Print this page
Saturday, 06 May 2023 19:06

ከማህበራዊ ሚዲያ በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የምስኪኖቹን መንደር  በስካቫተር  ያፈረሰው ሚሊየነር

በደቡባዊ ቻይና ግዛት የምትገኘው የደሳሳዋ  ዦንኪንግ  መንደር ነዋሪዎች፣ ሸቀጣሸቀጥ ጭነው ከሚመጡ አሮጌ ከባድ መኪኖች ውጭ አንድም መኪና ወደ መንደራቸው ዘልቆ አይተው አያውቁም።  ዛሬ ግን እጅግ ዘመናዊ  መርሰዲስ መኪና  መጥታ ቆማለች።
እናም ነዋሪዎች፣ በመኪናዋ በመንደራቸው  መገኘት በመገረም፣ ዙሪያውን ከበው በማየት ላይ እያሉ፣ አንድ በጠባቂዎች የታጀበ እድሜው በሀምሳዎቹ የሚገመት ሰው ከመኪናው ወጣ። ማንም ደፍሮ ሰላም ሊለው ወይም ሊያናግረው የመጣ ሰው ግን አልነበረም። እናም ሰውየው መንደሩን ለደቂቃዎች ከተመለከተ በኋላ ተመልሶ ወደ መኪናው ገብቶ ሄደ።
ይህ በሆነ በማግስቱ ወደዛች ደሳሳ መንደር ሌላ መኪና መጣ። ከመጡት ሰዎች ውስጥ  የትናንቱ ሰውዬ አልነበረም። በቁጥር በዛ የሚሉ መሀንዲሶች ነበሩ የመጡት። በዚህ ጊዜ ነዋሪዎቹ ነገሩ ገባቸው፤ የትናንቱ  ሰው ባለሀብት መሆኑን በሁኔታው  አውቀዋል፤ እናም ይህን መንደር ሊያፈርስ መሀንዲሶች ልኳል።
እነዚህ  ነዋሪዎች፤ ይህም ኑሮ ሆኖ  ደሳሳ ጎጇቸውን የሚያፈርስ ሰው ይመጣል ብለው መቼም አስበው አያውቁም ነበር። እና ሽማግሌዎች ቀርበው መሀንዲሶቹን አናገሯቸው። ፍርሀታቸው ልክ ነበር፤  ትናንት የመጣው ባለሀብት እዚህ መንደር ላይ ሪል እስቴት መገንባት ፈልጓል፡፡ ለዚህም ከመንግስት ፍቃድ እንዳገኘ፣ ከሰባ በላይ ለሚሆኑት ለመንደሩ ነዋሪዎችም ካሳና መኖሪያ ቤት የሚገነቡበት ገንዘብ እንደሚሰጣቸው፣ እስከዛ ግን በመጠለያ መቆየት እንደሚችሉ፤ እስከ ነገ ድረስም እቃቸውን አውጥተው በተዘጋጀላቸው ማረፊያ እንዲያስቀምጡ ነግረዋቸው  ሄዱ።
ከቀናት በኋላም  ብዛት ያላቸው ግሬደሮችና የህንጻ ሰራተኞች ትንሿን መንደር  አጥለቀለቋት።
ያለቻቸውን አሮጌ እቃ አውጥተው ከቤታቸው አቅራቢያ በተዘጋጀላቸው መጠለያ ውስጥ የገቡት የዦንኪንግ መንደር ነዋሪዎች፤  ቆመው እያዩ ለዘመናት የኖሩባቸው ደሳሳ ጎጆዎች በስካቫተር ፈረሰ።
ቃል የተገባላቸው ቤት መስሪያ ቦታም ሆነ ካሣ ሳይሰጣቸው ለወራት በመጠለያ እየተረዱ ቆዩ። ከዓመታት በፊት ከነሱ ብዙም በማይርቅ ቦታ የሚገኙ መንደሮች ልክ እንደነሱ በጨካኝ ባለሀብት ተፈናቅለው  መሰደዳቸውን እያስታወሱ፣ እጣ ፈንታቸውን መጠባበቅ ጀመሩ።ይህ በሆነ በጥቂት ወራት ውስጥም የባለሀብቱ ዘመናዊ ቪላዎች ተገንብተው ተጠናቀቁና፣ ነዋሪዎቹ በሥነስርአቱ ላይ እንዲገኙ፣ በፕሮግራሙም ላይ  ለነሱም ቃል የተገባላቸው ካሣ እንደሚሰጣቸው ተነገራቸው። ብዙዎቹ ነዋሪዎች ግብዣውን ተቃወሙ። ትንሿ የዦንኪንግ መንደር ዛሬ በልዩ ሁኔታ ደምቃለች። ከሰባ በላይ ዘመናዊ መኖሪያዎችን ለመመረቅ የተለያዩ እንግዶች ተገኝተዋል። ያቺ የድሆች መንደር፣ አይታ በማታውቀው ሁኔታ በዘመናዊ መኪኖችና በሀብታሞች ተጥለቅልቃለች።
የምረቃው ፕሮግራም ተጀመረ።
ያ፤ በመጀመሪያ ቀን መርሰዲስ መኪና ይዞ ወደዚህ መንደር የመጣው ባለሀብት፣ ንግግር ለማድረግ ወደ መድረኩ ወጣ።
“ክቡራንና ክቡራት የዦንኪንግ መንደር ነዋሪዎችና  ክቡራን እንግዶች፤ ዛሬ ልዩ የሆነውን ይህን የዘመናዊ መኖሪያ ቤት ፕሮጀክት ለመመረቅ ስለተገኛችሁ አመሰግናለሁ። እኔ የማየው ዛሬ ሚሊየነር መሆኔን አይደለም። የኔ ሰብዕና የኔ የሀብት ምንጭ ይሄ መንደር ነው።. ... እኔ .....  ትንሽ ልጅ ሆኜ የምታውቁኝ  Xiong Shuihua ነኝ።
 በርግጥ ከዚህ መንደር ከወጣሁ ብዙ  አመታት ተቆጥረዋልና  አላወቃችሁኝም። እኔ ግን ሁላችሁንም አስታውሳለሁ። ለኔና እጅግ ድሆች ለነበርነው ቤተሰቦቼ በየወሩ ቀለብ ይቆርጥልን የነበረው ሚስተር ዣይን፣ ከልጆቻቸው እኩል ልብስ ይገዙልኝ የነበሩት የሚስ ታዮኒ ቤተሰቦች፣ ሲርበን የሚያበሉን የዚህ መንደር ነዋሪዎች---ሁላችሁንም አስታውሳለሁ።  “የኔ የአሁን ህይወት ላይ የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጣችሁት እናንተ ናችሁ።
ለዚህም ነው መንደሩን ለመለወጥና የተሻለ ህይወት እንድትኖሩ ለማሰብ እዚህ የተገኘሁት። እናም እነዚህ ቤቶች የተሰሩት ለናንተ ነው። ያለምንም ክፍያ በእነዚህ ቤቶች ትኖራላችሁ።
ቤቶቹ ንብረቶቻችሁ ናችሁ። በነጻ የተሰጧችሁ አይደሉም፤ ከአመታት በፊት ለኔና ለቤተሰቦቼ መልካም ነገር በማድረግ  ኢንቨስት አድርጋችሁበታል።” እያለ እንባ እየተናነቀው  ሲናገር፣ የመንደሩ ሰዎች በሙሉ በታላቅ ድንጋጤ ውስጥ ሆነው ይሰሙት ነበር።
ባለሀብቱ ንግግሩን ቀጥሏል፡-
“እናም ከሀምሳ ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ ተደርጎባቸው የተሰሩት እነዚህ ቤቶች፣ በፈረሱት ቤቶቻችሁ ቁጥር ልክ የተሰሩ ናቸው፤ ነገ አዳዲስ የቤት እቃዎች የጫኑ መኪኖች ይደርሳሉ። መብራትና ውሀም  አትከፍሉም። መስራት ለምትችሉ የስራ እድል ይዘጋጃል፤ ለአቅመ ደካሞችና ማብሰል ለማይችሉ  ደግሞ ዘመናቸውን ሙሉ የሚፈልጉትን መርጠው የሚመገቡበት መመገቢያ አዳራሽም ተገንብቷል። የናንተ ውለታ ከዚህም በላይ ነው፡፡” አላቸውና፤ ከመድረኩ ወረደ።
በሌላ ሀገር፣ አንድ ግለሰብ ለወገኖቹ  ይህን ያህል ያስባል፤ በኛ ሀገር ደግሞ  የምስኪኖች ቤት ሀላፊነት ሊሰማው በሚገባ የመንግስት አካል  ፈርሶ ቤተሰብ ሜዳ ላይ ይበተናል። ልዩነታችን ይህን ያህል ነው።
(ዋስይሁን ተስፋዬ)

