Saturday, 20 May 2023 15:13

ፍሊንትስቶን ሆምስ አክሲዮኖቹን ለገበያ ሊያቀርብ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአነስተኛ ካፒታል በኢንጂነር ፀደቀ ይሁኔ  ተመስርቶ ከ30  አመታት በላይ በኮንስትራክሽንና በሪልእስቴት ዘርፍ ጉልህ ሥራዎችን እያከናወነ የሚገኘው ፍሊንትስቶን ኢንጅነሪንግ ፤ ከሃምሌ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ አክሲዮኖቹን ለህዝብ ክፍት በሆነ ገበያ ለሽያጭ እንደሚያቀርብ አስታወቀ፡፡   
ኩባንያው ይህን ያስታወቀው ባለፈው ማክሰኞ፣ ግንቦት 8 ቀን 2015 ዓ.ም፣  በሃያት ሪጀንሲ  በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ  ነው፡፡
የኩባንያው መሥራችና ባለቤት ኢንጂነር ፀደቀ ይሁኔ የአክሲዮን ሽያጩን ለመጀመር ያስፈለገበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ “ፍሊንትስቶን ኢንጅነሪንግ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በግለሰብ ደረጃ ተመሥርቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን በመገንባት ለተጠቃሚዎች ማድረስ ከቻለ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ባለአክሲዮኖችን በውስጡ ቢይዝ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን ለመገንባት ይችላል።” የሚል እሳቤን መነሻ ማድረጋቸውን  ገልጸዋል።
10 ሚሊዮን አክሲዮኖች ለሽያጭ መዘጋጀታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ የአንድ አክሲዮን ዋጋ አንድ ሺህ ብር ሆኖ የአክሲዮን ባለቤትነቱ ከ20 ሺህ ብር የማያንስና ከሁለት ሚሊዮን ብር የማይበልጥ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡
ለሽያጭ የቀረበው አነስተኛ የአክሲዮን መጠን ዝቅተኛው 20 ሺህ ብር፣ ከፍተኛው ደግሞ ሁለት ሚሊዮን ብር የተደረገበትን ምክንያት በተመለከተ  የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ ማቲያስ ሲያስረዱ፤ ከፍተኛ የገንዘብና የዕውቀት አቅምን በመገንባት መካከለኛ ገቢ ካላቸው ደንበኞች ጀምሮ ብዙኃኑን ተጠቃሚ የሚያደርግ የሕዝብ ኩባንያን ለመፍጠር በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል።
የአክሲዮን ገዢዎች ለአክሲዮኑ ያዋሉት ገንዘብ በቀጣይ ለቤት መግዣነት ማዋል ቢፈልጉ፤ በማንኛውም ጊዜ ኩባንያው አክሲዮናቸውን ገዝቶ፣ ያላቸውን ገንዘብ በካሬ ሜትር በማስላት የቤት ባለቤት የሚሆኑበት ሥርዓት መዘርጋቱም ተገልጧል፡፡የግል ድርጅቶችን ለህዝብ ክፍት በሆነ ገበያ ማቅረብ ሁለት ቁልፍና ተመጋጋቢ ፋይዳ እንደሚያስገኝ የተጠቆመ ሲሆን፤ አንደኛው ከፍተኛ የገንዘብና የዕውቀት አቅም ማምጣቱ ነው፤ ሁለተኛው  ደግሞ ተጠያቂነትንና ግልጽነትን በማስፈን መልካም የኮርፖሬት አስተዳደርን  ያሰፍናል ተብሏል፡፡
ከተቋቋመበት ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በመላ ሃገሪቱ በልዩ ልዩ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራ ተቋራጭነት ሲንቀሳቀስ ቆይቶ ከአስራአምስት ዓመታት በፊት ወደ ቤቶች ልማት ገበያ የተቀላቀለው ፍሊንትስቶን ሆምስ፤ በትምህርት፣ በውሃ፣ በመብራት ሃይል፣ በመንገድና በመንግስት የቁጠባ ቤቶች ፕሮጀክቶች ላይ ግዙፍ አሻራዎችን ማኖሩ ታውቋል፡፡
ወደ ሪልእስቴት ከተቀላቀለ በኋላ ባሉት አስራአምስት ዓመታትም በሺህ የሚቆጠሩ ደንበኞችን የቤት ባለቤቶች ማድረጉ ተጠቁሟል፡፡
“ሁሌም በለውጥ ሰዓት ለባለሃብቶች ሦስት ነገሮች የመሆን ዕድል ያጋጥማል፤ ቆዛሚም፣ አዝጋሚም፣ ተምዘግዛጊም መሆን ይቻላል፡፡ እንደ ንግድ ድርጅት ተምዘግዛጊ መሆኑ ግን እጅጉን ያዋጣል፤ ሀገራችንን በጋራ፣ ሀብታችንን በአክሲዮን እንገንባ” ብሏል፤ፍሊንትስቶን ሆምስ በመግለጫው፡፡


Read 1915 times