Saturday, 13 May 2023 20:08

በአዲስ አበባ ከ1250 በላይ የግል ት/ቤቶች እጥፍ የክፍያ ጭማሪ ለማድረግ መዘጋጀታቸው ተጠቆመ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 ጭማሪው በት/ቤቶችና በወላጆች መካከል ከፍተኛ አለመግባባትን ፈጥሯል መንግስት ት/ቤቶቹ ከወላጆች ጋር በቂ መግባባት ላይ ሳይደርሱ  ጭማሪውን ተግባራዊ ማድረግ አይችሉም ብሏል

         በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ 1558 የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ 1257 የሚሆኑት ለቀጣዩ 2016 የትምህርት ዘመን ከእጥፍ በላይ ክፍያ ጭማሪ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ለማወቅ ተችሏል። ት/ቤቶቹ በጭማሪው ዙሪያ ከወላጆች ጋር ለመነጋገር የጠሩት ስብሰባ በአብዛኛው የከተማዋ ት/ቤቶች ከፍተኛ ተቃዉሞ እንደገጠመውና ት/ቤቶቹ በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ለማድረግ ያሰቡት የዋጋ ጭማሪ ከወላጆች አቅም በላይ የሆነ በመሆኑ ተቀባይነት እንዳላገኘ ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል። በሌላ በኩል፤ የአዲስ አበባ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን፣ ትምህርት ቤቶቹ ከወላጆች ጋር በቂ መግባባት ላይ ሳይደርሱ ምንም አይነት ጭማሪ ለማድረግ እንደማይችሉ አስታውቋል፡፡ እነዚህ ት/ቤቶች የዋጋ ጭማሪውን ለማድረግ የተገደዱባቸውን ጉዳዮች ሲገልፁ፤ ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እንዳይችሉ በከተማ አስተዳደሩ ት/ቢሮ አማካኝነት ተከልክለው መቆየታቸውን፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚታየውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም የሚያስችል የደመወዝ ጭማሪ ለማድረግ አለመቻላቸውንና ከዋጋ ንረት ጋር ተያይዞ የተከሰተው የአስተዳደራዊ ወጪ ንረት መቋቋም ስላቃታቸው እንደሆነ ያብራራሉ።
በከተማዋ በሚገኙ አብዛኛዎቹ የግል ት/ቤቶች ባለፈው እሁድ ሚያዝያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም በመጪው የትምህርት ዘመን ሊደረግ በታሰበው የዋጋ ጭማሪ ላይ ከወላጆች ጋር ውይይት የተካሄደ ሲሆን በአብዛኛዎቹ ት/ቤቶች ስብሰባው ያለ ስምምነት መበተኑን ለማወቅ ተችሏል።
በሳፋሪ አካዳሚ ልጆቻቸውን የሚስተምሩ ወላጆች ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት እንደገለፁት፤ ት/ቤቱ ሚያዝያ 29 ቀን 2015 በጠራው ስብሰባ በቀጣዩ የትምህርት ዘመን በተማሪዎች ክፍያ ላይ ለማድረግ ያሰበውን የ125% ጭማሪ ለወላጆች በማሳወቁ ሳቢያ ከወላጆች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል፤ ት/ቤቱ በተማሪዎች ክፍያ ላይ ከእጥፍ በላይ ጭማሪ ለማድረግ ያቀረባቸው መነሻ ምክንያቶች ጨርሶ አሳማኝ አለመሆናቸውን የሚገልጹ ወላጆች፤ ምክንያታቸው አሳማኝነት ቢኖራቸው እንኳን በዚህ መጠን የተደረገን ጭማሪ ለመሸከም የሚችል ጫንቃ ያለው ሰው እንዴት እናገኛለን ብለው አሰቡ ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ት/ቤቶቹ በወላጆች ላይ ይህን አይነት ዱብእዳ ለማውረድ ሞራሉንስ ከየት አገኙት በማለትም ያክላሉ፡፡እጅግ አስገራሚው ጉዳይ ደግሞ የወላጅ ኮሚቴ ተብለው የተቀመጡት ሰዎች ወላጆችና ት/ቤቱን ለማስማማት ብለው ያቀረቡት የ80% ጭማሪ ሃሳብ ነው ይላሉ አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው ወላጆች፡፡ ይህ በወላጅ ኮሚቴ የቀረበው የጭማሪ ሃሳብም ከወላጆች በወቅቱ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል ብለዋል። ወላጆች የወላጅ ኮሚቴ ተብሎ በተቋቋመው አካል ላይ እምነት እንደሌላቸውም ተናግረዋል፡፡
