Saturday, 13 May 2023 21:02

ትንሽ ትዝታ፤ለረጅም መንገድ

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(3 votes)

ከሰው መርጦ ለሹመት ከእንጨት መርጦ ለታቦት _ከጓደኛም ጓደኛ ይኹን እል ነበር። መነሻዬ ውልደት ነው መደምደሚያው ደግሞ ሞት _ውስጡስ ለቄስ ይተው? መሐሉ አይነገርም፤ቢነገርም ሕመም ነው። ሳቆች ኹሉ የደስታ እንዳይደሉ ፤እንባዎችም የኀዘን አይደሉም። ግጥም ሲጻፍ የሚመጣ፣በደስታ ውስጥ ቀልጦ መሞትን የመሰለም አለ ።ኀዘንን አገልድሜ ደስታን ደግሞ በጥርሴ ሾሜ እታይ ነበር ፥እታያለሁም።
        ድረስ ጋሹ


        እያደር የሚቀለው ስንቅ እንጅ ትዝታ አይደለም።ከትናንት ሜዳ የቀሩ የመሰሉኝ ድርጊቶቼ ነፍስ ዘርተዋል። የዛሬ፣የነገም መንገዴ ላይ እንቅፋት ሊጥሉ ከየጎሬው አንገታቸውን ብቅ ሲያደርጉ አያለሁ።ማምለጫ ሐሳብ ፈልጌ ፣ስለ ዓለም ብርኅን ብየ አውቃለሁ። የዓለም ብርኀንን የፈሩ ሰጥተውኛል።«እኔን የፈራ ይስጥህ»ም ተፈጽሟል።
ተማሪ ነኝ_ለሕይወት።
ከሰው መርጦ ለሹመት ከእንጨት መርጦ ለታቦት _ከጓደኛም ጓደኛ ይኹን እል ነበር። መነሻዬ ውልደት ነው መደምደሚያው ደግሞ ሞት _ውስጡስ ለቄስ ይተው? መሐሉ አይነገርም፤ቢነገርም ሕመም ነው። ሳቆች ኹሉ የደስታ እንዳይደሉ ፤እንባዎችም የኀዘን አይደሉም። ግጥም ሲጻፍ የሚመጣ፣በደስታ ውስጥ ቀልጦ መሞትን የመሰለም አለ ።ኀዘንን አገልድሜ ደስታን ደግሞ በጥርሴ ሾሜ እታይ ነበር ፥እታያለሁም።
 ተስፋዬ።
ስሙን ያልኖረው ከንቱ ሰው። የደሬ እንጨት ፍም የመሰለ ድድ ፣በስሱ የተበተነ ጺም፣ከእውቀት የጸዳ አእምሮ፤ረጅም ምላሥ ተጨምሮ... መች ከአእምሮዬ ይርቃል ይህ ሰው? ትዝታ ክፋት አላት፤ከንቱ ነገሮችን ብረሳ ምናለበት፣ምናለበት ብትተወኝ? ተስፉ፣አእምሮው ከአካሉ ጋር ኅብረት የለውም። የሚናገረውን አያስብም፤የሚያስበውንም አይናገርም።አንደበቱ የመርዝ ዕቃ ነው።ከአፉ ቀና ቃል ሲወጣ ሰምቼ አላውቅም። ሲያሰኘው የጎሪጥ ያየኛል (ደም በጎረሰ ዓይኑ)። መንገዱ ላይ የገባች የትኛዋም ነፍስ ከመኖር ትቀነሳለች። በእጃቸው የያዙትን ላለመልቀቅ እንደሚንጨረጨሩት ህጻናት ይሆናል።
አሸናፊ።
