Saturday, 13 May 2023 20:48

“አባታር” አርቴፊሻል ኮንሰርት

Written by  -ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

  በለንደኑ የኦሎምፒክ ስታዲዮም አጠገብ ነው፤ የሙዚቃ ኮንሰርት ማሳያ የተገነባው። ምንም አይደል! ያው ሁለቱም ይዛመዳሉ። የስፓርት ኦሎምፒክም፣ የሙዚቃ ጥበብም፣… መንገዳቸው ቢለያይም፣ የመንፈስ ማርና ወተት ናቸው።
ለጥበበኞቹና ለስፓርተኞ፤ የኑሮ መተዳደሪያም ጭምር ይሆናሉ ከመንፈሳዊ ባህሪያቸው በተጨማሪ።
ለተመልካችና ለአድናቂ ግን፣ የኦሎምፒክ ውድድርና የሙዚቃ ትእይንት፣… መንፈሳዊ ድግስ ናቸው። ያው፣…ፋይዳቸው፣… እያዩ ለመደነቅና ለመቦረቅ፣ እያደመጡ ለመመሰጥና በምናብ ለመክነፍ ነው።
የፊልምና የትያትር ተመልካቾች፣ የገፀባሕርያት ውጣውረድ እንደራሳቸው ጉዳይ እየቆረቆራቸው፣ በተስፋና በስጋት ልባቸው መንጠልጠሉ፣… እንዲህ፣… መንፈሳቸው ተቀስቅሶ መንቃቱ ነው ትርፋቸው። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣ ለሰው ህይወት፣ ለሰው በጎ አላማ፣ ለሰው ብቃትና ጥረት፣ ለመልካም ተግባርና ለግል ማንነት ከምር ደንታ እንዳላቸው ያውቁበታል። ቀላል ነገር አይደለም። “ሰው ከመሆን ክብር” ጋር የተሳሰረ ትልቅ ትርጉም አለው። ይህንንም፣ በሃሳብና በስሜት፣ በሁለመናቸው በሚሰርፅ መንፈስ ያጣጥሙታል።
የዚህን ያህል ውድ ነው ዋጋቸው። ኦሎምፒክ ውስጣች ነው፤ ስእልና ሙዚቃ ነፍሳችን ነው ቢባል ያስኬዳል። አየር እንደ መተንፈስ፣ ምግብ እንደመብላት፣ በጤናማ የአካል እንቅስቃሴና በንቁ አእምሮ ኑሮን እንደ መምራት፣… የኦሎምፒክ ውድድሮችና የኪነጥበብ ስራዎችም እንደዚያው የመንፈስ ጤንነት ናቸው - የነፍስ ማርና ወተት። መንፈስን ለኩሰው የሚያሞቁ፣ በህብረ ቀለማት የሚያደምቁ፣ ነፍስ የሚዘሩና ውስጥን የሚያድሱ፣ የሰብዕና እስትንፋስና መዓዛ ናቸው።
ለዚያ ነው፤ መረጃ ለማግኘት ወይም እውቀት ለመማር ባያገለግሉን እንኳ፣ ሙያዊ ስልጠና ወይም ገቢ ማስገኛ፣ የእለት ጉርስ ወይም መጠለያ ባይሆኑልንም እንኳ፣… ይማርኩናል፣ ይመስጡናል፤ ያዝናኑናል።
እናም፣ የብቃት አምባ የነበረውን የኦሎምፒክ መንደር፣… የሙዚቃ መድረክ፣ የጥበብ አምባ ሲያደርጉት፣… ከመነሻ አላማው ብዙም አልራቁም። ደግሞስ፣ በባዶ ከሚቀመጥ፣ ገቢ ቢያስገኝ አይሻልም?
ለማንኛውም፣ ለበርካታ ወራት በብዙ ወጪ ለሙዚቀኞችና ለታዳሚዎች እንዲመች ተደርጎ ተዘጋጅቷል። ግንባታውና የኮንሰርት መሰናዶው፣ 175 ሚሊዮን ዶላር እንደፈጀም ተነግሮለታል።
ሙዚቀኞቹ፣ ‹‹ABBA›› በሚል ስያሜ የሚታወቁ ‹‹ወጣቶች›› ናቸው።
በትክክል ወጣቶች ናቸው፤ ግን ደግሞ አይደሉም።
 መድረክ ላይ ሙዚቃ ሲያቀርቡ፣ ሲዘፍኑና ሲደንሱ የሚታዩት ጥበበኞች፣ ያለጥርጥር ወጣት ናቸው። ገብቶ ያየ ሁሉ ይመሰክራል።
ነገር ግን፣…‹‹ABBA›› በመላው ዓለም ተወዳጅነትን ያተረፉትና ዝነኛ የሆኑት መቼ ነበር? ታሪክ ካላነበብን ላናውቃቸው እንችላለን። ከ40 እና ከ30 ዓመት በፊት ነው፤ የወጣቶቹ አልበምና ዘፈን በዓለም ማእዘናት ያስተጋባው፣ የተደመጠውና የተወደደው። ዛሬ እንደገና ተመልሰው ወጣት ሊሆኑ አይችሉም። ይሄም እውነት ነው። ማየትና ማረጋገጥ ይቻላል።
በቴሌቪዥን በሚቀርቡ ቃለ ምልልሶች፣ በጋዜጣ የሚታተሙ ፎቶዎች ላይ ለሚያያቸው፣… ዝነኞቹ ዘፋኞች፣ ዛሬ ወጣቶች አይደሉም።
በአዲሱ የሙዚቃ መድረክ፣ የኮንሰርቱ ትእይንት ላይ ለሚያያቸው ግን፣ ዛሬም ወጣቶች ናቸው። እንዴት ሊሆን ይችላል?
