Monday, 15 May 2023 00:00

የእግዚሔር ብልሃት

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(2 votes)

ጠሐይ ብርሃኗን ላለመለገስ ባንገረገበችበት ቅጽበት ከሰማይ አፍ ዝልግልግ የዝናም ልሃጭ ተዝረበረበ…
…ይህኛው ደግሞ ከእኔ አፍ፡-
‹ፈጣሪ የሰው ልጆችን ከፈጠረ በኋላ ሁለት ዋና-ዋና የማሰናከያ ዘዴዎችን ፈጥሮ ከእንቅስቃሴ ገንትሯል። ቀጭቃጫው የሰው ልጅ ወደ የትም አቅጣጫ ውልፍት እንዳይል ምግብና ወሲብ የፈጣሪ የማዘናጊያ ብልሃቶች ሆነው ይታዩኛል…
…ወንዱ ዶሮ እንኳን በተጋረጠበት ተፈጥሯዊ አሠራር ጭሮ ቀፈቱን ከመሙላት አንስቶ በቀን ከሰባት ሴት ዶሮዎች ጋር ሰባት ጊዜ አሸሸ-ገዳሜ እስከማለት ድረስ ብያኔ ማግኘቱ ዕሙን ነው። ሰባት ሲባዛ በሰባት…›
…ይኼንን እያሰላሁ ራዲዮኑ፡-
ዶሮ ውኃ ጠምቶት፣ ተንጋሎ ይጠጣል፤
ከዋሉ ካደሩ፣ መረሳት ይመጣል፤…
ከማለቱ አባቴ አናጠበ፡-
‹‹ተናህያው ሞተ! መጠጫ አጥቼ ዓይኔ ይጠናበራል፤ አዋቂ ነኝ ባይ ግን ስለ ዶሮ የውኃ አጠጣጥ ስልት ይተርክልኝ ገባ!›› ያማርር ያዘ
እናቴ ተቃወመች፡-   
‹‹አቤት እርሶ ሰውዬ! ሰው ጉባኤ ይታደማል፤ ተዚያ ሲያልፍ በእየአድባራቱ ሱባኤ ይገባል፤ እኔ የምለው አንቱን ሰው ከጠጅ ሸንጎ የሚያናጥብዎ ምን ዓይነት ብልሃት ይሆን? ወይስ ጠጅ ቤት ሊመነኩሱ ኖሯል?››
አባቴ እጅግ ስለነጣ የደመና ቁራሽ የመሰለ ጋቢውን ተወዲህ - ወዲያ በስልት እያመሳቀለ ጥቂት ተቁነጠነጠ፤ ሊናገር የፈለገው ነገር እንዳለ ገብቶኛል
‹‹ያው ባይሆንልኝም መታደሙ እንዳይከፋ ዕሙን ነው! ደግሞ መታደሚያዬን አትንሳኝ ማለትም ሸጋ ነው›› አፉን አበሰ
‹‹ኧረዲያ፣ የጠጅ ሸንጎ ለመታደም ይህን ያህል መጀነንዎ በጤናዎት አይመስለኝም፤ እንደው ጠጅ ቤቶቹንም እሳት ያንሳቸው እቴ!››
‹‹ካሟረትሽ አይቀር እንግዳውስ ቤት ጎልተሽ ወጥ አስቀቅዪኛ››
§
ያልከረረ ክርክራቸው እየጣመኝ ሲመጣ ሕብስት ሰላላ አፍንጫዋን አስቀድማ ገባች። ከውጭ እየሰማች ስለነበር እንደ በግ በድዷ እየሳቀች ነበር ስትገባ
‹‹ሕብስቴ መጣሽ፣ አባትሽስ?›› አባቴ ነው
ነጠላ ከሚቋጭበት ተነስቶ ሳማት
‹‹ደኅና ነው›› በድዷ እየሳቀች
እናቴ በሆዷ ‹እነዚህ በጠጅ የተወዳጁ ሁለት አምቡላሞች› ማለቷ አይቀርም። ለማይደርስ ምሣ ዕቃ እያተረማመሰች ነው፤ ወይስ የዛሬው ምሣ የሚወጣው የቀበሌው አስተዳዳሪ ቤታችን ተገኝተው ሪዣን ከቆረጡ በኋላ ነው?   
ሳሎን ደርሳ ሕብስትን ስማ ተመለሰች። ምሣውን ለማንዛዛት ካላት ጽኑ ፍላጎት የተነሳ እንጂ ትላንት የሳመቻትን ዛሬ መድገም ምን ማለት ነው? ትሪው ለአስራ ምናምንኛ ጊዜ ሲንኳኳ ብሰማም ምሣው የለም፤ እንግዲህ እንደ ታቦታ አጨብጭበን እስካልወጣ…
‹‹የጣት ውኃ ውሰዱ›› ተሽቀዳድሜ ጓዳ ገብቼ ውኃ አሰናዳሁ…
…ገበታው ሲነሳ ሕብስት የእጅ ውኃ አቀረበች
‹‹እንደ አድባር በሬ ሳትሠራ ትበላ?›› እናቴ ጎፈላች
ሕብስት የሠፈራችን ልጅ ናት፤ ውበቷ የሚረብሽ ዓይነት። ሴት ለሴት አይገጥምምና ሴት ጓደኛ አልነበራትም። አሥራ ሁለተኛ ክፍልን አጠናቃ ሱቅ ተከፈተላት። እኒያ ሞላላ ጡቶቿን የመተዋወቅ ዕድል ገጥሞኝ አንድ ሁለቴ፣ ሦስት አራቴም ተምነሽንሼአለሁ። ግን ምን ያደርጋል አንጎለ ቢስ ናት። ታዲያ አንጎል ባያድላትም ሕሊና አልነፈጋትምና ፈር ስታ አታስኮንንም። ያፈነገጠ ዳሌዋ ፈር ያስታል እንጂ
‹‹እንሂድ፣ ልጁ እየጠበቀህ ነው›› ዓይኖቿን አስለምልማ
‹ልጁ› ያለችው የተረገመ ወንድሟን ነው፤ የልጅ ማሽንክ። ሥራ በመፍታቴ በአስጠኝነት ተቀጥሬ ሳበቃ አንድ ቀን ጥያቄ አቀረብኩለት፡-
‹‹ማሙሽዬ፣ ሰዎች ትዳርን እንዴት ሊመሠርቱ ይችላሉ?››
ትንሽ ራሱን ሰልሎ…   
‹‹በትዳር አገናኝ ደላላ አማካኝነት›› ትክን እንዳልኩ ሌላ ጠየኩ፡-
‹‹በረት ውስጥ አንድ ሴት ፈረስ አለች እንበል… አንድ ወንድ አህያ ብናስገባ ስንት ይሆናል?››
‹‹ሦስት፤ አህያው ፈረሷን ስለሚያጠቃት በቅሎ ይጨምራሉ››
በብስጭት አልጎመጎምኩ
§
ሕብስት በብልጣ-ብልጥ ዓይኖቿ አጨንቁራብኛለች። የለበሰቺው ባለ ወርቅ መሳይ ጉብ-ጉብ ቀሚስ ዓይን ያጥበረብራል። (ቀሚሱ ወይስ ዳሌዋ?) እንደረመጥ የሚፋጁ ከናፍሮቿን እርስ-በርስ እያባበሰች፡-    ‹‹በል እንጂ›› ልምጥምጥ ብላ፤ ልታላምጠኝ እላመጥ፤ እንዳስጠና ሳይሆን ሕቡዕ ተልዕኮዋን እንድፈፅም
ቀመሯ ገብቶኛል…
‹‹ማንጎላጀቱ የት ይሄድብሃል? እግዚሔር ይመስገን እንዳንተ ሥራ ፈቶ አምሥት ዓመት የመንቀዋለሉን ልምድ ማን ታደለ? ማንም። አትሰማ፤ አትለማ የሰው ገልቱ›› አባቴ ንግግሩን ጥቂት ገትቶ መጀመሪያ እኔን ቀጥሎ ዙሪያ-ገባውን ከገረመመ ወዲህ ቀጠለ…
‹‹ያንተ ነገር ከስርፋ ስርፋ መንጦልጦልና መንቦላፋት ሆኖ ቀረ፤ ብታውቅ ያለ ሥራ ተጎልቶ መዋል ለጤናህ ጠንቅ ነው አዕምሮህም ይወይባል፤ ለካ አዕምሮ የለህም (ወደኔ እያየ)… ‹‹ያልሠራ እንደሆን ክንድም ይርዳል፤ ስንቴ ይርዳል?›› በአንድ ትንፋሽ አልጎመጎመ
ቀመሯ አልገባውም…
§
…የዓለም ሳንባ ሰው ሰልችቶኛል፤ እኔም ሰልችቼውአለሁ። አንድ ሰሞን ልክ እንደ ነብዩ ዮናስ ከዕጣ-ፈንታዬ ተላትሜ መድረሻ ቢጠፋኝ ግዘፍ የነሳ ዳሌዋ ዓሳ አንባሪ ሆኖ በመሰልቀጥ ሦስት ቀን ብቻ ሳይሆን ከሠላሳ በላይ ቀናቶችን በምቾት አሳድሮኛል። እና ይኼንን ሚስጥር ሰማይና ምድር ልብ ብለዋልና የምጽዐት ቀን ያሳብቁብኛል፤  
‹‹ተነስ እንጂ›› ወደ ዓሳ አንባሪው
እየተቆናጠረች ቀደመች፤ አልሃም ዱልላህ፣ የእግዚሔር የማሰናከያ ብልሃት እንዲጋረጥብኝ ዕሙን ሆነ፤ የሚውጠኝ ሞንዳሌ ዳሌዋን እየወረብኩ ተከተልኩ፤ እንደ ንጉሥ ዳዊት ‹ሕግህ በልቡናዬ ውስጥ ናት› ማለት እየቃጣኝ።
*‹‹ገበጣ›› ከሚል ካልታተመ ድርሰት የተቀነጨበ።

Read 1772 times