Saturday, 06 May 2023 18:45

ለቻይና የጠቀሙ፣ ያበለፀጉና ያፈረጠሙ ሦስት መርሆች ለኢትዮጵያም ይበጃሉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ሦስቱ መርሆች፣ የመታቀብ መርሆች ናቸው። ከአላስፈላጊ ጦርነት መታቀብ፣ ኢኮኖሚን አለማደናቀፍ፣ በነውጠኛ ፖለቲካ አገርን አለመረበሽ።
“አዲስ የዓለም ሥርዓት እንፈጥራለን” የሚሉ ንግግሮች ዛሬ ዛሬ ወሬና ምኞት ብቻ አይደሉም። በርካታ አገራት፣ ዓለምን የሚቀይር የኢኮኖሚ አቅምና ወታደራዊ ጉልበት እያገኙ ነው። የቀድሞዋ ራሺያ አለች። ቻይና ደግሞ መጥታለች። ቻይና፣ ራሺያና ኢራን የጋራ የጦር ልምምድ ሲያካሂዱ ማየት፣ ራሱን የቻለ አዲስ ታሪክ ነው። በዚያ ላይ፣ የዛሬዋ ሕንድ፣ የድሮዋ ሕንድ አይደለችም።
ሕንድ፣ በሕዝብ ብዛት፣ ዘንድሮ ከቻይና በልጣለች የሚል ዜና አልሰማችሁም? አዎ፣ የሕዝብ ቁጥር ብቻውን፣ ኃያልነትን አያስገኝም። ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ሲሆን ግን፣… ያው የማባዛት ጉዳይ ነው። የመቶ ዶላር አመታዊ የገቢ እድገት፣ በ1.4 ቢሊዮን ሲባዛ፣ ብዙ ነው። ኑሮን ያሻሽላል። ግን ደግሞ፣ ወታደራዊ አቅም ለማፈርጠምም ያገለግላል። የደርዘን አገራት የመከላከያ በጀት፣ አንድ ላይ የመደመር ያህል ነው።
ብዙ የሕዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ እድገት ሲገጣጠም፣ በጎ ጎኑ ብዙ ነው። ለሌሎች አገራትም ሰፊ ገበያ ይፈጥራሉ። ችግሩ ምንድነው? ፀበኛና ጦረኛ መሆን ለሚፈልጉ መንግስታት፣ አመቺ እድል ይሆንላቸዋል። ለጦር ኃይልና ለጦርነት የሚውል ገንዘብ በብዛት ያገኛሉ። እናም፣ትልልቅ አገራት፣ አደገኛ አገራት ይሆናሉ።  
ዛሬ፣ የዓለማችንን “የኃይል” ሚዛንና አሰላለፍ የሚቀይሩ ክስተቶች በዝተዋል። የታሪኩ መነሻ ግን፣ የዛሬ 45 ዓመት የተፀነሰው የቻይና ሕዳሴ ነው።
ለወትሮ የብዙ አገራት ስጋት ከቻይና ሳይሆን ከራሺያ በኩል ነበር። ዛሬ ግን፣ ቻይናን በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ የማይፈራ አገር፣ ወይ ተስፋ የቆረጠና “የመጣው ይምጣ” ብሎ የተቀመጠ ነው። ወይ አላዋቂ ነው። ወይም… ዓለም ሲተራመስ ከዳር ሆኖ ለማየት የሚያስመኝ ክፉ መንፈስ? ለማንኛውም፣ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ነፍስ ዘርቶ በፍጥነት እየገዘፈ የመጣው የቻይና ኃያልነት፣ የዓለምን “አሰላፍ” የሚያናጋ ትልቅ ክስተት ነው።