“አርቴፊሻል” ኮንሰርት ቢሆን ነዋ። የቴክኖሎጂ ፈጠራ! የድሮዎቹን ወጣቶች የሚመስሉ ተዋናዮች ተመልምለው ወደ ኮንሰርቱ አልመጡም። ድሮ የተቀረፀ ፊልምም አይደለም።
የሙዚቃው መድረክ፣ እንደ ዘመናዊ ኮንሰርት፣ በመብራቶችና በድምፅ ማጉያ መሳሪያዎች የተሟላ ነው። የሙዚቃ መሳሪያዎችና ተጫዋቾችም አሉ።
ዘፋኞቹ ግን፣… እነሱም መድረክ ላይ ሲዘፍኑ ይታያሉ። ነገር ግን “በምስላቸው” ብቻ ነው መድረክ ላይ የሚንቀሳቀሱት፣ የሚደንሱትና የሚዘፍኑት። መድረኩ እንደ ፊልም አዳራሽም ነው ማለት ይቻላል።
በእርግጥ ፊልሙ ግድግዳ ላይ ወይም ነጭ ሸራ ላይ አይደለም።
“ወለሉ ላይ የቆመ፣ አየር ላይ የተንሳፈፈ ፊልም” ብንለው ይሻላል። ከጀርባ በኩል ያሉት ሙዚቀኞችና ቁሳቁሶችም በግልፅ ይታያሉና።
ነገሩ እንዲህ ነው። አራት ወጣት አርቲስቶች፣ እንደ ፊልም ተዋናይ፣ ስቱዲዮ ውስጥ ለ6 ሳምንታት ሲደንሱና ሲዘፍኑ ከርመዋል። ቀረፃው ግን ከፊልም ይለያል። የእጅና የእግር፣ የአንገትና የወገብ እንቅስቃሴዎች በሙሉ፤ የአይን እና የቅንድብ፣ የከንፈርና የፈገግታ ንቅናቄዎች ሁሉ፣ “ልቅም ተደርገው” ተቀርፀዋል።
ምን ጥያቄ አለው። በ160 ካሜራዎች ነው ቀረፃ የተካሄው። የፀጉር ዘለላ ሽውታ፣ የሸሚዝ ጫፍ ውልብታ አልቀረም። መቶ ምናምን ካሜራ ጥቃቅኗን ነገር ሁሉ ካልቀረፀ ምን ይሰራል?
ከዚያስ? ስራው ገና ተጀመረ እንጂ አልተጋመሰም። ከቀረፃ    ው ውስጥ፣ የተዋናዮቹ ማንነት አያስፈልግም። ቅርፃቸውና እንቅስቃሴያቸው ብቻ ነው የተፈለገው። እናም የቅርፅና የእንቅስቃሴ ቀፎ ለብቻው ተነጥሎ ይወሰዳል። በዚህ ቀፎ ላይ፣ የድሮዎቹ ዘፋኞች መልክና ቁመና ይሸመናል። የድሮ የወጣትነት ፎቶና ምስላቸው፣ የሙሉ አካል ቅርፅ ይላበሳል። ግራ ቀኝ ይራመዳል። “ለዘመኑ ቴክኖሎጂ” ምን ይሳነዋል?
