Saturday, 13 May 2023 20:28

ሂሩት በቀለ (1935 - 2015)

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ሂሩት በቀለ ከ50ዎቹ መጀመሪያ እስከ 80ዎቹ መጨረሻ ድረስ በጊዜው ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ጥቂት ስመጥር የሴት አርቲስቶች መሐከል አንዷና ተወዳጅ ድምፃዊ ስትሆን፤  የግጥምና የዜማ ደራሲም ነች:: ሂሩት የተጫወተቻቸው ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃዎቿ አሁን ድረስ በህዝብ ዘንድ በጣም ተወዳጅና እንደውም ለብዙ አዳዲስ ወጣት ሴት አርቲስቶች መነሳሻና አቅም መፈተሻ መሆናቸው ግልጽ ነው።  
የህይወት ታሪክ
ሂሩት በቀለ  በእለተ ሰኞ መስከረም 28 ቀን 1935 ዓ.ም. ከእናቷ ከወ/ሮ ተናኜወርቅ መኮንንና ከአባቷ የመቶ አለቃ በቀለ ክንፌ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ቀበና ተወለደች:: እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስም ቀበና ሚሲዩን ት/ቤት[1] በመግባት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷ ተከታትላለች::
የስራ ዝርዝር
ሂሩት በትምህርት ቤት በነበረችበት ወቅት ለክፍል ጓደኞቿና ለሰፈሯ ልጆች ማንጎራጎር ታዘወትር ነበር:: ይህን ችሎታዋን የተመለከቱት ጓደኞቿም ወደ ሙዚቃው አለም እንድትገባ በተደጋጋሚ ያበረታቷትና ይገፏፏት ነበር:: በዚህ መሰረት  በ1951 ዓ.ም. ከቅርብ ጓደኛዋ ጋር በመሆን ወደ ምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል[2] በመሄድ በድምፃዊነት ተፈትና ለመቀጠር በቃች:: ብዙም ሳትቆይ ለመጀመሪያ ግዜ በተጫወተችው “የሐር ሸረሪት” በተሰኘው ዜማ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትንና ተቀባይነትን አገኘች:: ይሄኔ ነበር የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ክፍል አይኑን የጣለባት። ጥሎባትም አልቀረ፤ በ1952 ዓ.ም. ላይ ከምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል እውቅና ውጪ የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ሂሩትን በመጥለፍ  በጊዜው ኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ወደሚባለው የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ በመውሰድ በልዩ ኮማንዶዎች የ24 ሰዓት ጥበቃ እየተደረገላት ከወር በላይ ተደብቃ ቆየች:: ከአንድ ወር ያላሰለሰ ጥረት በኋላ የምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል ፍለጋውን ለማቋረጥ በመገደዱ፣ የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ክፍል ሂሩትን በይፋ በቋሚነት የሠራዊቱ የሙዚቃ ክፍል አባል አድርጎ ቀጠራት::
ሂሩት ከተጫወተቻቸው አያሌ ሙዚቃዎቿ መሀከል እንደ ህዝብ መዝሙር በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታወቀውና ከትንሽ እስከ ትልቅ በሀገር ፍቅር ስሜት እስካሁን የሚያዜመው “ኢትዮጵያ” አንዱ ነው::
ሂሩት በፖሊስ ሰራዊት የሙዚቃና የትያትር ክፍል ውስጥ በቅንነት ለ35 ዓመት አገልግላለች:: በእነዚህም 35 ዓመታት ውስጥ ከ200 በላይ ሙዚቃዎችን የተጫወተችና ለህዝብ ጆሮ ያደረሰች ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ በሸክላ የታተሙት ከ38 በላይ ሙዚቃዎች፣ በካሴት ደረጃ ደግሞ 14 ካሴቶች እያንዳንዳቸው 10 ዘፈኖችን የሚይዙ ለሙዚቃ አፍቃሪዎቿ አበርክታለች::
