ ጋር፣ የቤተመንግስት ታሪክ ከስልጣን ሽኩቻ ጋር ፣ የኦርኬስትራና ባንድ ታሪክ ከባለሞያዎች የግል ታሪክ ጋር፣ የመብት እና የነፃነት ጥያቄዎች ከፈጠራ ችሎታ ጋር በጋራ በአንድ ማዕድ ቀርበዋል። ይሄንን ማዕድ ነው ይነገር “ጠመንጃ እና ሙዚቃ “ ሲል የሰየመው።
ይህ የአፃፃፍ ስልት ለይነገር የመጀመሪያው - ወይም ሁለተኛው አይደለም። የመጀመሪያው ያልኩት ከዚህ ቀደም ካሳተመው በ“የከተማው መናኝ “ ከተሰኘው የሙዚቃው ባለሞያ ኤልያስ መልካ የህይወት ታሪክ አንጻር ሲሆን ሁለተኛው አይደለም ማለቴ ከዚህ መፅሀፍ ቀድሞ የተፃፈው ይሄ መሆኑን ስለማወቅ ነው፡፡ ያነበባችሁት እንደምታስታውሱት ደራሲው የኤልያስን የህይወት ታሪክ አንደወረደ አልሰነደውም፡፡ ነገር ግን ኤልያስ ከነበረበት ማህበራዊ፣ ሀይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ ህይወት ጋር እያሰናሰለ አቀረበው እንጂ :: ይህንን መንገድ በይነገር አፃፃፍ ውስጥ “ጠመንጃ እና ሙዚቃ” ቀድሞ የተለመው ነው::
በሁለተኛ ደረጀ ይህ መጽሀፍ ሰፊውን የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ በተቻለው ሁሉ መስመር አበጅቶ ድንበር ከልሎ ለማቅረብ ሞክሯል። ከላይ እንደገለጽኩት በሰፊው ታሪክን፣ መለስ ሲል ደግሞ የሞያዎችንና የባለሞያን ታሪክ መፃፍ (በተለይ በቂ የተሰነደ መረጃ በሌለበት ሀገር እና ማህበረሰብ) እጅጉን ሲበዛ አዳጋች ነው። ጊዜን ይወስዳል፤ አቅምን ይፈትናል። ለምሳሌ በዚህ መጽሐፍ እንደምናነበው ትልልቅ የምንላቸው ተቋሞቻችን - መጽሀፉ የተመረቀበት የሀገር ፍቅር ቴአትር የቀድሞ መጠርያው “ያገር ፍቅር ማኅበር” ጨምሮ፤ አመሰራረታቸው እንዲሁም ማን እንደጀመረው? የት እንደተጀመረ? ቦታው የት እንደነበር? የሚለው አከራካሪ ሀሳብ ሆኖ “ያገር ፍቅር ማህበር” የተሰኘውን ምዕራፍ አራት ገፅ ያህል ይወስዳል። ተሰንዶ የተቀመጠ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ፣ እርስ በራሱ የሚጣረስ ታሪክ ያለን ስለሆንንም ለእንዲህ ያለ ተመራማሪ ፈተናውን ያበዛዋል። ይህ መጽሀፍ በተቻለው አቅም ለማሸነፍ ሞክሯል ብዬ የማስበው ይህንን የታጠረ ድንበር ለመስበር ሙከራ ማድረጉ ነው፡፡ በተቻለው አቅም አወዛጋቢ ታሪኮችን ከነታሪኮቹ ባለቤቶች ሀሳቦች ጭምር በይፋ አስቀምጧል፡፡ አንዳንዶቹን ለአንባቢው ፍርድ ትቶታል፡፡
በሶስተኛ ደረጃ የአፃፃፍ ስልቱን በጥቂቱ ለመመልከት እወዳለሁ። በተለምዶ የምርምር ፅሁፎች በአቀራረባቸው ደረቅ ስለሚሉ ለዘወትራዊ አንባቢ ብቻም ሳይሆን በአካዳሚ ውስጥም አስቸጋሪ ይሆናሉ፡፡ በመሆኑም አሁን እየተለመደ እና እየተመረጠ የመጣው ስልት አንባቢ ሳይሰለች፣ አካዳሚያዊ የምርምር ቃላት ሳይንጋጉ ሳቢ በሆነ መንገድ ታሪክ የመንገር ጥበብ ነው- Post Academic Writing (ድህረ አካዳሚያዊ አፃፃፍ) ይባላል:: ይህም ማለት ሰፊውን የምርምር ሥራ እንደ አንድ የፈጠራ ታሪክ አሳምሮ አስውቦ መናገር መቻል ማለት ነው-አካዳሚያዊ ፅሁፍ ታሪክ ነገራ ነው እንዲሉ፡፡ ይነገር በዚህ መጽሀፍ የተካነበት ጉዳይ ይህ ነው:: የጋዜጠኝነት ሞያውን ተጠቅሞ ፅሁፉ የምርምር ክብደቱን ሳይለቅ፣ ስነ ፅሁፋዊ ውበቱ ሳይጠፋ ለሁሉም እንዲሆን አድርጐ በሚስብ መልኩ ከትቦታል። በተለይ ለጥናቱ መግቢያ ያደረጋቸው ሰዋዊ ታሪኮች /Human stories/ ዋናውን የምርምር እንኳር ሀሳብ ሳይለቁ ነገር ግን ደጋፊ እና አጋዥ ሆነው ይታያሉ :: አስረጅ ብንጠቅስ።  ረፋድ ነው !