ከአቫታር ጋር ያመሳስሉታል። አባታር ብለውም ሰይመውታል። AABAtar መሆኑ ነው። ነገርዬው ግን፣ እንደ “3D አኒሜሽን” ነው። ፎቶዎች ላይ ነፍስ እንደመዝራት፤ ሀውልቶችን ህያው እንደማድረግ ቁጠሩት። ቀላል ስራ አይደለም። የካሜራዎች ብዛት ያህል፣ ሃይለኛ የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂዎችና ምርጥ የሙያ ጥበበኞች ተጨምረውበታል። እናም፣… “ዙሪያ ገብ” የሆነ፣ “ከብዙ አቅጣጫ የሚታይ” የሙዚቃ ምስልና ትዕይንት ተፈጥሯል።
ይህም ግን በቂ አይደለም። “ዙሪያ ገብ (3D)” ፊልም ብቻውን ድንቅ ስራ ሊሆን ይችላል። ግን “ኮንሰርት” አይሆንም። ሸራ ላይ ወይም ግድግዳ ላይ የሚያርፍ ፊልም፣… ተመልካቾች በልዩ መነጽር ሲመለከቱት ዙሪያ ገብነቱ ድንቅ ቢሆንም፣… ያው ፊልም እንጂ፣ የመድረክ ኮንሰርት ሊሆን አይችልም።የሙዚቃ መሳሪያው፣… ጊታሩና ሲንተሳይዘሩ፣ ከበሮና ታምቡሩ፣ የሙዚቃ ተጫዋቾቹ የት ይሆናሉ? ከመጋረጃ ጀርባ፣ በሸራ ተከልለው?
ለዚህም ችግር ሌላ የቴክኖሎጂ መፍትሔ ተመርጦለታል። በዓይን የማይታይ፣… የፊልም ብርሃን ካላረፈበት በቀር፣ ከወዲህ ከወዲያ ብርሃን የማይጋርድ ልዩ ሸራ!
መድረኩ መሃል ላይ የተዘረጋው ልዩ ሸራ ለተመልካች አይታይም። ጥርት ተደርጎ የተወለወለ፣ ብርሃን የሚያሳልፍ ንፁህ መስተዋት እንደማለት ነው። “ከፕሮጀክተር” የሚመጣው ጨረር ሸራው ላይ ሲያርፍበት ግን፣ ፊልም ያሳያል። ታዲያ፣ ከጀርባ ያሉትን ሙዚቀኞች አይጋርድም። በጥራት ይታያሉ።በሌላ አነጋገር፣ መድረኩ መሃል ላይ ሲደንሱና ሲዘፍኑ የሚታዩት ዝነኛ ድምፃውያን፣ እንደ ሌሎቹ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች፣ እዚያው መድረክ ላይ ያሉ ይመስላሉ።በአካልና በመንፈስ፣ በሃሳብና በተግባር፣ በህይወት የሚታይ፣ የምር የተሟላ የሙዚቃ ትእይንት ይመስላል - ለተመልካች ሁሉ። “ኮንሰርት” ለሚል ስያሜ የበቃውም፣ በዚህ ሁሉ ጥበብና ቴክኖሎጂ አማካኝነት ነው።
ግን፣… “በጣም ይመስላል” ከማለት አልፈን፣ “የውን ትእይንት (Live concert ) ነው” ማለት እንችላለን?
“በከፊል የውን”፣ “በከፊል የማስመሰያ” እንደሆነ ለመግለፅ፣ ቨርቹዋል ወይም አጉመንትድ ሪያሊቲ የሚሉ ስያሜዎችን መጠቀም ይቻላል። ታዲያ የቴክኖሎጂውን ምንነትና ዘዴውን ለማስረዳት ያህል እንጂ፤ ለማጋለጥ አይደለም።
“የተሟላ፣ የውን የእውነት ኮንሰርት” ከምር መምሰሉ ነው፤ የዝግጅቱ አላማና አስደናቂነቱ። አስመስሎ ለማታለል በሚል ትርጉም አይደለም። እንደ ልብወለድ ድርሰት ወይም እንደ ዘፈን ግጥም ነው (የውን ዜና ወይም የእውነት ታሪክ አለመሆናቸው፣… ባህርያቸው ነው)።
ኮንሰርቱ ለተመልካቾች አስደናቂ የሆነውም፣… የውን ኮንሰርት አለመሆኑና ከምር መምሰሉ ላይ ነው።በእርግጥ ለዘፋኞቹ የገቢ ምንጭ ነው። ለዚያውም፣ በቦታው መገኘት አያስፈልጋቸውም። ተመልካች እስከተገኘ ድረስ፣ የዘፋኞቹ የገቢ ምንጭ ከሳምንት ሳምንት አይቋረጥም።
መድረክ ላይ የሚታዩት ዘፋኞች፣… ማለትም “ምስሎች”፣…
ደከመን ሰለቸን አይሉም።
በጉንፋን ድምፃቸው አይበላሽም፤
በዘፈን ብዛት ጉሮሯቸው አይዝልም፤አይቆጣም።
ምግብና መጠጥ አይፈልጉም። ጉዳይ ገጠመን ብለው አይዋከቡም።
በመሃላቸው አለመግባባትና ቅሬታ አይፈጠርም።
አርቴፊሻል ኮንሰርት፣… ወርቅ የምትጥል፣ ቀልቡኝ የማትል የምትሃት ዶሮ ትመስላለች።
በእርግጥ፣…”የፈጠራ ባለቤትነት መብት” የሚሉት ነገር፣ በሁሉም አገር እንደ ቁም ነገር ይቆጠራል ወይ የሚለው ጥያቄ፣ ለዘፋኞች ከባድ የራስ ምታት ነው። የፈጠራ ባለቤትነት በሌለበት አገር፣… አርቴፊሻል ኮንሰርት፣ ለሙዚቀኞና ለዘፋኞች የምትሃት ዶሮ አይሆንላቸውም። ባዶ እጅ የሚያስቀር ነጣቂ ቀበሮ ይሆንባቸዋል። የ”ወሮ-በላ” ሲሳይ ያደርጋቸዋል።
ለአርቴፊሻል ኮንሰርት፣ ዘፋኞች አያስፈልጉማ!