ሂሩት በሙዚቃ አለም በቆየችባቸው አያሌ አመታት ውስጥ ከብዙ ስመጥር ድምፃውያን ጋር በመሆን ስራዋን ለህዝብ አቅርባለች፤ ከነዚህም መሀከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል:- ማህሙድ አህመድ[3]: አለማየሁ እሸቴ[4]: ቴዎድሮስ ታደሰ: መልካሙ ተበጀ: ታደለ በቀለ: መስፍን ሀይሌ: ካሳሁን ገርማሞና ሌሎችም ይገኙበታል።
ሂሩት በቀለ ከ1987 ዓ.ም. በኋላ እራስዋን ከሙዚቃ አለም በማግለል፣ ጌታን እንደ ግል አዳኟ በመቀበል ሙሉ ጊዜዋንና ህይወቷን ለመንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት ከ28 ዓመት በላይ በአገር ውስጥና በውጭ አገር በመዘዋወር ስለጌታችን እየሱስ ክርስቶ ታላቅነት ላልሰሙ በማሰማት፣ አያሌ ወገኖች የእግዚአብሄርን መንገድ እንዲከተሉና ወደ ህይወት እንዲመጡ ምስክርነት በመስጠት፣ በጸሎት በመትጋት ጌታን በዝማሬ እያገለገለች ቆይታለች፡፡  
ሂሩት በቀለ በሙዚቃ አለም በነበረችበት ጊዜ ከፍተኛ አድናቆትንና ዝናን ያተረፈች እንዲሁም ደግሞ በመንፈሳዊ ህይወቷ ደስታንና የመንፈስ እርካታን ያገኘች ቢሆንም፣ የግል ህይወቷን በተመለከተ ግን ያላትን ትርፍ ግዜ ሁሉ ከልጆቿና ከቤተሰቧ ጋር ማሳለፍ እጅግ አድርጎ ያስደስታት ነበር::
ሂሩት ከሙዚቃ ስራዋና ከመንፈሳዊ ህይወቷ በተጨማሪ፥ በጨዋታ አዋቂነቷም ትታወቃለች፡፡ ሂሩት በቀለ 7 ልጆችና 10 የልጅ ልጆችን አፍርታለች::
ሽልማቶች
ሂሩት በቀለ በሙያዋ ላበረከተችው አስተዋጽኦ ከአገር ውስጥና ከውጭ ሀገር በርካታ ሽልማትና የእውቅና ምስክር ወረቀት ያገኘች ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ለመጥቀስ ያህል:
1ኛ) ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ እጅ ከወርቅ የተሰራ የእጅ አምባር እና የምስጋና ደብዳቤ
2ኛ) ከኢትዮጵያ ፖሊስ ሰራዊት ኮሚሽነር የከፍተኛ ስኬትና የላቀ አስተዋጽዎ ሽልማት ከምስክር ወረቀት ጋር
3ኛ) በሙዚቃው ዓለም ላበረከተችው ተሳትፎ ከፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ የብር ዋንጫና የምስጋና ደብዳቤ
4ኛ) በሙዚቃው ዘርፍ ለእናት ሐገሯ ላበረከተችው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም እጅ ሰርተፍኬት
5ኛ) ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በኢትዮጵያና በሱዳን ህዝቦች መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማደስ ላበረከተችው አስተዋፅኦ የእውቅና የምስክር ወረቀት
6ኛ) ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላበረከተችው የሙዚቃ አስተዋፅዖ ከኢትዮጵያ አብዮታዊ ጦር የፖለቲካ አስተዳደር የምስጋና ደብዳቤና ሽልማት
7ኛ) ከፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ የቲያትር እና ሙዚቃ ክፍል የ25-ዓመታት ከፍተኛ ስኬት እና የላቀ አስተዋፅኦ የምስክር ደብዳቤ ከፍተኛ ሽልማት ጋር
8ኛ) ከቀድሞ የሰሜን ኮርያ ፕሬዘዳንት ኪም ኢል ሱንግ እጅ ከወርቅ የተሰራ ሜዳልያ
9ኛ) ከኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽነር: ለፖሊስ ሃይል ስፖርት ፌስቲቫል ላበረከተችው አስተዋፅኦ የእውቅና ሰርተፍኬት
10ኛ) ከመሰረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን: ላበረከተችው አስተዋፅኦ ልዩ እውቅና እና የምስጋና ሰርተፍኬት
11ኛ) ከወንጌል ብርሃን አለማቀፍ አገልግሎት ቤተክርስቲያን: በሃይማኖታዊ ህይወት ላሳየችው ትጋትና አስተዋፅኦ የምስጋና ሰርተፍኬት ይገኙበታል፡፡



Read 757 times