በእርግጥ፣ የኃያልነቷ ምስጢር፣ መጥፎ ስለሆነ አይደለም።
በጃፓን እንደታየው፣ ስርዓት አክባሪ ነባር የባሕል ቅኝት፣ ለቻይናም ጠቅሟል። የጨዋነት ዝንባሌና ስርዓት አክባሪ ልማድ፣ ሁልጊዜ ይጠቅማል ማለት አይደለም። አንዳንዴ፣ ስርዓት አክባሪ ልማድ፣ ለመጥፎ ስርዓት አመቺ ይሆናል - ለምሳሌ ለኮሙኒዝም። ግን ደግሞ፣ ወደተሻለ ስርዓት ለመሸጋገርም፣ ይጠቅማል። እንዲህ አይነት እድል በቻይና አጋጥሟል - የዛሬ 45 ዓመት።
ወደተሻለ ስርዓት የመሸጋገር እድል የተፈጠረው፣ የሦስት መርሆች ጥምረት አማካኝነት እንደሆነ የዴንግ ዚያዎፒንግ አማካሪ ይገልጻሉ።
አንደኛ፣ አላስፈላጊ ጦርነት ውስጥ አለመግባት።
ሁለተኛ፣ ኢኮኖሚን የሚያበለጽጉ የነጻ ገበያ አሰራሮችን ማስፋፋት።
ሦስተኛ፣ መስመር የያዘ የፖለቲካ መረጋጋት።
ዴንግ ዚያዎፒንግ፣ የቻይና ትንሣኤ አብሳሪ ወይም የህዳሴዋ ደወል ተብለው የሚጠቀሱ መሪና የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ናቸው። የማዖ ዜዱንግ የአብዮትና የነውጥ ዘመን በኋላ ማለት ነው።
ሦስቱም የዚያዎንግ መርሆች፣ “ችግር ከመፍጠር መታቀብ!” ብለን ልንገልጽላቸው እንችላለን። መንግስት በዜጎቹ ላይ እንቅፋቶችን ከመደርደር ከታቀበ፤ ብዙ ሸክሞች ይቃለላሉ።
አዎ፣ ሽፍቶችና አማፂዎች፣ ተቃዋሚዎችና ተቀናቃኞችም አገርን ሊረብሹ ይችላሉ። ደግሞም በተደጋጋሚ አይተናል።
ደግነቱ፣ ስርዓት አልበኞች ሲበጠብጡ፣ ወንጀለኞች ሲያጠፉ፣ መፍትሔ አይጠፋም። ህግና ስርዓትን ማስከበር፣ አገርን ማረጋጋትና ሰዎችን ከጥቃት መጠበቅ ነው የመንግስት ስራ። የመንግስት አካላት፣ ነውጠኛ ሲሆኑ ነው ችግሩ። አዎ፣ ነውጠኛ ተቃዋሚዎችና አመፀኞችም፣ አደጋ ያመጣሉ።
በዓመቱ የመጀመሪያ ወራት ላይ እንደታዘብነው ግን፣ የመንግስት ባለስልጣናትና የገዢው ፓርቲ ጎራዎች  በየእለቱ የቀውስ ሰበብ ሲፈጥሩ፣ አደጋው ከሁሉም ይብሳሉ።
ታዲያ፤ “ችግርና እንቅፋት ከመፍጠር መቆጠብ” የሚለው ሃሳብ ትልቅ ቁምነገር መሆኑ ይገርማል?