እንደ ሙዚቃ አልበም ነው። እየተባዛ ይበተናል። “የሙዚቃ ኮንሰርት ተሰረቀ” ወደሚባልበት ዘመን ደረስን ማለት ነው?

___________________________________________________


                አርቴፊሻል ስጋ፣ “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” አርቴፊሻል አልማዝ!


         90 ቢሊዮን ዶላር ነው፣ የዓለማችን የአልማዝ ጌጣጌጥ ዓመታዊ ገበያ። ታዲያ፣ የጌጣጌጦቹ ምንጭ፣ የአልማዝ ማዕድን ብቻ አይደለም። የፋብሪካ አልማዝም ተጨምሮበታል - ማለትም አርቴፊሻል አልማዝ። ግን አትናቁት። “አልማዝ መሳይ” ማለት አይደለም።
“ተፈጥሯዊ አልማዝ”፣ የአንድ ካራት ዋጋ፣ 5,600 ዶላር ነው።  ባለ አንድ ካራት እንቁዎች፣ አምስቱ አንድ ግራም  ይሆናሉ። ዋጋቸውን ብናሰላው 28,000 ዶላር ይሆናል። በብር ባትመነዝሩት ይሻላል።
የገበያ ምንዛሬና አርቴፊሻል ተመን
መቼም፣ የዛሬ ጉዳያችን፣ በተፈጥሯዊና በአርቴፊሻል ነገሮች ዙሪያ አይደል? የዘመናችንን ባሕርይና የወደፊት አዝማሚያውን ለመረዳት ይጠቅመናል። “አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ” የዘመናችን ልዩ ክስተት ነው። “አርቴፊሻል ገንዘብም” እንደዚያው። በዚያ ላይ “አርቴፊሻል ስጋ” ጨምሩበት። የአገራችን የዶላርና የብር ምንዛሬም፣ በዚሁ መነፅር ልናየው እንችላለን። እውነተኛው ምንዛሬና አርቴፊሻሉ ምንዛሬ ተምታቶብናል።
የአገራችን የምንዛሬ ስርዓት፣ እንደ እንቁና እንደ እርሳስ፣ ዋጋውና ተመኑ ተራርቋል። የመንግስት ምንዛሬና የገበያ ምንዛሬ የትና የት። በእርግጥ፣ የገበያ ምንዛሬው፣ ሕገወጥ የጥቁር ገበያ ዋጋ ነው ይባላል። ከገበያው ጋር እጅግ የተራራቀው ሕጋዊ የምንዛሬ ተመን ደግሞ፣ ባለዶላሮች የሚሸሹት ሆኗል።
በእርግጥ የተዛባው የምንዛሬ ተመን በአንዴ ይስተካከል ቢባል፣ ገበያውን ይረብሻል። ነገር ግን፣ በአርፊሻል ተመን፣ ለረዥም ጊዜ  መቀጠልም አይቻልም። መስተካከሉ የግድ ነው።
ለማንኛውም፣ ወደ አልማዝ እንደመለስ።
አልማዝ፣ ያው አልማዝ ነው- አርቴፊሻሉም።
የሴቶች የጋብቻ ቀለበት አማካይ የአልማዝ እንቁ፤ 1.5 ካራት ነው።  ከሩብ ግራም ትንሽ ቢበልጥ ነው። ዋጋው ግን፣ 9,500 ዶላር ገደማ ይሆናል።
ይሄ የ2023 ትኩስ መረጃ፣ አንድ ነገር ጎድሎታል። እንዲህ አይነት መረጃ ከ10 ዓመት በፊት በቂ ነበር። ዛሬ ግን፣ “የትኛው ዓይነት አልማዝ?” የሚል ጥያቄ ያመጣል። የሌላኛው አልማዝ ዋጋስ ምን ያህል ነው? የሚል የማነጻጸሪያ ሃሳብ ተፈጥሯል።
የአልማዝ የነፀብራቅ ሕብር ወይም የጥራት ደረጃውን  በአይን ተመልክቶ፣ በመሳሪያ አስመርምሮ ማማረጥ፣ ድሮም የነበረ ነው። “የአልማዝ ዓይነት” የሚል  የንጽጽር ጥያቄ ግን፣ አዲስ የ21ኛው ክፍለዘመን ጥያቄ ነው።
አልማዝ ያው አልማዝ ነበር ለወትሮው።