“ት/ቤቱ የወላጅ ኮሚቴ ተብየው ባቀረበው የ80% ጭማሪ የተስማማ ቢሆንም ወላጆች ሃሳቡን ባለመቀበላቸውና የ35% ጭማሪ እንዲደረግ ጠይቀው ከት/ቤቱ ተቀባይነት ባለማግኘታቸው ስብሰባው ያለስምምነት መበተኑን እነኚሁ ወላጆች ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ት/ቤቱ ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ጋር በመመካከር የሚደርስበትን ስምምነት ለወላጆች እንደሚያሳውቅ መግለፁም ተነግሯል፡፡
በከተማዋ ት/ቤቶች ሊሆን የታሰበውን ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አስመልክቶ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ዶ/ር አስቻለው ይታገስ በሰጡት አስተያየት፤ “የግል ት/ቤቶች ለትርፍ የተቋቋሙ እንደመሆናቸው መጠን በአገሪቱ አሁን እየታየ ካለው የዋጋ ግሽበት አንፃር ተመጣጣኝ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እንደሚኖርባቸው መታወቅ አለበት፡፡ ካለው የአገሪቱ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታና ከገበያው ጋር የሚመጣጠን ጭማሪ ማድረጋቸው ሊወገዝ የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለዚህም የወላጆች ጥያቄ ለምን የዋጋ ጭማሪ ተደረገ የሚል ሳይሆን ከአቅም በላይ የሆነ ጭማሪ ሊደረግ አይገባም የሚል መሆን አለበት፡፡ መንግስት በበኩሉ አማካይ የትምህርት ዘርፍ ተመጣጣኝ ትርፍ ህዳግ ማስቀመጥ፣ በት/ቤቶቹና በወላጆች መካከል በግልጽ መረጃ ላይ የተመሰረተ መግባባት እንዲኖር ማድረግና የት/ቤቶቹንና የወላጆችን ጥያቄ የሚያቀራርብ ስራ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ አሊያ ግን በየጊዜው መንግስት ጣልቃ በመግባት የሚስቀይረው ውሳኔ ገበያው እንዳይረጋጋ በማድረግ ውጥረት ይፈጥራል” ብለዋል፡፡ ለጊዜው የታፈነ የዋጋ ጭማሪ ፍላጎት አመቺ አጋጣሚ ሲያገኝ ጭማሪ ለማድረግና በጣልቃ ገብ ውሳኔ አጣሁት ብሎ የሚታስበውን ጥቅም ለማስመለስ በሚያደርገው ጥረት ከፍተኛ የገበያ አለመረጋጋት ይፈጠራል፡፡ ይህ ደግሞ የሚፈጥረው ችግር በቀላሉ ልንቋቋመው የምንችለው አይሆንም ብለዋል-ምሁሩ። መንግስት እንደ መንግስት ዘላቂ መፍትሄዎች ላይ ሊያተኩር እንደሚገባ የሚገልፁት ምዑሩ በመንግስት ት/ቤቶች ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ የመንግስት ት/ቤቶች ከግሎቹ ጋር ተቀራራቢነት ያለው ተፈላጊነት እንዲኖራቸው ለማድረግ መስራት አለበት ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በመንግስት የሚተዳደሩና ተመጣጣኝ ክፍያ የሚጠየቅባቸው ለወላጆች ተጨማሪ አማራጭ ሊሆኑ የሚችሉ ት/ቤቶችን ማቋቋም ሌላው መፍትሄ ሊሆን እንደሚችልም አመልክተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የአዲስ አበባ የትምሀርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን፣ ት/ቤቶች በቀጣይ የትምህርት ዘመን ሊያደርጉ ባሰቡት የዋጋ ጭማሪ ላይ ከወላጆች ጋር በቂ መግባባት ላይ ካልደረሱ ጭማሪውን ማድረግ ማሳወቃቸውን አስታውቋል፡፡
ባለስልጣኑ ከትናንት በስቲያ በከተማዋ ለሚገኙ የግል ት/ቤቶች በላከው ደብዳቤ እንዳስታወቀው፤ ት/ቤቶቹ ከወላጆች ጋር በቂ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ በቀጣዩ የትምህርት ዘመን የክፍያ ጭማሪ ማድረግ እንደማይችሉ አሳስቧል፡፡ ባለስልጣን መ/ቤቱ በከተማዋ በሚገኙ አንዳንድ የግል ት/ቤቶች በክፍያ ጭማሪው ላይ ከወላጆች ጋር በቂ ስምምነት ላይ ለመድረስ አለመቻላቸውን በአካል ተገኝቶ ማረጋገጡን ገልፆ የክፍያ ጭማሪው ከተማሪ ወላጅ ተወካዮችና ከባስልጣኑ መስሪያ ቤት ጋር በሚደረጉ ውይይቶችና በሚቀመጥ የጋራ አቅጣጫ ብቻ ወደ ተግባር እንደሚገባ ገልጿል፡፡
እስካሁን ድረስ 1031 የሚሆኑ ት/ቤቶች በክፍያ ጭማሪው ላይ ከወላጆች ጋር መስማማታቸውን ለባለስልጣን መ/ቤቱ ማሳወቃቸውንና ስምምነት ላይ ያልደረሱ ትምህርት ቤቶችም እስከ መጪው እሁድ ከወላጆች ጋር ተወያይተው የደረሱበትን ለባለስልጣን መ/ቤቱ እዲያሳውቁ መመሪያ መተላለፉ ታውቋል፡፡


Read 1598 times