ታኅሳስ 12 ቀን 1955 ጋዜጠኛ ጌታቸው ደስታ የተወዳጁን ያገር ፍቅር ማኅበር ድምፃዊ አሰፋ አባተ ዜማ በኢትዮጵያ ራድዮ ጋበዘ፡፡ በአዲስ አበባ ዋና ዋና አደባባዮች የነበሩት ድምጽ ማጉያዎችም ያንን የጊዜው ተወዳጅ ሙዚቃ አስተጋቡ፡፡ ለደስታና ተድላ የታሰበው ይህ ዜማ ግን ፒያሳ ላይ ብዙዎችን በእንባ እያራጨ ነበር፡፡ ለቀብር የወጣው ሕዝብ በድንገት ሕይወቱ ያለፈውን አሰፋ አባተ አጅቦ ምኒልክ አደባባይ ሲደርስ መረጃው ያልነበረው ጌታቸው ደስታ ፤ሙዚቃውን በራዲዮ ሲጋበዝ እኩል ተገጣጠሙ፡፡ ወዲህ በግራማፎኑ የሚሰማው የአሰፋ አባተ ዜማ ወዲያ ለቀብር የመጣው ሕዝብ ዋይታ ፒያሳን በጉራማይሌ ስሜት ናጣት፡፡ ዛሬ ተንጋሎ የቀብር ቦታው የደረሰው ሰው ከትናንት በስትያ በዓየር ኃይል ይህን ሙዚቃ ተጫውቶታል፡፡ስለሆነም ከፊሉ ወገን ሕመሙ ሳይሰማ ሕልፈቱ መነገሩ አስደንግጦታል፡፡ የሰው እጅ አለበት የሚል ጉርምርምታም ይሰማ ይዟል፡፡ ኢዩኤል ዮሐንስ አሁንም በሀሳቡ እንደፀና ነው፡፡ የአሰፋ አባተ አስከሬን ሳይመረመር ሊቀበር አይገባውም ብሎ መሞገቱን ገፋበት፡፡126 ይሁንና በቦታው የነበረው ህዝብ “ከዚህ በኋላ ምን ሊፈይድ ነው ይብላኝ ለሟች እንጂ” በማለት ተቃወመው፡፡ ተደማጭነቱና ሌሎችንም ሰዎች ማሳመኑ ተጨምሮበት ይመርመር የሚለው ሀሳብ ተቀባይነት አገኘ፡፡ በዚህ መነሻም ለቀብር የመጣው ሕዝብ በምኒልክ ሆስፒታል ተገኝቶ ሀሜቱን በሐኪም ውጤት ሊያረጋግጥ ወደዛው ተጓዘ፡፡ በሙዚቃው ቀብሩን ያጀበው አሰፋ፣ በሕልፈቱ ዋዜማ ከጥላሁን ገሠሠ እና ግርማ ብሥራት ጋር ሲጫወት ነበር-የሕመም ስሜት የተሰማው፡፡ እናም “ጥልሽ ግርምሽ እኔ ልሂድ” አላቸው፡፡ ተነስተው ሸኙት፡፡ ከዶሮ ማነቂያ የተነሱት ጓደኛሞች፣ ያን ወዳጃቸውን ቤቱ አደረሱት፡፡ በነጋታው “እንዴት ሆንክ?” አሉት፤ ለውጥ የለውም ሲል መለሰ፡፡ ሞቱን ቁጭ ብሎ አልጠበቀም፡፡ አሮጌው ፖስታ ቤት አጠገብ ወዳለ ክሊኒክ አምርቶ መርፌ ተወግቶ የሚዋጥ መድኀኒትም ተቀብሎ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ስለ ህልፈቱ እንጂ ስለሆነው ጉዳይ የሚያወራ አልተገኘም፡፡ ታኅሣሥ 11 ቀን 1955 በ 28 ዓመቱ ንጋት ላይ ሕይወቱ ማለፉ ተነገረ፡፡ (ይነገር፤ 127)
ይህንን ታሪክ ካጫወተን በኋላ የዝነኛውን ድምፃዊ አሰፋ አባተን የህይወት ታሪክ እና ስራዎቹን ይተነትናል፡፡ በቀጣዩ አንቀፅም ታሪኩን ይቋጫል፡፡
…………………………………………….