አስቡት። “በመታቀብ” ብቻ ፍሬያማ መሆን! እውነት አይመስልም። ግን እውነት ነው። ከማፍረስ መታቀብ፣ ግንባታን ከማደናቀፍ መቆጠብ ነው። የሰዎችን ኑሮ ማክበር፣ ንብረታቸውን መጠበቅ፣ ሕግና ስርዓትን ማክበር ማለት ነው- አደናቃፊ  አለመሆን ማለት። መንግስት የአገራቱ ኢኮኖሚና የሰዎች ኑሮ በዋጋ ንረት አለማናጋት ማለት ነው። መንግስት አለስራው አለቦታው ከመግባት ሲታቀብ፣ ትክክለኛ ሃላፊነቱን የማከናወን አቅምና ጊዜ ይኖረዋል። ይህ አንድ  ዚያዎፒንግ መርህ ነው። “ሁሉም ነገር የመንግስት፣ ሁሉም እንቅስቃሴ በመንግስት ይሁን” ተብሎ አላዋጣም። እናስ ምን ተደረገ?  በመንግስት ትዕዛዝ በግዳጅ የተመሰረቱ “የጋርዮሽ የእርሻ ማህበራት” እየፈረሱ ገበሬዎች የየግል ማሳቸውን እንዲያለሙ፣ የምርታቸው የግል ባለቤት እንዲሆኑ፣ መሸጥም እንዲችሉ ተፈቀደ፡፡ ሚሊዮኖችን እየፈጀ ቻይናን እንደራሱ ግዛት እየነገሰባት የነበረ የረሃብ መከራ፣ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ባይጠፋም ተቃለለ፡፡ “ተዓምር” ነው። መንግስት እጁን ሲሰበስብ ማሳዎች ያፈራሉ።
የግል ቢዝነስና ንግድ፣ ቀስ በቀስ እየተፈቀደና እየተስፋፋ ሲመጣስ፣ ቻይና የዓለም ፋብሪካ ትሆናለች ብሎ ማን አሰበ?… በቅድሚያ በሆንክኮንግ፣ በሲንጋፓርና በታይዋን አቅራቢያ ነው የኢንዱስትሪ መንደሮችና ከተሞች እየተበራከቱ፣… ከጊዜ ወደ ጊዜ በቁጥርና በጥራት፣ በዓይነትና በግዝፈት እየጨመሩ፣… የአገሪቱ አንቂ ሞተሮች ሆነዋል።
ደግነቱ ደግሞ መንግስት ትንሽ በትንሽ እጆቹን ከኢኮኖሚ ውስጥ አውጥቶ ሲሰበስብ ፍሬያማ ውጤት በግል ቢዝነስ ሲበረክት፣… በቃ አልተባለም። የነፃ ገበያ አሰራሮችን ለማስፋፋት ተጨማሪ ማሻሻያዎች ተከናውነዋል።
በጃፓን፣ በደቡብ ኮሪያና በታይዋን የታየው የብልፅግና “ተዓምር” በቻይናም ብቅ ሲል ታየ። ያው፣ከጊዜ በኋላ፣ ቻይና የዓለማችን ፋብሪካ የምትባልበት ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ የዴንግ ዚያዎፒንግ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሃሳቦች የካፒታሊዝምን መስመር የተከተሉ ናቸው። ነገር ግን፣ የነፃ ገበያ ስርዓትን እንደመርህ በመቀበል ሳይሆን፣ እንደጠቃሚ የብልፅግና ዘዴና አሰራር በመቁጠር ሊሆን ይችላል፡፡
ቢሆንም፣ በዚያው ልክ ፍሬያማ መሆናቸው አልቀረም፡፡ ሦስተኛው የዚያዎፒንግ መመሪያ፣ ሥርዓትና መስመር የያዘ የፓለቲካ እርጋታ ለቻይና ህዳሴ ያስፈልጋል የሚል ነበር፡፡
የፓለቲካ እርጋታ ያለ ሥርአትና ያለመስመር በጉልበት ወይም በብልጠት ብቻ አይመጣም፡፡
አገሪቱ ደግሞ፣ ለበርካታ ዓመታት እርጋታ እጅግ የናፈቃት የግርግር ምድር ሆናለች። ተማሪዎች በአስተማሪዎች ላይ ዘምተዋል። ከሳሽ፣ ምስክርና ዳኛ ሆነው ይፈርዱባቸዋል። መደበኛ ፍርድቤቶች ተዘግተዋል።
ሰራተኞች በአለቆችና በባለስልጣናት ላይ አባራሪና አሳሪ ሆነዋል። ጎረቤት በጎረቤቱ ላይ ይፈርዳል።
ህግና ሥርዓት የማይገዛው፣ የግለሰብ መብቶችን በማስከበር ላይ ያልተመሰረተ ገደብ የለሽ ዲሞክራሲ ማለት የያኔውን ትርምስ ይመስላል።“በማያቋርጥ የአብዮት ለውጥ” የተናወጠው አገር፣ እርጋታን ይሻል። እንደገና እንዳይናወጥ ደግሞ ሥርዓትና መስመር ያለው እርጋታ ያስፈልገዋል።
የዚያዎፒንግ የእርጋታ መርህ  ይህን እውነታ የተገነዘበ ነው። በተግባር ሲሞክሩትም፣ ሰምሮላቸዋል ማለት ይቻላል።
ከዛሬ 30 ዓመት በፊት፣ የአገሪቱን መንግስትና ገዢውን ፓርቲ የሚያንገራግጭ ዓመፅ የተፈጠረ ቢሆንም፣ ሌላ ቀውስና ነውጥ እስከ ዛሬ አልተከሰተም፡፡ ነገር ግን ሁሉም እርጋታ እኩል አይደለም፡፡
አንድ አገርና መንግስት፣ አንድ ፓርቲና መሪ የሚል ነው የቻይና ኮሙኒስት ቅኝት ወይም ሥርዓት፡፡ ይሄ ይዘልቃል ወይ?