======================================

ኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በኋላ ምን አይነት ዜጋ ይኖራት ይሆን?


በቤተ ክርስቲያን አካባቢ፣ በምግብ ቤቶች፣ በትራንስፖርት መሰለፊያዎችና በየመንገዱ ላይ የመንገደኛውን ልብስ ይዘው ‹‹ጋሼ ዳቦ ግዛልኝ›› የሚሉትን…. በአጠቃላይ ከወላጆቻቸው ጋርና ብቻቸውን ልመና ላይ የወደቁ ልጆች ባየሁ ቁጥር እነዚህ ጥያቄዎች ይመጡብኛል፡፡
ዓለም ከዓመታት በኋላ አሁን ከምናየው የረቀቀ ቴክኖሎጂ በላይ አስገራሚ ነገሮችን ታሳያለች፡፡ በውጭ አገራት የምናያቸውና የምንሰማቸው የሥልጣኔና የቴክኖሎጂ ምጥቀቶች አስደማሚ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያስ ከዓመታት በኋላ ምን አይነት ዜጋ ይኖራት ይሆን?በብዙ የገጠር አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ ነዋሪዎቹ በሰላም እጦት እየተሰደዱ በከተማ  ልመና ላይ ናቸው፡፡ ሕጻናቱ ከትምህርት ውጭ ናቸው፡፡ እነዚህ ዛሬ በየጎዳናው ዳርቻ የወዳደቁ ልጆች፣ ከዛሬ አሥራ ምናምንና ሃያ ዓመታት በኋላ ወጣቶች ናቸው፡፡
አገር ተረካቢ የሚሆኑ ናቸው፡፡ አገር ተረካቢ ማለት የግድ ሥልጣን መያዝ ብቻ አይደለም፡፡ በየትኛውም ደረጃ መኖር  አገር ተረካቢነት ነው፡፡ ከዓመታት በኋላ አገር የሚረከቡ እነዚህ ልጆች ናቸው፡፡
ከዓመታት በኋላ የዓለም አገራት አስደናቂ የሥልጣኔ ደረጃ ላይ ሲደርሱ፤ መጻፍና ማንበብ የማይችል  ሕዝብ የሚኖራት አገር ምናልባትም ኢትዮጵያ ብቻ ልትሆን ትችላለች!
(ዋለልኝ አየለ)


Read 1495 times
Administrator

Latest from Administrator