አሰፋ አባተን በተመለከተ የቅርብ ጓደኛ የነበሩት አቶ ግርማ ብሥራት እንደ ነገሩኝ፤ ሙሉ ሱሪ መልበስ የማይወድ፤ ለያገር ፍቅር ማኅበር ድምፃዊያን መከታ የነበረ ጀብደኛ ሰው ነው፡፡ በውቤ በረሃ መዝናናት ይወዱ የነበሩት የያኔዎቹ ሙዚቀኞች፤ ፀብ ቢኖር እንኳን አሰፋ አለልን ይሉት እንደነበር አውግተውኛል፡፡ አሰፋ ለመጨረሻ ጊዜ ያስቀረጻት ሙዚቃው “የማትበላ ወፍ” ስትሆን፤ ቀብሩም የታጀበው በእሷ ነበር፡፡ (ይነገር፤ 128)
ዘመናዊነትና የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ታሪክ ምሁራን በተለያየ መንገድ አስተሳሰረው ሊመለከቱ ሞክረዋል። የቅርብ ምሳሌአችን Modernist Art in Ethiopia የተሰኘው የዶ/ር ኤልሳቤጥ ወ/ጊዮርጊስ ነው:: በዛ ባሉ ምሁራን ዘንድ የአድዋ ድል እና እሱን ተከትሎ የመጣው ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ እና ማህበራዊ ለውጥ፡ የኢትዮጵያ ዘመናዊነት ጅማሮ ወይም የጉዞ መነሻ ተደርጐ ይወሰዳል። ይነገርም በዚህ መጽሐፍ ይህንን ጐራ የተቀላቀለ ይመስላል። ከሁለተኛው የጣልያን ወረራ ቀደም ብሎ እና ከዚያም በኋላ የተቀጣጠለው የፖለቲካ እና የአስተዳደር ለውጥ ኪነ ጥበቡን በሰፊው በተለይ ግን ሙዚቃን በሚገባ አነቃንቆታል። በልዩ ደግሞ የአዲስ አበባ እንደከተማ መስፋፋት አስተዳደራዊ እና ፖለቲካዊ ብቻም ሳይሆን ኪነጥበባዊ አንድምታም ነበረው። በተለይ ከ1953 መፈንቅለ መንግስት ሙከራ በኋላ፡ የአፄ ሀይለስላሴ መቀመጫቸውን ወደ ኢዮቤልዩ ቤተ መንግስት መቀየር :- ይህንንም ተከትሎ የመጡት የመንግስት ቢሮዎች ግንባታ፣ የመንገድ እና መዝናኛ ግንባታ----ከአራት ኪሎ አንስቶ ፒያሳ ማዘጋጃ ቀጥሎም ቸርችል ወደ ታችም ወደ  ሀይለስላሴ ቴአትር ከፍ ስንል ደግሞ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር...... ይህ ለውጥ በራሱ ይዞት የመጣው በዛ ያሉ በረከቶች ነበሩት። ከነዚህም አንዱ በሙዚቃችን የተቀጣጠለው የፈጠራ ሀይል ነበር። በተለይ በዘመን መለወጫ በቀድሞ የሀይለስላሴ ቴአትር፣ አሁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ልደት አዳራሽ የታየው ፉክክር እና የአዲስ ፈጠራ ውጥረት በዚህ መፅሀፍ በደንብ ተዳስሷል። በተለይ እንደኔ ቆየት ያሉ ሙዚቃዎችና ታሪኮችን ለምታጣጥሙ ደግሞ መጽሀፉ ሲበዛ ጠቃሚ ነው:: እነዚህን ጉዳዮች በተነተነባቸው ክፍሎችም ሰፊ የሃሳብ ሙግትም ይዞ ይነሳል፡፡ ለምሳሌ የአድዋን ታሪክ ሲተረክ ከዋና ዋና የጦር መሪዎች ጀብዱ በቀር ሌሎች ተያያዥ/አጋዥ ጉዳዮች አልተተረኩም ይለናል፡-
የኢትዮጵያ ታሪክ እጅጉን ለፖለቲካ ያደላ ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም የአንጋቹን እንጂ የአራሹንና የቀዳሹን ትዝታ የሰነዱልን ብዙ አይደሉም፡፡
ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለማርያምም ይህ አስቆጭቷቸው ይመስላል የአድዋን ድል ዋና ባለቤትነት ልብ ላልተባሉት በቅሎዎችና ሴት አገልጋዮች የሚሰጡት፡፡ ተክለሐዋርያት እንዲህ ይላሉ፤ “የሴቶችን አገልግሎት ስገምት ደግሞ የበቅሎዎቹ አገልግሎት ይታወሰኛል፡፡ በመጨረሻም ድምሩን ስንገምተው የአድዋ ድል የተገኘው በሴቶች አገልጋዮችና በበቅሎዎች ብርታት መሆኑ ይታወቀኛል፡፡”53 ትረካቸው ለሰርኩ ዓለም ሐተታ ብርቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የጦርነቱን ድል አስመልክቶ ሌሎች ባለድርሻዎች መኖራቸው የሚያከራክር አይደለም፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አዝማሪዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የሚይዘውን የአድዋ ድል ታሪክ የዘገቡልን የአገር ውስጥ ጻሕፍት በአውደ ውጊያው የዛለውን ያበረቱትን፣ወደ ኋላ የቀረውን የገፋፉትን አዝማሪዎች በወጉ አላስታወሷቸውም፡፡ (ይነገር፤ 19)
ይህ መከራከርያ ነው ረዥሙን የመፅሀፉን ጉዞ የሚያስጀምረው፡፡ ካልተነገሩ ሰፊ ታሪኮቻችን መሃል፤ ካልተተረኩ ጥልቅ ህይወቶቻችን ውስጥ አንድ የሚገደውን ጉዳይ መዝዞ መተንተን፣ መመርመር፡፡
ከዘመናዊነት ትንተና ጋር በተያያዘ አንድ ትኩረትን የሚስብ ጉዳይ ደግሞ አለ፡፡
ይህም በተለይ የውጭ ሀገር የሙዚቃ አሰልጣኞች እና በሀገራችን የሙዚቃ ባለሞያዎች ዘንድ የሙዚቃ ስልት ምርጫ ላይ የተደረጉ ትግሎች ናቸው፡፡ ሀገርኛ የሙዚቃ ስልቶች በማህበረሰቡ ዘንድ እንዲስፋፉ እና እንዲታወቁ በሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ባለሞያዎች እና የራሳቸውን ሀገር ባህል ማስለመድ በሚፈልጉ የውጭ ሀገር ዜጎች መሀል የሚታየው መፋተግ ሰፊ የሆነ ማህበረ ፖለቲካዊ ዓውድን የሚያሳየን ነው፡ ለምሳሌ፡ በቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ እና ኬቮርክ ናልባንዲያን እንዲሁም ብርጋዴር ጄኔራል እሸቴ መኮንን  እና አንድሬ ኒኮ መሀል የነበረው ፍጥጫ ከዚህም ከፍ ያለ ጥናትን የሚጋብዝ  ነው፡፡  
ብርጋዴር ጄነራል እሸቴ መኮንን ከንጉሡ በዓለ ሲመት በኋላ ከፍ ያለ ዕውቅናን ቢያገኝም ከክቡር ዘበኛው የሙዚቃ አሰልጣኝ አንድሬ ኒኮ ጋር ግን ተጣጥሞ መጓዝ አልቻለም፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አስቀድመን በዮፍታሔ ንጉሴና ኬቮርክ ናልባንድያን መካከል መቃቃር ፈጥሯል ያልነው የትውፊትና የምዕራቡ ዓለም አጨዋወት ፍጥጫ ነበር፡፡ እሸቴ በምዕራቡ ዓለም የሙዚቃ መሣሪያዎች የሀገረሰብ ዜማዎችን መጫወት አለብን የሚል አቋም ሲያራምድ፣ የክፍሉ አሰልጣኝ አንድሬ ኒኮ በአንፃሩ ነገሩን የማይጠቅም ሲል አጣጥሎታል፡፡