አሁን ግን፣ “የማዕድን አልማዝ” አለ። “የፋብሪካ አልማዝ” ደግሞ መጥቷል።
ነባሩን አልማዝ አስበልጣችሁ ለማሞገስ፣ መጤውን አልማዝ ለማጣጣል ከፈለጋችሁ ደግሞ፣ “የተፈጥሮ አልማዝ” እና “አርቴፊሻል አልማዝ” የሚሉ ስያሜዎችን መጠቀም ትችላላችሁ። ግን ልብ በሉ። እውነተኛ አልማዝ እና የውሸት አልማዝ ማለት አይደለም። አንደኛው ዘላለማዊ ሌላኛው ሳምንታዊ አይደለም።
እንዲያውም ልዩነት እንደሌላቸው በመግለፅ፣ የንግድ ህጎች ተሻሽለዋል። ያኛውም ያኛውም ያው አልማዞች ናቸው ተብሏል። ጠንካራ፣ ዘመን ተሻጋሪና ጌጠኛ ናቸው- ሁለቱም አልማዞች።
ደግሞም፣ ከ7 ዓመት በፊት፣ ዋጋቸው እኩል ነበር። የማዕድን አልማዝ በቀላሉ  በየቦታው አይገኝም። የፋብሪካ አልማዝም፣ በቀላሉ እንደመስተዋት አይመረትም። ጠንካራና ተጫጭረው የማይበላሹ ስለሆኑ፣ ልሙጥና አንጸባራቂ ውበታቸው ሳይደበዝዝ “ለዘላለም” ይዘው ይዘልቃሉ።
እንዲያውም፣ የተፈጥሮ አልማዞች፣ በከርሰ ምድር ከቢሊዮን ዓመታት በፊት የተፈጠሩ ናቸው ይላሉ ተመራማሪዎች።
እንቁነታቸው ዛሬም ድረስ አለ። ወደፊትም ምዕተ ዓመታትን ይሻገራል። የፍቅርና የጋብቻ ምልክት እንዲሆን የአልማዝ እንቁ መመረጡ አይገርምም። ጠንካራ፣ ብሩህ፣ ብርቅ፣ ውድና ውብ የዘላለም በረከት ነውና፤ ሰዎች እንደዚህ አይነት ፍቅርና ጋብቻ ይመኛሉ። እስከዛሬ በተፈጥሮ ከተገኙ ነገሮች ሁሉ በጥንካሬ ይበልጣል- አልማዝ። አይዝግም፤ አይበረዝም፣ አይሸረሸርም፣ አይደበዝዝም፤ መልኩን አይቀይርም… እቶን ውስጥ ካልጨመሩት በቀር፣ በመዶሻ ካልሰባበሩት በቀር፣… የአልማዝ ምንነትና ውበት አስተማማኝ ነው። ከፍቅርና ከጋብቻ ጋር ያለው ዝምድና አይበዛበትም።
በዚህ በዚህ ሁሉ፣ የማዕድን አልማዝ እና የፋብሪካ አልማዝ ልዩነት የላቸውም። በማዕድን ቁፋሮ፣ በተለያየ የጥራት ደረጃ፣ የአልማዝ እንቁዎች ተገኝተዋል፤ እየተገኙም ነው። በዚያው ልክ፣ በፋብሪካም እየተመረቱ ነው። ታዲያ ቴክኖሎጂው በአንዴ አልተራቀቀም። ሰው ሰራሽ አልማዝ ለመፍጠር የሳይንስ ሙከራ የተጀመረው ከ150 ዓመታት በፊት ነው። ወዲያው አልተሳካም። የዛሬ 70 ዓመት ገደማ፣ የስዊድንና የአሜሪካ ትልልቅ ኩባንያዎች ቴክኖሎጂውን መልክ ካስያዙት በኋላም እንኳ፣ የአልማዝ እንቁዎችን መፈብረክ ቀላል አልሆነላቸውም። ቴክኖሎጂ ግን ብዙ የማሻሻያ እድሎች አሉት። አመታትን ቢፈጅም፣ በተለይ ባለፉት 10 ዓመታት አስደናቂ ፈጠራዎች ተጨምረውበት፣ የፋብሪካ አልማዝ በጥራትና በስፋት ወደ ጌጣጌጥ ገበያው ገብቷል።
አሜሪካ ውስጥ ከመቶ የጋብቻ ቀለበቶች መካከል 30ዎቹ በፋብሪካ አልማዝ ተሰሩ ሆነዋል። ዋጋቸውም ከቴክኖሎጂው ጋር ተሻሽሏል። የአንድ ካራት ዋጋ ከሁለት ሺ ዶላር በታች ሆኗል። ግን “አልረከሰም”። ጥራቱ ተሻሽሏል። ዋጋው ነው የቀነሰው። ፈላጊውም እየበረከተ መጥቷል።