በጠባብ ክፍል ውስጥ ነው የሚኖረው። ሁሉን ነገር ቀንሷል። ቤቱ ውስጥ አንድ ወንበር ፣አንድ ብርጭቆ፣አንድ መለኪያ፣አንድ ሳህን፣አንድ ...አንድ ሌሎች ዕቃዎች።ለፍላጎቱ ለከት ሰርቷል። ለራሱ የሚሆን ካለው ለሰው አይዘናበልም። ጓደኛዬ ቢመጣ የት ይቀመጣል? በምን ይጠጣል? በምን ይበላል ጉዳዩ አይደለም። ክትት ያለች ኑሮ ይኖራል። ከተደፋችበት ዶርሙ ብቅ ሲል ላየው ኤሊን ይመስላል።
አንድ ቀን የተከራየንበት በር ተንኳኳ።
ተስፋዬ እሳት ጎርሶ ከጎረቤቴ አሸናፊ ፊት ቆሟል።
ኮስታራ ፊት፣የሚወናጨፍ እጅ ይታየኛል። ተደብቄ አንድ በአንድ መስማቴን ቀጠልኩ፡፡ ስለሌለው ማህበራዊ ኑሮ ጥቅም ያስረዳዋል። «አባቴ ንጡል ነበር።ከቤት አይወጣም።ዕድር ሰንበቴ አይኼድም። ሰርግ ቤት ተዝካር ቤት አይዞርም። እኔን የዳረ ዕለት ደገሰ፣ፍሪዳ ጥሎ አገሩን ጠራ_ሊያበላ።አንድም ሰው  አልመጣም። ብዙ ብር አፍስሶ የገዛውን ሥጋ ሜዳ ጣለው።እህል ውኃ ላይ ግፍ ሰራህ ተብሎ ተከሰሰ፤ታሰረ።»
«ይታሰራ!» (አሸናፊ ተቆጣ)
«አመጽህን በእንጭጩ ግራው» ብሎ ራቀ_ተስፋዬ።
ተለያዩ።
ተስፋዬ ማህበራዊ ኑሮን ይወዳል።ለሰርግ ጨፍሮ ለኀዘን አንጎራጉሮ ቡሌ መጥለፉ ያሳሰዋል። ልቡ መደባለቅን ትሻለች። እግሩ ሰው ወደተሰበሰበበት ታዘግማለች። ብቻውን የተወለደ አይመስልም። ሰው ከአጠገቡ ካጣ ይገባበት ቀዳዳ የሚቸግረው፣የብቸኝነት ዋመን የሚውጠው ይመስለዋል። ዓለም አከንባሎ የምትሆነው መቼ ነው? ቢሉት ...ብቻን የዋሉ ዕለት ነው መልሱ። የእሱ ተቃራኒ ነው አሹ። አይሞቀው አይበርደው ዓይነት። ሰው ኖረ ሰው ጠፋ ግድ የማይሰጠው ሕይወትን በአርምሞ ሊያደምጥ የተላከ እስኪመስል ዝም ያለ..ሌላኛው ዝምታ!
ትዝ ይለኛል...
አሹና ተስፋዬን ያወቅኳቸው ካፌ ውስጥ ነው። የመመረቂያ ጽሑፌን በብቸኝነት ዙሪያ ልሰራ መረጃ የምቃርምበት ወቅት ነበር። እንደ ናሙና የኹለቱን እንቅስቃሴ በዓይኔ መንቀስ ያዝኩ። ተስፋዬ ፊቱን ሲሰበስብ (ግንባሩ ላይ ዋይፋይ ምልክትሲፈጥር)፣ከንፈሩን ሲነክስ ፣ኀዘን ቢጤ ሲነበብበት ፣ዓይኑን ወደ ተሰባሰቡት ሰዎች ወርውሮ እንደገና በሚያሳዝን ሁኔታ ሲያቀረቅር አየሁት። ተስፍሽ ኤርፎኑን በጆሮው ደቅኖ «የስንብት ቀለማትን»ያነባል፣ካፌው ውስጥ ሰው ይኑር አይኑር የገደደው አይመስልም። በየመሐሉ ፈገግ፣በየመሐሉ ራሱን በአድናቆት ነቅነቅ ያደርጋል።
ኢዮሪካ (I have it!)፤እንደ አርኪሜዲስ።