በመሆኑም ከአብሮነት ይልቅ መገፋፋትና መፎካከሩን መረጡ፡፡በመጨረሻም ተለያዩ፡፡ (ይነገር፤ 77)   
ሌላው የዚህ መጽሐፍ ልዩ ባህርይ ቴያትር እና ሙዚቃን በአንድ አዋድዶ ማቅረቡ ነው:: በተለይ በቴአትሩ ዓለም ሁነኛ የሆኑ ሰዎች እና ተቋማት በሙዚቃውም ዘርፍ ሌላ መልክ ይዘው እናገኛቸዋለን። በተለይ ሁለቱ የትምህርት ቤት ቴአትሮችን የመሩት ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ እና መላኩ በጎሰው እዚህ በሙዚቃው ዘንድ ስማቸው ጐልቶ ሲጠቀስ እናስተውላለን፡፡
 የሀገር ፍቅር ቴአትር፣ የሀይለስላሴ ቴአትር እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባህል ማዕከልም ልክ እንደ ቴአትሩ ሁሉ በሙዚቃ ስራም ጐልተው ይታያሉ። ይህ የሁለቱ ሞያዎች መገናኘትም በተለይ ሁለቱን ሞያዎች ያሳደጉትን ዋነኛ ባለሞያዎችን እንድናስባቸው፤ የሞያ ድርሻቸውንምን ከፍ አድርገን እንድንገምተው እድል ይሰጠናል፡፡
በመጨረሻ የማነሳው ሀሳብ ቀደም ብዬ ካነሳሁንት የአድዋ ሃሳብ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በዚህ መፅሀፍ በጣም ከመሰጡኝ እንዲሁም ደግሞ የፀሀፊውን ብቃት እና የተመራማሪ የንስር ዓይንን ያየሁበት ምዕራፍ “ዓይነ ሥውራን እና የኢትዮጵያ ሙዚቃ”  የተሰኘውን ነው፡፡ ይህ ምዕራፍ ልክ እንደ አድዋው በቅሎዎች እና አዝማሪዎች ሁሉ የኢትዮጵያ ኪነጥበብ ሲጠና እና ሲነገር በብዛት የሚታለፍ ምዕራፍ ነው ብዬ ስለማምን ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ምዕራፍ የተሟላ የሚመስለውን ነገር ግን የጎደለውን የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ የአይነ ስውራንን የሙዚቃ ሚና በማካተት ምሉዕ ለማድረግ ይጥራል፡፡ ምዕራፉን ሲጀምርም፦
ዓይነ ሥውራን በአገራችን ታሪክ ጥናት ውስጥ ያላቸው ሥፍራ እምብዛም ነው፡፡
ይህ ግን በአገሬው ታሪክ ውስጥ ረብ ያለው ነገር ካለመፈጸም ጋር አይተሳሰርም፡፡እንደውም የኢትዮጵያ ዓይነ ሥውራን ከሌላው ዓለም በላቀ መልኩ ለቤተ-መንግስቱም ሆነ ለቤተ-ክሕነቱ ቅርብ ሆነው ኖረዋል፡፡
 ምልከታችንን ከመካከለኛው ዘመን እንጀምር ብንል ከአጼ ይኩኖ አምላክ እስከ ዳግማዊ ቴዎድሮስ የሥልጣን ዘመን ዓይነ ሥውራን የመንግስቱ አማካሪና የቤተ-ክሕነቱ ሥርዓት ተሟጋች ሆነው መዝለቃቸው አይካድም፡፡ ለዚህ ደግሞ ኤስድሮስ፣አርከለዲስ ፣ ምናሴ በቀለና ደብሪቱ መኮንን ተጠቃሽ ናቸው፡፡(ይነገር፤ 191)    
የነዚህን ሰዎች ታሪክ ጠቅሶ መከራከርያውን ካፀና በኋላ ወደ ሙዚቃ ታሪክ ያቀናል፡፡ እሱ በራሱ ሌላ ታሪክ ነው፡፡
“ጠመንጃ እና ሙዚቃ” በዘመናዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ታሪክ ሁነኛ ስፍራ የሚሰጠው እና በተለምዶ “የታህሳስ ግርግር” እየተባለ የሚጠራውን የአስራ ዘጠኝ ሀምሳ ሶስቱ የንዋይ ወንድማማቾች መፈንቅለ መንግስት ሙከራ፣ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ የከፈተውን አዲስ ምዕራፍ ከጅምሩ አንስቶ ያስቃኘናል፡፡