በእርግጥም፣ “አርቴፊሻል” ማለት፣… ሁልጊዜ ቀሽም አይሆንም።  ደረጃውን ያልጠበቀ ገልቱ ስራ፣ የማስመሰያ ቁሳቁስ ማለት አይደለም። አንዳንዴ አዎ እንደዚያ ነው። ከዚያም ሊብስ ይችላል - ለምሳሌ በጥንቃቄ ያልተሰራ ቀሽም የፕላስቲክ አበባ። በጣም ሲብስበት ደግሞ፣ የውሸትና የማታለያ ዘዴም ይሆናል- ማስመሰያ እና ፎርጅድ ማለቴ ነው። ሌላ ጊዜ ደግሞ፣ አርቴፊሻልነቱ ይፈለጋል። ልብስ ላይ የተነደፈ የአበባ ወይም የልብ ቅርፅ፣ እውነተኛ አበባ ወይም እውነተኛ ልብ ቢሆን፣… ይቅር ይበላችሁ። የእጅ ስራ መሆኑ ነው፣ ጌጥነቱ።
የድግስ ፎቶ፣… “አርቴፊሻል ስጋ የ2025 ሞዴል”።
የቢሮ ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠ፣ የቤት ግድግዳ ላይ የተሰቀለ፣… ወይም የኮምፒዮተርና የሞባይል ገፅ ላይ የሚታይ የፍቅረኞች ፎቶ፣… ከነነፍሳቸው ቢሆን አያምርም። አያድርገው ማለት ይሻላል። ይልቅስ “አምሳል” መሆኑ ነው የፎቶ ተፈላጊነቱ።
ለጊዜው በአካል ተራርቀው ይሆናል። ግን ፎቶ አለ።  ከነነፍሳቸውና ከነመንፈሳቸው በአካል የተቀራረቡ ያህል ይሰማቸዋል - ለጊዜው ቢራራቁም። አርቴፊሻልነቱ ነው ቁም ነገሩ። ወይም የእጅ ጥበብ፣ ሰው ሰራሽ ነገር መሆኑ ይፈለጋል።
በእርግጥ፣ የኬክና የዳቦ ፎቶ፣ የጥብስ ወይም የቁርጥ ስጋ ቪዲዮ… ለማስታወቂያ እንጂ ለቁርስና ለምሳ አይሆንም። እውነተኛው ዳቦና ኬክ ያስፈልጋል። አይተው የሚያደንቁት ብቻ ሳይሆን፣ የጥብሱ መዓዛ፣ ሚጥሚጣውና አዋዜው፣ የሚጎርሱትና የሚያጣጥሙት ሲሆን ነው - ኑሮውና እርካታው።
አርቴፊሻል ስጋ?... የፋብሪካ ስጋ በሰፊው መምጣቱ የሚቀር አይመስልም። ቴክኖሎጂውማ ተፈጥሯል። እንዲያውም ቴክኖሎጂውን ገበያ ውስጥ እየሞካከሩት ነው። ምን ይሄ ብቻ! ባለፈው ጥቅምት ወር፣ ከዚያም በመጋቢት ወር፣ ሁለት የአሜሪካ ኩባንያዎች “የዶሮ ስጋ” አምርተው፤ የጥራት ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል። ለጊዜው ግን፣ “አርቴፊሻል የዶሮ ስጋ” ለገበያ እንዲቀርብ የተፈቀደው በሲንጋፖር ብቻ ነው። በእርግጥ ጥቃቅን ነው ስጋው።   ገና ለወግ ለማዕረግ አልደረሰም። ደግሞም ጥያቄ አለ።
ምግብነቱና ጣዕሙ ተፈጥሯዊውን ስጋ የሚፎካከር ይሆናል ወይ? ወይስ የሚያስንቅ? ተፈጥሯዊው ስጋ፣ ብዙም የመሻሻል እድል የለውም። አርቴፊሻል ስጋ ግን፣ ከቴክኖሎጂ ጋር ቢራቀቁበት፣ ከዓመት ዓመት ይሻሻላል።
የ2025 ሞዴል የ2030 ሞዴል ስጋ ሲመጣ አስቡት።  “ቦራ ስጋ ሞዴል 15” ቀምሳችሁታል? ይባባላል ሰው።
እንግዲህ፣ የፋብሪካ ስጋ “እጅ የሚያስቆረጥም” ቢሆን፣ ለማን አቤት ይባላል? እልልታ ነው ወይስ አቤቱታ? ለማንኛውም፣ ገና ነው - ጊዜው። ለነገሩ፣ ማን ያውቃል? ይሄኔ የቴክኖሎጂ ሰዎች በአዲስ ዘዴ ተዓምር እየሰሩ ይሆናል።መቼም በየአቅጣጫው ብዙ የእጅ ጥበብ  (አርቴፊሻል) እየተፈጠረ ነው።
አርቴፊሻል ኮንሰርት፣ አርቴፊሻል አልማዝ፣ አርተፊሻል ስጋ፣… ምግብ፣ ጌጥ፣ መዝናኛ ምን ቀረ? አርቴፊሻል ሃሳብ?

