Saturday, 13 May 2023 20:11

“ይሉሽን በሰማሽ...”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በፊት እኮ... “ደግሞ ግንቦት ገባ፣ ሙቀቱን እንዴት ይሆን የምናልፈው!” ይባል ነበር፡፡ አሀ፣ በፊት ግንቦትም ያው የሚታወቀው ግንቦት፣ በጋውም ያው የሚታወቀው በጋ ነበሩ፡፡ አዎ...አሱም ያው የምታውቁት እሱ፣ እሷዬዋም የምታውቋት እሷዬ ነበሩ...ነገሮች እንዲህ ‘ሚስቶ’ ነገር ሊሆኑ!
ደግሞላችሁ...ስለ ራሳችን ያለን አመለካከትና ሌሎች ስለእኛ ያላቸው አመላለከት አንድ ባይሆን ትንሽ እንኳን መቀራረብ ያቅተው! ባንግባባ ምኑ ይገርማል፡፡ በቦተሊካ በሉት፣ በፍራንክ በሉት፣ ‘በተንታኝነት’ በሉት (ቂ...ቂ...ቂ...) ሁሉ ዙፋን ፈላጊ ሆነና ተራው ወንበር ላይ ማን ይቀመጥ! በርጩማዋ ላይ ማን ይቀመጥ! እዛች ጥጓ ላይ ማን ይቀመጥ! ችግር ከተፈጠረ የእኛ ሳይሆን የሌሎች፣ የተበላሸ ነገር ካለ የእኛ ሳይሆን ‘የእነሱ!’
ይቺን ስሙኝማ...የአንድ ኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ (በዘመኑ ቋንቋ) የድርጅቱን የህዝብ ግንኙት ያስጠራውና እንዲህ ይለዋል፡፡ “ስማ፣ የሆነ ተቋም ድርጅታችንን ሊገዛ እያሰበ ነው፡፡ በሆነ መንገድ የአክስዮኖቻችን ዋጋ ከፍ እንዲል አስደርግ፡፡ ውድ ስለሚሆንባቸው አርፈው ይቀመጣሉ፡፡ እንዴት እንደምታደርገው አላውቅም፤ ብቻ በሆነ ዘዴ አሳካው፡፡” የህዝብ ግንኙነቱ አድርግ እንደተባለው ተሳካላት፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚውም እንዴት እንደተሳካለት ጠየቀው፡፡
“አይ በአክስዮን ገበያው አካባቢ አሉባልታ ነዛሁና ሁሉም ደስ ብሏቸው አክስዮኖቻችን በከፍተኛ ዋጋ ተሸጡ፡፡” ዋና ሥራ አስፈጻሚው ደስ ብሎት ስድሳ አራት ጥርስ ሆነ፡፡
“ለመሆኑ ምን አይነት አሉባልታ ብትነዛ ነው እንዲህ የተሳካው?” ሲልም ጠየቀው፡፡ ሕዝብ ግንኙነቱ ምን ቢል ጥሩ ነው...
“እርሶ በገዛ ፈቃድዎ ሥራውን ሊለቁ መሆኑን...” ብሎት እርፍ!
ራስን ያለማወቅ የመሰለ ቀሺም ነገር የለም፡፡
ሰውየው ጸጉር አስተካካይ ነው፡፡ እናላችሁ በቃ ሀገር ውስጥ የእኔን ያህል ችሎታ ያለው ጸጉር አስተካካይ አይገኝም ባይ ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ለሁሉም ነገር...አለ አይደል....አሉታዊ (ኔጌቲቭ እንደሚሉት አይነት) መልስ ነው የሚሰጠው፡፡ ታዲያላችሁ አንድ ቀን ከሆነ ደንበኛው ሰው ጋር ይገናኙና ደንበኝዬ “ረስቼው፣ ሳልነግርህ...” ይለዋል፡፡
“ምኑን ነው ያልነገርከኝ?” ይለዋል፡፡
“እኔና ባለቤቴ ለአንድ ወር ያህል ጣልያን ሽርሽር ልንሄድ ነው፡፡”
“ስለ ጣልያን ብዙ ሰምቻለሁ፣” ይላል ጸጉር አስተካካዩ፡፡ “ሰዎቹ ስርአት የላቸውም፡፡ ምግባቸው አይጣፍጥም፡፡ ገጠሩ ደግሞ ያስጠላል አሉ፡፡”
“ለአንድ ሳምንት ያህል ሮም ነው የምንቆየው፣” ይላል ሰውየው፡፡
“ታዲያ ምኑ ያስደስታል! ሮም እኮ ባረጁ ህንጻዎች የተሞላች ከተማ ነች፡፡”
“ደግሞ ጳጳሱ በአካል እናገኛኝሀለን ብለውኛል፡፡” “እሳቸውም በአካል ማገናኘት የሚሉት እኮ በሚሊዮን ሰው የተሞላ አደባባይ ውስጥ ትገባለህ ማለት  ነው፡፡ በቃ ጳጳሱ ከመድረኩ ላይ ሆነው ነው እጃቸውን የሚያውለበልቡት፡፡”
ከዚህ በኋላ ሰውየው ጣልያን ወር ከርሞ ተመለሰ፡፡ ጸጉር አስተካካዩም “ጉብኝትህ እኔ እንዳልኩት አስቀያሚ ነበር፣ አይደል!” ይለዋል፡፡
“በጭራሽ፣” ይለዋል ሰውየው፡፡ “ሰዎቹ እንግዳ ተቀባዮች፣ ምግቡ ጣት የሚያስቆረጥም፣ ገጠሩ ደግሞ ገነት የሚመስል ነው፡፡”
“ከጳጳሱ ጋር እናገናኝሀለን ያሉህስ?”