በአንድ በኩል፤ “ሥርዓትና መስመር የያዘ የፓለቲካ እርጋታ” የሚለው የዚያዎፒንግ ሦስተኛ መመሪያ ተሟልቷል ማለት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ግን፣ “ምን ዓይነት ሥርዓትና መስመር” የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡
የግለሰብ ነፃነትን መነሻና መድረሻ ያደረገ ሥልጡን የፓለቲካ መርህ ላይ የተመሰረተ ህግና ስርኣትም የፖለቲካ እርጋታን ሊፈጥር ይችላል፡፡
የሁሉንም ዜጎች መብት፣ የእያንዳንዱን ግለሰብ ነፃነት የማሰከበር ሃላፊነት የተሰጠው መንግስት፣ ሥልጣኑ ከዚህ ውጭ እንዳይንሰራፋ በህግ የተገደበበት፣ የህግ የበላይነትንና ካፒታሊዝምን ያጣመረ ሥልጡን ፖለቲካ፣ ያለ አፈናና ያለ ነውጥ ለረዥም ዓመታት ሊዘልቅ ይችላል - በአሜሪካና እንግሊዝ እንደታየው፡፡
ፓርቲዎች እየተፎካከሩ፣ ፖለቲከኞች እየተወዳደሩ፣ በምርጫ እየበለጡ፣ በተከታዩ ምርጫ እየተቀደሙ፣ አንዱ እየተሰናበተ ሌላው እየተተካ፣ ያለ ዓመፅና ያለ ጉልበት፣ ያለ ነውጥና ያለ ቀውስ ስልጣን ላይ የሚፈራረቁበት ሥርዓት፣… ከብዙ ጥፋትና ከክፉ አደጋ ሊያድን የሚችል የእርጋታ ሥርዓት ነው ለዚያውም ከትክክለኛ መርህ የመነጨ፡፡
የዚያዎፒንግ ሦስተኛ መመሪያ፣ ይህን ለይቶ የሚገልፅ አይደለም፡፡ “ሥርዓትና መስመር የያዘ የፓለቲካ እርጋታ” የሚል ነው በደፈናው፡፡ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲም ይህን መመሪያ አሟልቼ አሳክቼዋለሁ ሊል ይችላል፡፡ በተወሰነ ደረጃም ብቃቱን ይመሰክርለታል፡፡ እንደሌሎች ገዢ ፓርቲዎች አልተዝረከረከም፡፡
ነገር ግን፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲመጡበት በፍፁም አይፈቅድም፡፡ ይሄ “በራስ የመተማመን ብቃትን” አያሳይም።
የአንድ ፓርቲ አገዛዝ እስከ መቼ እንደሚያዛልቅም አይታወቅም።
ለጊዜው ግን፣ ሦስቱ መመሪያዎች ለቻይና ይዘውላታል ማለት ይቻላል።
በዚያው ልክም፣ የኢኮኖሚ ብልፅግናንና ኃያልነትን የሚያስገኙ መንገዶች ሆነውላታል- የሕዳሴ መርሆች።
ወደ ጦርነት አለመሮጥ፣…
በነፃ ገበያ አሰራር ኢኮኖሚን ማበልፀግ፣…