_______________________________________________________


                  “አርቴፊሻል አእምሮ” መጣላችሁ! መጣባችሁ!



       አንዳንድ ነገር፣… ከዛሬ ነገ መጣ፣ ደረሰ ሲባል ለዓመታት ይዘገያል። ጊዜው ቀርቧል ሲሉት ለምዕተዓመታት ይርቃል። ትንቢት ማለቴ አይደለም። ግን፣ ለትንቢትም ይሰራል።
“አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ”፣… “ሰው ሰራሽ አእምሮ”፣… ለስንት ዓመት የምስራች ዓዋጅ ተነገረለት። ስንቴስ የመልካም አቀባባል መድፎች ተተኮሱለት። ቢያንስ ቢያንስ 60 ዓመት። የመጀመሪያዎቹ ኮምፒዩተሮች የተሰሩ ጊዜ፣ ከካልኩሌተር የተሻለ አቅም ያልነበራቸው ቁምሳጥን የሚያካክሉ የያኔዎቹ ኮምፒዩተሮች የተፈጠሩ ጊዜ ነው፣… ትንቢቱ የተጀመረው።
“ሰው ሰራሽ አእምሮ መጣላችሁ!” ተብሎ ተበሰረ። ከሕልመኞቹ በተቃራኒ ከማዶ በኩል ወይም ጎን ለጎን ሆነው፣ “ሰው ሰራሽ አእምሮ መጣባችሁ” ብለው የሚያሟርቱ መዓተኞችም ነበሩ።
ከዚያ ወዲህ የኮምፒዩተሮች አቅም፣ በስንት እጥፍ እንዳደገ አስቡት። ቁምሳጥን የሚያካክል ኮምፒዩተር ዛሬ የለም። የቁምሳጥኑ ትንሽ መሳቢያ ውስጥ ኮምፒዩተሮችን ማስቀመጥ ይቻላል። ላፕቶፕ ወይም ሞባይል ከሆነ፣ ደርዘኖችን ይይዛል። የአንድ ሞባይል አቅም ግን፣ ከያኔዎቹ ኮምፒዩተሮች በብዙ ሚሊዮን እጥፍ ይበልጣል።
በዛሬ አይን ካየናቸው፤… ኮምፒዩተር ለመባል ብዙ የሚቀራቸው ሊመስለን ይችላል። ቢሆንም፣ ያኔ ገና፣ “ኮ…” ብለው የጀመሩ ጊዜ ነው፣ ስለ “አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ” መተንበይ የተጀመረው። ደረሰ ሲባል፣ ስንት ዓመቱ!
እንዲያውም፣ ሕልመኞቹና ሟርተኞቹ ትንበያቸው አልደርስ ብሎ የአዳሜ መሳቂያና ማላገጫ ከመሆን አልዳኑም። የተናገሩት አልያዘላቸውም። አቤት ውርደት! አቤት ቅሌት! ስኬታማ ነቢያትማ፣ “ቃላቸው መሬት ጠብ አይልም”። ንግግራቸው፣… ወደ መሬት የሚጣል ነገር የለውም ለማለት ነው።
በእርግጥ፣ የከሸፉ ትንቢቶችም፣ “ቃላቸው ፍሬ አያወጣም፣ መሬት ጠብ የሚል ነገር የላቸውም” ብንላቸው የሚያስኬድ ይመስላል። የሚጨበጥ የሚቀመስ ቁም ነገር እንደሌላቸው ለመግለፅ ነው። ያው፣ አንዳንድ ነባር አባባሎች፣ ለተቃራኒ አተረጓጎም የተጋለጡ ናቸው። “መወለድ ቋንቋ ነው” ይባላል። ዋናው ነገር፣ ከመወለድ በኋላ ያለው ተግባርና ፍቅር ነው። መወለድ ብቻውን ግን፣… የእነ እገሌ የልጅ ልጅ፣ የእነ እከሊት ብሔረሰብ ልጅ መባል፣ የቅድመ-ታሪክ ክስተትን ከማስታወስ ያለፈ “ትርጉም” የለውም ለማለት ነው - የአባባሉ ፍሬ ነገር።
ግን ደግሞ፣ ይህን የሚቃረን ትርጉም ሊይዝ ይችላል። “መወለድ ቋንቋ ነው” ሲባል፣… “ሙዚቃ ዓለማቀፍ ቋንቋ ነው” ከሚለው አባባል ጋር ካዛመዱት፣ “መወለድ መግባቢያ ነው” የሚል ትርጉም ሊሰጥ ይችላል።