የጽሑፌ መድረሻ ታወቀኝ። ቀርቤ ተግባባኋቸው፤በሥራም በምንም አቻ አይደለንም ግን ፊት አልነሱኝም። በቴአትር ትምህርቴ ውስጥ «ከውስጥ ወደ ውጭ ትወና»ን ተመክሪያለሁ። ለጽሑፌ ተገበርኩት፤ከአሹ ጎረቤት ተከራየሁ። በእኔ አማካኝነት እነሱም ተወዳጁ። ሕይወታቸውን ልጋራ ተጠጋሁ። ኑሮ ከተስፋዬ ጸባይ በላይ አይከብድም ነበር። አሸናፊ በራሱ ዓለም ያለ ሰው መሆኑ አልተነካካኝም።ለምጠይቀው ይመልሳል፤ ትርፍ ቃል አይወጣውም።ለጽሑፍ ግብአት ቀርቤ ጓደኝነትን  መሠረትን፤ለመሞት መጥተን መኖርን እንደለመድነው።
ይኸው ዛሬም ከሐሳብ ጋር ነቃሁ።
ኹለቱም ትዝታ ናቸው። ለስላሳ ትውስታ።ያለፉ ቀናቶች ጉንብንባታቸውን ሲገልጡ የሚታዩኝ የደም ፍንጣቂዎች። የተስፋዬ ረጅም እጅ ከመኖር የነጠላቸው ግቡሳኖች ናቸው።አነፍንፎ ቀርቦ አነፍንፎ የሚያርቃቸው ሰዎች በዙ። የእሱ ግፍ ቢጠራቀም ዓለምን በጎርፍ ያጥባል።ለመቀላቀል የሚፈልገውን ሰው ለምን ይጠለዋል? ለምንስ ከአሹ አይማርም?...ያልተመለሰ ጥያቄዬ ነበር።
እኔ ጋር፣ዛሬ የሚባል ቀን የለም፤ ለብቻው የሚታወስ። ወይ በትናንት ነው ወይም በነገ ነው ቅንፉ የሚዘጋው። ከጉበን መልስ ብቻዬን አስባለኹ። ተስፋዬ ይበጅ አሸናፊ?...
መምረጥ ግዴታ ቢሆን ኹለት መልክ አለው።
ወይ እገሌን ማለት ...ወይም አለመምረጥ። ምክንያቱስ አለመምረጥም መምረጥ ነውና። ይኸው አልመርጥም። ከአፈር በታች ውለዋል አንዴ። ተነስተው ምስክርነት በማይሰጡበት ለክርክር አልጋብዛቸውም። ካፌ ውስጥ ያገኘሁት፣ኀብረት ወዳዱ ነገር ግን ብቸኛው ተስፋዬ ከማህደሬ ይመዘዛል። መቀላቀልን እየፈለገ ሰዎች ይገፉታል። ሳይወድ በግዱ የብቸኝነትን ጽዋ ይጎነጫል። ይኼ ዓይነቱ ብቸኝነት በሽታ ነው። ወድዶ እና ፈቅዶ ለፈጠራ ሲል መነጠልን የተላመደው አሹም ብቅ ይላል።«ዓለማዊ በአት »ግንባታን ያቀነቅናል። ገዳማዊያኑ ለነፍሳቸው ይመንናሉ...በበአታቸውም ክትት ብለው ይኖራሉ። በዓለማዊው ኑሮ  ውስጥ በአቱን የገነባው_ አሹ።
ብዙ ጊዜያትን በጓደኝነት ገፋን።ለጽሑፌ ግብአት ከመሆን ጀምሮ አኗኗሩኝ። የተነጠልኩ ወይም የተገፋሁ(ብቸኛ) አልሆንኩም። አለመምረጥን ነው የመረጥኩት። ረጅም መንገድ ስንጓዝ ለትዝታ እንደሚኖሩ አልነገሩኝም ነበር። በሚኒስቴር ደረጃ የሚሰራው ተስፋዬ (ባለሥልጣን ነው)፣በ«አስቦ አደር»መልኩ የተቀመጠው አሹ ተከታትለው ወደ ማይመለሱበት ኼደዋል። ከመኼዳቸው በፊት ሦስታችንም ተጣላን። ተነቋቆርን። የአሹንም በአት በነገር ቧጠን አነሳን። ከጥሩ ሕይወታችን ራቅን...
         የተያየን ጨለማ ውስጥ
          የተለያየን በብርኀን
          የተገናኘን በደሃ ጎን
          የተገፋፋን ሲደላን !