 ሥርዓት የያዘ የፖለቲካ እርጋታን ማስፈን፣…
በእነዚህ መርሆች አገሪቱ የብልፅግና ፍሬዎች ከበረከቱላት በኋላ፣… በዓለማቀፍ ንግድ እየጎለበተች በቴክኖሎጂው መስክም  ከዋና ተዋናዮች ጎራ እየተቀላቀለች፣ በዓለማቀፍ ዲፕሎማሲ ከፍተኛ ጉልበት እያገኘች፣ በወታደራዊ አቅምም ኃያልነትን እየተላበሰች ስትመጣ፣… አደገኛ የጦርነት ስጋት ሆና መታየቷ ነው ትልቁ ችግር።
የአሜሪካ ወይም የአውሮፓ መንግስታት እንዳሻቸው ጦርነት ማወጅ አይችሉም። ከዓለም ዙሪያ ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥም ከፍተኛ ተቃውሞና ትችት ይገጥማቸዋል። እንደ ቻይና እንደ ራሺያ የመሳሰሉ አገራት ውስጥ ግን፣ ተቃውሞዎችንና ትችቶችን ዝም ማሰኘት ይቻላል። አደጋውም እዚህ ላይ ነው።
አዎ፤ የዚያዎፒንግ የቁጥብነትና የመታቀብ መርህ፣ እስካሁን ሰርቷል።
ይበልጥ አስፈላጊ የሚሆነው ግን ከእንግዲህ በኋላም ነው።
ድሮ የኢኮኖሚ አቅም ሳይኖር፣ ፀበኛና ጦረኛ ከመሆን መቆጠብ ብዙም አያስቸግር ይሆናል። ወታደራዊ ጡንቻ ከፈረጠመ በኋላ ግን፣ አላስፈላጊ ፀብና ጦርነት ውስጥ ላለመግባት መጠንቀቅ፣ ከባድ ፈተና ሊሆንባቸው ይችላል።
ይህም ብቻ አይደለም። ከኢኮኖሚ እድገት ጋር አብረው የሚመጡ ሌሎች ፈተናዎችም አሉ። የኢኮኖሚ ነፃነትን የሚመጥን የፖለቲካ ነፃነትና የመከባበር ሃላፊነት፣… የሥልጡን ፖለቲካ ማሻሻያና ከዚሁ ጋር የሚጣጣም ነባሩን ልማድ የሚያዳብር የባህል ቅኝት ያስፈልጋል። ይህ በዛሬ ዘመን አስቸጋሪ ነው። እጅግ ከባድ ጥበብና ትጋትን ይጠይቃል።
ከዚያ ይልቅ፣ ዜጎችን በጭፍን ስሜት በማነሳሳትና በፀበኝነት መንፈስ ሰዎችን በመቀስቀስ የሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት መሞከር በጣም ቀላል ሆኖ የሚታያቸው ፖለቲከኞች ይኖራሉ። በእርግጥም ቀለል ይላል።
ከማረጋጋት ይልቅ መረበሽ፣ ከመገንባት ይልቅ ማፍረስ፣ ከማስተማር ይልቅ ማስጮህ ቀላል ነው።
ግን ምን ዋጋ አለው? ኢኮኖሚን ያናጋል፤ እርጋታን ያጠፋል፤ በአላስፈላጊ ፀብና በጦርነት ከንቱ እልቂትና ውድመትን ይበረክታል። ከእነዚህ ለመሸሽ ነበር የሦስቱ መርሆች አላማ። ለአገራችንም ይሰራሉ። በቂ ባይሆኑም።


Read 1939 times