“የትኛው አተረጓጎም ነው ትክክል?” ብለው፣ ከአባባሉን አመጣጥና አውድ አጥንተው ማወቅና ማሳወቅ የሚችሉ ሰዎች ይኖራሉ። ለጊዜው ከሌሉም፣ ያው፣… የትኛው አስተሳሰብ ነው ትክክል ብለን ማመዛዘን አያቅተንም። ስለ “ትውልድ ሐረግ” የሚኖረን አስተሳሰብ በአንድ አባባል አተረጓጎም የሚወሰን አይደለም።
ስለቋንቋ ከተነሳ አይቀር፣ ዘመነኛውን የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ወግ እናውራው። ደግሞም እነ ማይክሮሶፍት እነ ጉግልን የሚነካ ስለሆነ አይከፋም።
ቋንቋ የሚተረጉም ቴክኖሎጂ ለመፍጠር፣ በሺ የሚቆጠሩ ምርጥ ምሁራን ለበርካታ ዓመታት ደክመዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ የቋንቋ የአጠቃቀም  ደንቦችን፣ በዝርዝር ቀምረው ቴክሎጂውን በእንፉቅቅ አሻሽለውታል። በዚህ በመሃል ነው ሁለት የኮምፒዩተርና የሂሳብ ተመራቂዎች፣ ለአጭር ጊዜ የስራ ጉብኝት ወደ ጉግል እና ወደ ማይክሮ ሶፍት ጎራ ያሉት። ብዙ አልቆዩም።የጉግል ጉብኝታቸውም ከጥቂት ሳምንታት በላይ አልዘለለም።
 ከሦስት ሳምንት በኋላ የሙከራ ውጤታቸውን ለጉግል ተመራማሪዎች ለመግለጽ ወደ አዳራሹ ገቡ። የሙከራ ውጤታቸው ምንድነው?
ቋንቋ የሚተረጉም አዲስ ቴክሎጂ ነው። እና ደግሞ፣ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ከነበሩት ቴክሎጂዎች ይበልጣል- አተረጓጎሙ።
በሺ የሚቆጠሩ የቋንቋ ሊቃውንትና ተመራማሪዎች፣ ለአምስት ለአስር ዓመታት የለፉበት ቴክኖሎጂስ?... እንደዋዛ ተበለጠ?
ለዚያውም ስለቋንቋ ብዙም በማያውቁ በሁለት አዲስ ተመራቂዎች፣… ለዚያውም በሦስት ሳምንት በተሰራ አዲስ ቴክኖሎጂ? አንዱ የቋንቋ ፕሮፌሰር አዳራሹ ውስጥ ራሱን ስቶ ወደቀ። በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል። ደግነቱ፣ የልብ ወይም የአንጎል ችግር አይደለም። የድንጋጤና የፍርሃት ቅፅበታዊ ነውጥ ነው ፕሮፌሰሩን የጣለው። Panic Attack ነው ተብሏል። የእልፍ ጠቢባን ልፋት፣ የእልፍ ሊቃውንት እውቀት በአዲስ ቴክኖሎጂ ሳቢያ ከንቱ የቀረ ዋጋ ያጣ ሲመስለው ምን ያድረግ? ቴክኖሎጂው፣የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ቴክኖሎጂ ነው። ሁለቱ አዲስ ምሩቃንና አስተማሪያቸው ጀፍሪ ሂንተን፣… በአዲስ ፈጠራ ከግዙፎቹ ኩባንያዎች ቀድመዋል። በ40 ሚሊዮን ዶላር “የዝውውር ዋጋ” የጉግል ተቀጣሪ ተመራማሪዎች እንዲሆኑ ተደረገ። “Deep Mind” የተሰኘ ሌላ አነስተኛ ኩባንያም፣ በጎግል ተገዝቷል- በ360 ሚሊዮን ዶላር።
ማይክሮ ሶፍት ደግሞ፣ በ10 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት Open AI የተሰኘውን ኩባንያ ገዝቷል።እነዚያ የዓለማችን ግዙፍ የቴክሎጂ ኩባንያዎች፣ ምን ሲሰሩ ነው፤ “በጥቃቅንና አነስተኛ” ተቋማት የተቀደሙትና የተበለጡት?
ተቀድመውም ተበልጠውም ግን፣ ዛሬ የቴክሎጂው ባለቤቶችና ጌቶች ሆነዋል- ከፍለው፤ በጨረታ ገዝተው።


Read 1292 times