                   እኛ።
ሦስት ነን ለቁጥር ፤ለሕይወት አናሳ። መጡ ብዬ ሳልጀምር፥ኼዱ ቀርቷል ለአፌ። ለብቻው በአት የሰራው አሹ ፊቴ ለይ ነው። ማዕዱን ለብቻው ሲጋተር፤ራሱን በ«አትድረሱብኝ» ጉመሮ ሲያጥር፣ደጃፉን በአጋም በጋሬጣ ሲዘጋ፣ከዓለም ራሱን ሲቀንስ ...ከሰው ደጅም ሳይደርስ፣ካልቀላቀላችሁኝ ብሎ ሳይከስ _የኖረ። ተስፍሽ አለ በዚያ። የተሰበሰቡ በጎችን የሚወድ። በመሐላቸው ተኩላ መሆንን የሚፈቅድ። ለብቻው ዓለም ትጫነው የሚመስለው፤ሰው መሐል ኑሮ የሚቀለው። ዓለም ላይ ዓለም የሚጨምር...ጣጣ ላይ ጣጣ የሚመዝ ..።
ረጅም ነው መንገዱ።
ይኸው ብቻዬን ነኝ (በማወቅም ባለማወቅም)።ደጋግመው ይታወሱኛል ፤ደጋግሜ ራሴን እወቅሳለሁ። ከብቸኛው ነኝ ወይስ ከተነጠለው (ገለል ካለው)?_አለውቅም። አለመምረጤ ትዝ ይለኛል ፤ምርጫው መርጦኝ ከሆነስ? ፤መሞት እንደማንፈልገው ሞት ግን መግደል እንደሚፈልገው...። ኑሮ ራሰ ከብዶ ሲሆንብኝ ትዝታ ሲያምሰኝ የት ልድረስ እላለሁ ።አእምሮዬን የሚያነቃው ሙዚቃ «አጉል ጃዝ አብዝቼ ኳኳታ»ሊያስብለኝ ይቃጣዋል።
ዓለም ልቀንስ?
ወይስ
ዓለም ልጨምር?
ዓለም ብጨምር  የተስፍሽ ዕጣ _መገፋቱ። ተገፍቶ ብቻን መሆኑ ያስፈራኛል። ዓለም ብቀንስ በአቴ ውስጥ ታፍኜ ድንጋይ የተጫናት ሳር (ቢጫ የምትሆነዋ) መስዬ መኖር ያስፈራኛል።ሲውል ሲያድር ጊዜ ልቤ ወደ ኹለተኛው ያደላል።ሻማ ቀልጦ እንደሚበራው መሆን...እንደዛ መሆን ያሻኛል። በጎጆዬ ውስጥ ኩርትም ብዬ ንባብንና ጽሕፈትን ማሽሞንሞን ያምረኛል። ለሥነ-ጽሑፍ አዲስ መልክ ሰጥቶ ማለፍ ፣ፊቱን ለፊት ወዳዶች ትቼ ኋላውን መግዛትም ያሰኘኛል።
ድፍን 4 ዓመት ፤ከዝርዝር 26 ቀን።
ትዝታ ብቻ ነበረች። አጠገቤ እሳት አንድዳ ሙቅ እንሙቅ የምትለኝ።ተስፋም ነበረ በሩቁ መሠላል መስሎ የቆመ። እርከኖቹ የላሉ። ለመውደቅም የሚጋብዙ። «የፈራ ይመለስ» የሚያስብሉ...።ሰበዝ መዘዝኩ ለሐሳብ። እንደ ሸለመጥማጥ ግለኝነቱን ልጣባው። «ዞር በል» የሚለኝ ሳይኖር ዞር ልል፣ተቀነስ የሚል ድምጽ ሳልሰማ ልቀነስ ፈቀድኩ።
[  ረጅም ዕድሜ ፡ በጠባብ ሐሳብ...]
አእምሮዬን ሐሳብ ሰጠሁ፤ተግባር ነሳሁ።እርፍ እንዴት እንደሚጨበጥ ፣ከጥል እንዴት እንደሚመለጥ ግራ ገባኝ። ማሰሪያ እንዳሰለቸው በሬ..ሜዳ ሲያገኝ እንደሚፈነጥዘውም ሆንኩ። ትንሽ ቀዳዳ ባገኘሁ ቁጥር በእሷ ሾልኬ አጽናፈ-ዓለሙን መዳበስ ያሰኘኛል።
በአጭር ቁመት በውስን ስፋት የቀነበብኳት ጎጆዬ ታወራኛለች። ስለ መነጠል ና ስለ ብቸኝነት። ወደው ስለሚያደርጉት ሽሽት እና ተገፍተው ስለሚደርስ ስሜት።
 ሰዎች ለምን ገዳም ይገባሉ?