“ጳጳሱ ሠገነቱ ላይ ሆነው እኔ ህዝቡ መሀል ነበርኩ፡፡ ከዛ ሁለት ዘቦች መጡና ጳጳሱ ሊያናግሩህ ይፈለጋሉ፣” አሉኝና ወደ እሳቸው ይዘውኝ ሄዱ፡፡”
“እና ምን የተለየ ነገር ነገሩህ?”
“ምንም የተለየ ነገር አልነገሩኝም፡፡ ግን አንድ ጥያቄ ብቻ ነው የጠየቁኝ፡፡
“ምን ጠየቁህ?” አለ ጸጉር እስተካካዩ፡፡ ሰውየው ምን ቢል ጥሩ ነው...
“የእኔ ልጅ ጸጉርህን እንዲህ የተጫወተበት ማነው ብለው ነው የጠየቁኝ፣” ብሎት እርፍ፡፡
እናማ እዛ ማዶ ስለእኛ የሚባለውን ስለማናውቅ የሌሎች የሆነውን ሁሉንም ነገር ማጣጣል፣ ከሁሉም በላይ አንደኛ ነኝ ምናምን ማለት አሪፍ አይደለም ለማለት ያህል ነው፡፡   “ይሉሽን ባልሰማሽ ገበያም ባልወጣሽ፣” አይነት ነገር ነው፡፡ ሰውየው መጀመሪያ በቅጡ የደንበኞችን ጸጉር ማስተካከል ሳይችል ሽለላውን አያችሁልኝ!
“ይሉሽን በሰማሽ ገበያም ባልወጣሽ!” የሚለው ጥቅስ ዋና፣ ዋና ቦታዎች ላይ ይደረግልንማ!
ደግሞላችሁ ይሄ በባዶ ሜዳ የመሸነጋገል ነገር አይገርማችሁም! የምር እኮ...አለ አይደል... በአራዶቹ አነጋገር ‘‘እየተሸዋወድን’ መሆኑን እየተዋወቅንም “ልቤ! ሆዴ!” ስንባባል፣ ምን አለፋችሁ... ተራውን የሚጠብቅ የቲቪ ሲትኮም በሉት፡፡
ስሙኝማ...ቀሺም የሆነች፣ የአገልግሎት ጊዜዋ ካበቃ የከረመች የነጋዴዎች አባባል አለችላችሁ፡፡ “ለአንተ ብዬ ነው ባመጣሁበት ዋጋ የምሸጥልህ፡፡” እንዴት እንዴት! አንተዋወቅ፣ ተያይተን አናውቅ፣ አንዳችን ሌላኛችን ላይ ውለታ የለብን! እንዴት ብለህ ነው ፍጹም ከእነመፈጠሬ ለማታውቀኝ ሰው ትርፍህን ትተህ ባመጣህበት ዋጋ የምትሸጥልኝ? የቤት ኪራዩስ፣ የመብራት ውሀ የመሳሰሉት ወጪዎችስ?” አፍ አውጥተን እንዲህ አንበል እንጂ ስሜቱ ይኸው ነው፡፡ “ያልወለድኩት ልጅ አባባ ቢለኝ አፌን ዳባ፣ ዳባ አለኝ፣” አይነት ነገር ነው፡፡ ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ... እነሱ እንደዛ ማለታቸው ብቻ ሳይሆን እንዲህ ብንል ያምኑናል ብለው ማሰባቸው ነው፡፡
ለምሳሌ የራሳቸውን ልጆች ስነ ስርአት የተላበሱ ጨዋዎች፣ የሌሎችን ልጆች ደግሞ ስነስርአት የጎደላቸው ችግር ፈጣሪዎች አድርገው የሚያዩ ወላጆች መአት ናቸው፡፡