የክብር ዘበኛ ጦር፣ የምድር ጦር፣ እና ፖሊስ በስራቸው ያቋቋሟቸው የሙዚቃ ቡድኖች፣ የሀገር ፍቅር እና ብሄራዊ ቴአትር ያሰለፏቸው ባለሞያዎች፣ ከነዚህ ውጭ ሆነው የተሰለፉ ታላላቅ የኪነጥበብ ፈርጦች በመፅሀፉ ተካተዋል፡፡ በተለይ የጦር ቡድኖች ኦርኬስትራ ዘመን መክሰም የጀመረበትን አጋጣሚ ከ “ታህሳሱ ግርግር” መሀል ይነገር አንጥሮ ያወጣበት መነሽር የንግግሬ መቋጫ ላድርገው፡፟     
የአራዳ ጊዮርጊሱ አለቃ ንዋይ ተክለሐይማኖት ሁለተኛ ልጅ ያስነሳው ሰደድ የበላው የጦሩን አለቆች ብቻ አልነበረም፡፡ በአገሪቱ ሙዚቃ ውስጥ ተፎካካሪ የነበሩ የአራት ኦርኬስትራ መሪዎችን አሳጣ፡፡ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ዕድገት ጉልህ ሚና የነበራቸው ከዋክብት ብርጋዴር ጄነራል መንግስቱ ንዋይ ፣ብርጋዴር ጄነራል ጽጌ ዲቡና መኮንን ኃብተወልድ ከኪኑ ሰማይ ላይ ወደቁ፡፡ የብርጋዴር ጄነራል መንግሥቱ ተግባር ክብር ዘበኛ ኦርኬስትራን ለወራት ከሥራ ውጭ አደረገው፡፡የመኮንን ኃብተወልድ ሞትም የሀገር ፍቅር ማኅበር ገቢን እያደረቀ ሄዶ ሰራተኛ እስከመቀነሰ አደረሰው፡፡ የብርጋዴር ጄነራል ጽጌ ማሸለበብም ከሲምፎኒ እስከ ጃዝ የተዘረጋውን የፖሊስ ኦርኬስትራ እንቅስቃሴ አኮሰመነው፡፡
የዚህ ሁሉ ጥቅል ድምርም ከሌሎች ምክንያቶች ጋር ተጨምሮ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ወደማያወቀው አዲስ ልማድ ወሰደው፡፡ ከሥራቸው የታገዱ የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ አባላት በልቶ ለማደር እጃቸው ላይ ባሉ የሙዚቃ መሳሪያዎች በምሽት ቤቶች ሙዚቃን መጫወት ጀመሩ፡፡ የሌሎች ኦርኬስትራ አባላትም ከመደበኛ ሥራቸው ጎን ለጎን የምሽት ሙዚቃን ልማዳቸው አደረጉ፡፡
አዲስ አበባም በባንድ ሙዚቃዎች ትታጠን ጀመር፡፡ ነዋሪዎቿም ሰርክ የኦርኬስትራን ሙዚቃ መናፈቅ ትተው ወደታወቁት ሆቴሎች ጎራ ይሉ ያዙ፡፡(ይነገር፤ 264)
ይልና ወደ ባንዶች እና ግለሰቦች ይዞራል፡ ራስ ባንድ ... ዘ- ሶል ኤኮስ ባንድ ... ኦል ስታር ባንድ… ኢትዮጵያዊው ፌላ ኩቲ ... ራሱን አዳኙ ግርማ ...የዓለማየሁ -ዓለም ... በጣቶቹ የሚጮኸው ሰው ... የመርካቶው ኤልቪስ ... ተሾመ ምትኩ ... ባሕታ ገብረሕይወት…. እያለ ይቀጥላል፡፡
መፅሀፉ በኪነጥበቡ መንደር ላሉ ብቻ ሳይሆን ታሪክን ማንበብ እና መመራመር ለሚወዱ፤ ሰፊውን የኢትዮጵያን ማህበራዊ ታሪክ ማወቅን ለሚሹ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዘመናዊ ጉዞን መመርመር ለሚፈልጉ ሁሉ ሁነኛ ምርጫ ይመስለኛል፡፡Read 1439 times