ጎጆዬን እጠይቃታለሁ። ዓለም ብትሰለቻቸው፤ቢንቋትም ትለኛለች። ዓለም ቅነሳ ገባኝ።ከድሎቱም ከምቾቱም እንደመራቅ...እንደማፈግፈግ። ዓለማዊ ሰውም ተሆነ መንፈሳዊ ሰው ዓለም ቅነሳ አለ። አሹ ትዝ ይለኛል። ሚኒማሊስት ይሉታል። ሁሉን ቀንሶ ...ራሱን በሕግጋቶቹ አጥሮ መሰናዘሪያ አልነበረውም። ከቤቱ በወጣ ጊዜ የሰው ልጅ እንግዳ ፍጥረት የሚሆንበት ነው። ሁሉ ነገር አዲስ..የህንጻ ኮረት ከተማዋን አጨናንቋት፣የልብስ ማአት መንገዷን ሞልቷት፣የኔ ቢጤው በገፍ ሰፍሮባት ያያል።
ተመልሶ ወደ ጎጆው።
ሚስቱ ዕቃ ወዳድ ናት። እሷን ፈትቶ ሲካፈል ከሁሉም አንድ አንድ አነሳ። ለአንድ ሰው አንድ አይበቃም? ..መሞገቻው ናት።
ሐሳብ ውርስ።
ከአሹ ጋር የነበረን የተለየ ቅርበት ይጠቅም ይጉዳኝ አላውቅም።ይኸው ቤቴ ውስጥ «አንድ»ይበዛል። ንፉግነት አይደለም ...ንቀትንም አይመስልም ..እንዲያው ዝም ብሎ ዝም ማለት ፤ እንዲያ ራቅ ብሎ ራቅ ማለት።
ያልሞቅኩት እሳት።
የሚታየኝ ብርኀን አድማሱን ፍም ረመጥ አስመስሎታል። ያልተተኛ እንቅልፍ ብዙ አለኝ።አምነው የተቀበሉት አይጎረብጥም። ቀን ተሌት አሹ ..አሹ ትላለች ጎጆዬ። ጣሪያ ግድግዳዋ፣ምሶሶ ባላዋ፣ማገር አዋርጇ ኹለ ነገሯ _ትዝታ።
[መልከ መልካም ሴት ፥ቀትሩን እየተዳፈረች...
በጎጆዬ አጠገብ ስታልፍ ወጣሁ። በመልኳ ተማርኬ አጠገቧ መገኘቴን ከቅዠት መልስ ነው ያወቅሁት። የጀመርንበትን አላውቅም፤የአሹም የተስፋዬም ፍቅረኛ እንደነበረች ስትነግረኝ ፈዘዝኩ። በአት የሰራው አሹ ሊሞት አቅራቢያ ሰው ሰው አሰኝቶት እንደነበር ፤ከሰው የሚውለው ተስፍሽም ሊሞት አቅራቢያ ሰው ለምኔ? ማለት ጀምሮ እንደነበር አጫወተችኝ። ለሁለቱ ፍቅረኛ መሆን አይከብድም? እንደ ማዕረግስ የሚወራ ነው? በማለት ፋንታ የሰው ልጅ ምርጫ እንደ እስስት መልክ ቋሚ ስለመሆኑ አሳሰበኝ።
እኔም በተራዬ ሳልከጅላት ተለያየን። የሦስቱ ጓደኛማቾች ሚስት ከመባል ያተረፍኳት ይመስለኛል። የሐሳብ ውርሴ ጽናት ዘለቄታ አላስተማመነኝም። እስከ መቼ ነው በበአቴ የምጸናው?_ብዬ ራሴን መጠየቅ ያስፈራኛል። ሰው ራሱን ከፈራ ደግሞ መደበቂያ ያጣል፤ የት ልሸሸግ?


Read 783 times