Saturday, 13 May 2023 21:03

የኢትዮጵያ ቦክሰኞች

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

  በኡዝቤኪስታን አስደናቂ ተሳትፎ

       ባለፉት ሁለት ሳምንታት በኡዝቤኪስታን ታሽኬት ሲካሄድ የቆየው የ2023 የዓለም ቦክስ ሻምፒዮና በነገው እለት ፍፃሜውን ያገኛል፡፡ በሻምፒዮናው ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ሶስት ቦክሰኞችና ሁለት አሰልጣኞች አስደናቂ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡  ቦክሰኞቹ ዳዊት በቀለ (በ48-51  ኪ.ግ)፤ መስፍን ብሩ  (በ60-63 ኪ.ግ) እንዲሁም ቢንያም አበበ (በ63-67 ኪ.ግ) የክብደት ምድቦች ሲሆን ቢኒያም አበበ ከፌደራል ፖሊስ ወይም ከኦሜድላ፤ መስፍን ብሩና ዳዊት በቀለ ደግሞ የአዲስ አበባ ፖሊስ ክለቦችን የወከሉ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ቡድን  በዋና አሰልጣኝነት የመሩት ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተገኙት ኢንስፔክተር ቴዎድሮስ ጥላሁን ሲሆን በረዳት አሰልጣኝነት ደግሞ ሽመልስ ውቤ ከኦሜድላ ተሳትፈዋል፡፡
በዓለም ሻምፒዮናው ኢትዮጵያን በመወከል የተሳተፈው ቡድን ያስመዘገበው ስኬት ስፖርቱን ከማስቀጠልና የአገር ውክልና ከማረጋገጥ አንፃር አድናቆት የሚቸረው ነው፡፡ ቦክሰኞቹ በሻምፒዮናው ከተለያዩ አገራት ምርጥ ቦክሰኞች ጋር ባደረጓቸው ግጥሚያዎች በመጀመርያው ዘር ለማሸነፍ ከመብቃታቸውም በላይ፤ ተሳትፏቸው በጥሎ ማለፉ ከተወሰነ በኋላም  በተለያዩ የልምምድ ግጥሚያዎች ላይ በመጫወት በዓለም አቀፍ ደረጃ  ያላቸውን ከፍተኛ ልምድ አሳድገዋል፡፡ የቦክሰኞቹ ቡድን ከሻምፒዮናው በፊት  በአየር ትራንስፖርት መቀያየርና  በበጀት እጥረት ለተሟላ ተሳትፎ ፈተና ቢገጥማቸውም በፌደሬሽኑ በኩል በተደረገው ጥረት ስኬታማ ተሳትፎ ለማድረግ ችለዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ውድድሩ ላይ አገራቸውን በመወከል በቦክሱ ሪንግ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጋቸው ይደነቃል፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው ያገኙትን ልምድ በመጠቀም ወደ ፓሪስ 2024 የኦሎምፒክ ዝግጅታቸው የሚገቡበትን አቅጣጫ አመቻችተዋል፡፡ የኦሎምፒክ ተሳትፏቸውን ለማረጋገጥ በ2023 እኤአ ላይ በጋና በሚደረገው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች መወዳደር ያለባቸው ሲሆን የዓለም ሻምፒዮናው ልምድ ይህን የሚያጠናክር ነው፡፡
በኡዝቤኪስታኑ የዓለም የቦክስ ሻምፒዮና ላይ ቢኒያም አበበ በ67 ኪግ ከሩስያ ተጋጣሚው ጋር በአስደናቂ ብቃት ሶስት ዙር ተጫውቶ በነጥብ ተሸንፏል፡፡ በሌላ በኩል ዳዊት በቀለ በመጀመርያ ግጥሚያው በ3 ዙር ጨዋታ የብሩንዲ ተጋጣሚውን በነጥብ በማሸነፍ ወደ ሁለተኛው  ግጥሚያ ካለፋ በኋላ በሁለተኛው ፍልሚያ  ከታይዋን ቦክሰኛ ጋር ተጫውቶ በነጥብ ብልጫ ተሸንፎ ወጥቷል፡፡ መስፍን ብሩ ደግሞ በመጀመርያ ጨዋታው የቆፕሮስ ተጋጣሚውን አሸንፎ ነበር ወደ ሁለተኛ ዙር የገባው፡፡ ከዚያም በጣም ከፍተኛ ልምድ ካለው የኩባ ተጋጣሚ ጋር በሁለተኛው ግጥሚያው ተገናኝቶ  የማሸነፍ ግምት ሁሉ አግኝቶ በጥቂት ነጥቦች በመበለጥ ወደ ቀጣዩ ዙር ሳያልፍ ቀርቷል፡፡ ሶስቱ ቦክሰኞች በዓለም ሻምፒዮናው ካደረጓቸው ዋና ግጥሚያዎች ባሻገር በልምምድ ጨዋታዎች ከ7 በላይ ፍልሚያዎችን ከተለያዩ አገራት ቦክሰኞች ጋር በማድረግ ልዩ ልምድ አግኝተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቦክስ ስፖርት አንቅስቃሴ ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግና በማህበራዊ ሚዲያዎች ትኩስ መረጃዎችን በማቅረብ የሚታወቀው አብዱራዛቅ ሐይሩ (ካዞ) ከስፖርት አድማስ ጋር ባደረገው አጭር ቆይታ እንደገለፀው በዓለም ሻምፒዮናው ላይ የቦክሰኞቹ ተሳትፎ ስፖርቱን በከፍተኛ ደረጃ ያነቃቃዋል፡፡  ካዞ/Cazo የአዲስ አበባ ፖሊስ ክለብ የቀድሞ ቦክሰኛ የነበረና በስፖርቱ ከ8 ዓመት በላይ ለመጫወት በቅቷል፡፡ ከዓለም ሻምፒዮናው ጋር አያይዞ  በተጨማሪ በሰጠው አስተያየት እንደተናገረው ቦክሰኞቹ በዓለም ሻምፒዮናው ኢትዮጲያን ወክለው መሳተፋቸው፤ ከፕሮፌሽናል ቦክሰኞች ጋር በመጋጠም ጥሩ ፉክክር ማሳየታቸውና ልምድ ማግኘታቸው በስፖርቱ እየሰሩ የሚገኙትን ባለድርሻ አካላት ያበረታታል፡፡ ካዞ እንደሚያስረዳው ከጥቂት አመታት በፊት በቦክስ ስፖርት የሚንቀሳቀሱ ክለቦች ከ15 በላይ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን የክለቦቹ ብዛት ከአምስት አይበልጥም፡፡ ለቦክስ ስፖርቱ ትኩረት በመስጠት እየሰሩ ያሉት በመንግስት ደረጃ ከፍተኛዎች የፀጥታ ተቋማት የፌደራል ፖሊስ ወይም ኦሜድላ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ፤ የኢትዮጵያ ማረሚያ ቤቶች ናቸው፡፡ የድሬዳዋና የፋሲል ከነማ ክለቦች እንዲሁም በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የሚደረጉ አበረታች እንቅስቃሴዎችም አሉ፡፡ በኢትዮጵያ የቦክስ ስፖርት እንቅሰቃሴው እንዲቀጥል ከፍተኛ የፀጥታና የደህንነት ተቋማት የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ስፖርተኞችን በመያዝ፤ በልምምድ ማዕከሎቻቸው እንዲሰሩ በማገዝ፤ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፏቸውን በማሳካት መስራታቸው የሚመሰገንና በብዙ መልኩ ድጋፍ የሚያስፈልገው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌደሬሽን ምንም እንኳን የበጀት እጥረት ቢኖርበትም ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ሻምፒዮኖችን በመሳተፍ እልህ አስጨራሽ ትግል ማድረጉን በማድነቅ በቀጣይ ለሚያከናውናቸው ተግባራት በዚህ አጋጣሚ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ከዓመት በፊት የዓለም ቦክስ ፌደሬሽኖች ማህበር መሰል ዓለም አቀፍ ግጥሚያዎችን ከማደራጀትና ከማካሄድ አግዶት ቆይቷል፡፡ በዓለም አቀፍ የቦክስ እንቅስቃሴ በፋይናንስ፤ በአስተዳደር፤ በስነምግባር፤ በዳኝነትና በተለያዩ አሰራሮች ሲፈጠሩ የቆዩ ግድፈቶችን ምክንያት በማድረግ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የዓለም የቦክስ ሻምፒዮናው በ2024 እኤአ ከሚካሄደው የፓሪስ ኦሎምፒክ ጋር እንደማይያያዝና እንደማጣርያ እንደማይቆጠር አስታውቋል፡፡ የዓለም ቦክሰኞች ወደ ኦሎምፒክ የሚያስገባቸውን ውጤት ለማስመዝገብ በየአህጉራቸው የሚካሄዱ የቦክስ ሻምፒዮናዎች ላይ ማተኮር እንደሚኖርባቸው ተጠቁሟል፡፡
በ2023 የዓለም የቦክስ ሻምፒዮና 107 አገራትን የወከሉ 538 ቦክሰኞች የተሳተፉበት ሲሆን በ13 የክብደት ምድቦች ግጥሚያዎች ይካሄዱበታል፡፡ በሻምፒዮና  የራሽያና የቤለሩስ ቦክሰኞች መሳተፋቸውን በመቃወም 19 አገራት አልተካፈሉም፡፡ ከእነሱም መካከል የአሜሪካ፤ የእንግሊዝ፤ የሆላንድ፤ የካናዳና የቤልጅየም የቦክስ ፌደሬሽኖች ይጠቀሳሉ፡፡ዓለም አቀፉ የቦክስ ፌደሬሽኖች ማህበር IBA ለሻምፒዮናው የሜዳልያ ድል ለሚያስመዘግቡ አትሌቶች እስከ 5.2 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት አዘጋጅቷል፡፡ ለወርቅ ሜዳልያ 200ሺ ዶላር፤ ለብር ሜዳልያ 100ሺ ዶላር እንዲሁም ለነሐስ ሜዳልያ 50ሺ ዶላር እንደሚበረከትም ታውቋል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናውን ያስተናገደው ሁሞ የተባለውና በ175 ሚሊዮን ዩሮ የተገነባው ሁለገብ የስፖርት ማዕከል ነው፡፡ የስፖርት ማዕከሉ ከቦክስ ሻምፒዮናው ባሻገር ለሆኪ፤ ለእጅ ኳስ ፤ ለመረብ ኳስ፤ ለቅርጫት ኳስ፤     ለቴኳንዶ እንዲሁም ለተለያዩ የቤት ውስጥ የስፖርት ውድድሮችና የኮንሰርት ዝግጅቶች የሚያገለግል ነው፡፡

Read 182 times