“የእኔ ልጆች እቤት ውስጥ እንኳን ዕቃ ነካክተው ሊያበላሹ የትምህርት ቤት ቦርሳቸውን እንኳን ለእኔ ሳይነግሩ ንክች አያደርጉም፡፡” ኮሚኩ ነገር እኮ የብዙ ወላጆች ልጆች ቤት ውስጥ “መልአክ...” ሆነው እደጅ የዲያብሎስ ወጣት ክንፍ አባል ነገር የሚሆኑበት ምስጢር አይገባችሁም፡፡ ልጅየው መንደሩ ውስጥ ሰፈርተኛ እያየው ወይም ትምህርት ቤቱ ውስጥ መምህራንና ሌሎች ተማሪዎች እያዩት በአደባባይ ጥፋት እየሠራ ማዘርና ፋዘር ”መጥፎ ጓደኞች እያሳሳቱት ነው አንጂ፣ እሱ እንዲህ አይነት ጠባይ የለበትም፡፡ የእኛ ልጅ ስርአት ያለው ነው፣” ይባላል፡፡
“ይሉሽን በሰማሽ ገበያም ባልወጣሽ!” የሚለው ጥቅስ ዋና፣ ዋና ቦታዎች ላይ ይደርልንማ!
መንደሩ ውስጥ እኮ ልጁ...አለ አይደል.... መልካም አስተዳደግ የሌለው ልጅ ምን አይነት ባህሪይ እንዳለው እንደማሳያም፣ ለሌሎች እንደማስጠንቀቂያም ተፈጥሮ ያስቀመጠችው ነው የሚመስለው... “እንደሱ አይነት የሰይጣን ቁራጭ ከመውለድስ ለምን ጥንቅር ብሎ አይቀርም!” ነገር የሚባልለት አይነት ማለት ነው፡፡ እናማ ወላጆቹ ልጃቸውን ከንፍ ሳይሰጠው መልአክ ሲያስመስሉት ሌላው ያምነናል ብለው ማሰባቸው ዘይገርም አያስብልም!  
እኔ የምለው... ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...”ልጄን አስተማሪ ተቆጣው...” ብለው ‘ፒስቶልየዋን’ ይዘው ትምህርት ቤት ይሄዳሉ የሚባሉት አይነት ወላጆች አሁንም አሉ እንዴ! ነው ወይስ አስተማሪዎች መቆጣት ትተዋል!
ይቺን ስሙኝማ...ከአንዲት የአቤ ጉበኛ መጸሐፍ ላይ ያገኘኋት ነች፡፡
“እንካ ስላንትያ፡፡”
“በምንትያ?”
“በሐሞት፡፡”
“ምናለ በሐሞት?”
“አንተ በጉራ አንጂ መቼም በህመም አትሞት፡፡” የምር እኮ... እንግዲህ ጨዋታም አይደል...እንዲህ በአንድ ሺህ አንድ ችግሮችና መከራዎች ተተብትበን ሁሉ ጉራ በሽ ነው፡፡  ትኩስ ቦተሊከኛ፣ ትኩስ ባለገንዘብ፣ ትኩስ “አይ ላቭ  ሞር ዛን አይ ካን ሴይ፣” ትኩስ ለእረፍት የመጣ ዳያስፖራ፡፡ ኸረ ቢያንስ፣ ቢያንስ ጉራውን ተዉንማ! ሌሎችማ ጉራ በባዶ ሜዳ የቻይና ፊኛ እያሳከለን ላለነው የምር አሪፍ አመለካከቶች ይኖሯቸዋል፣ ቢነግሩን ጭጭ፣ ምጭጭ የሚያደርጉን አመለካከቶች... አይነግሩንም እንጂ!
“ይሉሽን በሰማሽ ገበያም ባልወጣሽ!” የሚለው ጥቅስ ዋና፣ ዋና ቦታዎች ላይ ይደርልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!Read 455 times